‹‹ሀገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን በነፃነት በመጠቀም ለማደግ የሚያደርጉት ጥረት የማይዋጥላቸው በርካቶች ናቸው››አዳነች ያሬድ (ዶ/ር) በናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ የናይል ቤዚን ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ቀጣናዊ አስተባባሪ

አዳነች ያሬድ ዶ/ር የተወለዱት በጌድኦ ዞን ነው። የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ‹‹በሃይድሮሊክ ኤንድ ወተር ሪሶርስ ኢንጂነሪንግ›› ፤ የሶስተኛ (ዶክተሬት ዲግሪያቸውን) ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ኢንስቲትዩት (Ethiopian Institute of Water Resources) አግኝተዋል፡፡

ዶክተሯ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ብሎም አዲስ አበባ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስተምረዋል እስከ ረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግም ደርሰዋል፡፡ ከትምህርት ተቋማት ውጭ የተፋሰሶች ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የቴክኒካል ኮሚቴ አባልና ተደራዳሪም ነበሩ፡፡

በአሁኑ ወቅት በዑጋንዳ የናይል ቤዚን ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ቀጣናዊ አስተባባሪ በመሆን እያገለገሉ ነው፡፡ እኛም በምሥራቅ አፍሪካ ተፈጥሮ ሀብት፣ በተለይም የውሃ ሀብት አጠቃቀምና ፍላጎቶች ዙሪያ ባሉ የሚስተዋሉ ፈተናዎችና ዕድሎች ዙሪያ ጥያቄዎችን በማንሳት እንግዳ አድርገን አቅርበናቸዋል፤ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- የህዳሴው ግድብ ላይ የነበርዎት ሚና ምን ነበር?

አዳነች ዶ/ር፡– የህዳሴ ግድብ ድርድር የበርካታ አካላት ተሳትፎ የነበረበት ነው፡፡ በግድቡ ድርድር ላይ የቴክኒካል ኮሚቴ ነበር፡፡ በዚህ ውስጥ የተለያዩ ባለሙያዎች ተሳትፈው የየራሳቸው ሚና ተወጥተዋል። የዲፕሎማሲ ሥራው ላይ ትኩረት ሰጥተው የሚሰሩ ነበሩ፤ በኃይድሮ ፓወር በኩል ጉዳዩን በዋናነት ይዘው ሲደራደሩ የነበሩበት ነበሩ። የዓባይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት የኢትዮጵውያን የኩራት ዓርማ ነው፡፡ እኔም በዚህ ውስጥ የቴክኒካል ኮሚቴ አባል ሆኜ በርካታ ዓመታት አገልግያለሁ፡፡ በጥረታችንም ጥሩ ውጤቶች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ የመልማት መብትም ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ የተቻለበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ በነበርዎት ተሳትፎ ምን የተለየ ነገር አስተዋሉ?

አዳነች ዶ/ር፡- በድርድሩ ላይ የነበው ዋነኛ ጉዳይ በአንድ በኩል የተፈጥሮ ሀብት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም ፍላጎት ጎልቶ የተስተዋለበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህ እንዲሆን ያለመፈለግ የተንጸባረቀበት ነው። እንደሚታወቀው እኛ ግድቡን ስንገነባ ዋነኛ ዓላማችን የሌሎችን ጥቅም ሳንጎዳ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ተፈጥሮ በሰጠን ሀብት መልማትና ሕዝባችንን ከድህነት አረንቋ ማውጣት ነው፡፡ ይህ አግባብ አይደለም ብለው የሚሞግቱ እና ጥቅማችን ተነካ የሚሉ ሀገራት፤ ምንም እንኳን በእኛ የመልማት ፍላጎት ጥቅማቸው ባይነካም በውሃ ሀብቱ በብቸኝነት ለመጠቀም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፡፡

በድርድሩ ማስተዋል የቻልኩት አንድ መሠረታዊ ነገር ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ብዙ መሥራት እንደሚገባ ነው፡፡ እኛ የሚገባንን እንኳን ሳንጠቀም ሌሎች ከሚገባቸው በላይ የመጠቀም ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም የኢትዮጵያን የመልማት መብት ለማስከበር የተደረጉ ድርድሮች ፍሬያማ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህ መጠናከር ያለበት ጉዳይ ነው፤ ተፈጥሮ የቸረንን ሀብት ከመጠቀም አኳያ ግን ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።

አዲስ ዘመን፡- ከድርድሩ ባሻገር የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሀብትን በፍትሃዊነት ለመጠቀም ያላቸውን ቁርጠኝነት ምን ይመስላል?

