በብሪክስ አዲስ የዓለም ሥርዓት የመፍጠር መሻት

ዓለም በለውጥ ሥርዓት ውስጥ ናት። ከትናንት ዛሬ፣ ከዛሬ ነገ የተሻሉና በሃሳብ ሙግት ውስጥ አሸናፊዎች የሚወጡበት ምህዳር እየታየ ነው። ከዚህ አኳያ አሮጌውን ጥለን አዲሱን ለመውረስ በሰፋና በበረታ አማራጭ ውስጥ እንደሆንን መገንዘብ እንችላለን። በዙሪያችን እንደነበር የሚቀጥል ምንም እንደሌለ በብዙ አዳዲስ አስተሳሰቦች የተዋቀሩ የለውጥ ሥርዓቶችን እያስተዋልን ነው።

ከዚህ ለውጥ ውስጥ አንዱ በአራት ሀገራት ተጀምሮ በአምስት በርትቶ ወደአስራ አንድ ከፍ ያለውን የብሪክስ ጥምረት ማንሳት እንችላለን። ይሄ የሀገራት ጥምረት ነባሩ ሥርዓት እየተቀየረ መሆኑን እና እንደነበር የሚቀጥል ምንም እንደሌለ አንዱ አመላካች እውነታ ነው።

እንደፈረንጆቹ የዘመን ስሌት በ2001 መሠረቱን ጥሎ ከስምንት አመታት በኋላ በ2009 አራት አባል ሀገራትን ይዞ፣ በ2010 ደቡብ አፍሪካን አክሎ በአምስት የአባላት ቁጥር ወደሥራ የገባው ብሪክስ አሁን ላይ ብዙ የአባልነት ጥያቄዎች እየቀረቡለት ነው። የጋርዮሽ የኢኮኖሚ ጥምረትን መሠረት አድርጎ የተመሠረተው ብሪክስ በአዲስ ሃሳብ ወደአዲስ የሥርዓት እምርታ ጉዞ ላይ ነው።

በሃሳብ ማዕቀፍ ኢኮኖሚ ተኮር የጋራ ጥምረትን እንደዋነኛ ግብ አድርጎ የተነሳው ጥምረቱ በኃይል ክንድ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን በሃሳብ ሊሞግት ለሁሉም የሚበቃ፣ ከሁሉ የተውጣጣ የአንድነት ሃሳብን ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። ዓለምን በሃሳብ አካሎ ብዙኃነት ባለው የሃሳብ ማዕቀፍ ውስጥ የቆመው ብሪክስ አዳዲስ ሃሳቦችን በማመንጨትና የሥርዓት አቅጣጫዎችን በመጠቆም ለበጎና ለሁነኛ ጋርዮሽ ይተጋል ተብሎ ይታሰባል።

በዓለም አቀፍ ሃሳብ የተቧደነው ብሪክስ አፍሪካን ከዋጀ ሰንበትበት ብሏል። በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው አባልነት አንድ ሁለት ብሎ ሀገራችን ላይ አርፏል። ሰኔ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በግልጽ በተጻፈ ደብዳቤ የአባልነት ጥያቄዋን ያቀረበችው ሀገራችን በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የብሪክስ የአባላት ጉባኤ ላይ ጥያቄዋ ምላሽ ማግኘቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ሀገራችን በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ መግባቷ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን እንደሚያስገኝላት የተለያዩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ በመተባበርና በፍትሐዊነት ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ሁለንተናዊ እድገት ለማስመዝገብ ይረዳል የሚሉት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ለአዲስ ዘመን በሰጡት ቃለ መጠይቅ ነው። የቀድሞ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አምባሳደር ጥሩነህ ዜናም፤ ‹የብሪክስ አባልነት ከዲፕሎማሲው አንጻር ላለፉት አምስት አመታት ያልታየ ስኬት ነው› ብለውታል።

እኚህንና መሰል በረከቶችን ይዞ እንደሚመጣ የሚታሰበው የአባል ሀገራቱ ጥምረት ከኢኮኖሚና ከመሰል ትሩፋቶቹ ጋ ቀጣዩን ጊዜ ተስፋ እንድናደርግ መንገድ የከፈተልን ነው። በኢኮኖሚያቸው ፈርጣማ የሆኑ ሀገራትን ያሰባሰበው አዲሱ የብሪክስ ስብስብ የዓለምን ነባር ገጽታ ወደተሻለ እንደሚቀይረው በብዙዎች ዘንድ ታምኖበታል። ለዚህ የኅብረቱ አባል ሀገራት የያዙት የሕዝብ ቁጥርና እየመሩት ያለው የኢኮኖሚ አቅማቸው ለዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው።

