አረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር -ትውልድ በላቡ እየጻፈው ያለው አዲስ ታሪክ ነው!

 በዘመናት ሂደት የሰው ልጅ ብዝኃ-ሕይወትን እያመናመነ፣ አካባቢውን እያዛባ፣ ምድርን እያጎሳቆለ የዓለምን የምቹነት ዋስትና በራሱ እጅ እየተነጠቀ እንደሚገኝ በተጨባጭ እየታየ ነው። ችግሩ ከትውልድ-ትውልድ የዕጽዋት መመናመን፣ የደን ሽፋን መራቆት፣ የአካባቢ መበከልን እያባባሰ የዓለምን ጉስቁልና እያከፋው መጥቷል።

ችግሩ የዓለምን ሕዝብ መልከ- ብዙ ለሆነ ቀውስ እየዳረገው ነው፤ በቀጣይም መጪዎችን ትውልዶች ለከፋ ዘርፈ ብዙ ፈተና ሊያጋልጥ እንደሚችል መረጃዎች በስፋት እያመላከቱ ነው። ችግሩ ከሁሉም በላይ ዛሬን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ለማለፍ እየተገደዱ ለሚገኙት አፍሪካውያን የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይህንን ዓለም አቀፋዊ ችግር፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶችን ማድረግ ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም እያስመዘገቡት ያለው ስኬት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከማትረፍ ባለፈ እንደሀገር እያስገኘ ያለው ጥቅምም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።

ከዚህ ውስጥ ለቀደሙት ለአራት አመት (2010 ዓ.ም-2014 ዓ.ም) የቆየው የመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር አንዱ ነው። በዚህ መርሐ ግብር እንደ ሀገር 25 ቢሊዮን ችግኞች ተተክሏል። በአንድ ጀንበር 350 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከልም አዲስ ታሪክ በመጻፍ፤ የዓለምአቀፍ ክብረወሰን መስበር ተችሏል። ይህም ታሪክ መሥራት ባህሉ ለሆነው ሕዝባችን ተጨማሪ ድምቀት አጎናጽፎታል።

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነበት በዚህ ዘመን ተግባራዊ እየሆነ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፣ ኢትዮጵያና መላው ሕዝቦቿን በዓለም አቀፍ አደባባዮች ከፍ ብለው እንዲታዩ አድርጓል፤ በዘርፉ እያስመዘገበች ያለው ስኬትም የብዙዎችን ቀልብ የሳበና በተሞክሮ ደረጃም ከፍ ያለ ዕውቅና እየተቸረው ያለ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት ሆኗል።

ባለፈው አመት 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር የመጀመሪያው ዓመት ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም «ነገን ዛሬ እንትከል» በሚል መሪ ሃሳብ በአፋር ክልል አስጀምረዋል፤ በወቅቱም 6 ነጥብ 5 ቢሊ ዮን ችግኞችን ለ መትከል ዕቅድ መያዙ ተገልጦ እንደነበር ይታወሳል ።

በዚሁ መርሐ ግብር፤ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደ የችግኝ ተከላ እንደ ሀገር ቀደም ሲል በእጃችን የነበረውን በአንድ ጀንበር 350 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ዓለም አቀፍ ክብረወሰን ወደ 566 ሚሊዮን ተሻሽሏል። ከዕቅዱ በላይም ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። በዚህም በታሪክ ላይ ታሪክ መሥራት የሚያስችል ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር እና ውጤታማ ማድረግ ተችሏል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ፤ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ለጀመርነው ሀገራዊ ጥረት ብርቱ ጉልበት እንደሚሆን የሚታመነው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር፤ ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ እና የሥራ ምንጭ እየሆነ ነው። በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገሪቱ ከካርቦን ሽያጭ ትርጉም ያለው ገቢ እንዲኖራት እንደሚያስችል ይታመናል።

ከዚህም ባለፈ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ከዚህ ትውልድ አልፎ ለመጪው ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ለጀመርነው ብሔራዊ ንቅናቄ ትልቅ አቅም የሚሆን ነው። በተለይም ለመጪው ትውልድ ምቹና ደህንነቷ የተጠበቀች ሀገር ለማውረስ የሚኖረው ሁለንተናዊ ፋይዳ ከቋንቋ ያለፈ በተጨባጭ እየታየ ያለ እውነታ ነው።

እንደሚታወቀው እኛ ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሂደት ውስጥ የማይቆራረጥና የማይደበዝዝ ታሪክ ባለቤቶች ነን። የእነዚህ ታሪኮች ትርክት በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ከማስታወስ ባለፈ፣ ለተተኪ ትውልዶች የብሔራዊ ክብር ምንጭ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብርም ይህ ትውልድ የታሪክ ሠሪዎቹ አባቶቹ ልጅ ስለመሆኑ ማረጋገጫ፤ ታሪክ ሠሪ ስለመሆኑ ተጨባጭ ማሳያ ነው። የሀገሩን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ለመጪዎቹ ትውልዶች ብሩህ ነገ መሠረት የሚጥል ጊዜውን የሚዋጅ በታሪክ ሂደት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ተግባር ነው።

በዓድዋ የተፈጸመው የተጋድሎ ታሪክ፣ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያን የነፃነት ቀናኢነት ታሪክ ከመዘከር ባለፈ ቀጣይ ትውልዶች በነፃነታቸውና በሉአላዊነታቸው እንዳይደራደሩ አድርጓቸዋል። የዓባይ ግድብም ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው የመወሰን መሻታቸው ቁልፍ እንደሆነ ዓለምን ባስደመመ ቁርጠኝነት በተግባር አሳይተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለምን እያስጨነቀ ባለበት በዚህ ወቅት እንደሀገር ተግባራዊ እያደረግነው ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብርም፤ እንደ ቀደሙት ትውልዶች ሁሉ ይህ ትውልድ በተለየ መልኩ በላቡ እየጻፈው ያለው፤ ዓለም አቀፍ ዕውቅናውም አሁን ላይ ጎልቶ የሚሰማ አዲስ ታሪክ ነው። ይህንን ታሪክ በበለጠ ስኬት ማስቀጠልም የአሁኑ ትውልዱ ትልቅ ኃላፊነት ነው!

 አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You