አዳነች ዶ/ር፡- ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትከተለው የነበረው አካሄድ ይታወቃል፡፡ አሁንም የምትከተለው ለዘመናት ከመጣችበት አካሄድ ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ የነበረው አካሄድ እና አሁንም ያለው ፍትሃዊነትን የተላበሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም መብት እንዳላት የሚታወቅ ቢሆንም ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ መሆኑን ትገነዘባለች፡፡

ድርድሩ ቢኖርም ባይኖርም በፍትሃዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሀገር ናት፡፡ ይሁንና አንዳንድ ሀገራት ይህ የኢትዮጵያ አካሄድን አይቀበሉትም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያት አላቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ለዘመናት የማይገባቸውን ሲጠቀሙ ነበር፤ አሁንም እርሱን ማስቀጠል ይፈልጋሉ፡፡ መሰል አስተሳሰቦች ደግሞ በአንድ ቀን ወደ መደበኛ አስተሳሰብ አይመለሱም። ይህ እንዲሆን ጉዳዩ በቀዳሚነት የሚመለከታት ኢትዮጵያ በግልጽ ማሳወቅና ሀገራዊ ጥቅምን ማስከበር አለባት፡፡

አዲስ ዘመን፡- አሁንም ድረስ አንዳንዶቹ እያፈነገጡ ቢሆንም ውይይቶች እንደቀጠሉ ነው፡፡ ይህን እንዴት ይታያል?

አዳነች ዶ/ር፡- የሚያስተሳስር ጉዳይ እስካለ ድረስ የሚመለከታቸው አካላት መወያየታቸውን አያቆሙም። በዚህ ረገድ እኛም ሆነ የታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ያቆራኘ ነገር አለ፤ የዓባይ ውሃ፡፡ ይህ አለ ማለት ደግሞ የግድ መወያየትና መነጋገር አለብን ማለት ነው። ይህ አስፈላጊ የሚሆነው ደግሞ ለጋራ ተጠቃሚነት የጋራ ውይይትና መፍትሄ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡

የዓባይ ጉዳይ እስካለ ድረስ ከእነዚህ ሀገራት ጋር መነጋገራችን አይቀሬ ነው፡፡ ዋናው ነገር ድርድር ወይንም ውይይት ለምን ተካሄደ ወይንም እንዴት ይካሄዳል የሚለው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ምን ማድረግ አለባት፤ አካሄዷ ምን ይመስል፤ ምን ትጠቀማለች የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው።

በዚህ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለመልማት የጀመረችው ጉዞ የሚበረታታ ብሎም ብሄራዊ ጥቅሟና መብትን መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ ዙሪያ በመሠረታዊነት ሊታወቁ የሚገባቸው ነጥቦች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የሚያገናኙን ወይንም የሚያስተሳስሩ ጉዳዮች በመኖራቸው ከላይኛው ሆነ ከታችኛው የአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ጋር መነጋገር ግድ ነው፡፡

ሁለተኛው ከማናቸውም አካላት ጋር የሚደረገው ድርድር ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አኳያ መመርመር ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር የሚደረገው ጥረት ምን ይመሰል የሚሉት ናቸው። ቀደም ሲል ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮችም በዚህ አግባብ ሲከናወኑ የነበሩ ናቸው፡፡ በድርድሩ ላይ የሌሎች አቋም ምንም ይሁን ምንም መወያየት አይከፋም፡፡ ከውይይቶችና ድርድሮች በመነሳትም ኢትዮጵያ ምን መሥራት እንዳለባት የጠራ ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ ድርድር ለመጀመር በግብፅ በኩል ፈቃደኝነት አሳይታለች። ይህ ለኢትዮጵያና ለተፋሰሱ ሀገራት ምን ትርጉሙ ይኖረዋል?