በሕዝብ ቁጥር ደረጃ ስናያቸው አምስቱ አባል ሀገራት ከጠቅላላው የዓለም ሕዝብ 3.4 ቢሊዮን የሕዝብ ቁጥርን ለብቻቸው ይይዛሉ። አዲስ የተቀላቀሉት አባል ሀገራት ሲጨመሩበት ደግሞ 4.2 ቢሊዮን ይደርሳል። ይሄ ማለት አሁናዊውን የዓለም የሕዝብ ቁጥር ግማሽ ማለት ነው። አስር የሚሆኑ ሀገራት ከዓለም አጠቃላይ የሕዝብ ቁጥር ግማሹን ያዙ ማለት ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ አኳያ መጪው ጊዜ በእነዚህ ሀገራት የለውጥ ንቅናቄ አዲስ ሥርዓትን እንደሚጀምር መገመት አይከብድም።

ወደሚያንቀሳቅሱት የኢኮኖሚ አቅም ስንመጣ ደግሞ የበለጠ ነገሩን ተአማኝ ያደርገዋል። አምስቱ ሀገራት ማለትም ቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ፣ ብራዚልና ደቡብ አፍሪካ ለብቻው ከጠቅላላው የዓለም ኢኮኖሚ 26 በመቶውን ይይዛሉ። ይህ ከያዙት የሕዝብ ብዛት ጋር ተዳምሮ ምን ማለት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም። ይሄን በመሰለው ሁለንተናዊ ተጽእኖ በዓለም ፖለቲካና የገበያ ሥርዓት ላይ አዲስ ነገር ያሳዩናል እንላለን።

እንደጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከሁለት አስርት አመታት በፊት ጂም ኦኔል በተባለ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደተጠነሰሰ የሚነገረው ብሪክስ ስምንት የሚሆኑ አመታትን ዘግይቶ ራሱን ለዓለም አስተዋውቋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው ብሪክስን ሲጠነስስ አብሮ ከአመታት በኋላ የሚሆነውን መጻኢ ዕድሉንም አብሮ ተንብዮአል።

እንደእሱ ትንበያ፤ በሚቀጥሉት ሃያና ከዚያ በላይ አመታት ውስጥ ብሪክስ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ የሚዘልቅ የኃያላኖች ስብስብ ይሆናል። ነባሩ የዓለም ሥርዓት በአዲስ ሀሳብ ተቀይሮ ዓለምን እንደአዲስ የምናይበት ጊዜ ይመጣል። እንዳለውም ኅብረቱ አሁን ላይ ኃያላን ነን ለሚሉት ስጋት ሆኖ ለአዲሶቹ የዓለም አንቂ እና ተረካቢዎች ብስራት ሆኖ ከትናንት ወደዛሬ መጥቷል።

ስለብሪክስ ከሰማናቸው መልካም አላማዎች በላይ ወደፊት የምንሰማቸው እንደሚበዙ ብዙዎች ይስማማሉ። የማደግ መሻት ላላቸውና አሁናዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓቱ ተግዳሮት ለሆነባቸው ሀገራትና ሕዝቦች ባለብዙ ተስፋ እንደሆነም ይታመናል። በተለይም በኅብረቱ መሥራች አባል ሀገራት የተመሠረተው ‹ብሪክስ ባንክ› ለአባል ሀገራቱ የኢኮኖሚ እድገት የሚያስፈልገውን ገንዘብ በብድር (በወለድ ሆነ ከወለድ ነፃ) ፤ በእርዳታ እና በኢንቨስትመንት መልክ በማቅረብ ሊኖረው የሚችለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ለሚፈልጉ ሀገሮች ትልቅ እፎይታ የሚፈጥር ነው።

