«የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንሰት በምሥራቅ አፍሪካ ሊስፋፋ ይገባል»- የኬንያ ምሁራን

አዲስ አበባ፡- የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንሰት በምሥራቅ አፍሪካ ሊስፋፋ ይገባል ሲሉ የኬንያ ምሁራን ገለፁ።

በጆሞ ኬንያታ ዩኒቨርሲቲ አግሪካልቸራል ቴክኖሎጂ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ሴልቨስተር አናሚ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ እንሰት በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ለምግብነት እያገለገለ የሚገኝ ተክል ነው። ተክሉ በዝናብ አጠር እና በድርቅ ቦታዎች መብቀል የሚችል በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምሥራቅ አፍሪካ ሊስፋፋ ይገባል።

በተለይ የእንሰት ተክልን የምግብ ውጤቶች ለማዘመን በኢትዮጵያ በሚገኘው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተሠሩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች በጣም አስደንቀውኛል ያሉት አናሚ (ዶ/ር)፤ የተሠሩት ቴክኖሎጂዎች እንሰትን በአግባቡ በማምረት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት ይደግፋል ብዬ አምናለሁ ብለዋል።

እንደ አናሚ ገለፃ፤ ኬንያ ወቅቱን የጠበቀ ዝናብ ያላት ሀገር ብትሆንም እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች አሏት። ዝናብ አጠር በሆኑ እና ድርቅ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች እንሰትን መጠቀም ሰዎች የምግብ አማራጭ እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው። እንሰት በተቀናጀ መልኩ በእንደዚህ ዓይነት አካባቢዎች በደንብ ከተዋወቀ ውጤት ማምጣት ይቻላል።

በኢትዮጵያ ከእንሰት የተዘጋጀ ኩኪስ፣ ኬክ፣ ቆጮ እና ቡላ መቅመሳቸውን ተናግረው፤ ይህን መሰል ዕሴት ጭመራ እና ምግብን በተለያየ ዓይነት መንገድ መሥራት የምግቡን ተወዳጅነት የሚያሳድግ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

በኬንያ የሴቶች እና ልጆች ዓለም አቀፍ ድርጅት ፕሮግራም ዳይሬክተር ዴኒስ ሞቲሶ በበኩላቸው፤ አፍሪካ በዓየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች መሆኑን ገልጸው፤ እንሰት ይህን የዓየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችል የምግብ ተክል በመሆኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በምሥራቅ አፍሪካ ሊስፋፋ ይገባል ብለዋል።

እኛ ኬንያውያን እንሰትን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ልምድ መውሰድ እንፈልጋለን ያሉት ፕሮግራም ዳይሬክተሩ፤ የተክሉ የምግብ ይዘት በተለይ ለሴቶች እና ለልጆች አስፈላጊ ነው ብለዋል።

«እንሰት በሁሉም በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በአጠቃላይ በአህጉሪቷ መዳረስ የሚገባው ምግብ ነው። ምግቡም ጣፋጭና ተስማሚ መሆኑን ቀምሼ አረጋግጫለሁ» ሲሉ አክለዋል።

እንደ ፕሮግራም ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በምግብ ራስን መቻል የአፍሪካ ትልቁ ችግር ነው። እንደዚህ ዓይነት የዓየር ንብረትን የሚቋቋሙ የምግብ ተክሎች ይህን ችግር ለመወጣት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ። መንግሥትም እዚህ ላይ ጠንክሮ በመሥራት እንሰት ወደሌሎች ሀገራት ኤክስፖርት የሚደረግበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል።

ውብሸት ሰንደቁ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You