አዳነች ዶ/ር፡- ድርድር ወይንም ውይይት በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ችግር የለውም፡፡ በመርህ ደረጃም ከውይይት መግባባት ላይ የሚያደርሱ መንገዶች ስለሚገኙ የሚበረታታ ነው፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ቀደም ብሎም ቢሆን በድርድር ታምናለች፤ በዚሁ መንገድም ስትሠራ ቆይታለች፡፡ አሁን ከግብጽ በኩል የታየው ፍላጎትም ችግር የለውም፡፡ ቁምነገሩ ድርድሩ በምን ሁኔታ እና ለምን የሚለው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት በርካታ ውጣ ውረዶችን በድል እየተወጣች የመጣች ነች። በድርድሩ ላይ ብሄራዊ ጥቅሟን በማስከበር እና ዓለም አቀፍ መርሆችንም በአግባቡ በማክበር በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድም እውነታውን ለማስረዳት ትልቅ ጥረት አድርጋለች፡፡ ይህ በቴክኒካል ሆነ በዲፕሎማሲው ድርድር የተሠራው ሥራ ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

አሁንም የሚደረገው ድርድር ደግሞ የዚህ ድል ውጤት እና ተከታይ ክፍል ነው፡፡ በመሆኑም በመርህ ደረጃ ድርድር ማድረጉ ይጠቅም ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም፡፡ ዋናው ነገር እነርሱ ተስማሙ አልተስማሙ ስራችንን መቀጠል አለብን። ነገ መስማማት ይመጣል።

 እኛ ያደረግነው ሌሎች ሀገራት ከሚያደርጉት የተለየ አይደለም፡፡ በመሆኑም እንደራደር የሚለው ጥያቄ መምጣቱ ከዚህ በፊት ከነበራቸው አቋም አንጻር ችግር የለውም፡፡ ድርድሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም የሚያስነካ አይደለም፤ የመሆንም ዕድል የለውም። በዚህ ዙሪያ የእኛ ተደራዳሪዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርገው እንደሚሄዱ በአግባቡ መታወቅ አለበት፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዓባይን ወንዝ ጨምሮ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንን በቀጣይ ለመጠቀም በምናደርገው ጥረት ሊገጥሙን የሚችሉ ፈተናዎች ምን ሊመስሉ ይችላሉ?

አዳነች ዶ/ር፡- ይህ እውነት ነው፡፡ የዓባይ ወንዝን ጨምሮ በርካታ ወንዞቻችን ድንበር ተሻጋሪ ናቸው። አሁን ላይ ትኩረት የተደረገው በዓባይ ግድብ ላይ ነው፡፡ በዚህ አንድ ነገር ማወቅና መረዳት ተችሏል። እንደ ሀገር ያለንን የመደራደር አቅም በትልቁ ማየት ተችሏል፡፡ አሁን የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን (የውሃ ሀብታችንን) ለመጠቀም ስንነሳ ከፍ ያለ ተቃውሞ እያጋጠመን የመጣው፤ አንደኛው ተፈጥሮ የቸረችንን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀማችንና ሌሎች ለዘመናት ሲጠቀሙ መቆየታቸው ነው፡፡ እኛ የበይ ተመልካች ሆነን በመኖራችን ነው፡፡ ለዚህ ነው በዛሬ በጥቂቱም ቢሆን ሀብታችንን እንጠቀም የሚለው አካሄዳችን ዕረፍት ይነሳቸዋል፡፡

ሁለተኛው ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና መፍጠር የሚፈልጉ አካላት በርካቶች መሆናቸውን ነው፡፡ እኛ ግን አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ የተፈጥሮ ሀብቶቻችን የሌሎችን መብት ሳንነካ እና የዓለም አቀፍ ሕጎችን ሳንቃረን መጠቀም የምንችል መሆናችንን ማሳየት ነው፡፡ ዋናው እና አስፈላጊው ነጥብ ግን እኛ እነዚህ ድንበር ተሻጋሪ ስለሆኑ እንጠቀም ብለን መነሳት የለብንም፡፡ ዋነኛ ትኩረታችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ማተኮር ነው። እኛ በዚህ ላይ ያለን አቋም እና ዓለም አቀፍ ሕጎችን የምናከብርበትና የምንተገብርበት ሁኔታ ወሣኝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለመጠቀም እንዴት ዓይነት አሠራር መከተል አለባቸው ይላሉ?

