«የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች በማልማት እድገትና ብልጽግናን የማረጋገጡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል»የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች

 አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች በማልማትና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ።

ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች «ከዕዳ ወደ ምንዳ» በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በሥልጠናው ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን «ሀብት መፍጠር እና ማስተዳደር» በሚል መሪ ሃሳብ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ በርካታ የልማት ክንውኖች መኖራቸውን እንደተመለከቱ ጠቅሰው፤ የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አመራሩን ጨምሮ የሕዝቡ ትብብርና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሀብቶች በማልማትና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አመራሮቹ የተናገሩት።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ በሁሉም መስክ ያሉ የኢትዮጵያ እምቅ ሀብቶችን በአግባቡ ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ በየትኛውም ጊዜ ባልታየ መልኩ የነበሩ ተግዳሮቶችን የሚያሻግሩ ሥራዎች መሥራቱን አንስተዋል።

በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ሥራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ሁሉም አመራር ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፤ ያሉንን አቅሞች በሚገባ ሥራ ላይ በማዋል ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ የብዙ ሀገራት ስኬታማ ታሪክ የሚያሳየው ይህንኑ ነው ብለዋል።

የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴም፤ ኢትዮጵያን መቀየር በአመራሩና በሕዝቡ እጅ ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑንና ኢትዮጵያ ያሏትን ሁለንተናዊ ጸጋዎች ወደ ተጨማሪ አቅም ለመቀየር በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ሀብቶች ያሏት ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ እነዚህን ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መቀየር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከአስተሳሰብ እንዲሁም ከጊዜ አጠቃቀም አንጻር አመራሩ ለአንድ አላማ ቆርጦ መነሳት እንዳለበት ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ለድንገተኛ አደጋ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በተለይም ‘ባንዴጅ’ እና ‘ጎውዝ’ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት መተካታቸውን ገልጸዋል።

ይህም ከተደራሽነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው፤ ለቀጣይ ሥራዎች ትልቅ ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ ያሉንን ሀብቶች መረዳት እና ማስተዳደር ከቻልን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል አመላክተዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ፤ ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም ከቻለች በአጭር ጊዜ ወደ ጥሪት ማፍራት መሸጋገር እንደሚቻልም ነው ያስረዱት።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ፤ ኢትዮጵያ የሰው ኃይልን ጨምሮ የማዕድን እና የታዳሽ ኃይል ሀብት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።

እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም ሀብትን በመፍጠር ሀገርን ወደ ተሻለ ብልጽግና ማምጣት እንደሚቻልም ነው ያመለከቱት።

እንደ ሚኒስትሮቹ ገለጻ የኢትዮጵያን እምቅ ሀብቶች በማልማትና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አመራሩን ጨምሮ የሕዝቡ ትብብርና የጋራ ጥረት ወሳኝ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You