ባተሌዋ ወይዘሮ የጓዳቸውን ጣጣ ከውነው ወደ ገበያ ሊሄዱ ተዘጋጅተዋል። ጊዜው ሳይረፍድና ፀሐይ ሳትበረታ ለሚያዘጋጁት በርበሬ ቅመም መግዛት አለባቸው። ሁሌም ወጥተው እስኪመለሱ ለጨቅላዋ ልጃቸው ይጨነቃሉ። ዛሬ ግን ሕፃኗ ከሞግዚቷ ጀርባ ስለተኛች እምብዛም አላሰቡም። ልጃቸውን ስመውና እንደሁልጊዜው «አደራ» ብለው ወደ ገበያው ገሰገሱ።
አጋጣሚ ሆኖ የሄዱበት ሸመታ አላቆያቸውም። ያም ሆኖ ግን ልባቸው ተንጠል ጥሏል። ወደ ቤታቸው አቅራቢያ ሲዳረሱ የተሰማቸው የሕፃን ለቅሶ እየረበሻቸው ነው። ይህ ድምጽ የልጃቸው መሆኑ አልጠፋቸውም። ከወትሮው በተለየ አምርራ ማልቀሷ አስደንግ ጧቸዋል። ፈጥነው ከቤት ሲደርሱ ልጅቷን ባዶ ቤት አገኟት። ደነገጡ። «አደራ» ያሏት ሞግዚት ጥላት ስለመሄዷ ገባቸው። ነገሩ ቢያናድዳቸውም በልጃቸው ሰላም መሆን ተጽናኑ። ጨቅላዋ ከእናቷ ብትገናኝም ለቅሶዋን በቶሎ አላቆመችም።
እንዲህ ከሆነ ጊዜያት ተቆጠሩ። ነገሮችም ውለው ሲያድሩ የተረሱ መሰሉ። የሕፃኗ መነጫነጭና ማልቀሷን ግን ቀጥላለች። የእናቷ ሀሳብና ጭንቀትም እንዲሁ። ልጅቷ ዕድሜዋ ሲጨምር እናት አባቷ «ዳዴ…» ስትል ማየትን ናፈቁ። አሁን እንደ ዕድሜ እኩዮችዋ እየዳኸች ለመራመድ የምትሞክርበት ጊዜ ነው። ይህ ጉጉት ግን እንደታሰበው እውን አልሆነም። ልጅቷ ከመቀመጥና ሲይዟት አምርራ ከማልቀስ ሌላ ሙከራውና መፍጨርጨሩ አልታየባትም። ይህ መሆኑም «ልክፍት… ነው» የሚል ግምት በቤተሰቦቿ ዘንድ አሳዳረ ።
ከቀናት በአንዱ ቀን ግን ጉዳዩን «እናውቅ ነበር» ያሉ ጎረቤቶች አየነው ስላዩት እውነት ተናገሩ። ከወራት በፊት ሕፃኗን ባዶ ቤት ትታ የሄደችው ሞግዚት የመጥፋት ሰበብ ልጅቷን አዝላ መውደቋ ነበር። ይህን በጊዜው አለመናገራቸው ግን ሁኔታውን የከፋ አድርጎታል። የጨቅላዋ ክፉኛ ጉዳትና በወቅቱ አለመታከም እያደር ችግር ማስከተሉ ታውቋል። ይህ ሁሉ ግን «ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ » እንደማለት ነው።
ምስጢሩ እንደታወቀ በሀኪምና በወጌሻ የተደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ ሆነ። የአካሏና የሁለቱ እግሮቿ ጉዳት አሳሳቢ ነበር። የችግሩ ክፋትም ሕፃኗ በክራንች እንድትንቀሳቀስ አደረገ። ይሁን እንጂ በወገቧ የታሰረላት ማገዣና ክራንቹ በእኩል መስማማት አልቻሉም። የዕድሜዋ ማነስ ለእርምጃዋ ፈተና ሆኖ ሰውነቷ እንዲላላጥ አስገደደ።
በሙከራቸው ሁሉ ተስፋ ያልቆረጡት ወላጆች «ቼሻየር ሆም» የተባለ ድርጅት መኖሩን በሰሙ ጊዜ ልጃቸውን ይዘው ወደ ድርጅቱ አቀኑ። ድርጅቱም የሕፃኗን አቋም መርምሮ አካላዊ ድጋፍ እንዲሰጣት ፈቀደ።