አዳነች ዶ/ር፡- ይህ ዘመናትን የተሻገረ ፈተናም ጥያቄም ነው፡፡ በርካቶቹ ሀገራት ትልቅ ሀብት አላቸው። ሀብት ብቻ ሳይሆንም በጂኦ ፖለቲክስ ያሉበት ቀጣና ተፈላጊ ቀጣና ነው፡፡ ይሁንና ግን በተፈላጊነቱ ደረጃ የበለፀገ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ኢትየጵያ ካላት የተፈጥሮ ሀብትና የመልማት አቅም አንፃር እጅግ ብዙ ወደ ኋላ ቀርታለች፡፡ ስለዚህ ይህን ለመለወጥ የሚያስችል አዲስ ዕይታ ይፈልጋል፡፡

የዕድገትና ትብብር ማዕቀፎች መጠናከር አለባቸው። ቀጣናው ለማደግ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ትልቁ ማነቆ ቴክኖሎጂ እና ፋይናንስ ነው። ይህን እንዴት መፍታት ይቻላል በሚለው ላይ ልዩ ትኩረት መስጠትና ብስለት የተሞላው አካሄድ መከተል ግድ ይላል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሂደት ውስጥ የዓለም ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት ሚና ምን ሊሆን ይችላል?

አዳነች ዶ/ር፡- ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ተቋማት የየራሳቸው ዓላማ አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ብቻም ሳትሆን ሌሎች ሀገራትም ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ አይፈለግም፡፡ ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገራት የውሃ እና ሌሎች ሀብቶቻቸውን ሳይንሳዊ እና በተጠና መንገድ መጠቀም ከጀመሩ ከጥገኝነት እየተላቀቁ ይሄዳሉ ማለት ነው፡፡ ይህን ደግሞ ፈጽሞ መቀበል የማይፈልጉ አካላት አሉ፡፡ በመሆኑም ወሣኝ ለሚባሉ የልማት አውታሮች ብድር አይፈቅዱም፡፡ አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት እየተጠቀመች አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ ዘመናትን የተሻገረ እና የተከማቸ የቤት ሥራ ስለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡

ይህን ፈተና ነው ብሎ ከመቀመጥ ሌሎች የፋይናንስ አማራጮችንና አሠራሮችን መከተል ያስፈልጋል። የቀኝ ገዥዎች ፍላጎትም በዚሁ ውስጥ ጎልቶ ይወጣል። ሲገዟቸው በነበሩ ሀገራት ውስጥ ተፅዕኖ ማሳደር ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የአፍሪካን ዕድገት የመወሰን ፍላጎታቸው አሁንም አለ ማለት ነው። በአጠቃላይ ለማደግ በሚደረገው ግብግብ ብዙ ፈተናዎች አሉ፡፡ እነዚህ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ደግሞ መፍትሄ ካልተሰራላቸው የታሰበውን ማሳካት አይቻልም ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት የሚባል ነገር አለ ፤ እውነት የውሃ ማማ ናት?

