አዲስ ዓመት፣ ምክንያታዊ ትውልድ፣ኃያል ሀገር!

 የራሷ የዘመን አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ፣ 2016 ዓ.ምን ልትቀበል ነው።ሀገሪቱና ዜጎቿ አዲሱ ዓመት ምን ይዞባ(ላ) ቸው እንደሚመጣ እርግጠኞች አይደሉም።ኢትዮጵያውያን ከአንድም ሁለት፣ ሦስት ጊዜ አዲስ ዓመት ሲመጣ መልካሙን ተመኝተውና አልመው ነበር፤በተግባር የታየው ግን ‹ይሆናል› ብለው ያላሰቡትና ያልጠበቁት ነበር።የሰላም እጦት፣ የዜጎች አሰቃቂ ሞትና መፈናቀል፣ የሀብት ዝርፊያና ውድመት … ተደጋግመው ታይተዋል።በእርግጥ ‹‹ሀገሪቱ በእነዚህ ሁሉ መከራዎች ውስጥ ሆና ስኬቶችንም አስመዝግባለች›› ተብሎ የሚነገረው ትርክትም የሚዘነጋ አይደለም።ነገር ግን ሌላው ሁሉ ይቅርና ‹‹በማንነት ምክንያት ከመገደልና ከመፈናቀል ስጋት ነፃ ሆኖ በሰላም ወጥቶ መግባትን እውን ማድረግ የተሳነውን ‹ስኬት› እንደስኬት መጥቀስ ተገቢ ነው?›› የሚለው ጥያቄ አጥጋቢ ምላሽ የማግኘቱ ነገር አጠራጣሪም አከራካሪም ነው።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ለመሆን የሚያግዟት እምቅ የተፈጥሮ ሀብት፣ ግዙፍ የሰው ኃይል፣ የተከማቸ የታሪክ እርሾ እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ ግብዓቶች ያሏት ሀገር ናት።እነዚህን ግብዓቶች አቀናጅታ ታላቅና ኃያል ሀገር የመሆን እድል ቢኖራትም ይህን እድል በተግባር የመተርጎሙ ነገር ግን በተጨባጭ ሊሰምር አልቻለም።ከሺ ዓመታት በፊት በበሬ የሚያርሰው የኢትዮጵያ ገበሬ ዛሬም ከዚሁ የአስተራረስ ዘዴ መላቀቅና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ከመምራት መሻገር አልቻለም።ረሀብ ደጋግሞ ጎብኝቶን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለው ስም የረሀብና የችጋር ምሳሌ ተደርጎ ቆይቷል።ጦርነት የሀገሪቱ ዋነኛ መገለጫ እስኪመስል ድረስ ለቁጥር የሚታክቱ ደም አፋሳሽ ጦርነቶች በኢትዮጵያ ምድር ተካሂደዋል።የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች ከውጭ ሀገራት እየተቀዱ መጥተው ሕዝብ ያለምንም ማሰላሰል እንዲሸከማቸው ተደርጎ ብዙ ዋጋ አስከፍለዋል።የውሸት ትርክቶች ‹‹ለምን፣ እንዴት …?›› የሚል ጠያቂ አጥተው የአንድ ሀገር ልጆች ጎራ ለይተው እንዲጫረሱ አድርገዋል፤ በጠላትነት መፈራረጅን አስከትለዋል፤የሀገሪቱ ቅርጽ (ካርታ) እንዲቀየርም አድርገዋል።እነዚህ ችግሮች ከመቃለል ይልቅ ይበልጥ እየተወሳሰቡ መጥተው ዛሬም ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መራራ ዋጋ እያስከፈሉ ቀጥለዋል።

