ብሔራዊ ምክክር – ዘላቂ ሰላም

ሀገራችን ኢትዮጵያ ለተሻለ ሀገራዊ ተግባቦት በብሔራዊ ምክክር በኩል እንቅስቃሴ እያደረገች እንደሆነ ይታወቃል። ይሄም እንቅስቃሴ በተመረጡ ባለሙያዎች ለዓመታት ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበት ወደ ሥራ ሊገባ ቀናቶች እየቀሩት ነው።

እንደ ሀገር የተደቀኑብንን ማናቸውንም አይነት ፈተናዎች በጦርነት ሳይሆን በሰላም፣ በጥላቻ ሳይሆን በይቅርታ ለመሻገር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚደነቅ ነው። እንዲህ አይነቱ ዘመነኛ እሳቤ ከትናንት ወደዛሬ መጥተው እድፍ ያለበሱንን የፖለቲካ ትኩሳቶች ሽሮ አንድነትን እንደሚሰጠን ይታመናል።

አንድ እግራችን ትናንት ላይ አንዱ ደግሞ ዛሬ ላይ ቆሞ በመንታ ልብ ጥንድ ሃሳቦችን ስንካድም ከሚገባን ፊተኝነት ተቆራርጠናል። ወዴት እንደምንሄድ መንገድ ጠፍቶን አሻጋሪ ስንፈልግ ታይተናል። አዲስ መንገድ መስራት አቅቶን በተራመድነው መንገድ ላይ ተጋግመን ስንመላለስ ዓመታት ተቆጥረዋል።

እነዛ ከመሄድ ባለፈ፣ ከድካም ባለፈ ብርታት ያልሰጡን ጎዳናዎች ዛሬ ላይ በምክክርና በውይይት ሎጥ የሄደባቸው የጸጋ ጎዳናዎች እንዲሆኑ ተረት ወለድ ትርክቶቻችንን ሽረን በእርቅና በመተቃቀፍ ዳግም ልንሄድባቸው ጥርጊያ ጀምረናል። ለአዲስ ሃሳቦች ቅድሚያ ሰጥተን ያለፈው የቁርሾ ጊዜ ባለፈ አስተሳሰብ ስር እንደነበር አምነን በመቀበል አዲሱን የእርቅ መንገድ በአዲስ ሃሳብ ለመጀመር እያሟሟቅን ነው።

ብዙ ተራምደን ወደረፍት የሚወስድ የማርያም መንገድ ያላገኘነው ልባችንን ከጥላቻ ስላላጸዳን ነው። ማናችሁ ስንባል ኢትዮጵያዊ ነን እንላለን በማንነታችን ውስጥ ግን ከአባቶቻችን የወረስነው የአንድነትና የፍቅር እውነት የለም። ይሄን መሰሉ ኢትዮጵያዊ ሆኖ በመለያየት ውስጥ መቆም የደስታ መንገዳችንን ሰውሮብናል።

ኢትዮጵያዊ ሆኖ እኔነት የለም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ዘረኝነት የለም። ኢትዮጵያዊነት መነሻው አንድነት መድረሻውም እኛነት ነው። የአባቶቻችን ሀገር የመፍጠር ዓላማ ከዛም ባለፈ ሀገር የማጽናት እውነት በዚህ አንድነትን መሰረት ባደረገ የመነሻና የመድረሻ እሳቤ ውስጥ የጸና ነው።

እኛ የዛኛው ትውልድ በአንድነቱ ሀገር የሠራው የአባቶቻችን መልክ ነን። በዚህ መልክ ውስጥ የብሄር ሽኩቻ፣ የእኔነት ውዳሴ የለም። ይሄ መልክ በኢትዮጵያዊነት የቆነጀ፣ በህብረ ብሄራዊነት ያጌጠ የብዙሃነት ቀለም ነው። ከብዙሃነት ውስጥ እኔ ብለን ራሳችንን ብቻ ስናወድስ ኢትዮጵያዊነት የተሠራበትን የጋራ እውነት እያላላን ነው።

ዛሬ ላይ ጠብቆ ተገምዶ ግን ደግሞ የላላው የአባቶቻችን እውነት ከብዙ ማንነት ውስጥ ራሳችንን ብቻ የማድመቃችን፣ የማወደሳችን፣ የመነጠላችን፣ የማሞካሸታችን ጣጣ ነው። በብሄር ስም ተቧድነን፣ ከትናንት አብራክ ውስጥ ነውር እየመዘዝን የምንጠላላው ጥላቻ፣ የምንቀያየመው ቅያሚ የጸነሰው ጋፍ ጽንስ ነው።

