ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህልተጠናክሮ ይቀጥል!

 እንደ ሀገር አሮጌውን 2015 ዓመተ ምህረት አሰናብተን ፤ አዲሱን ዓመት 2015 ዓ/ም በብዙ ተስፋ ከተቀበልን ቀናቶች ተቆጥረዋል። የዓመቱን መለወጥ ተከትሎም ዜጎች ለአዲሱ ዓመት በፈጠሩት ዝግጅት መጠን ተስፋ ሰንቀው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ይህ ማኅበራዊ ሂደት በየዓመቱ የተለመደ፤ ግን ሁሌም አዲስ ነው።

በዚህ አዲስ ዓመት መባቻ በቀደመው ዓመትም ሆነ በቀደሙት ዓመታት ብዙ ዋጋ ያስከፈሉንን መጥፎ ልምምዶችን አቆማለሁ፣ በቀጣይ ሕይወታችን አትራፊ የሚያደርጉንን በጎ ልምምዶች ደግሞ እጀምራለሁ፣ በዚህም ትናንቶቼን እክሳለሁ ማለት የተለመደ ነው። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠርም የዚሁ እውነታ አካል ነው።

ይህ እውነታ ከግለሰብ ሕይወት አልፎ ማኅበረሰብ የጋራ ሕይወት ውስጥም የሚከሰት፣ የማኅበረሰብን ትናንቶች የተሻለ ለማድረግ በሚደረግ ጥረት ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው። ትውልዶችም ከትናንት ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተምረው የተሻለ ማኅበረሰብ ለመገንባት ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጎላ ሚና የሚኖረው ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ጥንታዊ ትልቅ ሕዝብ/ማኅበረሰብ በጥሩነትም ሆነ በመጥፎነት የሚጠቀሱ የሰፋፊ ማኅበራዊ ልምዶች ባለቤት ነን። ከነዚህ ልምምዶች ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉልንና አንገታችንን አቅንተን፤ በልበ ሙሉነት እንድንሄድ ያስቻሉን እንዳሉ ሁሉ፤ አንሰን እንድንታይ ያደረጉንም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

በተለይም ብሔራዊ አንድነታችንን በየዘመኑ ለአደጋ የሚጥለው የጠብመንጃ /በኃይል የመታመን ልምም,ዳችን /ባህላችን በጊዜ ሂደት ውስጥ ሊታረም ባለመቻሉ አሁን ላለንበት ኋላ ቀርነትና ድህነት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ የታሪክ ምሁራን ይስማማሉ ። የታሪካችን የአብዛኛው ገጽ በዚሁ ትርክት የተሞላ መሆኑ በራሱ እውነቱን አምኖ ለመቀበል አስቸጋሪ አያደርገውም።

በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶች ይህንን ሀገራዊ እውነታ በአግባቡ ተረድተው፤ ማስተካከል የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ አለመቻላቸው፤ ችግሩ በማኅበረሰባዊ ስነልቦና ውስጥ የራሱን አቅም ፈጥሮ አሁነኛ ሀገራዊ ፈተና ከሆነ ውሎ አድሯል። ለይቅርታና ለፍቅር የተዘረጉ እጆችን ሳይቀር በማቁሰል የገነገነ አቅሙን በተጨባጭ አሳይቷል።

ይህ ከዘመኑ በብዙ ያፈነገጠ አስተሳሰብ፤ ሀገሪቱ ካላት ሁለንተናዊ የማደግና የመበልጸግ አቅም ወጥታ፤ ሊመጥናት በማይችል ድህነትና ከዚህ በሚመነጭ ኋላቀርነት ያልተገባ ዋጋ እንድትከፍል፤ ዜጎቿም ሀገራቸው ሰላምና መረጋጋት በማጣቷ ባላቸው አቅም ማድረግ የሚችሉትን እንኳን ማድረግ ሳይችሉ ከሌሎች ጠባቂ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ይህንን በዘመናት ውስጥ ከገነገነ አስተሳሰብ የተወለደ፤ ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ያስከፈለ ማህበራዊ ልምምድ በቀጣይ ተጨማሪ ዋጋ እንዳያስከፍለን፤ በዚህ የአዲስ ዘመን መባቻ ላይ ቆመን ለችግሩ ትኩረት ሰጥተን ልናስብ፤ ልምምዱ በየዘመኑ የነበሩ ትውልዶችን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለ በአግባቡ ልናጤን ያስፈልጋል። ለዚህ ዘመን ተሻጋሪ ችግራችንም ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ ይጠበቅብናል።

ወቅቱ እንደ ሀገር በጠብመንጃ እና ጠብመንጃ ከሚወልደው ኃይል መታመን ወጥተን፤ በሀሳብ የበላይነት/ልዕልና የምንገዛበት፤ ለዚህ የሚሆን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የአስተሳሰብ መሰረት የምንጥልበት፤ ከዚህ የሚመነጭ ማኅበረሰባዊ ባህል/ልምምድ የምንፈጥርበት እና ለመጪዎቹ ትውልዶች በጠንካራ መሰረት ላይ አዋቅረን የምናስረክብበት ነው።

እንደ አንድ ጤነኛ ዜጋ በአዲስ ዓመት ምኞታችን ለሀገራችን የተመኘንላትን ሰላምና መረጋጋት፤ ከዚህ የሚመነጨው ብልጽግና በተጨባጭ መሬት ሊረግጥ የሚችለው፤ ከዚህ በጠብመንጃ እና ጠብመንጃ ከሚወልደው ኃይል መታመን ስንወጣ ነው፤ ለዚህ ደግሞ በእያንዳንዱ ዜጋ መንፈስና አዕምሮ ውስጥ ለዚህ ልምምድ የተገዛውን ስፍራ ማጽዳት ያስፈልጋል።

እንደ ሀገር በየዘመኑ ብዙ ያልተገባ ዋጋ ያስከፈለንን ልምምድ አሸንፈን ለመሻገር፤ በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል የተጀመረውን ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት አዲስ ባህል ለመፍጠር እና ለማስቀጠል ባለን አቅም ሁሉ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል። ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ደግሞ ከሁሉም ሀገሩንና ሕዝቡን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው !

አዲስ ዘመን መስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You