
አዲስ አበባ፡- የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለመደገፍና የእርሻ መሳሪያዎች ፍላጎት መጨመሩን ተከትሎ በዓመት አስር ሺህ ትራክተሮችን ለማምረት እቅድ መያዙን የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ አስታወቀ።
በኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ስር የሚገኘው የአዳማ የግብርና ማሽነሪ ማምረቻ ኢንዱስትሪ የግብይትና ሽያጭ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አሰፋ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ኢንዱስትሪው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከስምንት እስከ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች በማምረት ላይ ይገኛል። እንዲሁም የትራክተር ተቀጽላዎችንና የውሃ ፓምፖችን በማምረት ለተጠቃሚዎች ያስረክባል። የኢንዱስትሪው ዓላማ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ እንዲደግፍ ማድረግ ስለሆነ በዚሁ አግባብ ሰፊ ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ የእርሻ መሳሪያዎች ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱና የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማገዝ በዓመት አስር ሺህ ትራክተሮችን ሊያመርት የሚችል ፋብሪካ ሞጆ ከተማ ለመገንባት ስምምነቱ አልቋል። ፋብሪካው ከተገነባ በኋላ በዓመት አስር ሺህ ትራክተሮችን የማምረት አቅም ይኖረዋል።
የግብርና ሥራ መስፋፋቱን ተከትሎ ፍላጎቱ እየጨመረ የመጣ በመሆኑ በዓመት አስር ሺህ ትራክተሮችን በማምረት ኢኮኖሚውን የመደገፍ ሥራ እንሰራለን ያሉት ኃላፊው፤ አሁን በዓመት ውስጥ በትንሹ ሦስት ሺህ ትራክተር የማምረት አቅም አለን ብለዋል። ከትራክተር ጋር የሚቀጠሉ እንደ ማረሻ፣ ጋሪና መከስከሻን ጨምሮ ከስድስት ሺህ በላይ የግብርና ምርቶችን እያመረትን እንገኛለን።
በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የመስኖ ልማት ስራዎች በስፋት እየተስፋፋ ነው ያሉት ኃላፊው፤ በናፍጣና በሞተር የሚሰሩ የአርሶ አደሩንና የኢንቨስተሮችን አቅም ያማከሉ የተለያየ አቅም ያላቸውን ፓምፖችን አምርተን ለተጠቃሚዎች በማስረከብ ለግብርና እገዛ እያደረግን ነው። የተለያየ አቅም ያላቸውን የውሃ ፓምፖች በዓመት ውስጥ በፍላጎት ልክ እያመረትን እንገኛለን ብለዋል።
ተቋሙ ግብርናውን ከመደገፍ አኳያ ትልቅ ተልዕኮ ወስዶ የሚንቀሳቀስ የመንግሥት የልማት ድርጅት በመሆኑ የሚመረቱ ትራክተሮች ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን የሚያከናወኑ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ አነስተኛ ፣መካከለኛና ከፍተኛ አቅም ያላቸው ትራክተሮች በሰዎች የመግዛት አቅም ልክ እየተመረቱ ለአገልግሎት ይውላሉ ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር ሰዎች ያላቸውን የመሬት ስፋት ከግምት በማስገባት አነስተኛና ትላልቅ ትራክተሮችን በማምረት የአርሶ አደሩን ፍላጎት የማርካት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለእርሻ አገልግሎት ከሚውሉ ትራክተሮች በተጨማሪ ለውሃ ቁፋሮ፣ እቃ ለመጫን፣ ለማውረድና ቦይ ለማውጣት የሚያገለግሉ የኮንስትራክሽን ትራክተሮችንና ጋሪ እየጎተተ እቃዎችን የሚጭን የትራንስፖርት ትራክተሮችን በማምረት ለሀገር ገቢ እያስገኘ ነው። በተቻለ መጠን ወደፊት ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን በመቀነስ ሀገራዊ ምርትን የመጨመር እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱን አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም