በብዙ ስኬቶችና ተሞክሮዎች የተቀበልነው አዲስ ዓመት

አሮጌውን የ2015 ዓ.ም ሽኝተን እነሆ አዲሱን 2016 ዓ.ም ከተቀበልን ቀናቶች እየተቆጠሩ ነው። በዘመናት አቆጣጠር ሄደት ውስጥ እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን! እየተባባልን፣ አሮጌውን ዓመት እየሸኘን አዲሱን ዓመት በተስፋ ስንቀበል ኖረናል፤ ተስፋ የመኖር ትልቁ አቅም ነውና ዘንድሮም አዲሱን ዓመት በተመሳሳይ መልኩ በብዙ ተስፋ ተቀብለናል፡፡

አዲሱን ዓመት በተስፋ ስንቀበል በቀደመው ዓመት የጀመርነውን ለማስቀጠል፣ በቀደመው ተሞክሯችን ላይ ተመስርተን አዲስ ነገር ለመስራት በማሰብና በማቀድም ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዳችን በሕይወታችን እውን ልናደርገው የምንፈልገውን ትልቁን ሕልማችን እና ይዞት ሊመጣ የሚችለውን ፈተና በማሰብ ጭምር ነው፡፡

ሀገርም እንደዚያው ናት፡፡ በዘመናት ውስጥ ለመሆን የምትፈልገውን መሻቷን ሆና ለመገኘት ተስፋ አድርጋ ትንቀሳቀሳለች ። ተስፋዋን ወደሚጨበጥ ራእይ ለመለወጥ ሕዝቦቿን በንቃት አሰልፋ የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁነት ትፈጥራለች። ዝግጁነትን ወደ ተጨባጭ አቅም በመለወጥም መሆን የፈለገችውን ሆና ትገኛለች ። ለዚህ ደግሞ አመታትን የስኬት መለኪያ አድርጋ ትጠቀማለች።

ሀገራችን ኢትዮጵያም በዘመናት መካከል በነበሩ ትውልዶች ብዙ የብልጽግና ተስፋ ሰንቃ ተንቀሳቅሳለች። ተስፋዎቹ በብዙ ተግዳሮቶች ተፈትነው የተጠበቀውን ያህል ፍሬ ማፍራት ባይችሉም እንደሀገር በለውጥ ውስት ስለመሆንዋ የተለያዩ የታሪክ ትርክቶች የሚያረጋግጡት እውነታ ነው።

በተለይም ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ሀገራዊ ብልጽግና ለማምጣት በሀገሪቱ የተፈጠረው መነቃቃት፣ መነቃቃቱ የፈጠረው ራዕይ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነ ይታመናል። ራዕዩን ተጨባጭ ለማድረግ ስትራቴጂዎች ተነድፈው፣ በየዓመቱ እቅዶች እየወጡ እየተተገበሩ ስኬቶችም እየተመዘገቡ ናቸው። እነዚያ ስኬቶች ለቀጣይ እቅዶች ጥሪት፣ ተሞክሮና መንደርደሪያ እየሆኑም ይገኛሉ፡፡

በ2015 ዓመት በጀት ዓመትም የሆነው ይሄው ነው፡፡ በዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች እቅዶች ወጥተው መተግበራቸውን ተከትሎ እንደ ተቋም፣ እንደ ክልል፣ እንደ ሀገር ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ እንደ ስኬቶቹ አዲሱን ዓመት በባዶ እንዳንቀበለው፣ ጥሪት ይዘን እንድንቀበለውም አስችለውናል፤ እጅህ ከምን እንዳይለን አርገውናል፡፡

በዓመቱ ስኬት ተመዝግቦባቸው ለአዲሱ ዓመትም ጥሪት ማፍራት ከተቻለባቸው ዘርፎች አንዱ የግብርናው ዘርፍ ነው፡፡ በዘርፉ የተመዘገበውን ስኬት መጥቀስ ለቀጣይ ስራም ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በዘርፉ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ሲሆን፣ በዚህም የሀገሪቱን የግብርና ምርት ፍላጎት ማርካት እየተቻለ ይገኛል።