ባንኩ በአሜሪካ እና በምዕራባውያን የበላይነት የሚተዳደሩትን እንደዓለም ባንክና መሰል ተቋማትን የሚተካ አማራጭ የፋይናንስ ተቋም ሆኖ የሚያገለግል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በአባል ሀገራቱ የማደግና የመበልጸግ መሻት ላይ የራሱን ዐሻራ የሚያሳርፍ የገንዘብ ተቋም እንዲሆን እየተሠራም እንደሆነ ጥቁምታ ተሰጥቶበታል።

ከዚህ በተጨማሪ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በጤናና በትምህርት፣ በግብርናና የተሻለ እምርታን በሚያመጡ ማኅበራዊ እሴቶች ላይ እንደሚሠራ፤ በፋይናንስና በኃይል እጥረት በድሀ ሀገራት ላይ እየደረሰ ያለውን የምጣኔ ሀብት ማሽቆልቆል ለመታደግም እንደሚረዳ በስፋት እየተነገረለት ነው። ከዚህ ላቅ ሲል ደግሞ ለተነሳበት የኢኮኖሚና የአብሮ ማደግ አላማ እንደትልቅ ማስፈጸሚያ ሆኖ እንደሚያገለግል እሙን ነው።

በአሜሪካ ጠንካራ ወዳጅነታቸው የሚታወቁት ሳዑዲ ዐረቢያና ግብጽ የብሪክስ አባል መሆናቸው በቀደመው የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ያልተለመደ መሆኑ ኅብረቱ/ብሪክስ በመጪው ጊዜ አዲስ የለውጥ አብዮትን በማቀጣጠል ፋና ወጊ ሊሆን ስለመቻሉ አመላካች እየሆነ ነው።

ብሪክስ ተባብሮ ማደግን ለሚመርጡ የዓለም ሀገራት ግን እንደመልካም ዕድል የሚታይ ነው። የሆነው ሆኖ የብሪክስ ጥምረት ዓለምን እንደአዲስ አፍርሶ የሚሠራ የሃሳብና የርዕዮተዓለም ተራማጅ ምልከታ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። እንደ አሜሪካው የኢንቨስትመንት ተቋም ጎልድማን ሳክስ አተያይ፤ በሚቀጥሉት አርባና ሃምሳ አመታት ውስጥ የብሪክስ አባል ከሆኑ ሀገራት መካከል ቻይናና ሕንድ አሜሪካንን ቀድመው በኢኮኖሚያቸው የዓለም አድራጊ ፈጣሪ ይሆናሉ ሲል ተንብዮዋል።

ይህ አዲስ አሰላለፍ ለሀገራችን ብዙ በረከቶችን ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል። የኢኮኖሚ ትብብርን በመፍጠር ለጀመርናቸው የለውጥና የእድገት መሻቶች አዲስ ኃይልን የሚፈጥር ነው። ዓለም አቀፍ ንግድን፣ የውጪ ኢንቨስትመንትን እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማበረታታት የሥራ ፈጣሪነት ክህሎትን ከፍ በማድረግ ለወጣቱ የሥራ ዕድልን ለዜጎች ደግሞ የተሻለ የኑሮ እምርታን የሚያስተዋውቅ ይሆናል።

ከሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ከፖለቲካ ጥምረትና አኳያ ፋይዳው የማይናቅ ነው። ሰላምን ለማምጣትና ተነጋግሮ ለመግባባት የሄድንበትን ረጅም ርቀት የሚያቀና የተሀድሶ መንፈስንም የሚፈጥር ነው። ከኢኮኖሚ መረጋጋት ጋር አብረው የሚረጋጉ፣ ከፖለቲካ ስክነት ጋር አብረው የሚሰክኑ እልፍ ጉዳዮች አሉን። እኚህ ለችግሮቻችን ዋና መነሻ የሆኑ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎች በጥምረቱ በኩል የወዳጅነት ሃሳብ አዳብረው የሚረግቡበት መንገድም እንደሚፈጠር ተስፋ ማድረጉ ካለማድረግ የተሻለ ነው ።

ሀገራችን በብዙ ጥያቄዎች ትልሟን እያሳካች ያለች ሀገር ናት። በዲፕሎማሲው ረገድ የተሠራው አመርቂ ሥራ እንደብሪክስ ባሉ ዓለም አቀፍ ጥምረት ውስጥ አባል እንድንሆን አድርጎናል። በጋራ ሃሳብ ሰላማችንን መልሰን በአንድነት የቆምን ሰሞን ደግሞ ከዚህ በበለጡ ዓለም አቀፍ ዕድሎች ላይ ከፊት እንደምንሰለፍ ተጠራጣሪ አይኖርም።