አዲሱን ዓመት ስንቀበል ከምንሰናበተው አሮጌ ዓመት ጋር አብረው የማይሰናበቱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ።በአዲሱ ዓመት ሊከናወኑ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎችም አሉ።ኢትዮጵያ ብዙ ሺ ዓመታትን ባስቆጠረው እድሜዋ ‹‹ረሀብንና ጦርነትን ደጋግማ የማስተናገዷ ምክንያት ምንድን ነው? ደጋግመው ካጋጠሟት ችግሮቿ መላቀቅ ያልቻለችውስ ለምን ይሆን?›› የሚለው ጥያቄ የሰከነ ውይይትና አጥጋቢ ምላሽ የሚፈልግ መሠረታዊ ጉዳይ ነው።ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች አካላት ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ ብዙ ምላሾችን ሰጥተዋል።ከእነዚህም መካከል የውጭ ኃይሎች ሴራ፣ መደማመጥ አለመቻል፣ የልኂቃን በጎ ያልሆኑ እሳቤዎች፣ የሕዝቦቿ ማኅበራዊ ስሪት … የሚሉት ምክንያቶች ተጠቃሽ ናቸው።ሀገሪቱ በችግሮች ውስጥ ደጋግማ የመገኘቷ ምክንያት ‹‹የመለኮታዊ ኃይል ቁጣ›› እንደሆነ የሚያምኑም አሉ።

ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት አልተሞከረም።የአንዱን ንጉሥ ንግሥና ያልተቀበለ የግዛት አለቃ በንጉሱ ላይ ሲሸፍት፤ልኂቃን ከውጭ ሀገራት የሰሟቸውንና ያነበቧቸውን የፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ርዕዮተ-ዓለሞች ያለምንም ማሰላሰል ወደ ኢትዮጵያ አምጥተው ሀገሪቱና ሕዝቧ ላይ ሲጭኑ ሕዝቡ ‹‹የባሰ አታምጣ›› በሚል ግራ የመጋባት ስሜት ሲቀበል፤ እሳቤዎቹን የተቃወሙ አካላት ደግሞ አለመስማማታቸውን ለመግለጽ ብረት አንስተው ‹‹ጥራኝ ጫካው›› ሲሉ … ኢትዮጵያም ባለፈችበት መንገድ ደጋግማ እየተመላለሰች ኖረች።ረሀብ፣ ጦርነትና ድህነት ደግሞ ያለማንም ከልካይ ደግመው ደጋግመው ሀገሪቱን እንዲያሰቃዩ እድል አገኙ።

ቀደምት ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ነፃነት፣ ክብርና አንድነት ሲሉ በዓድዋና በሌሎች ስፍራዎች ለማመን የሚከብዱ ከባድና አኩሪ ተጋድሎዎችን አድርገው ነፃ ሀገር ለ‹‹ተተኪው ትውልድ›› ቢያስረክቡም ‹‹ተተኪው ትውልድ›› (በተለይ ልኂቃኑ) ግን እነዚያ መስዋዕትነቶች ያስገኟቸውን በረከቶች በመመንዘር ለታላቅ ሀገር ግንባታ ግብዓትነት ሊጠቀምባቸው አልቻለም።ታዲያ ይህን የባከነ እድል በእልህና በቁጭት የመጠቀም ኃላፊነት የወደቀው በዚህ፣ በእኛ ትውልድ ላይ ነው።ይህ ትውልድ በብሔርና በሃይማኖት ተከፋፍሎ ሀገር ለማፍረስ የሚደረገውን አሳዛኝና አሳፋሪ ግብግብ የመታገልና የመመከት አደራ አለበት።የተረሳውና የባከነው የቀደምት ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ትርጉም እንዲኖረው እልህ አስጨራሽ ትግል ይጠብቀዋልና ለትግሉ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መነሳት ይጠበቅበታል።

ታዲያ ቅንነት፣ ትጋትና ፅናት ተላብሶ የሀገሪቱን ችግሮች ለመፍታት በቅድሚያ የምክንያታዊ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል።ምክንያታዊ አስተሳሰብ በሌለበት ቦታ፣ ትርጉም ያለውና ተጨባጭ የሆነ ለውጥን ማሳካት አይቻልም። ኢትዮጵያ ‹‹ለምን?›› እና ‹‹እንዴት?›› ብሎ ለመጠያየቅ፣ ለመከራከርና ለመወያየት የሚያስችል የሰለጠነ ባህል አላዳበረችም።ማሰብን፣ ማሰላሰልን፣ ሚዛናዊ ዕይታንና መመርመርን የሚጠይቀው እንዲሁም ‹‹ምን?››፣ ‹‹እንዴት?››፣ ‹‹ለምን?››፣ ‹‹መቼ?››፣ ‹‹የት?›› የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥ መሠረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሐሰት አብጠርጥሮ የማጥራት እሳቤን የያዘው ምክንያታዊነት የተባለው ጽንሰ ሃሳብ ቦታ አላገኘም። ‹‹ማን አለ?›› እንጂ ‹‹ምን/ለምን አለ?›› ለሚለው ጉዳይ ትኩረት መስጠትን ትኩረት ነፍገነዋል።ምንም እንኳ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ የመኖር አኩሪ ቢኖራቸውም፣ ይህ ድንቅ መስተጋብር ግን በተለይ በፖለቲካው ዘርፍ ምክንያታዊ እሳቤን መፍጠር አልቻለም።

