አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያን በአረንጓዴ የማልበሱ ተግባር ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን ምግብ መትከል እና ዝናብ መጥራትም ጭምር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ። በኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር እስካሁን 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ ሁለተኛው ምዕራፍ አንደኛ ዓመት ማጠቃለያ መርሐ ግብር ትናንት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ ጆጎ ተፋሰስ ሲካሄድ ባደረጉት ንግግር፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አካባቢውን በአረንጓዴ
የማልበሱ ተግባር ዛፍ መትከል ብቻ ሳይሆን፣ ምግብና መድኃኒት መትከል፣ ዝናብ መጥራት፣ ማር ማብዛት፣ ለከብቶች በቂ የሆነ መኖ ማዘጋጀት እና የአፈር መሸርሸርን መታደግ መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለልጆቻችን ለማስተላለፍ ካሉን ሀብቶች መካከል ዋነኞቹ መሬታችን፣ የተፈጥሮ ሀብታችንና ንጹህ ውሃችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ሀብቶችን ለትውልድ ለማሸጋገር እኛ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ ትልቅ ታሪክ እየሠራን ነው ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ በአንደኛ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 7 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር እስካሁን 32 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውንም አስታውቀዋል።
ይህ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ፤ ከተረት ተረት፣ ከስብሰባ፣ ከጉባኤና አበል ከመስብሰብ ያለፈ በተግባር በዚህ ደረጃ ኢንቨስት ያደረገና ተግባራዊ እርምጃ የወሰደ ሀገር የለም ነው ያሉት።
«በአረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ ቀዳሚና አርአያ የሆነ ተግባር ፈጽማለች፤ በሁለቱ ምዕራፎች የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብሮች 50 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል ነው ያቀድነው፤ አሁን ገና ቀሪ ሦስት ዓመት አለን፤ በየዓመቱ 6 ወይንም 7 ቢሊዮን ችግኞች ብንተክል ከአቅድነው በላይ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንችላለን» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራ ዕቅድን ለማሳካት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት አምስት ዓመታት ያሳየውን ትጋት፣ የሥራ ተነሳሽነትና ውጤት መንግሥት በእጅጉ ያከብራል ብለዋል።
«አሁን ያለንበት ስፍራ ከዛሬ አራትና ሦስት ዓመት በፊት ምድረ በዳ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፤ የዚህ ወረዳና አካባቢ ሕዝብ በጥቂት ዓመታት አካባቢውን አረንጓዴ ማድረግ ችሏል፤ አሁንም አካባቢያችንን አረንጓዴ ማድረጋችንን፣ አፈር መጠበቃችንን፣ የቡና፣ የፍራፍሬ እና የሻይ ቅጠል ልማታችንን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርብናል» ብለዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና የምናረጋግጠው አፈራችንን፣ ውሃችንና ምድራችንን በመጠበቅ ጭምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያውያን ብርቱ እጆች በጽናት ታሪክ መሥራት ቀጥለዋል ብለዋል። በተጠናቀቀው የክረምት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐግብር ካቀድነው በላይ አሳክተን 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል ሲሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ ዐሻራን ከአቅድነው ቀድመን እናሳካለን፣ ዓባይ ግድብንም እናሳካለን።
«በስንዴ ጀምረን በሌማት ትሩፋት ማለትም በዶሮ፣ በማር፣ በስጋ፣ በወተት፣ በእንቁላል ተስፋ ሰጪ ሥራዎች ተከናውነዋል፤ በሚቀጥሉት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከስንዴ ብዛት የተነሳ ዳቦ፣ ከዶሮ ብዛት የተነሳ ደግሞ ስጋ የማይወደድበት ሀገር ለመፍጠር ያለንን ትልም እናሳካለን» ብለዋል።
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ያለ አስደሳች ሥራ እንድንሠራ፤ የኢትዮጵያን የድህነትና የልመና ታሪክ በሚጨበጥ የታሪክ እጥፋት ወደ ብልጽግና ጎዳና እንድንወስድ አደራ እላለሁ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞና ሁለተናዊ ለውጥ የማጽናት ጉዞ ሊያቆመው የሚችል ምድራዊ ኃይል እንደሌለ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር)፤ ለልጆቻችን ውብ ሀገር እናስረክባለን፤ ለዚህም ተግተንና ጸንተን እንሥራ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም