አምራችና ሸማቹን ያማከለው የግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከል

አዲስ አበባ ከተማ በአዲስ ዓመት መቃረቢያ ላይ አንድ ግዙፍ የግብይት ማዕከል አስመርቃለች፡፡ የግብይት ማዕከሉ የግብርና ምርቶች የሚከማቹበትና የሚሸጡበት ሲሆን፣ አምራቹን እና ተጠቃሚውን ለማገናኘት አና የግብርና ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት በሚልም የተገባ ነው፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጭምር የተካተቱበት ይህ ማዕከል የችርቻሮና የጅምላ መሸጫ እንዲሁም መጋዘኖችና የመኪና ማቆሚያ ሥፍራን ያካተተ ነው፡፡

ማዕከሉ የግብርና ምርቶችን ሳይበላሹ ማቆየት የሚያስችሉ የማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂዎች እንዲሁም ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆነ የቆሻሻ ማስወገጃ ስርዓት /ዌስት ማኔጅመንት ሲስተም/ እና ሌሎች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ይገጠሙለታል።

ይህ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ጤና ጣቢያ አካባቢ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት ከሚገነቡት የከተማ አስተዳደሩ ሜጋ ፕሮጀክት መካከል አንዱ ነው፡፡ ማዕከሉ የተገነባው በኦቪድ ኮንስትራክሽን ፒኤልሲ ተቋራጭነት ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር ሲሆን፣ በኦቪድ ኮንስትራክሽን አማካኝነት በአጭር ጊዜ እየተገነቡ ከሚገኙ መሰል ፕሮጀክቶች መካከል /ሰሚት ፕሮጀክትና ቤቴል ፕሮጀክት/ በተመሳሳይ ዲዛይን፣ ስፋት እና ዓላማ የተገነባ ነው።

የግንባታው ተቋራጭ የኦቪድ ኮንስትራክሽን የአያት ፕሮጀክት የሳይት ኢንጂነር ኤርሚያስ ኃይሉ ፕሮጀክቱን ከዚህም በፈጠነ መስራት ይቻል እንደነበር ነው የገለጹት፤ እሳቸው እንዳሉት፤ የተመረቀውን ፕሮጀክት ሳይት በመረከብ ወደ ሥራ የተገባው በ2015 ዓ.ም ህዳር ወር መጨረሻ ላይ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ የሲሚንቶ እና የብረት እጥረት በማጋጠሙ እንጂ እስከ ግንቦት ወር ድረስ ማጠናቀቅ የሚቻልበት አቅም እንደነበር አስታውሰዋል። ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቃው ሎት አንድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግንባታውም በሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማዕከሉ እያንዳንዳቸው ሁለት ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፉ የችርቻሮና ጅምላ መሸጫ ህንጻዎች ያሉት ሲሆን፣ በጠቅላላ ወደ ስድስት ብሎኮች ተገንብተውለታል፡፡ እያንዳንዱ ብሎክም የመኪና ማቆሚያ ፓርክ እንዲኖረው ተደርጎ ተገንብቷል፡፡ ማዕከሉ የሰብል እና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በችርቻሮ የሚሸጡበት ሲሆን፣ እንዲሁም ለማከማቻነት የሚያገለግሉ ግንባታቸው አራት ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ያረፉ ማከማቻ አንድ እና ማከማቻ ሁለት መጋዘኖች አሉት።

የግንባታ ተቋራጩ ኦቪድ ኮንስትራክሽን ከዚህ ቀደም የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያስገነባውን የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች መንደርን የገነባ ሲሆን፤ በወቅቱ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የተጠቀመበትን ቴክኖሎጂ በማዕከሉ ግንባታ መጠቀሙም ተጠቅሷል፤ ይህ የኮሪያ የግንባታ ቴክኖሎጂ የሆነው የተገጣጣሚ ቤቶች ቴክኖሎጂ በአንድ ሳምንት ውስጥ አንድ ወለል መሙላት ያስቻለ እንደሆነም ተነግሯል።

ኢንጂነር ኤርሚያስ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ ከ100 ለሚበልጡ ንኡስ ተቋራጮች /ሰብ ኮንትራክተሮች/ የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ሲሆን፣ ሥራው ቀንና ለሊት ሲከናወን ቆይቷል፤ በቀንም በማታም በጠቅላላው በሺዎች ለሚቆጠሩ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር የተቻለበት ነው።

የለሚ ኩራ የዘመናዊ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከል ምክትል ፕሮጀክት ማኔጀር አቶ ዳንኤል በቀለ ግንባታው 24 ሰዓት እና ሰባት ቀናት የመስራት እድል የተፈጠረበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የበዓልና የእረፍት ቀናትን ጨምሮ በመጠቀም በተቀመጠው ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቅቆ ለማድረስ ጥረት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡ ለአዳሪ ሰራተኞች በእጥፍ በመክፈል፤ የቁርስ እና እራት በመቻል የማደሪያ ቦታ በመስጠት ጭምር ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል።

አቶ ዳንኤል እንደገለጹት፤ የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ ለማድረስ የሚቻልበት ሁኔታም ነበር፤ እንደ አገር በገጠሙት ችግሮች፤ የሲሚንቶ እጥረት፣ በሀገር ውስጥ የማይገኙ ቁሳቁስ መኖራቸው፣ ከኤልሲ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገቡ እቃዎች መዘግየት እና ሌሎች ተግዳሮቶች ፈተናዎች ሆነዋል፤ እነዚህን ሁሉ በመቋቋም ግንባታውን ለማከናወን ጥረት ተደርጓል።

በቀጣይ በሎት ሁለት ግንባታ ላይ እንደሚሰራ ገልጸው፣ የዚህ ሎት ግንባታም አብዛኛው ስራ ያለቀና 60 በመቶ ያህል መድረሱን ጠቁመዋል። በሎት ሁለት በቴክኖሎጂ የረቀቁ ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፣ የሙቀት እና ማቀዝቀዣ ክፍሎች፣ እንዲሁም አብዛኞቹ የአየር ሁኔታውን የሚቆጣጠሩ ቴክኖሎጂዎች አገር ውስጥ የማይገኙና ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ቁሳቁስ ሲገቡ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል። በተለይ ለፕሮጀክቱ የሚያገለግሉ እና አገር ውስጥ የማይገኙ ቁሳቁሶች በአጭር ጊዜ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የመንግሰት ተቋማት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ መንግስት ለማህበረሰቡ ጠቀሜታ ፍጆታ የሚውሉ መሰል ወሳኝ ፕሮጀክቶችን ጣልቃ በመግባት በልዩ ሁኔታ ቢመለከታቸው ፕሮጀክቶች ቶሎ እንደሚያልቁ እና ወደ አገልግሎት ገብተው ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሜጋ ፐሮጀክት ፅህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ደቦ ቱንካ በበኩላቸው፤ ለአምራቹ እና ለሸማቹ እፎይታን የሚሰጠው ይህ ፕሮጀክት መዲናዋን በአዲስ መንገድ ለማነፅና በዓለም ያላትን የዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚያዊ እይታን ከፍ ለማድረግ ከሚሰሩ የልማት ስራዎች መካከል አንዱ ነው። በትላልቅ ፕሮጀከቶች ግንባታ ፅህፈት ቤት ብቻ ባለፉት ሶስት ዓመታት በአጭር ጊዜ ተገንብተው እና ለነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት የጀመሩና ለከተማዋ መስህብ የሆኑ አራት ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አሁን እያስገነባቸው ከሚገኙ ሰው ተኮርና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ካላቸው ፕሮጀከቶች ውስጥ በከተማዋ ብሎም በአገሪቱ ለተከሰተው የኑሮ ውደነት እና የገበያ አለመረጋጋት መንስኤ ከሆኑ መካከል የግብርና ምርቶች መሸጫ ቦታዎች እና የገበያ ሰንሰለት ችግር አንዱ መሆኑን ኢንጂነር ደቦ ይገልጻሉ፤ ይህ ችግር እልባት እንዲያገኝ መሰራቱን ጠቅሰው፣ ፕሮጀክቱ ነዋሪዎች የግብርና ምርቶችን በየአካባቢያቸው እንዲያገኙ በማድረግ ገበያውን ማረጋጋት እና የገበያ ተደራሽነትን በማስፋት አምራችና ሸማችን በቀጥታ ለማገናኘት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።

በሁሉም የከተማዋ መግቢያ በሮች እነዚህ የግብርና ምርቶች የግብይት ማዕከላት እንዲገነቡ በ2015 ዓ.ም በማቀድ እና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ግንባታው ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ተጀምሮ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟሉ ሶስት ተወዳዳሪ የግብርና ምርቶች መሸጫ የገበያ ማዕከላት እውን እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል። ፕሮጀክቱ ለአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፣ ለሰብል ምርቶች እና የወተት ተዋፅኦዎችና ሌሎች ምርቶችንም ማዕከል ያደረገ አገልግሎት የሚሰጥባቸው 182 ሱቆች፣ ሰፋፊ መጋዘኖች፣ 150 የችርቻሮ መሸጫ ሱቆች፣ 30 የጅምላ መሸጫ ሱቆች እንዳሉት ገልጸዋል፤ 26 የማቀዝቀዣ ቦታዎች፣ እና ሶስት የማሞቂያ ሲስተሞች እንደሚገጠሙለትም አብራርተዋል።

ፕሮጀክቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ከግንባታ እስከ ዲዛይኑ ድረስ አንድ ነጥብ 46 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን ጠቅሰው፣ በፕሮጀከቱ ግንባታ ወቅት ሶስት ሺሀ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የእውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ 24 ሰዓት እና ሰባት ቀን የመስራት እድል የተፈጠረበት እና ሰራተኞቹም በዚህ ልምድ የተቀረፁ ስለመሆናቸው ኢንጂነር ደቦ ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ በስምንት ወር ውስጥ ለመጠናቀቁ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል።

ኦቪድ ኮንስትራክሽን 24 ሰዓት፣ ሰባት ቀናት፣ ቀን እና ሌሊት በእረፍት እና በበዓል ቀናት ጭምር የመሥራት ባህልን የተላበሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተሞክሮ ሌሎች እንዲወርሱት በማድረግ በኩልም ኦቪድ ኮንስትራክሽን የዚህ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ በዚህ ሁኔታ ካልሰራን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት አይቻልም ሲሉም አስገንዝበዋል። ፕሮጀከቶችን ስንገነባም አንድን ፕሮጀክት መገንባት እና መጨረስ ብቻ ሳይሆን አገርን መገንባት መሆኑ ስለሚገባን 24 ሰዓት፣ ሰባቱንም ቀናት በመፍጠን እና የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችንም በማከል መስራት ይጠበቅብናል ሲሉም አስታውቀዋል።

እነዚህን ፕሮጀክቶች በማስፋትም በአምስቱም የከተማዋ መግቢያ በሮች ዘመናዊ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ ናቸው ሲሉም ጠቅሰው፣ የመጀመሪያው ፕሮጀክትም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሐምሌ ወር ስራ መጀመሩን አስታውሰዋል። በቀጣይም በስፋት ምርት ሊያከማቹ የሚያስችሉ እና በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት እንደሚገነቡ ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባለፈው ሳምንት ፕሮጀክቱ በተመረቀበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የለሚ ኩራ የግብርና ምርቶች ማከማቻ ማዕከል ተመርቆ ወደ አገልግሎት መስጠት መሸጋገር የከተማዋን የምርት አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ ካለው ጉልህ ፋይዳ በተጨማሪ ከተማ እና ገጠሩን በመተሳሰብ ለማስተሳሰር ይጠቅማል፡፡

ለአምራቾች እና ለሸማቾች እፎይታ ሊሰጥ የሚችል የግብርና መሸጫ እና ማከማቻ ማዕከል ግንባታው ከተማዋን በመፍጠን እና በመፍጠር መርህ እንደ ስሟ አዲስ በማድረግ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጫና ለመቀነስ እገዛ የማድረግ አካል መሆኑን ተናግረዋል። የማዕከሉ ግንባታ የህዝባችንን ዋነኛ እና አንገብጋቢ የሆነውን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት የሚያቃልል እና ህዝቡ በቀጥታ ከአምራቹ የመጣውን ምርት በመሸመት ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀከት ነው ብለዋል።

ማዕከሉ ሰፋ ያለና ሁሉንም የምርት አይነቶች በችርቻሮም ሆነ በጅምላ ማቅረብ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል። ፕሮጀክቱን ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሰሩበት መሆኑንም አመልክተው፣ በትብብር ስንሰራ ብዙ መስራት እና መፍጠር እንደሚቻለን እና ለአንድ አካል ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም እንደሚሳካ ያመላከተ ነው ብለዋል።

በዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ምህረት ብርሃኑና ወይዘሮ ክቤ ዴሲሳ ይገኙበታል፡፡ ወጣት ምህረት በቀን 220 ብር የሚከፈላት እና በትርፍ ሰዓት ስራዎችም ተጨማሪም ገቢ እያገኘች መሆኑን ገልፃለች። ወይዘሮ ክቤ ዴሲሳ በበኩሏ በተመሳሳይ በቀን 220 ብር ከፍያ ለሰባት ወር ያህል በረዳት ለሳኝነት እና በጽዳት የቀን ሰራተኛነት ሰርታለች። በዚህም ባገኘችው የስራ እድል ደስተኛ ሆና ልጆቿን እያሳደገች መሆኑን ተናግራለች። ፕሮጀከቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ግንባታው በሚቀጥልበት ቦታ አብራ ለመስራት ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጸችው።

የኦቪድ ኮንስትራክሽን መስራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮናስ ታደሰ በበኩላቸው፤ የገርጂ ፕሮጀክትን ተከትሎ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ከቀን ሰራተኛ እና ግንበኛ ጀምሮ ሁሉም የተሻለ እውቀት አግኝቶ ወደ ሌላ ሳይት መዛወሩን ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ የስራ ባህል የተቀየረበት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በፕሮጀክቱ እየሰራ ያለው የሰው ኃይል ቀን እና ለሊት እየሰራ የዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You