ብሪክስን በተመለከተ ብዙ የባለሙያ ሃሳብ አድምጫለሁ። ብሪክስ በቀላሉ የሚገኝ ሳይሆን በብዙ ምዘናና ግምገማ ውስጥ የሚታለፍ የሂደት ውጤት ነው። የእኛም ሀገር የአባልነት ጥያቄ ቅበላ ይሄን መሰሉን የግምገማ ሂደት ያለፈ ነው። እንዳው ጠይቀን የተሰጠን ሳይሆን በብዙ ግምገማ ውስጥ አልፈን፣ ለአባልነት ብቁ የሚያደርገውን የምዘና መስፈርት አሟልተን ያገኘነው ዕድል ነው። በዚህ ረገድ ባለፉት አመታት ውስጥ የተሠሩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ወሳኝ ሚና ተጫውተውልናል።

ብሪክስ ሌላም አስተማሪ ገጽ አለው። ለአሁናዊው የሀገራችን ፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ቅድመ ሁኔታዎችን ከመጠቆም አኳያ ፋይዳው የትየሌለ ነው። እንደ ሀገር ላሉብን የውስጥ ጥያቄዎች ጨዋነትን ማስቀደም ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን ያሳየናል። በጨዋነት ተጉዘን ነው የብሪክስ አባልነትን ያገኘነው። ብዙ ያለን ሕዝቦች ነን። በሀገራችን ጉዳይ ላይ በጨዋነት መነጋገርና መግባባት ከቻልን እንደብሪክስ ለዓለም አቀፍ ድል እና ዕድል የማንታጭበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

ዕድሎቻችንን የሸፈኑብን አለመግባባቶቻችን ናቸው። ድሎቻችን ስንግባባ፣ ስንወያይ የሚመጡ ናቸው። ባለን ኃይል፣ ባለን ጥበብ፣ ባለን የተፈጥሮ ሀብት፣ ባለን የሕዝብ ቁጥር፣ ባለን ደማቅ ታሪክ፣ ባለን የእድገትና የለውጥ ግስጋሴ፣ ባለን የሰላም መሻት ከራሳችን አልፈን ለዓለም አዲስ ሥርዓት ለውጥ እንደምናመጣ ታምኖብን ከኃያላኖቹ ጎን እንድንቆም ተመርጠናል።

ዓለም ከመረጠን ለራሳችን መሆን ለምን አቃተን? ችግሮቻችንን ተነጋግሮ መፍታት ስለምን አልቻልንም? ከዚህ ጋር አያይዘን ልናነሳው የሚገባ አንድ እውነት አለ። ስለብሪክስ በተጻፉና በተነገሩ የባለሙያ ሃሳቦች ውስጥ አብዛኞቹ ሃሳቦች ሀገራችን ያሉባትን የውስጥ ችግሮች ፈትታ በሰላም ብትቆም ከዚህም ለበለጠ ዓለም አቀፍ ዕድል መታጨት ትችል ነበር የሚሉ ናቸው። ይሄ የሁሉም ባለሙያ የጋራ እምነት ነው። እያደግንና እየተመረጥን ያለነው በብዙ ባልተመለሱ ጥያቄ ውስጥ ሆነን ነው። ለብሪክስ አባልነት ስንመረጥ እንኳን ከፊትና ከኋላችን ጥቂት የማይባሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎችንም አንግበን ነው።

ታላላቅ ድሎች ከሰላም በኋላ የሚመጡ ናቸው። ችግሮቻችን እንዴትም ይተልቁ ከተነጋገርንባቸው የሚፍረከረኩ ናቸው። በሚፍረከረኩ ችግሮች ይሄን ያክል መከራ መክፈላችን ቢያስቆጨኝም በቀጣዩ ሀገራዊ ምክክር የማይደገሙ ጥፋቶችን አርቀን ለዘላቂ ሰላም በመትጋት እንደ ብሪክስ ያሉ ዕድሎችን መፍጠር እንችላለን። የውስጥ ጉዳዮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ለውጪው ዕድል በር ከፋች ስለሆነ በዚህ በኩል ልንተጋ ይገባል የመጨረሻ መልዕክቴ ነው።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

 አዲስ ዘመን ሰኞ መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You