ሕፃን እየሩስ ግርማ አምስት ዓመት እንደሆናት ማዕከሉን ተቀላቅላ ኑሮዋን በግቢው አደረገች። ውላ ስታድር ግን የቤተሰቧን ናፍቆት መቋቋም አልተቻላትም። ልጅነቷ ሆድ እያስባሰ ጠዋትና ማታ በዕንባ መታጠብ መለያዋ ሆነ። ይህኔ ማዕከሉ መፍትሄ ባለው አማራጭ ወደ ቤተሰብ እንድትቀላቀል ወሰነ። ዳግም በቤተሰብ እጅ ላረፈችው ጨቅላ ግን ህይወት እንደትላንቱ አልሆነም። ጉዳቷና የሚደረግላት ጥንቃቄ ስጋት ላይ ወደቀ። ይህ ደግሞ ልጆች ለማሳደግ ሮጠው ለሚያድሩት ወላጆች ፈታኝ መሆኑ አልቀረም። በተለይ የትምህርት ጉጉት ለነበራት ሕፃን በእንብርክክ እየሄደች ቄስ ትምህርት ቤት መዋል ቀላል አልነበረም።
ጥቂት ቆይቶ ግን እየሩስ በአንድ ሕፃናት ማሳደጊያ የተሻለ ዕድል አገኘች። ይህ ድርጅት ሙሉ ለሙሉ ተረከባትና ኑሮና ትምህርቷን እንድትቀጥል አገዛት። የነበረባትን ችግር አስወግዶም በዊልቸር እንድትጠቀም ረዳት። ለእየሩስ የድርጅቱ ቆይታዋ መልካም የሚባል ነበር። በራሷ እንድትተማመን፣ ጥንካሬ እንዲኖራትና የወደፊት ማንነቷን እንድትቀርጽ ብርታት ሆኗታል ።
የእሷ ስሜት በዚህ ቢቃኝም ለመማር የምትከፍለው ውጣ ውረድ ግን ቀላል አልሆነም። ወደ ትምህርት ቤት ሄዶ ለመመለስ የሌሎችን እገዛ መሻቷ ግድ ነበር። ክፍል ለመግባት ርቆ መሄድና ደረጃን ወጥቶ መውረድ በእጅጉ ፈትኗታል። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቃ ወደ ቀጣዩ ስታልፍ ደግሞ ሁሉም ነገር በእጅጉ ከበዳት። ዘወትር ጓደኞቿን ለእርዳታ መጠየቅ የማስቸገር ያህል ይሰማት ጀመር።
ዘጠነኛ ክፍል እንደደረሰች ወደ አስረኛ ለማለፍ አልቻለችም። ይህን ተከትሎ ለአቅመ ሄዋን መድረሷም ድርጅቱን እንድትሰናበት ምክንያት ሆነ። ከዚህ በኋላ እየሩስ ወደ ቤቷ ዳግም ተመለሰች። ትምህርቷን ባለመጨረሷ ሥራ የመፈለግ ሀሳብ አልነበራትም። አባቷ በህይወት አለመኖራቸው ደግሞ እናቷን እንድታግዝ ግድ አላት። ይህኔ ጀብሎ እየሸጠች ልብስ መነገድ ጀመረች። ራሷን አሸንፋ ለማደርም ዘወትር መጣጣር መለያዋ ሆነ።
እየሩስ ዕድሜዋ ሲጨምርና አቅሟ ሲጎለብት ሌሎች አማራጮችን አሰበች። አትክልት ቤት ከፍታ ለደንበኞች መሸጥ ፍላጎቷ ሆነ ። ይህን እንዳሰበች ወደሚመለከታቸው ሄዳ ቦታ ይሰጧት ዘንድ «አቤት» ስትል ጠየቀች። ሁኔታው ግን እንደታሰበው አልሆነም። «ችግሬን ይረዳሉ» ያለቻቸው አካላት እያመላለሱ ደጅ አስጠኗት። ፊት መነሳቷ ሆድ ቢያስብሳት ደጋግማ አለቀሰች። ጉዳዩን ለማስፈጸም ከአንዱ ወደሌላው መንከራተትም አቅምና ጉልበቷን ፈተነው።
ከብዙ ጥረትና ድካም በኋላ የታሰበው ይሆን ዘንድ ጊዜያዊ ቦታው ተፈቀደላት። ከአንድ መንገድ ዳርም ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆነች ሱቅ አቁማ አትክልትና ፍራፍሬ መነገድ ጀመረች። እንዲህ በሆነ ጊዜ የእየሩስ ብርታት መታየት ተጀመረ።
የምትሸጠውን ከገበያ ለማምጣት ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ወደ አትክልት ተራ ማቅናቷ ግድ ሆነ። ለእሷ በውድቅት ተነስቶ ለብቻ መጓዝ፣ ትራንስፖርት ለመያዝ መልፋትና ከስፍራው ደርሶ የሚፈልጉትን ማማረጥ የዘወትር ግዴታዋ ነው። ይህ ሁሉ ግን በዊልቸር ለምትጓዘው አካል ጉዳተኛ ቀላል አልነበረም። ከድካሙ ባሻገር ገበያው ይድራ ይቀዝቅዝ እንኳን እርግጠኛ መሆን አይቻላትም።