ሳያሰላስሉ በጅምላ የመደገፍና የመቃወም ድርጊት መለያችን የሆነ እስኪመስል እንዲሁም ‹‹ኢ-ምክንያታዊነት ብሔራዊ መገለጫችን ሆነ እንዴ?›› ተብሎ እስከሚጠየቅ ድረስ ደጋግመን ተመላልሰንበታል።ይህ የኢ-ምክንያታዊነት አስተሳሰብ ከረጅም ዓመታት በፊት ጀምሮ ዋጋ እያስከፈለን ዛሬ ላይ ደርሷል።በቂ ባልሆነ ምክንያትና ማገናዘብ የታጀበው የድጋፍና የተቃውሞ ባህላችን እንደሀገር ያገኘናቸው በርካታ የለውጥ እድሎች እንዲከሽፉ አድርጓል።ይህም ሀገራችን መድረስ የሚገባት ደረጃ ላይ እንዳትደርስ ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡

በእርግጥ ዛሬ የዓለምን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ በበላይነት የሚመሩት ሀገራትም በብዙ ችግሮች ውስጥ አልፈዋል።እነዚህ ሀገራት የችግሮቻቸውን ምንጮች በመገንዘብና ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ኃያላን ለመሆን በቅተዋል።ጊዜያቸውን ለአሉባልታ መስጠትንና በትናንት ታሪካቸው ላይ ተቸክለው መቅረትን አልመረጡም፤መራራ የሆኑ እውነቶቻቸውን ያለምንም ማድበስበስ በግልጽ ተነጋግረዋል።በችግሮቻቸው ላይ በግልጽና በድፍረት ተነጋግረው መፍትሄዎችን ማስቀመጥ በመቻላቸው አሁን ለደረሱበት ታላቅነት በቅተዋል።

ታላቅ ሀገር ለመገንባትና የኃያል ሀገር ባለቤት ለመሆን የታላቅና በጎ አስተሳሰብ ባለቤት መሆን ያስፈልጋል።ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው መንገዶቿ በጥልቀት ተፈትሸው፤ችግሮቿና ስብራቶቿ በግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው የእስካሁኑን የኋልዮሽ ጉዞዋን በማስቆም ወደፊት እንድትራመድ ማድረግ ይገባል።ለተደጋጋሚ ረሀብና ጦርነት የዳረጓትና ከተለመደና ከተሰለቸ የ‹‹ታላቅነት›› ወሬ ተሻግራ እውነተኛ ኃያልነትን እንዳትላበስ ያደረጓት የዘመናት ሰንኮፎቿ በግልጽ ሊነገሩና ምላሽ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል! ኢትዮጵያ ችግሮቿን በግልጽ የሚናገርላትና መፍትሄ የሚፈልግላት ልጅ/ትውልድ ትሻለች!

ምክንያታዊ አስተሳሰብን ባህሉ ያደረገ ትውልድ የመገንባት ተግባር በአንድ ጀንበር፣ በአንድ ዓመት የሚሳካ ባይሆንም ጉዞው ከአሁኑ መጀመር አለበት።ይህ ትውልድ ምክንያታዊ ትውልድ የመሆን ግዴታ ወድቆበታል።ይህን ግዴታ በብቃት አለመወጣት ግን ሀገርን የሚያሳጣ አደገኛ ዋጋ ያስከፍላል።አዲሱ ዓመት ደግሞ ስለኢትዮጵያ ችግሮች በግልጽ ተነጋግሮና ተማምኖ እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ሊሆን ይገባል! ተደጋጋሚ መከራዎች ወገቧን ያጎበጧት እናት ኢትዮጵያም ከዚህ በላይ ለመጠበቅና ጊዜ ለማባከን ዝግጁና ብቁ አይደለችም!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You