የአዲስ ዓመት ቃለ-ምህላና አፈጻጸሙ

ነጮች ከጀርባው ያለውን ስነልቦናዊ ጣጣ ለመመርመር ሲፈልጉ The Psychology Of New Year’s Resolutions ይሉታል በየዓመቱ የሚታቀደውንና ቃል የሚገባውን የአዲስ ዓመት የሰዎች ግለሰባዊ ቃለ-ምህላ። ሲጋራ ማቆም (አቆማለሁ)፣ ትዳር መያዝ፣ ልጅ መውለድ፣ ትምህርት መማር (መመዝገብ)፣ ገንዘብ ቁጠባ መጀመር፣ ክብደት መቀነስ፣ መጠጥ ማቆም፣ ከማንኛውም ሱስ መፅዳት፣ ለቤተሰብ ጊዜ መስጠት፣ በስራ የበለጠ ውጤታማ መሆን፣ ችላ ያሉትን ኃይማኖት ጠበቅ ለማድረግ ፊትን ወደ ቤተክርስቲያን መመለስ፣ ነጭናጫ አመልን ማስተካከል፣ ከጓደኞች ጋር ያለን ቅርርብ የበለጠ ማጠናከር ወዘተ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኞቹ ምህላዎች እ.አ.አ ከ1947 በኋላ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በአዲስ ዓመት ወደ ተግባር ለመቀየር ቃል የሚገባባቸው፤ ቃለ-ምህላ የሚፈፀምባቸው፣ ከራስ ጋር ፍልሚያ የሚገጠምባቸው፤ ማንነት የሚፈተንባቸው … ርእሰ ጉዳዮች (New Year’s Resolutions) ናቸው።

ከትዳር አጋር መፋታት፣ ትምህርት ማቋረጥ፣ ሲጋራ መጀመር (መልመድ)፣ ከሰው ጋር መጣላት፤ ዝሙት መፈፀም፣ መስረቅ፣ መግደል፣ መጋደል፣ መገዳደል… በአዲስ ዓመት ቃለ-ምህላ ከማይፈፀምባቸው፣ ወይም ሲፈፀም ከማይሰማባቸው፤ ነገር ግን ሁሌም ሲደረጉ የሚታዩ የዕለት ተዕለት የሰው ልጅ ሕይወት ገፅታዎች ናቸው። (የእነዚህ ቃለ-ምህላ በሆድ ይሆን እንዴ??)

የአዲስ ዓመት መግቢያ ሲቃረብ መገናኛ ብዙሀን ለሕይወት ልምድና ተሞክሯቸው ሲባል ወደ አደባባይ የሚያመጧቸው እንግዶች በርካቶች ሲሆኑ፤ ከሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎችም አንዱ “በአዲስ ዓመት ምን ለማድረግ አቅደዋል?” የሚል ነው። መልሱ እንደየመላሹ የሚለያይ ይሁን እንጂ የሁሉም መልስ ግን “ቀና” የሚባል ነው፣ ወይ ከሱስ መላቀቅ፣ አልያም ትዳር መያዝ፣ ልጅ መውለድ…። ጥያቄው፣ “አልኩ” ከማለትና ከጊዜያዊ የሥነልቡና እርካታ ባለፈ ምን ያህሎቹ ተሳክቶላቸዋል፣ ውሳኔዎቻቸው (Resolutions) መሬት ወርደዋል ወይ ሲሆን፣ እኛ አገር እንኳን የዚህና የዋና ዋና ጉዳዮችም መረጃ ስለማይገኝ እናልፈው ዘንድ እንገደዳለን።

ይህ እየተጨዋወትንለት ያለው የኮኮብ ጉዳይ ግለሰብ ሰዎች ላይ ብቻ የሚስተዋል ሳይሆን በተቋማት ላይም ተግባራዊ ሲደረግ መስማትም ሆነ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም።

በተቋማት በኩል ስናየው እንደውም በጣም እየተለመደ የመጣ ይመስላል። በአገራችን ያለውን እውነታ እንኳን ብንመለከት ከመዘወተርም ባለፈ “ሆቢ” (ተወዳጅና ተዘውታሪ ተግባር) እስከ መሆን የደረሰ ሲሆን፣ ለዚህም በየተቋሞቻችን ግንባር ላይ “በ20. . . ከአፍሪካ ተመራጭ የ. . . ሆኖ ማየት”፤ “በ20. . . አዲስ አበባን ከዓለም. . . ማድረስ”፤ “በ20. . . ድህነትን… መጥፋት” እና የመሳሰሉት ተውበውና ተኩለው መታየታቸው ነው።

ሰሞኑን፣ ነሐሴ ወር መጨረሻ አካባቢ 35 የሚሆኑ አገር በቀል ሲቪክ ማህበራት የጋራ መድረክ በመፍጠር በወቅቱ የአገራችን ሁኔታ ላይ ከመከሩ በኋላ “በ2016 ዓ.ም ኢትዮጵያን ምንም አይነት ጥይት የማይጮህባት፤ ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ ሠላም የነገሰባት፣ ምርት የተትረፈረፈባት፣ ጦርነት እና ግጭቶች የራቋት፣ የህዝቦች የእርስ በዕርስ መተማመን የተንሰራፋባት” ወዘተርፈ አገር ማድረግ የሚል ቃል ገብተውና ቃለ-ምህላ ፈፅመው ወደየቤታቸው ተመልሰዋል። (ምን ያህል ይሳካል አይሳካም የሚለውን በአዲሱ ዓመት የአፈፃፀም ሪፖርታቸው የሚነግረን ይሆናል።) ይህም ያው የአዲስ ዓመት ቃለ-ምህላ (በነገራችን ላይ፣ የምህላን ክብደት አስበነው እናውቃለን?) ነውና ጉዳዩ ከግለሰቦችም የዘለለ ለመሆኑ ጥሩ ማሳያ ነው።

ይህ ጥንታዊና በባቢሎናውያን ዘመን (2000 B.C.) እንደ ተጀመረ የሚነገርለት፣ የግለሰቦችን “የአዲስ ዓመት ቃለ-ምህላ” ጉዳይ ሰፋ አድርገን ከተቋማት አዲስ ዓመት (ሀምሌ 1 ከሚጀምረውና “በጀት ዓመት” የሚባለው) ጋርም አያይዘን ብንመለከተው ምርጥ ምርጥ ጉዳዮችን እንደምናገኝ የማይጠረጠር ሆኖ፤ ከእነዚህም መካከል ምን ያህሎቹ ምን ምን ጉዳዮችን ያቅዳሉ፤ ምን ያህሎቹ አዳዲስ እቅዶችን ያካትታሉ፤ ምን ያህሎቹስ የባለፈውን ይደግማሉ (በፓርላማ ሳይቀር እቅድ ሲደገም ማየት/መስማታችንን ልብ ይሏል)፤ ምን ያህሎቹስ ያቀዱትን አሳክተዋል፤ ምን ያህሎቹስ አላሳኩም፤ ምን ያህሎቹስ እቅዶቻቸውን የተለያዩ ምክያቶችን በመዘርዘር ወደሚቀጥሉት ዓመታት አስተላለፏቸው… የሚሉትን ብንመለከት ምናልባት ከግለሰቦች የአዲስ ዓመት ቃለ-ምህላ የተሻለ ሆኖ ላናገኘው እንችል ይሆናልና የሚሄድ ቢሄድበት ያወጣዋል ባይ ነን።

የዓለምን ሕዝብ አንድ ከሚያደርጉት ስነልቦናዊ ጉዳዮች አንዱ ይህ የአዲስ ዓመት መምጣት፣ መግባትና እሱንም ተከትሎ የተለያዩ ውሳኔዎችን (Resolutions፣ አንዳንድ አጥኝዎች ለጉዳዩ ልዩ ትኩረትን በመስጠት “Setting a New Year’s resolution” ይሉታል) በራስ ላይ መወሰንና የመሳሰሉት ናቸው። ይህ የትም እንሂድ የት የጋራና ሁሉም ለራሱ ቃል የሚገባው፤ ቃለ-ምህላም የሚፈፅምበት የግል ጉዳይ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ እከሌ ከእከሌ የሚባል ነገር የለም። መማር አለመማር አንድ ነው። ትልቅ ትንሽ ብሎ ነገር የለም። በወንድና ሴት መካከል ምንም አይነት ልዩነት ሳይኖር ሁሉም ቢያንስ ለራሱ ቃል ይገባል፤ ቃለ-ምህላም ይፈፅማል።

አንዳንድ ልዩነቶች አሉ ከተባለ እንኳን ያለው ልዩነት አንዳንዱ ቃል የገባውን፣ ቃለ-ምህላ የፈፀመበትን ጉዳይ (ጉዳዮች) በአእምሮው (እኛ “በሆዱ ይዞ” እንደምንለው) ወደ ተግባር ለመቀየር ሲታትር፤ አንዳንዱ ራሱን በቻለና ባማረበት አጀንዳ ላይ አስፍሮ መገኘቱ ነው። በቃ፣ ከእነዚህ ውጭ ልዩነት የለም። ሁሉም ቃል ይገባል። ሁሉም ያቅዳል። ለተግባራዊነቱ ሁሉም ይጥራል። ለፍፃሜው ግን… (በኋላ እንመለስበታለን)።

ቃል መግባትንም ሆነ ቃለ-ምህላ መፈፀምን የሁሉም ነው ስንል በቀዳሚነት የዛሬዋን ዓለም በዚህ፣ አሁን ባለችበት መልክ ያስረከቡን ፈላስፎች የተግባሩ ፊት መሪ ሆነው በማግኘታችን ነው። ለምሳሌ ሶቅራጥስ ለራሱ ቃል የገባት፣ ከራሱ ጋር ቃለ-ምህላ የፈፀመባት (በምሁራን ምዳቤ “excellent one-line idea” ከሚለው ስር የምታርፍ)፣ “ያልተመረመረ ሕይወት እንዳልተኖረ ይቆጠራል።” (The unexamined life is not worth living.) በማለት ለራሱ ቃል በገባው መሰረት በየጊዜው ራሱን እየመረመረ፣ እያረመ፣ የጎደለውን እየሞላ፤ ቃል የገባውን እየፈፀመ መኖሩ በታሪክ፣ በተለይም በፍልስፍና ታሪክ ሁሌም ሲነሳ የሚታይና ራስን የማየት ብቃትና “ሪዞሊዩሽን” ነው። ሀሳቡ መነሳት ብቻም ሳይሆን አገላለፁ ተጠቃሽ ጥቅስ (ኮቴብል ኮት) ለመሆን በቅቶ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁሌም ሲጠቀስ እየታየ ነው። (በነገራችን ላይ የግለኝነት (Individuality) ንጉሥ በመባል የሚታወቀው ፍሬደሪክ ኒች ከመንጋው በመነጠል “ራስን መሆን!” (Be­come who you are!)ም ከዚሁ ከ“ምርጥ አንድ መስመር ሀሳብ” (excellent one-line idea) ስር የምትመደብ ናት። ሌሎችም ብዙ አሉ።)

የዓመት መለዋወጥ (turning of the year) ነው የሚሉት ፈላስፎቻችን፣ ቅድመ ሶቅራጥስ አሰላሳዮችን (pre-Socratic thinkers) ይዞ በ1821 “New Year’s Eve.” በሚል ርዕስ አወዛጋቢ መጣጥፍ አስነብቦ የነበረውን እንግሊዛዊ እውቅ ፀሀፊ ቻርለስ ላምብን ጨምሮ፣ በፊዚክሱ ዓለም (በተለይም ከጊዜ አኳያ) ጭልጥ ብለው የገቡት እነ አነስታየንን አካትቶ፣ ጉዳዩን እንደ ቀላል አድርጎ በማየት የካላንደር ጉዳይ (“turning of the calendar” በማለት ነው የሚገልፀው) ያደረገውን የጀርመኑ ፈላስፋ ሀንስ (Hans Blumenberg) ድረስ በጉዳዩ ላይ ያልተጠበበ የለም። በእኛም አገር ያልዘፈነለት፣ ያልዘመረለት፣ ያልተቀኘለት… ማን አለ? ይሁን እንጂ አዲስ ዓመት ከነ ሙሉ ክብሩ፣ እውቅናውና ተወዳጅ/ተደናቂነቱ እዚህ ደርሷል።

በ2022 በተደረገ ጥናት እንደተረጋገጠው ከዓለም ህዝብ 6% በየዓመቱ በአዲሱ ዓመት ራሱን ለመለወጥ፣ ከባለፈው ዓመት ስህተቱ በመፀፀት በራሱ ላይ ውሳኔ የሚያሳልፍ፣ ቃለ-ምህላ የሚፈፅም (resolution የሚፈፅም) ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 47.4% የሚሆነው በራሱ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚያስተላልፍ ሆኖ ተገኝቷል።

በ2015 (እአአ) በተደረገ ጥናት አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ከአጠቃላይ የአሜሪካ ህዝብ 45 በመቶ የሚሆነው በአዲስ ዓመት በራሱ ላይ ለውጥ ለማምጣት ቃል የሚገባ ሲሆን፤ የሚሳካላቸው ስምንት በመቶ (8%) ያህሉ ብቻ ናቸው። ወደ አሁኒቷ አሜሪካ እንምጣ።

በ2020 በየደረገ የሶስት ተከታታይ ዓመታት ጥናት ከአጠቃላይ አሜሪካውያን 44% የሚሆኑት በየዓመቱ ለራሳቸው ቃል የሚገቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ዓመታት የስዊድናውያን ቃል-ገቢዎች ቁጥር ከ12% እስከ 14% ሆኖ ተገኝቷል። በዚህም ቃል በመግባት ደረጃ አሜሪካውያን የተሻሉ ሆነው ተገኝተዋል። እኛስ ጋ? ምንም አይነት መረጃ የለም።

ማርች 9 ቀን 2023 ለአደባባይ የበቃው፤ 1ሺህ 005 ወጣቶችን በመረጃ ምንጭነት የተጠቀመውና ”New Year’s Resolutions Statistics 2023” በሚል ርዕስ (በፎርብስ የጤናው ዘርፍ) የቀረበው ጥናት እንደሚያመለክተው (የአሜሪካኖች አመለካከት፣ አስተሳሰብና አተያይ፤ እንዲሁም ለምን ምን ጉዳዮች ቅድሚያ እንደሚሰጡ… የተንፀባረቀበት በመሆኑ ሙሉ ጽሑፉን ቢያነቡ ብዙ ያተርፋሉ) አብዛኞቹ ቃል የተገባባቸውና ምህላ የተፈፀመባቸው ጉዳዮች ተመሳሳይ ሲሆኑ እነሱም ሲጋራ ማቆም (14%)፣ አዳዲስ ክህሎቶችን ለማዳበር መማር (12%)፣ ሆቢዎችን ተግባራዊ ማድረግ – ለምሳሌ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ መጽሐፍ ማንበብ… (11%)፣ የጤና ጉዳዮችን በመከታተል ጤንነትን ማሻሻል (50%) ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ምን ያህሎቹ ተሳክቶላቸዋል፤ ቃላቸውንስ አክብረው ተገኝተዋል የሚለው በሚቀጥለው ዓመት ጥናት የሚታይ ይሆናል።

ብዙዎች እንደሚሉት አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አዳዲስ ቃለ-ምህላዎችን መፈፀም ጊዜያዊ የስነልቦና ህክምና ከማግኘት ያለፈ ምንም አይነት ፋይዳ የለውም። “ፋይዳ የለውም” የሚለው ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ደግሞ ምንም ማድረግ ሳይሆን በየዓመቱ ቃለ-ምህላ የሚፈፅመውንና በገባው ቃል መሰረት የሚያሳካውን ሰው ቁጥር ወስዶ ማነፃፀሩ ብቻ በቂ ነው። አብዛኛው ቃል ገቢ ቃል በገባ በማግስቱ ረስቶታል። እነዚህ ዝንጉዎች የጃንዋሪ ወር መግባትን ተከትሎ ባለው ሁለተኛው ዓርብ ላይ የሚከበር የአቋራጮች (ቃላቸውን ወደ ተግባር መቀየር ያልቻሉ) የሚያከብሩት “ዓመታዊ ቀን” ያላቸው ሲሆን እሱም “Quitter’s Day.” ይባላል። ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ የአንድ ተቋም ጥናትን (New Plate/Ipsos survey) እንመልከትና ከማቋረጥ ያውጣን ብለን እንውጣ።

ይህ የተቋሙ የ2020 ጥናት እንዳረጋገጠው ቃለ-ምህላቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረት ያደረጉ ያሉ ሲሆን፣ ከመላሾቹ 55% የሚሆኑት እንኳን እስከ ወዲያኛው ሊዘልቁ አንድ ዓመትን እንኳን መዝለቅ አልቻሉም፤ 11% የሆኑት ስድስት ወር ሳይሞላቸው ወደ ነበሩበት ተመልሰዋል። 14%ቱ እንደ ምንም ሶስት ወራትን ደፍነው ወደ ኋላ ተመልሰዋል። 19%ዎቹ በአንድ ወራቸው ከቃለ-ምህላቸው የተፋቱ ሲሆን፤ 11%ዎቹ ከወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለቀድሞው ሕይወታቸው እጅ ሰጥተዋል። (እኛ አገር ፆም ሲገባ ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻ ግሮሰሪዎች ጭር እንደሚሉት ማለት ነው።)

ሌላው ዘና የሚያደርገው ደግሞ ከግብ አንፃር የተሻለ ውጤታማ የሚሆነው የቱ እንደሆነ መጠናቱ ሲሆን፣ የአሜሪካው “PLoS One” ጥናት እንዳረጋገጠው ተግባር-ተኰር የሆኑት ግቦች (action-oriented goals)፣ ማስወገድ-ተኮር (avoidance-oriented goals) ከሆኑት የተሻለና ከአንድ ዓመት በላይ የመዝለቅ አቅም እንዳላቸው፤ በውጤት ደረጃም የመጀመሪያው 58.9%፤ ሁለተኛው 47.1% እንደሆነ መረጋገጡ ነው። በመሆኑም ለራስ ቃለ-ምህላ በሚገባበት ወቅት ዝም ብሎ በመጪው አዲስ ዓመት ሲጋራ አቆማለሁ፣ ፀባይ እገዛለሁ ወዘረተርፈ ማለት ብቻ ሳይሆን ግብ ቀረፃ (goal setting) ላይም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ማለት ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል። ሌላው ፈገግ የሚያደርገው ደግሞ የፈፀሙትን ቃለ-ምህላ መልሶ የማደሻ ጊዜ የመኖሩ እድል ነው።

ከላይ እንደጠቀስነው ተቋም ጥናት ከሆነ ሰዎች ወይኔ፣ ቃሌን አፈረስኩ፣ ቃለ-ምህላዬን ናድኩ ብለው መጨነቅ የለባቸውም። “ምክንያት?” ከተባለ ደግሞ ያፈረሱትን ቃል መልሰው የሚያድሱበት፣ መልሰው ቃለ-ምህላ የሚፈፅሙበት ዓመታዊ እለት ያለዎት መሆኑ ነው። አዎ፣ እንደ ጥናቱ ከሆነ በየዓመቱ “ጁን 1” ዳግም ቃለ-ምህላ የሚፈፀምበት ዕለት ሲሆን በራሳቸው ቋንቋ ሲቀመጥም “New Year’s Resolution Recommit­ment Day” በሚል ሰፍሮ ይገኛል።

ይህ ዓመታዊ የመልሶ ቃለ-ምህላ መፈፀሚያ ቀን (ቀኑ አደባባይ በመውጣት የሚከበር አይደለም) አንድ ለየት ያለና የማይገኝ አጋጣሚን ይዞ የሚመጣ ሲሆን፣ እሱም ያፈረሱትን ምህላ መልሶ ማፅደቂያነቱ ብቻ ሳይሆን በፊት ረስተዋቸው፣ ዘንግተዋቸው፣ ወይም “ግዴለም እነዚህን ወድጃቸዋለሁና ይዣቸው ልዝለቅ፤ አይለዩኝ…” በማለት የተዋቸውን እንደ ገና በመከለስ የዳግም ቃለ-ምህላዎ አካል የማድረግ ታላቅ እድልን ይዞ መምጣቱ ነው።

ዓመቱን የሠላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የብልጽግና ያድርግልን።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You