በታላቁ አባይ ላይ እየተሸረበ ያለው ሴራ ፤

መጀመሪያ በሦስት ዙር በተካሄደው የግድቡ የውኃ ሙሌት የተያዘው አጠቃላይ የውኃ መጠን 22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን፣ በዘንድሮውና ሰሞኑን በተጠናቀቀው አራተኛ ዙር የውኃ ሙሌት የተያዘው የውኃ መጠን ግን 20 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ይህ በግድቡ የውሃ አያያዝ ሒደት እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧል። አጠቃላይ 42 ቢሊየን ሜትር ኩብ መድረሱንና ከጣና ሀይቅ ከሁለት እጥፍ በላይ ውሃ መያዙ ግድቡን ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ይሄን ይፋ ባደረጉበት ሰዓት አራተኛውና የመጨረሻው የውሃ ሙሊት ተካሄደ ማለታቸውን የሰሙ “የመጨረሻው “ በሚለው ቃል ግራ ተጋብተው የነበር ቢሆንም የመጨረሻው ሙሌት የተባለው የዘንድሮው ሙሌት የመጨረሻው በግድቡ አናት ላይ የመፍሰስ ሂደት ያከናወነ መሆኑን ለማመልከት ነው። ስለዚህ ከግድቡ አናት ላይ የመፍሰስ ሁኔታ ከዚህ በኋላ የለም ለማለት ነው።

ቀጥሎ የሚያዘው ውሃ ከፍተኛ በመሆኑና በጀነሬተሮችም ስለሚወጣ overtopping (በአናት መፍሰስ) አይኖርም ለማለት ነው፣ impound­ing (ውሀ መያዝ) ግን ይቀጥላል።” impoundingን ከovertopping ጋር በማያያዝ የተፈጠረ አለመግባባት ይመስላል ሲሉ፣ የሕዳሴው ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢ/ር ክፍሌ ሆሮ ማብራርያ ሰጥተዋል። ለመንደርደሪያ ያህል ይሄን ካልሁ ወደተነሳሁበት ነጥብ ልመለስ።

የታላቁን የአባይ ወንዝ ትርክት ለመንጠቅ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ የሚመራ አዲስ ሴራ እየተሴረ ይገኛል። እስከዛሬ የምናውቀው ሀቅ ታላቁ አባይ ወይም ናይል በዓለማችን ረጅሙ ወንዝ መሆኑን ነው። አሁን ግን ይሄን ሀቅ ለመከለስ የሚፍጨረጨሩ ከላሽ ተመራማሪዎች መነሳታቸውን በዚያ ሰሞን ለንባብ የበቃው የ”Washington Post”ጋዜጣ አርድቶናል።

ዓለማቀፍ የተመራማሪዎች ቡድን የእነ ብራዚሉን የአማዞን ወንዝ ከመነሻ እስከ መድረሻ በማሰስና በመለካት ከናይል ወንዝ ይበልጣል ብሎ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ለማስመዝገብ ላይ ታች እያሉ ነው። ሆኖም እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ታላቁ አባይ ወይም ናይል ነው። ብሪታኒካ ደግሞ “የአፍሪካ ወንዞች አባት” ሲለው፤ “ስኮፍስ” የተሰኘው የፖርቹጊዝ ተናጋሪዎች አማዞንን በዓለማችን ከናይል ቀጥሎ 2ኛው ግዙፍ ወንዝ ይለዋል። አማዞን በምድራችን ብዙ ሀገራትን የሚያካልል ወንዝ ነው። ናይል ከኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽ ከዚያ ሜዲትራኒያን ውቅያኖስ ሲገባ፤ የአማዞን ወንዝ ደግሞ ከፔሩ አንዲስ ከፍተኛ ተራራማ ቦታዎች ተነስቶ ወደ ብራዚልና አትላንቲክ ውቅያኖስ ይገባል።

