ኔቶ አባል ሀገራቱን ለረጅም ጊዜ ጦርነት እንዲዘጋጁ አሳሰበ፡፡

ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከ570 ቀናት በላይ አስቆጥሯል፡፡ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶ መጀመሪያ ላይ በተዘዋዋሪ ዩክሬንን ይረዳ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን በቀጥታ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኔቶ ዋና ጸሀፊ ጀንስ ስቶልትንበርግ እንዳሉት የጥምረቱ አባል ሀገራት ራሳቸውን ለረጅም ጊዜ ጦርነት እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል ተብሏል፡፡

ፖለቲኮ ዋና ጸሀፊውን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዘገባ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የጀመረችው ጦርነት በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ዋና ጸሀፊው ጦርነት ሲጀመር ቶሎ እንደሚያልቅ ይገለጻል፤ ነገር ግን የትኛውም የዓለማችን ጦርነት በተባለበት ቀን ተጠናቆ አያውቅም እንዳሉም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡

ዩክሬን ከኔቶ እና ሌሎች ሀገራት በሚደረግላት ድጋፍ አማካኝነት ወደ ሩሲያ ዘልቃ በመግባት የድሮን ጥቃት በማድረስ ላይ የምትገኝ ሲሆን ሩሲያም የአጸፋ እርምጃዋን በመውሰድ ላይ ትገኛለች፡፡ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እንዲቆም የግድ ሞስኮ ውጊያ ማቆም አለባት ያሉት ዋና ጸሀፊው ዩክሬን ጦርነት ብታቆም ህልውናዋ ያከትማል እንጂ ሰላም አይመጣም ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ዩክሬን በበኩሏ ምዕራባውያን ሀገራት የጦር መሳሪያ በፍጥነት እንዲያስተላልፉ አሳስባ ይህ ካልሆነ ግን ሩሲያ ጦርነቱን እንድትገፋበት እንደማበረታታት ይቆጠራል ማለቷ ተገልጿል፡፡

ዩክሬን በግዛቷ ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን ለማስወጣት የመልሶ ማጥቃት እያደረገች ሲሆን ወደ ሩሲያ ግዛቶች በመዝለቅ ደግሞ የነዳጅ እና ወታደራዊ ማዘዣዎችን ኢላማ በማድረግ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You