በአዲሱ ዓመት ጥንካሬዎቻችንን አጎልብተን፤ ድክመቶቻችንን አርመን ለሀገራችንብልጽግና እንትጋ!

 አሮጌው 2015 ዓ.ም ጊዜውን ጨርሶ ለ2016 አዲስ ዓመት ቦታውን አስረክቧል።ሜዳ ተራራው በአበቦች አሸብርቋል፤ አደይ አበባ ወቅቷን ጠብቃ ተከስታለች፤የመስከረም ፀሐይ ምድሪቱን ማሞቅ ጀምራለች።ኢትዮጵያውያንም አዲሱን 2016 ዓ.ም በደስታና በተስፋ ተቀብለውታል።በወግና ልማዳቸው መሠረት እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሰህም ተባብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የራሳቸው ዘመን አቆጣጠር ካላቸው ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ነች።ይህቺ ጥንታዊት ሀገር ባህሏን፤ ወጓን እና እሴቷን ጠብቃ ሺ ዘመናትን ተሻግራ ዛሬ ላይ ደርሳለች።ባህሏን ሊበርዙ፤ወግና ታሪኳን ሊያጠፉ የመጡ ባዕዳን ወራሪዎችን አሳፍራ የመለሰችና ከራሷም አልፎ ለሌሎች ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነች ድንቅ ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያዊነት ባለብዙ ቀለማትና ባለብዙ ፈርጅ ሆኖ ትናንትን ተሻግሮ ለዛሬውም ትውልድ ኩራትና ድምቀት ሆኗል።በአዲሱ 2016 አዲስ ዓመትም ይህ አኩሪ ባህል ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።የሀገር ፍቅር፤ መስዋዕትነት፤ አገልጋይነት አንድነት እና አብሮነት የመሳሰሉት ማኅበራዊ ዕሴቶቻችን ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው።ከዚሁ በሻገርም ኢትዮጵያዊነትን የሚፈትኑና ለሀገራዊ ህልውና አደጋ የሆኑ ግጭቶችን ማስወገድና ሀገራችንን ከብልጽግና ማማ ላይ ማስቀመጥ የሁላችንም ዕቅድ ሊሆን ይገባል፡፡

አሮጌ ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ሲተካ ከግለሰብ ያለፈ ህልምና ዕቅድ ሊኖረን ይገባል።የግለሰብ ህልምና ዕቅድ ሊሳካ የሚችለውም የሀገር ህልም ሲሳካ ነው።ሀገር ሰላም ስትሆን ነው ያቀዱትን ማሳካት፤የወለዱትን መሳም፤የዘሩትን ማጨድ የሚቻለው።

ስለዚህም በአዲሱ ዓመት ሁሉም ለሀገሩ የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል። ጦርነት፤ግጭት፤ሞት፤አካል መጉደል መፈናቀል፤ ስደት በቃ ሊልም ይገባል።ልክ እንደተሸኘው 2015 ዓ.ም ጦርነት፤ ግጭት፤ አለመረጋጋት የመሳሰሉትን ጉድለቶቻችን ልናሰናብታቸው ይገባል።በምትኩም ሰላም፤ ፍቅር፤ አንድነትና አብሮነት ቦታቸውን መያዝ አለባቸው።

የሸኘነው 2015 ዓ.ም እንደሀገር በርካታ ውጤቶች ያገኘንበትና በዚያው መጠንም የተፈተንበት ዓመት ነበር።በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልታ የወጣችበት፤ በግብርና ምርት አመርቂ ውጤት ያስመዘገበችበትና ሰላምንም ለማጽናት ብዙ ርቀት የተጓዘችበት ዓመት ነው፡፡

ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ደም አፋሳሽ ጦርነት የቆመበትና የፕሪቶሪያው ስምምነት የተፈረመበት ታሪካዊ ቀን ነው።የፕሪቶሪያ ስምምነት ኢትዮጵያውያን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሀገራቸውን ሰላም ማስጠበቅ እንደሚችሉ ያሳየና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድም ግርማ ሞገስን ያላበሰ ታሪካዊ ክንውን ነው፡፡

ይህም ስምምነት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት አስተማማኝ በሆነ መልኩ የቋጨና ሞት፤ የአካል መጉደል፤ ስደትንና መፈናቀልን በማስቀረት ኢትዮጵያ ፊቷን ወደ ልማት እንድትመልስ ያስቻለ ነው።ይህ ስምምነት ኢትዮጵያውያን የጦርነት ብቻ ሳይሆን የሰላም ጀግኖች እንደሆኑ ያሳየና በሀገሪቱ ታሪክም አዲስ ታሪክ እንዲጻፍ ያስቻለ ነው፡፡

በ2015 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን ሌላ አዲስ ታሪክ ጽፈዋል።ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 569 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል፡፡ባለፉት አራት ዓመታትም ከ31 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከልም በበረሃማነትና በአየር ጸባይ ለምትሰቃየው ዓለማችን መድህን መሆን ችለዋል፡፡

ስንዴ ከራስ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያም የቀረበው በዚሁ በሸኘነው 2015 ዓ.ም ነው፡፡በዚህ ዓመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡ የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው፡፡በሩዝ ዘርፍም እየተከናወነ ያለው ተግባርም ኢትዮጵያን ከሩዝ ተቀባይነት ወደ አስመጪነት የሚያሸጋግራት ነው።

በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው በመገባደድ ላይ የደረሰው የዓባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜኬላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብርሃን መሆን ችሏል።አራተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም በመላ ኢትዮጵያውያን አንድነት በስኬት ተጠናቋል።

በ2015 ዓ.ም እንደ ሀገር ከተገኙ ስኬቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ደግሞ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን መቻሏ ነው።ኢትዮጵያውያን ባከናወኑት ስኬታማ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ብዙዎች የተመኙትን የብሪክስ አባልነት ኢትዮጵያውያን ማሳካት ችለዋል።ይህም ለሀገሪቱ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች ይዞ የሚመጣ ነው፡፡

የ20ሺ አቅመ ደካማ ቤቶች ታድሰው በአዲሱ ዓመትም ቤት ለእንቦሳ ተብለዋል።የኮይሻ ፤የጎርጎራ፤የወንጪ፤ የሃላላ ኬላ የቱሪስት መስህቦች እየተገባደዱ ነው።በአዲስ አበባም እየተከናወኑ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን ያመላክታሉ።

ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ ስኬቶች ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በግጭትና በኑሮ ውድነት ስትፈትን ቆይታለች።እዚህም እዚያም የሚነሱት ግጭቶች ሀገሪቱ እያደረገች ያለው ግስጋሴ ላይ የራሳቸውን ጥቁር ነጥብም ጥለዋል፡፡

ስለሆነም በ2016 አዲስ ዓመት የነበሩንን ጥንካሬዎች የበለጠ የምናጎለብትበትና ድክመቶቻችንንም የምናርምበት ዓመት ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You