አዳነች ዶ/ር፡- እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የውሃ ማማ ናት፡፡ ይህ ማለት ግን የተከማቸ ውሃ ወይንም ውሃ የሞላበት ምድር ናት ማለት አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የውሃ ምንጭ 80 እስከ 90 ከመቶ የሚሆነው በሰሜናዊ ምዕራብ አካባቢ በዓባይ እና ባሮ አካባቢ ባሉ ተፋሰሶች ውስጥ ነው። በዚህ አካባቢ የሚኖረው የሀገሬው ህዝብ ብዛት 40 ከመቶ ነው፡፡ እንግዲህ በዚህ ተፋሰስ ያለው ውሃ የገፀ ምድር ሲሆን ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ አይቀርም፡፡ ይልቁንም ከታችኛው የተፋሰሱ ሥፍራ የሚገኙ ሀገራት የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ውሃው ቀጥታ ወደ እነርሱ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የውሃ ምንጭና ማማ ናት ማለት ውሃው በሙሉ እኛ ዘንድ ይከማቻል ማለት አይደለም፡፡

በኢትዮጵያ የምስራቁ ክፍል ሰፊ ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን በዚህ አካባቢ ደግሞ 10 እስከ 20 ከመቶ ብቻ ነው የዝናብ መጠኑ፡፡ ይህ ማለት ሰፊ ህዝብ ውሃ በአግባቡ እያገኘ አይደለም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ ሀገራት ለምን ኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ውሃ አትጠቀም ብለው ይከሳሉ፡፡

እውነታው በምልክዓምድራዊ አቀማመጥ ሳቢያ ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ከምትጠቀመው ይልቅ ሌሎች የሚጠቀሙት ይበልጣል፡፡ ስለዚህ በዚህ አግባብ የውሃ ማማ ናት የሚለውን መረዳት ይገባል። በመሆኑም ወቀሳም ውሃ አይቋጥርም፡፡ ይህን ተጠቀሚ ይኸኛውን አትጠቀሚ የሚል አካልም ሊኖር አይገባም፡፡

አዲስ መዘመን፡- በእርሶ እይታ በምስራቅ አፍሪካ የሚስተዋለው ፈተና ምክንያቱ ምንድን ነው?

አዳነች ዶ/ር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ወይንም ምስራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ የተፈጥሮ ሀብትን በነፃነት በመጠቀም ሀገራት ለማደግ የሚያደርጉት ጥረት የማይዋጥላቸው በርካቶች ናቸው። በምስራቅ አፍሪካ ያለው የቀኝ ገዥዎች ፍላጎት ምን ይመስላል ብሎ መገምገም ተገቢ ነው፡፡ በተጨማሪም አሁናዊ ሁኔታዎች ወደየት ያመላክታሉ፤ ያለፉትስ ምንድን ነበሩ፤ በቀጣይስ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ መተንተን ጠቃሚ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ጉዳይ በተለይ ለማየት ስንሞክር፤ እንደ ሀገር ያለንበትን ሁኔታ መገምምና መረዳት ተገቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይሹ በርካቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሀብቷን በመጠቀም እድገት እንዲኖራት አይፈልጉም፡፡ ይህም በመሆኑም ኢትዮጵያ ታድግበታለች ወይንም ህዝቦቿ ይለወጡበታል ተብለው የሚታሰቡ መንገዶች ሁሉ ዝግ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡

ለአብነትም ለህዳሴው ግድብ ብድር ለማግኘት በዓለም ላይ ታላላቅ አበዳሪ አካላት በሙሉ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይህ የሚያመለክተው የራሳችንን ሀብት ለመጠቀም በምናደርገው ጥረት ፈቃድ እንድንጠይቅ የሚፈልጉ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩ በጎ ዕድገቶችን የማይፈልጉ አካላት የፋይናንስ ምንጮችና ገንዘብ አማራጮች እንዳይኖሩን የራሳቸውን ድብቅ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በቀጣናው ያለው ከፍተኛ ሀብት ወደ ጥቅም ሲቀየር ቀጣናው የመለወጥ አቅሙ ትልቅ ነው፡፡

ይህ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ለውጥ ደግሞ በትልቁ ከኢትዮጵያ ዕድገት የሚመነጭ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ይህ የማይዋጥላቸው በርካታ አካላት በተቻለ መጠንና አቅም ማደናቀፍ እንደሚፈልጉ መረዳት ያስፈልጋል። እነዚህ እና ሌሎች ፈተናዎች ተደማምረው ሊፈትኑን ይችላሉ፡፡ ይሁንና ግን በረጅም ጊዜ ራዕይ በመንደፍ እና ሀገራዊ ጥቅምን በማስከበር ኢትዮጵያን አሸናፊ ማድረግ ይችላል፡፡ አሁናዊ ፈተናዎች የነገ የጥንካሬ መሠረት መሆናቸውንም ማስተዋል ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል ለመወሰንና የተፈጥሮ ፀጋን ለመጠቀም ከምሁራንና መንግሥት ምን ይጠበቃል?

