ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ለማስገባት በሚደረገው ጥረት አበረታች ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። መንግሥት አቅም በፈቀደ መልኩ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዲጅታል ኢትዮጵያን በ2025 ዕውን ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል። በቅርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የመንግሥት ግዢን ከካሽ ውጪ በዲጅታል መፈጸም የሚያስችል የአገልግሎት ካርድ ይፋ አድርገዋል።
ማንኛውንም የመንግሥት ግዢ ከጥሬ ገንዘብ / ከካሽ/ ውጭ መፈጸም የሚያስችለው የግዢ ካርድ ይፋ በተደረገበት ወቅትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ፤ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝና ሌሎች የዘርፉ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ላለፉት በርካታ ዓመታት ባንኮች ወደ ዲጅታል ሥርዓት ለመግባት ሲያደርጉ የነበረው ጥረት በሚፈለገው መጠን መጓዝ ሳይችል ቆይቷል። ይሁንና በአሁኑ ወቅት መንግሥት ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን የማድረግ ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ችሏል።
እሳቸው እንዳሉት ፤ የዲጅታል ግብይት ሥርዓትን ለማህበረሰቡ ማለማመድ ለረጅም ጊዜ ፈተና ሆኖ የቆየ ቢሆንም መንግሥት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂን ተግባራዊ በማድረጉ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከባንኮች ቀድመው ወደ ዲጅታል የገቡ የመንግሥት ተቋማት ነበሩ ያሉት ፕሬዘዳንቱ፤ አሁን ላይ ሁሉም ነገር ዲጅታላይዝ እየሆነ በመምጣቱ ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ግልጽ የሆነ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት መቻሉንም አንስተዋል። አገልግሎት በኮር ባንኪንግ ሥርዓት በመተሳሰሩ የሁሉም ቅርንጫፍ ደንበኞች የተሟላ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ሆነዋል።
ንግድ ባንክ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በሚሰራው ሥራ በርካታ ለውጦች መመዝገባቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከአንድ ዓመት አስቀድሞ አንድ ትሪሊዮን መግባት ያልቻለው ዘመናዊ የገንዘብ ዝውውር፣ በአሁኑ ወቅት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። በመሆኑም በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ሦስት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ብር በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት የገንዘብ ልውውጥ መደረጉን አስታውቀዋል። ይህም የባንኩን አጠቃላይ ሀብት ሦስት እጥፍ ሊሆን ትንሽ የቀረው ገንዘብ እንደሆነ ነው ያመላከቱት። በዘመናዊ የገንዘብ ልውውጥ ሥርዓቱ ኤ.ቲ.ኤም፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ፖስት ማሽኖችን፣ ሲቢኢ ብርና ሌሎች በርካታ የዲጅታል ክፍያ አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸውንም አብራርተዋል።
ባንኩ የሀገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን የኅብረተሰቡን ኑሮ ለማቅለልና በኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ገንቢ ሚና ለመጫወት በከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀጣይም ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል የክፍያ ሥርዓቱን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ለማስገባትና ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማርካት የሚሠራ ይሆናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የዲጅታል ስትራቴጂ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲተገበር መቆየቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ አስታውሰው፣ በዚህም ትርጉም ያለው ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። እሳቸው እንዳሉትለ፤ የዲጅታል ስትራቴጂው ዋና ግብ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ማስገባት ነው፤ ይህም በመንግሥት ካልተመራ በስተቀር በተፈለገው ፍጥነት ሊጓዝ አይችልም። በተለይም በኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት ድርሻ ትልቅ በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት መንግሥት ትልቁ ቀጣሪና ገዢ ነው። ስለዚህ መንግሥት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን ትልቅ ድርሻ ተጠቅሞ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎችን በዋናነት ይዞ ይሰራል ።
መንግሥት ሀገራዊ የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ግቡ እንዲሳካ በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል ሲሉ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም የገንዘብ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የሠራው ሥራ የዚሁ ሥራ አካል እንደሆነ ጠቅሰዋል። ይፋ የተደረገው የግዢ ሥርዓትም አጠቃላይ የመንግሥት ወጪዎች ዲጅታል በሆነ መንገድ ዝውውር ማድረግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ነው ብለዋል። ለዚህም አስቀድሞ በተቀናጀ መንገድ ‹‹ኢፍ ሚስን›› ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፣ በተጨማሪም የተለያዩ አሰራሮች በየደረጃው ተግባራዊ ሲደረጉ መቆየታቸውን ዶክተር እዮብ አስታውቀዋል።
አሁን ደግሞ በተለያዩ የፖስ ማሽኖችና በኢንተርኔት ባንኪንግ ተቋማት ዲጅታሊ የገንዘብ ዝውውር ማድረግ እንዲችሉ የሚያስችል አሠራር ተግባራዊ መደረጉን ነው የገለጹት። እሳቸው እንዳሉት፤ ግዢ የሚፈጽም አንድ ባለሙያ ካሽ ተሸክሞ መሄድና ባንክ ሄዶ ጥሬ ብር ከባንክ ማውጣት ሳይሆን እንደ ሌሎች ዘመናዊ ሀገራት ካርድ ይዞ በካርድ ግዢ መፈጸም ይችላል። ይህ የግዢ ሥርዓትም ግዢው የተፋጠነ፣ የተሳለጠና ግልጽ እንዲሆን ያደርገዋል።
በአሁኑ ወቅትም ይህንኑ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ተቋማት ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ተቋማቱ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። አንዳንድ ተቋማት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት በፍጥነት ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ገና ወደ ዲጅታል ሥርዓቱ እየገቡ እንደሆነ ነው የተናገሩት።
‹‹በመንግሥት የተያዘው አቅጣጫ ሁሉም ተቋማት በተሟላ ሁኔታ ወደ ዲጅታል ሥርዓቱ እንዲገቡ ማድረግ ነው›› ያሉት ዶክተር እዮብ፤ በተለይም የታክስ ክፍያ የነዳጅ ግዢና ሽያጭ በሙሉ ዲጅታል መሆን አለበት ይላሉ። ሀገራት ከካሽ ዝውውር ሙሉ ለሙሉ እየወጡ ባሉበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያም ጥሬ ገንዘብን በካሽ ከማዘዋወር ሙሉ ለሙሉ ወጥታ ወደ ዲጅታል ሥርዓት እንድትገባ ይደረጋል ብለዋል። የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ከፍተኛ ወጪን እንደሚጠይቅ ተናግረው፤ ገንዘቡን ከማተም ጀምሮ፣ የደህንነት ግዢና ወጪውን ማለትም የገንዘብ ዝውውሩን በሚገባ ለመከታተልና ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የገለጹት። ወደ ዲጅታል ሥርዓት በመግባት የገንዘብ ዝውውርን ከካሽ ውጪ ማድረግ ግን እነዚህን ሁሉ ችግሮች መፍታት ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪም አገልግሎቱ ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።
ከጥቂት ዓመታት በፊት ምንም ያልነበረውና የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን ሥርዓት አሁን ላይ እየተስፋፋ መጥቷል ያሉት ዶክተር እዮብ፤ ይህም መንግሥት በቁርጠኝነት የዲጅታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳውን ለማሳካት እየሠራ እንዳለና ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጠው አንድ ማሳያ ነው ብለዋል። በቀጣይም ይህን አጠናክሮ በማስቀጠል በሁለተኛው የሪፎርም ምዕራፍ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ዲጅታል ወደ ማድረግ ሥራ ይገባል ነው ያሉት።
በየደረጃው እየተስፋፋ የመጣውን የዲጅታል ግብይት አጠናክሮ በማስቀጠል ሁሉንም የመንግሥት ተቋማት በሰፊው ወደ ዲጅታል ማስገባት በቀጣይ ከሚሠሩ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሹ መሆኑን ያነሱት ዶክተር እዮብ፤ በተለይም ከክልሎችና ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በክልል የሚገኙ ተቋማትን ሙሉ ለሙሉ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ ማስገባት ቀጣይ የቤት ሥራ እንደሆነ ነው ያነሱት። በመሆኑም ከየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የሚደረግ የገንዘብ ዝውውርም ሆነ ማንኛውም ግዢ በዲጅታል እንዲሆን ይሠራል ብለዋል።