በዓለማችን ብዙ ነገሮች እየተለኩና እየተመረመሩ ይነሱ የነበሩ ውዝግቦችን መፍታት ተችሏል። ረጅሙ ተራራ ኤቨረስት፣ ትልቁና ጥልቁ ውቂያኖስ ፓሲፊክ፣ አደገኛው መርዛማ እባብ ዌስተርን ታይፓን መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል። በዓለማችን እረጅሙ ወንዝ ናይል ነው። አይደለም አማዞን ነው የሚሉ ወገኖች እሰጥ አገባ ከያዙ ከረምረም አሉ። መጀመሪያ አካባቢ ሙግቱ መሠረታዊ የጆግራፊ፣ የሳይንስና የቁጥር ጉዳይ ብቻ መስሎ ነበር። እየዋለ እያደር ግን እየተወሳሰበ ሄደ።

አሳሾችንና ሳይንቲስቶችን ጎራ አስለይቶ የሚያወዛግብ የካርታጸፋዊ/cartographical/ ጉዳይ ሆኖ አረፈው ይለናል ጋዜጣው። ናይል ከአማዞን እንደሚረዝም ምንም ጥያቄ የለውም ይላሉ ናይልን ከመነሻው እስከ መድረሻው ያሰሱ ተጓዥ ሰር ክርስቶፈር ኦንዳጄ፤ ምንም እንዳትጠራጠሩ ይሉናል ደግመው።

የብራዚል የቀድሞ የጂኦሳይንስ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ጉይዶ ጌሊ ደግሞ ወዲህ የለም በዓለማችን ረዥሙ ወንዝ አማዞን ነው ሲል ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። አበው ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንዲሉ አማዞን የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል ጥርጥር የለኝም ይለናል። የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬ እና ብሪታኒካ በታላቁ የናይል ወንዝና በአማዞን እርዝማኔ መካከል ያለው ልዩነት 212.4 ኪ.ሜ ነው ይለናል። የታላቁ ናይል ወንዝ እርዝማኔ 6650 ኪሜ ሲሆን የአማዞን ደግሞ 6437.4 ኪ.ሜ እንደሆነ ነው የሚታወቀው።

ሰው ሰራሹ የናይልና የአማዞን እኔ እረዝም እኔ ግብግብን ለማስታረቅ አለማቀፋዊ የሳይንቲስቶችና የአሳሾች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ የአማዞንን እርዝመት ከመነሻው እስከ መድረሻው ለመለካት መታቀዱን ዋሽንግተን ፖስት እየነገረን ነው። ይህ የሳይንቲስቶችና የአሳሾች ቡድን በፈረንጆች የጸደይ ወር ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ወራት ከአማዞን መነሻ ከፔሩ የአንዲስ ከፍተኛ ቦታዎች እስከ ፓሲፊክ ለመለካት ይንቀሳቀሳል። ይህ እንደተጠናቀቀ ታላቁን የናይል ወንዝ ርዝመት ይለካሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ወደ ኤቨረስት ተራራ ጫፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኝዎችና አሳሾች የወጡ ሲሆን፤ 1500 አሳሾች ደግሞ የውቅያኖሶችን ስፋትና ጥልቀት መርምረዋል። የአማዞን ርዝመት የሚለካው ቡድን አስተባባሪ ብራዚላዊው ዩሪ ሳናዳ በቁጭት ከአማዞን መነሻ እስከ መድረሻ የተደረጉ ጉዞዎች ግን ከ10 አይበልጡም ይለናል። በአማዞን ወንዝ ላይ የሚደረግ ጉዞ ለአደጋ የተጋለጠ ነው። የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች እንደ ዋነኛ መተላለፊያ የሚጠቀሙበት ሲሆን የወንዝ ላይ ወንበዴዎችም በስፋት የሚንቀሳቀሱበት አደገኛ ወንዝ ነው።

