የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የብዙዎች ድካም ውጤት ነው

 – የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፡- የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የበርካታ ባለድርሻ አካላት ድካም ውጤት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ትናንት በሳውዲ ዐረቢያ ሪያድ በተካሄደው 45ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቧል።

ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በ45ኛው የዓለም ቅርስ ጉባኤ ላይ በመገኘት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አለን መልዕክታቸውን በመሥሪያቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገፅ ላይ ገልጸዋል።

በመልዕክታቸውም የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የበርካታ ባለድርሻ አካላት ድካም ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ንግግር፤ የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የበርካታ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ድንቅ የተፈጥሮ ፓርክ በመጠበቅ እና በመንከባከብም ያለውን ቁርጠኝነት አጠናክሮ ይቀጥላል።

ፓርኩን ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ከማውጣትና ተያያዥ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ከማፅደቅ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ላይ ግንዛቤ በመፍጠር የፓርኩን ጥበቃ ለማስፈን ያለመ ትምህርታዊ ፕሮግራሞች ስለመጀመራቸውም ሚኒስትሯ አክለዋል።

በተያያዘ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጉዳዩን በሚመለከት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የባሌ ዞን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሮብዳ ጃርሶን አነጋግሯል። እሳቸውም የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የሕዝቡና አመራሩ ያላሰለሰ ጥረት ውጤት ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ያለ እንደ ዓለም የሌሉ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ የፓርኩ በዓለም ቅርስነት መመዝገብ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ፍሰት ከመጨመር አንፃር አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊዋ ንግግር፤ በፓርኩ የዓለም ቅርስነት መመዝገብ ሂደት ውስጥ ከዚህ ቀደም በርካታ ሥራዎች የተሠሩ ሲሆን በቀጣይም ፓርኩን የሚመጥኑ ሥራዎችን ለመሥራት ቁርጠኝነት አለ።

ለምርምር ለሕክምናና ለጌጥ መሆን ከሚችሉ እጽዋቶቹ ጀምሮ እስከ ቀይ ቀበሮ ድረስ የሚገኝበት ፓርኩ መመዝገብ ዓለምአቀፋዊ ተቀባይነቱን የሚጨምርና ከውጭ የሚመጡ ጎብኚዎች ዓይን ውስጥ በመግባት ለሀገሪቷ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከት ያስችለዋልም ብለዋል።

የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በ1962 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን የቆዳ ስፋቱ ሁለት ሺህ 150 ካሬ ኪሎ ሜትር ቦታ ይሸፍናል። የመሬት ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ ከ1500 እስከ 4377 ሜትር ይደርሳል። ብሔራዊ ፓርኩ ከ40 በላይ ለሚሆኑ ወንዞች መነሻ ሲሆን፤ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑት እንደ ዋቢሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዱመል፣ ወልመል፣ ያዶት ወንዞች ይገኙበታል። በውስጡ የኢትዮጵያ ሁለተኛ ትልቁ ተራራ ቱሉ ዲምቱም ይገኛል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You