አሁን ላይ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ዲጅታል ግብይቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱ የተጠናቀቀ መሆኑን እና ካርዱ መዘጋጀቱን የጠቀሱት ዶክተር እዮብ፤ የአገልግሎት ካርዱ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ተደራሽ እንደሚሆንና በቀጣይም ወደ ክልሎች እንደሚወርድ አስታውቀዋል። እስካሁን በተደረገው ግምገማም የዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ ውጤታማ እየሆነ መምጣቱንና ካለው ፍላጎት አንጻር ገና የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በርካታ የዲጅታል አገልግሎቶችን ማስተዋወቅ እንደቻለ የገለጹት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጅታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳዕላክ ይገዙ በበኩላቸው የዲጅታል ዕድገቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል። እሳቸው እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት በጥቂት ካርዶችና ኤቲኤሞች ተወስኖ አነስተኛ ዕድገት የነበረው ቢሆንም፣ ኢንተርኔት ባንኪንግና ሞባይል ባንኪንግን እንዲሁም ሲቢኢ ብርን እና የተለያዩ የአገልግሎት ካርዶችን አስተዋውቋል። በዚህም ዲጅታል የገንዘብ ዝውውሩ እያደገ መጥቷል።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 64 በመቶ የሚሆነው የባንኩ የገንዘብ እንቅስቃሴ በዲጂታል አማራጮች ማንቀሳቀስ ችሏል። ይህም ማለት 36 የገንዘብ ዝውውር የተካሄደው በቅርንጫፎች ሲሆን፤ ቀሪዎቹ የገንዘብ ዝውውሮች ደግሞ ደንበኞች ባደረጉት የዲጅታል ቻናሎች አማካኝነት ነው። ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ወዲህ በዲጅታል የገንዘብ ልውውጥ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ይገኛል። ለተመዘገበው ዕድገትም መንግሥት ያስቀመጠው የዲጅታል አቅጣጫ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው።
መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በተለይም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ክፍያዎቻቸውን በዲጅታል ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ለተመዘገበው ዕድገት ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት አቶ ዳዕላክ፤ የዲጅታል ዝውውር ዕድገቱ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም ከፍ ያለ እንደሆነ ነው ያስረዱት፤ እሳቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገንዘብ ዝውውር የሚያደርግባቸው ሁለት መንገዶች ያሉት ሲሆን፤ አንደኛው በቅርንጫፎች አማካኝነት ነው፤ ሌላው ደግሞ ዲጅታል ቻናሎች ናቸው። ዲጅታል ቻናሎች በርካታ ሲሆኑ፣ ሞባይል ባንኪንግ፣ ኢንተርኔት ባንኪንግ፣ ኤቲየም፣ ፖስ ማሽን እና ሲቢ ብር የሚባሉ ናቸው።
ባንኩ ከመንግሥት ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር ጎን ለጎን እየሄደ ያለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዳዕላክ፤ መንግሥት ጥሬ ገንዘብን ማተም እስካላቆመ ድረስ ከካሽ ውጪ እንሆናለን ማለት የማይቻልና የካሽ ግብይት የሚቀጠል እንደሆነ ገልጸው፣ ዓለም ላይም ከካሽ ነጻ የሆነ ሀገር እንደሌለም ተናግረዋል። ነገር ግን አማራጭ ካላጣ በስተቀር ካሽን የማይጠቀም ማኅበረሰብ ለመፍጠር ባንኩ አቅዶ እየሠራ ነው ብለዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ አሁን ባለው ሁኔታም ባንኩ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ይፋ ያደረገው የመንግሥት የግዢ ካርድ የዲጅታል ሥርዓቱን ማሳለጥ ይቻላል፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሠራተኞች ደመወዝን ጨምሮ ትላልቅ ክፍያዎችን የሚፈጽም እንደመሆኑ በኢንተርኔት ባንኪንግ ይጠቀማሉ። የዕለት ተዕለት ግዢዎችን በካሽ ወይም ጥሬ ገንዘብ በመጠቀም ይፈጽማሉ። ስለዚህ ይህን ዲጅታላይዝ ማድረግ አስፈላጊና ተገቢ በመሆኑ ወደዚሁ መግባት ተችሏል። ለዚህም ሥራውን በዋናት የያዘው ገንዘብ ሚኒስቴር ከንግድ ባንክ ጋር በጋራ በመሆን ወደ ዲጅታል ለመቀየር ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
በመሆኑም ከዚህ በኋላ ሁሉም የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለሚፈጽሙት ማንኛውም ግዢ ካሽ ወይም ጥሬ ገንዘብ በቼክ የማይንቀሳቀሱ እንደሆነ የገለጹ አቶ ዳዕላክ፤ ለሁሉም መስሪያ ቤቶች ካርዱን ተደራሽ በማድረግ ግዢዎቻቸውን በሙሉ በካርዱ አማካኝነት በዲጅታል የሚፈጽሙ እንደሆነ ነው ያብራሩት። እሳቸው እንዳሉት፤ ሁሉም መስሪያ ቤቶች ኢንተርኔት ባንኪንግ ያላቸው በመሆኑ በየጊዜው የሚፈልጉትን የግዢ መጠን ከኢንተርኔት ባንኪንግ ወደ ካርዱ በመሙላት ግብይታቸውን መፈጸም የሚችሉበት የግዢ ሥርዓት ነው።
ተቋማቱ ካርዱን ለሌሎች ሰዎች አሳልፈው ካልሰጡ በስተቀር በኢንተርኔት ባንኪንግ የሚያደርጉት ግብይት ወይም ክፍያ መጭበርበር የሚገጥመው እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ዳዕላክ፤ ካርዱ የራሱ የሆነ የደህንነት አካሄዶች እንዳሉት ተናግረዋል። በዚህ በኩል የሚፈጠር ችግር አይኖርም ሲሉም ገልጸዋል። ባንኩ አጠቃላይ ሥርዓቱን እንደሚቆጣጠርና መጭበርበሮች እንደማይፈጠሩ ጠቅሰው፣ በዲጅታል ግብይቱ የሚገጥም ችግር አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም
ፍሬሕይወት አወቀ