በ2018 ዓ.ም ስድስት ወንበዴዎች አማዞን ላይ ለብቻው ጉዞ እያደረገች የነበረችውን ኤማ ኬልቲ አግቶ በመድፈር ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው ችሎት መቅረባቸውን ጋዜጣው ያወሳል። ዩሪ ሳናዳ ግን ለአማዞን ወንዝ ሲባል የትኛውም አይነት መስዋዕትነት ቢከፈል ይገባዋል ይለናል። ከማራኪነቱና ከያዘው ብዝሀ ሕይወትና የዱር እንስሳት ብዛትት አኳያ፤ የዘመናችንን የጆግራፊ እንቆቅልሽ ማለትም አባይ ወይስ አማዞን ይረዝማል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ እግረ መንገድም ደኑ በሕገ ወጦች እየተጨፈጨፈ መሆኑን ለዓለም ለማጋለጥ የሚደረግ ጉዞ ስለሆነ ምንም አይነት ዋጋ ቢከፈልለት ይገባዋል።

የወንዞችን እርዝመት መለካት ውስብስብና አስቸጋሪ ነው። የወንዞች ጆግራፊ ተለዋዋጭና ለአወዛጋቢ ትንተና የተጋለጠ ስለሆነ የአማዞንን ወንዝ እርዝመት መለካት ቀላል አይሆንም። የአማዞን መነሻ ከፔሩ ተራራማ ቦታዎች ይሁን ከሌላ ሩቅ ስፍራ ማረጋገጥ በራሱ ከባድ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ የወንዞችን መጨረሻና መዳረሻ በማያሻማ ሁኔታ መለየት አስቸጋሪ ነው። ብዙዎች ጆግራፈሮች የአንድ ወንዝ መነሻ ከአነስተኛ ምንጭ ሊሆን ይችላል ብለው ያምናሉ።

የወንዞችን እርዝመት እንዲህ ለኩት እንደዚያ አትለኩት ማለት አስቸጋሪና አወዛጋቢ ነው ይለናል የሪሞት ሴንሲንግ ሳይንቲስት የሆነው ሀንሰን ማቲው፤ ማንኛውም የወንዞች እርዝመት አለካክ ዝንፈት ካጋጠመው የተሳሳተ ውጤት ሊያስከትል፤ ረጅም ያልሆነውን ረጅም ወይም እረጅም የሆነውን አጭር በማለት የወንዞችን ደረጃ ሊያበላልጥ ይችላል። አንደኛውን ሁለተኛ፣ ሁለተኛውን አንደኛ ማድረግ እንደማለት።

ለምሳሌ በ1846 ዓ.ም ይፋ የሆነው የአትላስ ጠቃሚ መረጃዎች ካርታ አማዞን 5150 ኪ.ሜ እንደሚረዝምና ከምድራችን አንደኛ እንደሆነ ሲገልጽ ታላቁ ናይል ደግሞ 4425 ኪ.ሜ በመርዘም ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጠዋል። ብራዚላውያን ተመራማሪዎች እንዲሁ ሌላ አኃዝ በመጥቀስ አማዞንን አንደኛ ያደርጉታል። የአሜሪካ ጂኦጆሊካል ሰርቬ ግን ታላቁን የአባይ ወይም የናይል ወንዝ አንደኛ ያደርገዋል።

የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ አንጄላ ብሮክፓርት ወንዞችን እርዝመት የመለካት ሳይንስ የተወሳሰበ ነው ትለናለች። የተሻለ የሚሆነው የአማዞንም ሆነ የታላቁ ናይል መነሻ ካርታ ላይ በማይሻማ ሁኔታ ቢመለከት ነው። ይሁንና የእነዚህ ታላላቅ ወንዞችን እርዝመት በማያሻማ ሁኔታ ካርታ ላይ ማስቀመጥ ይከብዳል ትለናለች። ከአስርት ዓመታት በፊት በስራው የተሰላቸው ኒውሮሳይንቲስት ጄምስ ኮንቶስ እንደ ብዙዎቹ የአማዞን ወንዝ መነሻ የአንዲስ ተራራማ ቦታዎች ናቸው ብሎ ሲሄድ መነሻው ግን ከዚያ አልፎ ከሰሜን ፔሩ “ማራኞን” ወንዝ እንደሆነ አረጋገጠ ይለናል ዋሽንግተን ፖስት። ታዲያ ካረጋገጠ አሁን ለምን እንደ አዲስ አወዛጋቢ እንደሆነ ግን ጋዜጣው አያብራራም።