አዳነች ዶ/ር፡- ይህ መሠረታዊ ጥያቄ ነው። ከሁሉም ቀድሞ መምጣት ያለበት ጉዳይ ብሄራዊ ጥቅም ነው፡፡ ይህን ይሆን ዘንድ ደግሞ ሁሉም በየሙያ መስኩ መሥራት አለበት፡፡ ያለን የተፈጥሮ ሀብት ከመጠቀም አኳያ ብዙ አልተጓዝንም፤ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

የኢትዮጵያን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ከሚወስኑ ሀብቶች አንዱ የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ነው፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ምሁራን ሚናቸው ትልቁን ስፍራ ይይዛል፡፡ በመረጃ የዳበሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን ማከናወንና ለቀሪው ትውልድ ጭምር ማስቀመጥ ይገባል፡፡ ሀገራችን ያላትን ሀብት እንዴት፣ በምን ሁኔታ እና በምን ዓይነት መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል አለብን የሚለውን ሳይንሳዊ ትንታኔ በታከለበት መንገድ መመለስ ይገባል፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ምሁራን በሚያመጧቸው የጥናት ውጤቶች መሆን አለበት፡፡

እኛ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ያልሠራናቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ የዓባይ የታችኛው ተፋስስ ሀገራት በዓባይ ውሃ ላይ በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል፡፡ ከጥናትም ባሻገር በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እኛ ገና በጥቂቱ ለመጠቀም ስንጀምር እንኳን ፈተናዎች በርክተዋል። ይህ የሚያመለክተው ገና ሀብታችንን በአግባቡ አለመጠቀማችን ብሎም በዚህ ላይ የበሰሉ ጥናቶችን አማድረጋችን ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ምሁራን የጠለቀ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡

መንግሥትም ቢሆን ሚናው ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የሚነሱ አከራካሪ ነጥቦች ብዙ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፎች በአግባቡ እንዲተገቡ ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ በርካታ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እንደ መንግሥት እየተሠሩ ሲሆን፤ በቀጣይ ከዚህ በበለጠ ለመሥራት ፖሊሲዎችን መንደፍ፤ ምሁራንን ማሳተፍ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ መለየትና መጠቀም አስፈላጊ ነው።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ አሁን ባሉበት ቀጣናዊ ተቋም ውስጥ ሆነው የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር እስከምን ድረስ ይሠራሉ?

አዳነች ዶ/ር፡– እኔ አሁን የምሰራው እንደ ምስራቅ አፍሪካ ቢሆንም ለሀገሬ ጉዳይና ጥቅም ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ በመሠረቱ የምስራቅ አፍሪካ ዕድገት መሠረቷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች የምታስመዝግበው ዕድገት እና ልማት ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል፡፡

በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም እንዲከበር ቀደም ሲል ስሠራ ነበር፤ አሁንም እየሠራሁ ነው፤ የአገር ጉዳይ ሁሌም በትኩረት የሚሠራ እንጂ በአንድ ሰሞን እንቅስቃሴ የሚገደብ አይደለም። እንደ ሀገር ያሉንን መልካም ዕድሎችን ወደ ውጤት እንዲቀየሩ፤ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር በሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጌ እንቀሳቀሳለሁ፤ በቀጣናዊ ጉዳይም የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲጠበቅና እንዲከበር ብሎም ሃሳቧ ተደማጭነት እንዲኖረው እየሠራሁ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ላደረጉት ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አዳነች ዶ/ር፡- እኔም እንግዳችሁ ስለሆንኩ የጋራና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ እንድሰጥ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን  መስከረም 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You