የትምህርት ንቅናቄው ማኅበረሰቡ የአቅሙን እንዲደግፍ እድል ሰጥቷል

አዲስ አበባ፡- በትምህርት ሚኒስቴር አነሳሽነት ማኅበረሰቡ የተማረበትን ትምህርት ቤት እንዲያለማ በማሰብ የተጀመረው የትምህርት ንቅናቄ ማኅበረሰቡ የአቅሙን ሳይሰስት እንዲሰጥ እድል መስጠቱን የሶሻል አንትሮፖሎጂ መምህርና ተመራማሪው ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሚቶ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መልሶ ለማቋቋም በተደረገ ንቅናቄ ከ185 በላይ የቁም ከብትና ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ተዋጥቷል።

ኬይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል እቅድ ይዞ የተነሳው የትምህርት ንቅናቄ የመማሪያ ስፍራዎችን ከተማሩበት በኋላ ዞር ብሎ የማየትን እድል የሚሰጥ፣ ገበሬው የቁም ከብቱን የሰጠበት ነዋሪው ገንዘቡን የለገሰበትና ተማሪዎችም ሳይቀሩ ሳይሰስቱ እንዲተባበሩ ሁኔታን ያመቻቸ ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ያሉትን ትምህርት ቤቶች በሙሉ ያለ ማንም ረዳትነት ለማሻሻል በማይችልበት አቋም ላይ እንዳለ የተናገሩት ተመራማሪው፤ በኅብረተሰብ ንቅናቄ መሰራት ያለበት የሚል ስምምነት ላይ በመድረስ ትምህርት ቤቶቹ በምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት የሚለው ተጠንቷል፤ ሁሉም ወደየተማረበት ስፍራ ዞር ብሎ ተመልክቶ ቢረባረብ መልካም ስለመሆኑም መምህሩ ተናግረዋል።

ተመራማሪው በንግግራቸው፤ ሀገርን ለማሻገር እንዲሁም ቀጥ አድርጎ ለማቆም ካስፈለገ ትምህርት ላይ መሰራቱ አግባብነት ያለው ተግባር መሆኑን በመግለጽ፤ የድህነት ቅነሳ ስራዎች በዋናነት ትምህርትን የሚዳስሱ መሆኑም የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በየትምህርት ቤቶቿ የሚታየው የደረጃ ያለመመጠን ዘመናዊ ትምህርትን ከብዙ ሀገራት ቀድማ ለጀመረች ሀገር የማይመጥን ነው ያሉት ዶክተር ኬይረዲን፤ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያለውን ስብራት ለመጠገን መሰረቱ በታች ክፍል ላይ ያሉ ትምህርት ቤቶች ላይ መስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር ኬይረዲን ንግግር፤ ሀገርን ያለማስቀደምና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት አካሄዶች ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያልተሰሩ የቤት ስራዎች እንደነበሩ የሚያሳይ ሲሆን የትምህርት ንቅናቄውም ለዚህ ቁልፍ መፍትሄ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በትምህርት ንቅናቄው ውስጥ በየኔነት ስሜት ያሳያው ተነሳሽነትና ተሳትፎ በመልካም የሚታይ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ኬይረዲን፤ የአንዱ ትምህርት ቤት መነቃቃት ለሌላው መማሪያ ስፍራ በጎ የሆነ የፉክክር መንፈስ መፍጠር ስለመቻሉም ገልጸዋል።

አሁን ላይ በትምህርት ዘርፉ ላይ በመንግሥትም ይሆን በትምህርት ሚኒስቴር ላይ ያለው ተነሳሽነት የኢትዮጵያን የነገ ተስፋ የሚገነባ መሆኑን ያመላከቱት ምሁሩ፤ የሀገርን ችግር እንፍታ ከተባለ የትምህርት ችግሩን በማከም መሆን ይገባዋል ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሚቶ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መልሶ ለማቋቋም በተደረገ ንቅናቄ ከ185 በላይ የቁም ከብትና ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ተዋጥቷል። ተማሪዎችም በበኩላቸው በመተባበር ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ማዋጣት ችለዋል ሲሉም ዶክተር ኬይረዲን ገልጸዋል።

ዳግማዊት ግርማ

አዲስ ዘመን  መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You