የድህነት አቀበት በመያያዝ የሚታለፍ ነው። ሳይያያዝና በአብሮነት ሳይቆም ታሪኩን የለወጠ ሀገርና ሕዝብ የለም። የስልጥኖቹን የስልጣኔ ታሪክ ብናጠና የሀገር ፍቅር ስሜታቸው ከእኛነት መንፈስ ውስጥ እንደፈለቀ እንደርስበታለን። በተቃራኒው ብዙ ሕዝብ ይዘው፣ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል አቅፈው፣ በወጣትና በተፈጥሮ ደምቀው ግን ደግሞ ከምኞት ባለፈ ከነበሩበት ፈቀቅ ያላሉ ሀገራት ጥቂቶች አይደሉም። የእኚህን ሁለት ሀገራት የአስተሳሰብ አድማስ ብንፈትሽ እኔነትና እኛነት ሆኖ እናገኘዋለን።

እኛ ብለን እስካልተነሳን ድረስ ልዩነትን መፍጠር አይቻለንም። እኔነት ብዙዎች ለብቻቸው ኖረው፣ ለብቻቸው አስበው፣ ለብቻቸው የሚሞቱበት መቃብር ነው። ታላቁ ሩሲያዊ ደራሲ ፊዮዶር ዶስቶፍስኪ ይሄን የእኔነት እሳቤ ተንተርሶ እንዲህ ብሎ ነበር ‹እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ሲኦል ማለት ሌሎችን አለማፍቀር የሚፈጥረው የሕመም ስሜት ነው› ፤ ራስን ከሌሎች መነጠልን ክፉ ከሆነችው ሲኦል ጋር አዛም ዶታል።

አንድ አይነት ሆነን ከትናንት ወደዛሬ የመጣነው አንድ አይነት ሆነን ስለቆም ነው። እድሳት ያስፈልገናል። ዘመኑ ከትናንት ዛሬ ሌላ ነው። ዓለም በስልጣኔው ሩቅ በደረሰበት በዚህ ስልጡን ዘመን ላይ በትናንት ፖለቲካ፣ በትናንት ጥፋት፣ በትናንት ትርክት ዛሬን መኖር ከምንም የማይወዳደር ጥፋት ነው።

እኔነት ከነውርና ስር ከሰደደ ራስ ወዳድነት ባለፈ ለትውልዱ መጥፎ የሚያስተምር፣ በራስና በሀገር ላይ መጨከን ነው። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በራሳችን ላይ ጨክነናል። በምናስበው ሃሳብ፣ በምናራምደው እምነት እየጎዳን ያለነው ራሳችንን ነው። የሚጠቅመን በጋራ ሃሳብ የጋራ ጥቅማችንን መፍጠር ነው።

ሃሳቦቻችን ወደጥፋት ከማምራታቸው በፊት የሚገራ፣ የሚያቀና እውቀት ያስፈልገናል። ያልገባን እንዲገባን የገቡን የስህተት እውነቶች መሻር አለባቸው። አሁን የሚያስፈልገን ያልገባን እንዲገባን ነው። ከገቡን ይልቅ ያልገቡን እንደሚበጁን ገብቶናል ባለው ፖለቲካና ፖለቲከኞች የደረሰውን ጥፋትና ውድመት ማየቱ በቂ ነው።

ረፍታችን ያለው ባልገቡን እውነቶች ውስጥ ነው። ያልገቡን እውነቶች እንዲገቡን ራሳችንን በኢትዮጵያዊነት ስነምግባር ማነጽና የአባቶቻችንን ሀገር የመፍጠር እውነት መከተል አለብን። ያልገቡን እንዲገቡን ሰላምን በጦርነት ከማምጣት እሳቤ ወጥተን ከጦርነት በፊት ሰላም፣ ከጥላቻ በፊት ፍቅርን የሚል አዲስ እውቀት ሊዋሃደን ይገባል።

በኢትዮጵያ ስዕል ውስጥ የሁላችንም ብሩሽ አለ። ኢትዮጵያን የሳላት የሁላችን ሃሳብ፣ የሁላችን ሥርዓት ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ ቢጎል ደብዛዛዋን ኢትዮጵያ ነው የምናገኘው። የብኩርና ግፊያችን ማናችንንም ፊተኛ አያደርግም። ኢትዮጵያን ከመጣል፣ አንድነታችንን ከመነቅነቅ ባለፈ የሚጨምርልን የኃይል አቅም የለም።