በወጪ ንግድ እንደ ቡና፣ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ፣ የቅባት እህሎች፣ ወዘተ ያሉትን የዘርፉ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በመላክ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት በኩል አኩሪ ታሪክ ማስመዝገብ ተችሏል። ከግብርናው ዘርፍ ክንውኖች መካከልም ተጠቃሽ እየሆነ የመጣውን ስንዴ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈልጋል።

በስንዴ ልማት በተለይ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የተገኘው ስኬት ሀገርንና ህዝቧን ያኮራ ሆኗል። ሀገሪቱ ከሶስት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የመስኖ ስንዴ ልማት በቆላማው አካባቢ ስትጀምር ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ነበር ያመረተችው። በሁለተኛው ዓመት ደግሞ 26 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ተገኘ። ለሶስተኛ ጊዜ ባለፈው ዓመት 53 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ 47 ሚሊየን ኩንታል ማግኘት ተችሏል፡፡

ይህ ስኬት በአፍሪካ ልማት ባንክና በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር አድናቆትን ማግኘት ችሏል፡፡ በመስኖ ስንዴ ልማት የተገኘው የስንዴ ምርት ከመኸርና በልግ ስንዴ ምርት ጋር ተዳምሮ ከሀገራዊ ዓመታዊ የስንዴ ምርት ፍጆታ በላይ መሆኑ በመረጋገጡም ሀገሪቱ ስንዴ ለጎረቤት ሀገሮች የላከችበት ሁኔታ እንዲፈጠር አርጓል፡፡

ልብ በሉ፤ በሀገራዊ የስንዴ ልማቱ ሀገራዊ የስንዴ ፍላጎትን መመለስ ተችሏል፤ ስኬቱ ሀገሪቱ እስከ 700 ሚሊየን ዶላር በማውጣት ከውጭ ስንዴ የምታስመጣበትን ሁኔታ አስቀርቶታል፤ ስንዴ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለውጭ ገበያ የቀረበው፤ ዓመቱ ስንዴ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ ከማስመጣት ወደ መላክ የተጀመረበት ዓመት ነው፡፡

ዓመቱ በዩክሬንና ሩሲያ መካከል ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ የቆየበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሀገሮች ደግሞ በስንዴ ምርታቸውና በመሳሰሉት በዓለም ታዋቂ ናቸው፤ ጦርነቱ ይህን አቅርቦት በማስተጓጎሉ ከእነዚህ ሀገሮች ስንዴ ይገዙ በነበሩ ሀገሮች ላይ ከፍተኛ ችግር እንዲከተል አርጓል፤ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የስንዴ ምርት ባታመርት ኖሮ ሊደርስባት ይችል የነበረውን ማሰብ ይገባል፡፡

ከስንዴ አኳያ ስንመለከት ስኬቱ በቀደሙት ዓመታት የጀመረ ቢሆንም፣ ዓመቱ ከፍተኛ ስኬት የተመዘገበበት እንደመሆኑ በስንዴ ልማት ለ2016 አዲስ ዓመት ትልቅ አቅም ይዘን ነው ወደ አዲስ ዓመት የተሸጋገርነው ማለት ይቻላል፡፡ ዓመቱ በስንዴ ምርት ስኬታማ የተሆነበት ብቻ ሳይሆን በቀጣይም ይህን ስኬት በማጠናከር የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የታየበት ነው፡፡

ሌላው በዓመቱ የተመዘገበው ስኬት በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተመዘገበው ነው፡፡ ባለፉት አራት ዓመታትም በአረንጓዴ አሻራ ስኬት ተመዝግቧል፤ ይህን ስኬት በ2015 ዓመትም ማስቀጠል ተችሏል። እንደሚታወቀው ለአራት ዓመታት በተካሄደው የመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ከእቅድ በላይ 25 ቢሊየን ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡

በዚህ ወቅት በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀንበር ለመትከል ታቅዶ ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፤ ስኬቱ በዓለም በአንድ ጀንበር በርካታ ችግኞችን በመትከል የምትታወቀውን ሕንድን ክብረ ወሰን የሰበረና ታላቅ ክንውን ነበር፡፡

በ2015 ኢትዮጵያ ለመትከል ከያዘችው ስድስት ነጥብ ሶስት ቢሊየን ችግኞች ምን ያህል እንደተከለች የተጠናቀረ መረጃ ገና ይፋ ባይደረግም፣ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ከተያዘው እቅድ 567 ሚሊየን አካባቢ ችግኝ ተከላ መፈጸሙ የዓመቱ እቅድ ሊሳካ እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይህ ስኬት በሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስኬታማ ተግባር ለማከናወን በተሞክሮነት፣ በስንቅነት ያገለግላልና ሌላ ጥሪት ይዘን ወደ አዲሱ ዓመት የተሸጋገርንበት ነው፡፡

ከዓመቱ ስኬቶች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው ሌላው ተግባር የአያሌ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው እና ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ያደረሰው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም ስምምነት የቆመበት ዓመት መሆኑ ነው፡፡ ሀገሪቱ ወደ ጦርነቱ የገባቸው የሰላም ጥሪዋ ስለተገፋ ተገዳ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የተከፈተባትን ጦርነት እየመከተችም ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም።

አሜሪካና የተለያዩ ወገኖች የሰላም ውይይት እንዲደረግ ሲጠይቁም ችግሩ አፍሪካዊ ነው፤ መፍትሄውም አፍሪካዊ መሆን አለበት ብላ ጉዳዩ ወደ አፍሪካ እንዲመጣ አርጋለች፡፡ በዚህም በአፍሪካ ሕብረት፣ በኬንያና ደቡብ አፍሪካ አቀራራቢነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደ የሰላም ድርድር ጦርነቱ ቆሞ የስምምነት ስምምነት ላይ እንዲደረስ ተደርጓል፡፡

በሰላም ስምምነቱ መሰረትም በትግራይ ነገሮች ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው እንዲመለሱ ብዙ ተሰርቷል፤ ብዙም ለውጥም መጥቷል፡፡ መንግስት ፊትም ፍላጎቱ ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እንደነበረው ሁሉ፣ ሁዋላም ችግሩ በአፍሪካዊ መፍትሄ እንዲፈታ በነበረው ጸኑ አቋም መሰረትም ችግሩ በሰላማዊ አማራጭ መፍትሄ ማግኘት የቻለው በዚሁ ዓመት ነበር፡፡

ጦርነቱ ሀገሪቱን ለሰብአዊና ቁሳዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ቀውስ ዳርጓት ነው ያለፈው፡፡ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ እና በአንዳንድ ሀገሮች ጫና ሳቢያ ክፉኛ ተፈትናለች። ጫናው እየቀለለ የመጣውም የሰሜን ኢትየጵያውያን ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በሰላም ለመፍታት የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ነው፡፡

ዓመቱ ሀገሪቱ ባደረገችው የሰላም ጥረት መሰረት ጦርነት የቆመበትና ችግሮች በሰላማዊ መንገድ መፍታት የጀመሩበት እንደመሆኑ ሀገራችን ትልቅ ስኬት ያስመዘገበችበት ነው፤ ይህን ስኬት እና ስኬቱን ተከትሎ በሀገሪቱ የሰላም አየር መስፈን የጀመረበትና የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ተከትሎ አንዳንድ ጫናዎችም እየላሉ ያሉበት ሁኔታም መፈጠሩም በስኬት ሊያዝ ይገባል፡፡ እነዚህ ስኬቶች በአዲሱ ዓመት ብዙ መስራት የሚያስችሉ መደላድሎች ናቸው፡፡