አሳሾች ግን የአማዞን ወንዝ መነሻ ከዚያም አልፎ ከአፑሪኝማክ ወንዝ ነው ይላሉ። አሜሪካዊው አሳሽ ሎረን ማክኢቲየር ነው በ1971 ዓ.ም ይሄ ወንዝ የአማዞን መነሻ ነው ብሎ ያስተዋወቀው። ኮንቶስ ግን አይኑን ከዓለም ካርታ ላይ አላነሳም። የአማዞን ወንዝ መነሻ ከአፑሪኝማክ ወንዝም ያለፈ ነው ይለናል። በGPS በመታገዝ አድካሚ ጉዞና አሰሳ ካደረገ በኋላ ከአንድ ተራራ ስር የሚንፎለፎል ኩልል ያለ ምንጭ ያገኛል።

ይሄን ምንጭ የአማዞን ወንዝ መነሻ መሆኑን ገልጾ ያሳትማል። ወዲያው ከየአቅጣጫው ተቃውሞ ይቀሰቀስበት ጀመር። አንዳንድ ጆግራፈሮች ለናሽናል ጆግራፊክ የማይመስል ነገር ሲሉ አጣጣሉበት። አንዳንድ ጆግራፈሮች የናይል ወንዝ መነሻ ኡጋንዳ ነው አይደለም ብሩንዲ ነው የለም ሩዋንዳ ነው እያሉ እንደሚወዛገቡት ሁሉ የአማዞን ነገርም እንዲህ ነው ይለናል ዋሽንግተን ፖስት። አበው ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የአባይ ነገር ከተነሳ አይቀር አንዳንድ ነጥቦችን ላነሳሳ።

የአባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አህጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል። በዓለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው። የአባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት። ከቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ አባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር አባይ ነው። ለአባይ ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነ ለም አፈሩ በመገበር ጥቁር አባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው። ለዚህ ነው አባይ ወይም ናይል ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ይነሳል የሚባለው።

ለራሱ ለጥቁር አባይ ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር አባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን ሜትር ኩብ እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በዓመት ይገብራሉ። የጥቁር አባይ የፍሰት መጠን ከሀገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር በጠቃሚ ማዕድናትም የበለጸገ ነው። ጥቁርና ነጭ አባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና አባይ /ናይል/ ይሆናሉ። ዳሩ ግን የናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ናቸው።

የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም አልቻሉም። በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢፍትሐዊ ውል መሰረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል።

የሚገርመው ከጥር እስከ ሀምሌ ያለውን ፍሰት ያካትታል። ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ ሀገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እኤአ እስከ ተፈራረሙበት 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት፣ “ ከግብፅ መንግስት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ስራዎችን በአባይ ገባሮችና ሀይቆች ላይ መገንባት አይቻልም።

“ ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ “ ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት። “ የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው። እኔ ግን ግብፅ የአባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው። ጥንታዊ ስልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ህልውናዋ ከአባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ ሀገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ መስራቱ ይቅርና የምታሳየን ንቀት ያበግናል።

ከግርጌዋ ተፋሰስ ሀገራት ለዛውም ከሱዳን ጋር ስለ ዳግም የውሃ ክፍፍሉ ምክክር ካደረገች ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፈርኦኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል። ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም። የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀመረች።

የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጠለች። የተፋሰሱን ራስጌ ሀገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፤ ኢትዮጵያና ሳባቱ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቃሉ። የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በጋራ መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ ሀገራት የ1959ኙ ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች።

ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ ሀገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ሀገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ። ሆኖም የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የአባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም። ሱዳንና ግብፅ አባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብድር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው።

ሻሎም !

አሜን !

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You