አሰልቺውን ውጣ ውረድ መቋቋም የከበዳት እየሩስ በዚህ መንገድ መግፋቱ አልሆነላትም። ለወራት የተጓዘችበት ምልልስም የሚያዋጣት አልሆነም። ለዚህ መፍትሄ ለመሻት አማራጭ የወሰደችው ወጣት ሌሎች ሠራተኞችን በመቅጠር የሥራ ዕድልን ፈጠረች።
ከዚህ በኋላ ህይወት በወጣቷ ዘንድ መልካም ሆኖ ቀጠለ። ይህን ተከትሎ አንድ ቀን ጥሩ የሚባል ዜና ለጆሮዋ ደረሰ። እየሩስ ኮንዶሚኒየም እንደደረሳት ሰማች። ይህ ማለት በርካታ ችግሮችን ላለፈች አካል ጉዳተኛ ታላቅ ትርጉም ነበረው። ስለ ቤቷ ለማወቅ በሄደች ጊዜ ግን ዕጣው አራተኛ ፎቅ ላይ እንደሆነ ተነገራት። ይህን ስትሰማ ደስታዋ ፈጥኖ ደበዘዘ። በየቀኑ አራተኛ ፎቅ ድረስ በዊልቸር መጓዝ እንደማትችል ታውቃለች።
ቤቱን ለመቀየር ያደረገችው ጥረት አልተሳካም። እሷም ብትሆን የሌሎች ዕድል እንዲነጠቅ አልፈለገችም። ከዚህ በኋላ የደረሳትን ሽጣ ተመሳሳዩን አመቺ ቤት ገዛች። ይህ አጋጣሚም ከባለቤቷ ጋር ለመተዋወቅ ምክንያት ሆነ። እየሩስ ጎጆ ቀልሳ ትዳር እንደያዘች የመጀመሪያ ልጇን አረገዘች።
በወቅቱ ለልጇ ደህንነት አብዝታ ትጨነቅ እንደነበር ታስታውሳለች። ሕፃኑ በጤንነት እንዲወለድና መልካም ህይወት እንዲኖረውም የራሷን ጥረት ታደርግ ነበር። የሁለተኛው ልጅ እርግዝና ግን ከበፊቱ ይበልጥ እንደከበዳት ዛሬም ድረስ አትረሳውም። አካል ጉዳተኝነቷ በተለየ የፈጠረባት ችግር ባይኖርም ቁጭ ብላ መዋሏና ከእንቅስቃሴ መታቀቧ ጭንቀቷን ጨምሮት እንደነበር አትዘነጋም።
«አካል ጉዳተኝነት ብቻውን ችግር ሊሆን አይችልም» የምትለው ወጣት የእሷን መልካም ተሞክሮ ሌሎችም እንዲጋሩት ትመክራለች። እየሩስ እንደምትለው አካል ጉዳትን ሰበብ አድርገው እጃቸውን ለልመና የሚዘረጉ ወገኖች ያናድዷታል። በእሷ እምነት ማንም ሰው በጥረት ከተጓዘና «እችላለሁ» የሚለውን ጥንካሬ ካዳበረ ፈተናዎችን ማሸነፍ ይቻለዋል።
ዛሬ እየሩስ በንግድ ሥራ ባገኘችው ገቢ የራሷ ቤትና መኪና አላት። ልጆቿንም በአግባቡ በማሳደግ ታስተምራለች። እሷ ለአሁኑ ማንነቷ ያለፈችበት አስቸጋሪ የህይወት መንገድ ምክንያት ሆኗታል። እንደሷ መሆን ያልቻሉ በርካታ አካል ጉዳተኞች ግን ዛሬም በየቤቱ ተዘግቶባቸዋል። ዕድሉ የተነፈጋቸው እነዚህ ወገኖች እንደማንኛውም ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትሻለች።
ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ የአካል ጉዳተኞች ቀን ተከብሯል። ይህ ቀን ሲታሰብም «አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትንና እኩልነትን እናረጋግ ጣለን» የሚል መልዕክትን አንግቦ ነው። እየሩስ እንደምትለው ደግሞ ቀኑን ከማክበር ባለፈ ለእነዚህ ወገኖች እኩል ተሳታፊነት መንግሥት የተለየ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011