አዲሱን ዓመት እንደ ስሙ አዲስ ለማድረግ

በየዓመቱ ለእኛ እንቁጣጣሽ፤

ደስ ይበለን እንኳን ደህና መጣሽ፤

አንዱ ዘመን አልፎ፤ አንደኛው ሲተካ

ወፎች ሲዘምሩ፤ ፏፏቴው ሲያውካካ

አተኩረው ሲያዩት፣ በስሜት ተውጠው፤

ተራሮች በሙሉ፤ በአደይ አበባ አጊጠው፤

ይህ በርካታ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን ሲቀበሉ እያዜሙት የሚቀበሉት የዘመን መለወጥ ብስራት መገለጫ ነው። በዚህ ዝማሬ ውስጥ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ሕይወት፣ አዲስ ንጋት አዲስ ማለዳ፣ አዲስ ህልምና ራዕይ ስለመኖሩ አመላካች ነው፡፡

በአንድ ወቅት አቶ ብሩክ በርሄ የተባሉ ፀሃፊ የአዲስ ዓመት መግቢያን አስመልክተው፣ በአንድ ጽሁፋቸው ላይ እንዳስቀመጡት፤ ”በወርሃ መስከረም መግቢያ ዕፅዋት ይለመልማሉ፡፡ ሰዎች በብሩህ ተስፋ ይሰንቃሉ። በዋዜማው በደመራ ዙሪያ ሰፈርተኞች ከበው መልካም ምኞት ይለዋወጣሉ፡፡ ህፃናት ይቦርቃሉ። አባቶች፤ ዝናቡን ዝናበ ምሕረት፣ እህሉን እህለ በረከት ያድርግልን፣ ሰላም ይስጠን፣ እህል ይታፈስ፣ ገበሬ ይረስ፣ አራሽ ገበሬውን፣ ሳቢ በሬውን ይባርክ… በማለት ይመርቃሉ።››

”በዚህ ውስጥ የምንረዳው ማህበረሰቡ ለአዲስ ዓመትና ለውብ ተፈጥሮ ያላቸው ቁርኝት ብርቱ ስለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የጥበብ ስሜት ይበልጥ ለተፈጥሮ ታዛዥ ሲሆንም ይታያል፡፡ ለዚያም ይመስላል፤ ከጥንት ጀምሮ ጥበበኞች በስራዎቻቸው መስከረምና አዲስ ዓመትን አሳምረው ያወድሱት ሲሉም ይገልጹታል ››

ከክረምት ክራሞት ወደ አዲስ ዓመት መንደርደሪያ በመሆኑ ብዙዎች ይህን ወር ለየት አድርገው ይመለከቱታል፡፡ መስከረም ብዙ ነገሮች ፍንትው ብለው የሚለዩበት ወቅት ነው። ዝናብ ሲዳሸው የከረመው ቄጠማ ከጭቃው ተላቆ እጅብ ብሎ ይታያል። በየተራራው የአደይ አበባ ፍካት እይታን ሰቅዞ ይይዛል፡፡

ክረምቱ ለሰብል የተመቸ እንደሆነ አብዛኞቹ የሰብል ቡቃያዎች ከሚጠበቀው በላይ የሚያምሩና የተሻለ ምርት ሊሰጡ እንደሚችሉ በአርሶ አደሮች ዘንድ እንዲሁ ይታመናል፡፡ ይህን ለመረዳት ደግሞ ወደ ገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል በመሄድ ከአርሶ አደር ጋር መዋል መነጋገር ግድ ይላል፡፡

ወርሃ መስከረም ተማሪዎችም አዲስ ዓመትን ከተለመደው ከፍ ባለ ሁኔታ አዲስ ውጤት ለማስመዝገብ፣ አርሶ አደሩም ምርቱን ለመዛቅ የሚቋምጥበት ክረምት በዘራው ቡቃያ የሚመካበት፣ መምህሩን ጠመኔውን ጠንክር አድርጎ ይዞ ብዙ የአገር ተረካቢ ባለአደራዎችን ለማፍራት የሚተጋበትና ሁሉም በየሥራ ዘርፉ ውጤት የሚገኝበት እንደሚሆን በማመን በአዲስ መንፈስ በአዲስ እቅድ የሚነሳበት ነው፡፡

ይህን ሃሳብ እንደ መነሻ የወሰድኩት አዲሱን ዓመት እንዴት እናሳምረው ብለን ብዙዎቻችን ከወዲሁ በልባችን ስለምናስበው አብዝተንም ስለምንጨነቅ ነው፡፡ በርካቶቻችን አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ወይም ወደ አዕምሯችን ሲመጣ ወይንም በአካል ስንቃረብ ዕቅዳችን ስፍር ቁጥር የሌለው ነው፡፡ አንዱን ስናነሳው አንዱን ስንጥለው የሚሆነው ሁሉ ይቸግረናል፡፡