ስኬቱ በቀጣይ በፖለቲካው በምጣኔ ሀብቱና በማህበራዊው መስክ ሰፊ ስራ መስራት የሚያስችል እንደመሆኑ ለ2016 አዲስ ዓመት ትልቅ ስንቅ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይህ ስኬት በቀጣይ በፖለቲካው፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊው መስኮች ብዙ መስራት የሚያስችል መደላድል ሆኖ ያገለግላልናም በእርግጥም ጣፋጭ ስንቅ፣ ትልቅ አቅም ሆኖ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በኮቪድ፣ ግጭቶችና ጦርነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጫና ሳቢያ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ክፉኛ ተጎድቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እነዚህ እና ሌሎች ችግሮች ኢንዱስትሪዎች ግብአት፣ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ገበያም ጭምር እንዳያገኙ አርገዋል፡፡ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ስራ አቁመው ነበር፤ ኢንዱስትሪዎች በኤሌክትሪከ ኃይል አቅርቦት እጥረት የተነሳ ከማምረት አቅማቸው ከ50 በመቶ ያልበለጠውን ብቻ ነበር ሲጠቀሙ የቆዩት፡፡

ይህ አምራች ዘርፍ መነቃቃት ማሳየት የጀመረው በ2015 ዓመት ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ መንግስት ዘርፉ እንዲነቃቃ ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባሮች ነው፡፡ መንግስት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ባከናወነው ተግባር ስራ አቁመው የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ የተመለሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ንቅናቄው የአምራች ዘርፉ ጥያቄዎችም አድማጭ እንዲያገኙ እያረገ ነው፡፡

ሌላው የዓመቱ ስኬት ሀገሪቱ በቅርቡ የተጎናጸፈችው ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው፤ ብሪክስን የተቀላቀለችበት ድል፡፡ ይህ ድል በከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተመዘገበ ተብሏል፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ተቋማትና በአንዳንድ የበለጸጉ ሀገሮችና እነሱ በሚዘውሯቸው ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የደረሰባት ጫና ሌላ ተጨማሪ አማራጭ እንዲኖራት የሚያስገድድ ነበር፡፡ ብሪክስን መቀላቀሏ ይህን ክፍተት እንድትሞላ፣ ወዳጆቿን እንድታበረክት ያስችላታል፡፡

የብሪክስ መስራቾች ግዙፍ ሀብት የሚያንቀሳቅሱ፣ በገቢ ንግዳቸው የሚያማልሉ/ሶስት ትሪሊየን የሚሆን የገቢ ንግድ ያላቸው/፣ከዓለም ህዝብ 40 በመቶውን የሚይዙ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ህብረቱን የተቀላቀሉትን ስድስት አዳዲስ ሀገሮች/ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ የተባበሩት ኤምሬትና አውስትራሊያ/ሀብት፣ የህዝብ ብዛትና የገቢ ንግድ ሳይጨምር ነው። በእዚህ ላይ ሕብረቱ አዲስ የልማት ባንክ የሚባል ግዙፍ ተቋምም የመሰረተ ነው፡፡

ሀገሪቱ በተጠናቀቀው ዓመት መጨረሻ አካባቢ የተቀላቀለችው ትልቅ ገበያ፣ ኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ይዞ የመጣ ተቋምን ነው፤ ይህም ለ2016ና ቀጥሎ ለሚመጡት ዘመናት የሚሆን ትልቅ አቅም የተገኘበት ዓመት ነው፡፡ ሀገሪቱ ይህን ትልቅ አቅምም ይዛ ነው አዲሱ ዓመት የተቀበለችው፡፡

ሀገሪቱ ተቋሙን ስትቀላቀል ልማቷን ገበያዋን ታሳቢ አርጋ ነው፡፡ ሀገሪቱ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ራዕይ ሰንቃ እየሰራች ያለች፤ ስኬቶችንም ማየት የጀመረች ናት፡፡ በግብርናው በኢንዱስትሪውና በአገልግሎቱ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ሰፋፊ እቅዶችን እያወጣች እየተገበረችም ናት፡፡

ለእዚህ ሁሉ አጋር፣ ገበያ፣ ኢንቨስትመንት፣ የውጭ ፋይናንስ በእጅጉ ያስፈልጋታል፡፡ ብሪክስን መቀላቀሏ እነዚህን አቅሞች ለማግኘት ጥሩ አማራጭ ሕብረት ይሆንላታል፡፡ እየደረሰባት ያለው ጫናም ለማቅለል የራሱን ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡

በዚህ በኩል በ2015 ትልቅ ስራ ተሰርቷል፤ ለ2016 አዲስ ዓመት ስንቅ ሊሆን የሚችልም ስኬት ነው የተመዘገበው፡፡ ጫናዎች ይህም ድል ሀገር ትልቅ አቅም ይዛ ወደ አዲሱ 2016 ዓመት የተሸጋገረችበት በሚል ሊታይ ይችላል፡፡

በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን ደግሞ የአባይ ግድብ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ አድርገዋል። ግድቡ አራተኛውን ሙሌት ተከትሎ የያዘው የውሃ መጠን ከ42 ቢሊየን ሜትር ኩብ በላይ ነው፡፡

አሁን የሀገራችን ግዙፉ ሀይቅ ጣና የያዘውን ውሃ ያህል በታላቁ በአባይ ግድብ ተይዟል፡፡

ኢትዮጵያውያን ጣናን ያህል የውሃ አካል ፈጥረዋል፡፡ ይህ የአባይ ግድብ አራተኛው ዙር ሙሌት በስኬት መጠናቀቅና ግድቡ በጣና ልክ ላይ መድረሱ የዓመቱን ስኬቶች ከፍታ ይበልጥ የሚጨምር ታላቅ ስኬት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከ2003 ጀምሮ ለግንባታው የሚጠበቅባቸውን በማበርከት አሻራቸውን እያኖሩ፣ በየሙያ መስካቸውም ጠንከረው እየሰሩ፣ በግድቡ ላይ አንዳንድ የውጭ ኃይሎች ሲያካሂዱ የነበሩትን አፍራሽ ተግባር እየመከቱ፣ ለዚህ ታላቅ የስኬት ምእራፍ ያደረሱ እንደመሆኑ የግድቡ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የተጠናቀቀው 2015 ዓመት ከስኬትም በላይ ስኬት ተብሎ ይይዛል፡፡

እነዚህ ስኬቶች የተመዘገቡት በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ምንም እንኳ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ጦርነት ቢቆምም፣ በሀገሪቱ ላይ ይደረግ የነበረው ጫና መቀነስ የጀመረበት ቢሆንም፣ በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በቆየችበት ዓመት ነው፡፡ በተለይ የዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት፣ ድርቅ ፣ በሀገሪቱ እዚህም እዚያም የተከሰቱ ግጭቶችና ሌሎች ተግዳሮቶች ሀገሪቱን በእጅጉ ፈትነዋታል፡፡

ይህ በፈተና ውስጥ ስኬቶችን የማስመዝገብ ማንነት እንደ ትልቅ ጥንካሬ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በእዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ የተመዘገቡ ስኬቶችን ተይዘው ነው እንግዲህ ወደ አዲሱ 2016 ዓመት መሸጋገር የተቻለው፡፡ እነዚህና ሌሎች እዚህ ያልተጠቀሱ በገቢ አሰባሰብ፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብና በመሳሰሉት የተገኙ ስኬቶች ወደ አዲሱ ዓመት ጥሪቶችን በመቋጠር፣ ተሞክሮና ልምድ በመያዝ ወደ መሸጋገር የተቻላበቸው ናቸው፡፡

ወደ አዲሱ ዓመት እንደ የዋሆች ባዶ እጃችንን አይደለም የተሸጋገርነው፤ ከፍ ያሉትን ስኬቶች ጨብጠን፣ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል በቂ ተሞከሮ አግኝተን ነው፡፡ እነዚህ አቅሞች በአዲሱ ዓመት በሁሉም ዘርፎች የበለጠ እንድንሰራ የሚያስችሉን ጥሩ መደላድሎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You