ወዳልገቡን እውነቶች እንማትር። ፖለቲካው ያስተማረንን፣ ፖለቲከኞቻችን የሰጡንን የእኔነት ሃሳብ ሽረን የአባቶቻችንን እውነት እንከተል። ለእውነትና ለእርቅ ከተጠቀምነው ብሄራዊ ምክክር መንገድ የሚሰጠን ነው። በጥላቻ የዘጋነውን፣ በራስ ወዳድነት የራቅነውን የእረፍት መንገድ የሚቀድልን ነው።

መንገድ ያስፈልገናል። ወደሰላም መሄጃ፣ ወደአንድነት ማስተዋያ መንገድ። መንገድ ያስፈልገናል ወደእርቅ፣ ወደፍቅር የሚወስድ።መንገዶቻችንን የዘጋነው ራሳችን ነን። የአባቶቻችንን የእውነትና የሀቅ መንገድ ስተን ፖለቲከኞቻችን በሰጡን የእኔነት መንገድ ላይ የቆምነው ባልገባን እውቀት ነው።

የምክክር ጽንሰ ሃሳብ በየትኛውም ሀገርና ባህል ውስጥ አንድ አይነት ነው፤እርሱም መግባባትን መፍጠር ነው። ዓለም ላይ በእንዲህ አይነቱ የምክክር ዘዴ ሀገራቸውን ከተጣመመችበት ያቃኑ ብዙ ናቸው። አይደለም ሰው ከሰው፣ አይደለም ፖለቲከኛ ከፖለቲከኛ ቀርቶ በአንድ ልብና አእምሮ እየተመራ እንኳን እግር ከእግርም ይጋጫል።

ትልቁ እና ሊሰመርበት የሚገባው ነገር ያደናቀፈን እንቅፋት መልሶ እንዳያደናቅፈን ከመንገዳችን ላይ ገለል ማድረግ ነው። የእኛ ችግር እንቅፋቱን ከመንገዳችን ላይ ሳናነሳ አንድ ጊዜ ባደናቀፈን እንቅፋት ደጋግመን መደናቀፋችን ነው። ለጦርነት እና ለመለያየት እየዳረጉን ያሉ ችግሮችን መለስ ብለን ብናይ አንድ አይነት ሆነው እናገኛቸዋለን። ሌላው ቢቀር ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ የብሄር እሳቤ እያራመድን ያለነው ፖለቲከኞቻችን በፈጠሩት የሀሰት ትርክት ነው።

ከትናንት እስከዛሬ ፖለቲካችን መደናቀፊያችን ነው። ከድሮ እስከ ዘንድሮ የብሄር ጉዳይ መነታረኪያችን ነው። መንገዳችንን ማጥራት አለብን። ስናልፍና ስናገድም በአንድ አይነት መንገድ ላይ በአንድ አይነት እንቅፋት መመታታችን እንዲቀር በእንቅፋቶቻችን ላይ ለውይይት መቀመጥ መፍትሔ የሚሰጠን መላ ነው።

ፖለቲካችን እንዳያደናቅፈን፣ ያልኖርነው ትናንትና እንዳያቀያይመን በእውቀትና በሥርዓት የተመራ የተሀድሶ ንቅናቄ ያሻናል። ንቅናቄው የሚጀምረው በአዲስ ሃሳብ ነው። አዲስ ሃሳብ የአዲስ መላ፣ የአዲስ መፍትሔ አብራክ ነው። እስከዛሬ ባልታደሰ ሃሳብ ለውይይት ተቀምጠን ለውጥ ሳናመጣ ቀርተናል።

የምንወያየው ለለውጥ ነው። ያደናቀፉን እንቅፋቶች ዳግም እንዳይጥሉን እንዴት ከመንገዳችን ላይ ገለል እናደርጋቸው የሚል ምክረ ሃሳብን ለማዋጣት ነው። በተዋጣና በታመነበት ሕዝባዊ ተሳትፎ በእንቅፋቶቻችን ላይ ስንወያይ ብቻ ነው መንገዳችንን ከጋሬጣ የምንጠብቀው።

