የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች የደቀኑትን አደጋ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፡- አዳዲስ የወባና ትንኝ ወለድ በሽታዎች በአፍሪካና በኢትዮጵያ የደቀኑትን አደጋ ለመቆጣጠር እየተሠራ መሆኑን የፓን አፍሪካ የወባ ትንኝ መቆጣጠሪያ ማኅበር የኢትዮጵያ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ድልነሳው የኋላው አስታወቁ፡፡

ወባንና ሌሎች ትንኝ ወለድ በሽታዎችን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል በሚል ዙሪያ በተካሄደ ጉባዔ ላይ ፕሮፌሰር ድልነሳው እንደገለጹት፣ በአፍሪካ የወባ ወረርሽኝ ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በቁጥጥር ሁኔታው የተሻለ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት እያገረሸ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያልነበሩ በትንኝ የሚተላለፉ አንዳንድ በሽታዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ነው ያሉት ኃላፊው፤ ደንጌ የተባለ በኤዥያ ብቻ የነበረ በሽታ እ.ኤ.አ ከ2013 ዓ.ም ወዲህ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በመከሰት በመላው ኢትዮጵያ እየተስፋፋ ይገኛል በማለት ለአብነት አንስተዋል፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፣ አዳዲስ የወባ ትንኞች ከሌሎች አህጉሮች እየመጡ በአፍሪካና በኢትዮጵያ እየተስፋፉ ነው፡፡ የወባንና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ለመቆጣጠር አቅም በመገንባትና በጋራ በመሥራት በአፍሪካና በኢትዮጵያ የተደቀነውን አደጋ ለመቆጣጠር ምክክር እየተካሄደ ነው፡፡ እንዲሁም ትልቅ ስጋት በመሆኑ እንደ አፍሪካና ኢትዮጵያ ብዙ ሥራ መሥራትን ይጠብቃል ብለዋል፡፡

አዲስ የወባ ትንኝ ማስተላለፊያዎች የሚራቡበት ሥነ ምህዳር ምን ይመስላል የሚለውን በጥናት በመለየት ለመቆጣጠር ባህሪው አለመታወቁ፣ እንዴት እንደሚተላለፉና ባህሪያቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል ብለውም፤ ችግሩን አውቆ ለመቆጣጠርና ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ፤ እንደ ቅልጥም ሰባሪና ቢጫ ወባ ያሉ የወባ ትንኝ በሽታዎች ለዓመታት በተወሰነ የኢትዮጵያ ክፍል ብቻ የሚገኙ ሲሆኑ የተጠቂውም ቁጥር ዝቅተኛ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍጥነት በመስፋፋት በበሽታው የሚጠቃው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በኤዥያና በገልፍ አካባቢ የሚገኝ አኖፌሌስ ስቴፈንሲ የወባ አስተላለፊ ትንኝ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ በጀቡቲ ተከስቷል፡፡ በመቀጠል ከ2016 ጀምሮ በኢትዮጵያ 51 አካባቢዎች ተሠራጭቶ ይገኛል፡፡ እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ አልፎ በምዕራብ አፍሪካ ተሰራጭቷል፡፡ ወባን ከሚያስተላልፉ ነባር የወባ ትንኞች የሚለየው በአብዛኛው ከተማ ላይ የሚራባ ሲሆን ዘወትር የሚጠቀማቸው በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ባሉ ቁሶች ላይ የሚራባ በመሆኑ ትልቅ ስጋት የደቀነ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ጥናቶች እየተካሄዱ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትና በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለጥናትና ምርምር ለፖሊሲ ግብዓት እንዲውል የማድረግና ምክረ ሃሳብ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የፓን አፍሪካ ወባ ትንኞች መቆጣጠሪያ ማኅበር በኢትዮጵያ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን አቅዶ እየሠራ ነው፡፡ ከጤና ሚኒስትር ጋር በመተባር በመሥራት ወደፊት የወባንና ትንኝ ወለድ በሽታዎች ለመቆጣጠርና ለማስወገድ በጋራ መሥራትና እቅዱን ይፋ የማድረግ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል፡፡

ሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You