አዲስ ዓመት አዲስ እሳቤ መያዝ የሚበረታታ፤ የሚደገፍም ሃሳብ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ዘመን ስለተለወጠ ብቻ ለውጥ ይኖራል ብሎ ማሰብ ብቻውን የዋህነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት አገር ታቅዳለች፤ ድርጅቶች ያቅዳሉ፤ ግለሰቦችም እንዲሁ በየፊናቸው ያቅዳሉ፡፡ ቁም ነገሩ ግን እቅድን ከማቀድ በዘለለ ያቀዱትን ለመፈጸም ምን ማድረግ አለብን የሚለውን በቅጡ መረዳት ተገቢ ነው፡፡

እቅድ ልክ እንደሚታሰበው ተግባር ወለድ የሚሆነው አዕምሮ በማድረግ እና ባለማድረግ መካከል ያለውን ክፍተት በማሸነፍ ወደ ማድረግ ሲለወጥ ነው፡፡ በመፍራትና በመትባት መካከል ያለውን ልዩነት ልብ፤ በልበ ሙሉነት መፍራትን አሸንፎ ማድረግን ሲላመድ ነው፡፡ የማይሳኩ የሚመስሉ ነገሮችን በቁርጠኝነት ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ ዕቅድ አዕምሮ አምጦ የወለደው ሃሳብ ወደ ተግባር በመቀየርና ባለመቀየር የሚወሰን ነው፡፡

በመሆኑም አዲስ ዓመት ሲመጣ ማቀድ ብቻ ሳይሆን እቅድን በተግባር መመለስ መቻል ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ስታቅድ ተቋማትም እንደ ተቋም፤ ግለሰቦችም እንደ ግለሰብ ሲያቅዱ በጥልቀት ማቀድ፤ ከማቀድም በዘለለ የሚተገበር መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

ሰው የእቅዱ ባሪያ ነው፡፡ ያቀደውን ካሣካ ህልሙን አሸንፏል ወይንም ህልሙን እየኖረ ነው ማለት ነው፡፡ እንደ ሀገር የምናስባቸው ለውጦች ሊሳኩ የሚችሉትም በአዲስ ዝማሬ እና ተስፋ ስለታጀበ ሳይሆን በልበ ምሉዕነት ወደ ትግበራ ሲቀየሩ ነው። ተግባር የመፍትሄ አካል ነው፤ ተግባር የልብ መሻት የሚገለፅበት ውብ ደሴት ነው፡፡ ተግባር የማይሆን የሚመስለውን በመሆን ወይንም በድርጊት የሚገለፅበት ሁነኛ የልብ ማረፊያ ነው፡፡ በመሆኑም እቅዶቻችን በመሉ በተግባር የተደገፉ ሲሆኑ አዲስ ዓመትም አዲስ ይሆናል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከልብ መሻት የዘለለ ርባና ቢስ መሆን ነው፡፡

አዲስ ዓመት ከማህበረሰቡ አስተሳሰብና ሥነ-ልቦና ጋር የተጋመደ ነው፡፡ እቅዶቹም የሥነ ልቦና እና ጥልቅ የእሳቤ ትስስር ውጤት ናቸው፡፡ የሰዎችን የማድረግ እና የመሆን እሳቤ መለወጥ ይጠይቃሉ። ከሁሉም በላይ ነገሮች ሆነው የማየትን ሁለንተናዊ ዝግጁነትና ቁርጠኝነትን ይፈልጋሉ።

እራስን ከትናን ዛሬ ላይ ለውጦ መገኘትን፤ በተለወጠ ማንነት በተጨባጭ በተግባር መገለጥን ይፈልጋል። ለውጡ እና የለውጡ ውጤታማነት እንደየ ሁኔታው የሚለያይ ነው። አንዳንድ ለውጦች ሊመጡ የሚችሉት በሂደት ነው፤ እነሱን ለማምጣት የሚደረግ ጥረትም በተወሰነ ጊዜ ተከናውኖ የሚያበቃ አይደለም። ከዚህ አንጻር የተቋማት ግንባታ ወሳኝ አቅም በመሆን ያገለግላል።

ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር የጀመርነው ለውጥ ዓመታት እያስቆጠረ ነው። በዚህ የዓመታት ሂደት ውስጥ መሆን የፈለግነውን እየሆንን ከሆነ መልካም፤ ካልተቻለን ግን ቆም ብለን በአግባቡ ማሰብ ይኖርብናል። ችግሩን ለመፍታትም ተወደደም ተጠላም ወደ ራሳችን ማየት ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ አሁን ትክክለኛው ወቅት ነው። አዲሱን ዓመትም እንደ ስሙ አዲስ ለማድረግ ያለው አማራጭ ይኸው ነው።

ዶክተር ጀኔኑስ

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You