ለችግሮቻችን የመፍትሔ ሃሳብ ከሌለን ያ መንገድ፣ ያፖለቲካ፣ ያ እንቅፋት እንዲያደናቅፈን ፈቅደናል እንደማለት ነው። አሁን ላለችው ኢትዮጵያና አሁን ላለው ሀገራዊ ተግዳሮት ከችግሮቻችን የሚበልጥ የመፍትሔ ሃሳብ ነው የሚያስፈልገን። ከችግሮቻችን በሚበልጥ የመፍትሔ ሃሳብ ነው ፖለቲካችንም ሆነ ሌሎች ነውሮቻችን የሚታከሙት።

እስከዛሬ ተወያይተን መፍትሔ ያላመጣነው በችግሮቻችን ስለተበለጥን ነው። በችግር መበለጥ ልክ እንደ እኛ በአንድ አይነት እንቅፋት፣ በአንድ አይነት መንገድ ላይ ደጋግሞ መውደቅ ነው። ከችግሮቻችን የላቀ ሁሉን አቀፍ የለውጥና የተሀድሶ ተራማጅ እሳቤ ያስፈልገናል።

ብሄራዊ ምክክር ደግሞ ብሄራዊ ተሀድሶን የሚሰጠን የአዲስ ለውጥ ንቅናቄ ነው። እንቅፋቶቻችን በዛ መድረክ ላይ በሃሳብ የበላይነት ተኮርኩመው ተነቃንቀው መውደቅ አለባቸው። ከዛም ከዚም የመጡ አሁናዊና ድሮአዊ ነውጥ ፈጣሪ ተግዳሮቶች እንደ ልብስ በሃሳብ ሳሙና ታጥበው መጥራት አለባቸው።

ሃሳባችን ነውራችንን ካላጠራልን በምንም አንጠራም። ፍቅራችን እድፋችንን ካላጸዳልን ምንም አንጸዳም። እንደሕዝብ ለምክክር ስንቀመጥ እንዴትም፣ ከየትም ይምጡ በችግሮቻችን ላይ የበላይ ለመሆን ነው። ከፊታችን ያለው ሀገራዊ ምክክር ትኩሳቶቻችን የሚሽሩበት የብዙዎቻችን የትንሳኤ ጣይ የሚወጣበት የተስፋ ምስራቅ ነው።

ብሄራዊ ምክክር ለብሄራዊ ተግባቦት እንደ አንድ የዋርካ ስር ነው። ዛፍ በስሩ እንደሚጸና ሀገርም በሃሳብ ነው የምትጸናው። ሃሳብ ግን አይነት አለው። ሀገር የማጽናቱን ያክል ሀገር የሚያፈርሱ ሃሳቦች አሉ። ዓላማችን ሀገር ማጽናት፣ ብሄራዊ አንድነትን ማምጣት እስከሆነ ድረስ በስሮቹ እንደጸናው ዛፍ በዜጎቿ ሃሳብ የጸናች ሀገር ታስፈልገናለች።

ዛፍ ስር ከሌለው ግንድና ቅርንጫፉ፣ አበባና ፍሬው ምንም ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ ሀገር አስታራቂና አንቂ፣ አስማሚ ሃሳብ ከሌላት አበባና ፍሬ፣ ቅርንጫፍና ግንድ እንደሌለው የይስሙላ ዛፍ ናት። የዚህ ውጤቱ ደግሞ በፖለቲካ እንቅፋት መደነቃቀፍ፣ ባልተኖረ ትናንትና ባልመጣ ነገ መባላት የመሳሰሉት ነውሮች ናቸው።

እንደ ሀገር ወደራቀ ነገ ለመዝለቅ፣ አብሮ እንደመጣ፣ አብሮ እንደኖረ፣ አብሮ እንደተዋለደ ሕዝብ የጋራ ሀገርና የጋራ ታሪክ ለመሰነድ በተረት ሳይሆን በእውነት፣ በብሄር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት የሚያምን ፖለቲካና ፖለቲከኛ፣ ዜጋና ትውልድ፣ ምሁርና አስተማሪ፣ አንቂና አስታራቂ ያሻናል።

ኢትዮጵያን የሚያሽር፣ የሚታደግ፣ የሚደግፍ፣ የሚለውጥ ሃሳብ ከብሄራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ትጠብቃለች። ትውልዱ አንድነቱን ጠብቆ የጋራ ሀገሩን በጋራ እንዲያለማ አባቶቹን የሚያስታውስ ዝክረ አድዋን የመሰለ የአንድነት አውድ ያስፈልገዋል። እንዲህ በመሰለው መንገድ ላይ ስንራመድ ብቻ ነው ትናንት ያደሙን እንቅፋቶቻችን ዛሬ ላይ እንዳይደግሙን የምናደርገው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You