የሊቢያ አስተዳደር ከጎርፍ አደጋው ጋር በተያያዘ የቀረበበትን ወቀሳ አጣጣለ

ምሥራቅ ሊቢያ የሚገኘው አስተዳደር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከሞቱት መካከል አብዛኞቹ ቤት እንዲቆዩ የተነገራቸው ናቸው የሚለውን ክስ አጣጣለ።

ባንጋዚ ያለው አስተዳደር ቃል አቀባይ ኦታማን አብዱል ጃሊል እንዳሉት ነዋሪዎች ከደርና እንዲሸሹ ነው የተነገራቸው።

ከቤት እንዳይወጡና እዛው እንዲቆዩ እንዳልተገለጸም ቃል አቀባዩ አክለዋል።

ማስጠንቀቂያው የተጋነነ ነው በሚል በቤት የቆዩ ሰዎች እንዳሉ እንደሚገምቱ ገልጸዋል። ደርና የሚገኘው የቢቢሲ ዘገባ ቡድን ዓለም አቀፍ ሰብአዊ እርዳታ ተቋማት ገና እንዳልደረሱ ተመልክቷል።

በማዕከላዊ ደርና ሰዎችን ለመታደግና የሞቱ ሰዎችን ለመለየት ርብርብ እየተደረገ ነው።

በቦታው ከተገኙ መካከል የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን ባለሙያ ቶማሶ ዴላ በአካባቢው ያለው ውስብስብ ሁኔታ እርዳታ መስጠትን ከባድ አድርጎታል ብለዋል። መሠረተ ልማት በጎርፍ መውደሙ ደግሞ ነገሮችን አባብሷል።

የሟቾች ቁጥር ከ6,000 እስከ11,000 ሲደርስ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የደረሱበት አልታወቀም።

የደርና ከንቲባ አጠቃላይ ቁጥሩ 20,000 እንደሚደርስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የሟቾች አስክሬን እስከ 100 ኪሎ ሜትር በጎርፍ ተወስዷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ቃል አቀባይ ጄንስ ሌከር እንዳሉት አሁንም ከአደጋው የተረፉና የሞቱም ሰዎች በየቦታው ስለሚገኙ አጠቃላይ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ ይችላል።

ተጨማሪ ቀውስ እንዳይፈጠር ንጹሕ ምግብና ውሃ መቅረብ እንዳለበትም አክለዋል።

እስካሁን ከ1,000 በላይ ሰዎች በጅምላ መቃብር ተቀብረዋል። በጅምላ መቃብር መቅበር ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች ሥነ ልቦናን ስለሚጎዳ እንዲቆም የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል።

የአገሪቱ የተከፋፈለ ፖለቲካና ቀውስ የእርዳታ መስጠት ሂደቱን አክብዶታል።

የባንጋዚው አስተዳደርና በተመድ የሚደገፈው በመዲናዋ ትሪፖሊ የሚገኘው አስተዳደር ለጎርፍ አደጋው ምክንያት የሆነው ድልድል በአግባቡ እንዳልተያዘ አንዳቸው ሌላቸውን ይከሳሉ።

ሁለቱ ተቀናቃኝ አስተዳደሮች ነዋሪዎች ቤት ይቆዩ ወይስ አካባቢውን ለቀው ይውጡ በሚለው ላይ እርስ በእርሱ የሚጣረስ መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደነበርም ተገልጿል።

ታግሂር የተባለ ፓርቲ መሪ ጉማ ኤልጋማቲ እንዳሉት ለአደጋ በተጋለጠው አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው መውጣት ቢኖርባቸውም ከቤት እንዳይወጡ ተነግሯቸዋል።

የደርና ከንቲባ ግን ከአደጋው ሦስት ቀን ቀደም ብሎ ነዋሪዎች እንዲወጡ ተነግሯል ብለዋል።

አደጋው እየተባባሰ ሲሄድ ፖሊስና ወታደሮች ነዋሪዎች እንዲወጡ ቢገልጹም የከፋ ይሆናል ተብሎ እንዳልታሰበ የገለጹም አሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ሊቢያውያን አስክሬን በጅምላ መቅበር እንዲያቆሙ ተማጽኗል።

ከአንድ ሺህ በላይ አስክሬኖች በጅምላ መቀበራቸው ከተገለጸ በኋላ የዓለም ጤና ድርጅት አስክሬኖች ለቀብር በተከለለና በውል መለየት በሚቻል ውስን ቦታ ሟቾች ካልተቀበሩ የጀምላ ቀብር ኋላ በቤተሰቦች ላይ ዘላቂ ጠባሳ ጥሎ ያልፋል ሲል ስጋቱን ገልጧል።

በሺህ የሚቆጠሩ አስክሬኖች ደግሞ በጎርፍ እስከ መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ ተወስደው ባሕር ዳርቻ ላይ ተንሳፈው ይገኛሉ ይላሉ ዘገባዎች።

ቡልዶዘሮች የደርና መንገዶችን ፍርስራሽ እያነሱ ቢሆንም ሥራው አዝጋሚና ተስፋ አስቆራጭ ነው። አሁንም ድረስ ከፍርስራሾች ሥር አስክሬኖች ይኖራሉ።

በአንዳንድ ቦታ የአስክሬን ምልክቶች ሲገኙ ሰዎች አስክሬኑ የቤተሰባቸው አባል ይሆናል በሚል ጎትተው ካወጡ በኋላ ማንነቱን ለመለየት የሚሞክሩበት መንገድ ዕጅግ አሳዛኝና የከፋ ስሜትን የሚፈጥር ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታ አንድ ከፍተኛ የረድኤት ጉዳዮች ኃላፊ የአየር ንብረት ለውጥና የሊቢያ መንግሥት ችግሮችን ለመቋቋም ያለው ዝግጁነት አናሳ መሆን ሁኔታዎች የከፉ እንዲሆኑ አድርጓል ይላሉ።

አስክሬኖች በጎርፍ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ መወሰዳቸውና ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ መውጣታቸው ምናልባት ከዚህ ወዲያ ደግሞ ወረርሽኝ ይከሰት ይሆን የሚል ፍርሃት ፈጥሯል።

ከዚያ ይልቅ ከተፈጥሮ አደጋ ማግስት በማኅበረሰብ ውስጥ ከንጽህና ማነስ የሚፈጠር አስከፊ ሁኔታ ወረርሽኝ ሊጭር ይችላል ብለው ይሰጋሉ።

በሊቢያ የቀይ መስቀል ኃላፊ ታሚር ረመዳን የረድኤት ሠራተኞች በጭቃ ውስጥ ገብተው፣ ፍርስራሽ በእጃቸው ጭምር እያፈሱ ነፍስ ለመታደግ ቀን ተሌት እየሠሩ ነው ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ የውሃ ምንጭ አጠገብ የተጣሉ አስክሬኖች የጤና እክል ሊፈጥሩ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጧል።

በሊቢያ፣ ደርና በምትባል ጠረፋማ ከተማ ግድብ ጥሶ የወጣ ጎርፍ ባስከተለው በዚህ አደጋ ከ30ሺህ ሰዎች በላይ መፈናቀላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን እሁድ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You