
- የዋጋ ጭማሪው ሚዛናዊነትን የጠበቀ ነው ሲል ድርጅቱ ገልጿል
አዲስ አበባ፦ በተማሪዎች ሰርቪስ (ስኩል ባስ) ላይ የ 150 በመቶ ጭማሪ መደረጉ ተገቢ ያልሆነና አቅማችንን ያላገናዘበ ነው ሲሉ የተማሪ ወላጆች ቅሬታ አቀረቡ። የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፤ የዋጋ ጭማሪው ሚዛናዊነትን የጠበቀ እንጂ ከወላጆች የተለየ ትርፍ ለማግኘት የተደረገ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
በስኩል ባስ አማካኝነት ተማሪ ልጃቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንደሚወስዱ የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ ገረመው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም የጉዞ ርቀቱ እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ድረስ ለሆነ ትምህርት ቤት በአንድ ተማሪ 500 ብር የሰርቪስ አገልግሎት ክፍያ ስንከፍል ቆይተናል።
በአሁኑ ጊዜ በማናውቀው ምክንያት ለአንድ ተማሪ አንድ ሺህ 250 ብር እንድንከፍል ተጠይቀናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
እኔንም ጨምሮ ሌሎች የተማሪ ወላጆች የካቲት 2015 ዓ.ም ስብሰባ ተጠርተን ነበር ያሉት አቶ ተስፋዬ፤ በስብሰባው ላይ ከ2016 ጀምሮ የጉዞ ርቀቱ እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ድረስ ለሚጓዝ አንድ ተማሪ 750 ብር እንደሚከፈል ተወስኖ እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን ግን ይህ ውሳኔ ተቀልብሶ የ 150 በመቶ ጭማሪ ለምን ተደረገ ብለን ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ የሚሰጠን አካል አላገኘንም ሲሉ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
አንዴ ስለተወሰነ መክፈል የምትችሉ መጥታችሁ ውላችሁን አድሱ፤ ካላደሳችሁ ግን አናስተናግዳቹሁም የሚል ምላሽ በማስታወቂያ እንደተለጠፈ አስረድተዋል።
ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪና የተማሪ ወላጅ ወይዘሮ ሕይወት በቀለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሀገርና በግለሰብ ደረጃ ያለው የኑሮ ውድነት መፍትሄ ባላገኘበት ሁኔታ በተማሪዎች ሰርቪስ ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ ተገቢ አይደለም ብለዋል።
አውቶቡስ አገልግሎቱ ልጆቻችን ደህንነታቸው ተጠብቆ በጊዜ በትምህርት ገበታችው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ረገድ የሰርቪስ አገልግሎት መልካም መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ሕይወት፤ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ግን ፍትሃዊ ያልሆነና ኑሮአችን ላይ ጫና የሚያሳድር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አዳነ አብደታ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ምላሽ፤ በተማሪዎች የሰርቪስ አገልግሎቱ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ወቅቱንና ሚዛናዊነትን የጠበቀ እንጂ ከወላጆች የተለየ ትርፍ ለማግኘት ታስቦ የተደረገ አይደለም ብለዋል።
ድርጅቱ ለተከታታይ አምስት ዓመታት የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት ላይ ምንም አይነት የዋጋ ማሻሻያ ሳያደርግ አገልግሎት መስጠቱን የገለጹት አቶ አዳነ፤ ከተማሪ ወላጆች የሚሰበሰበው ገንዘብ የነዳጅ፣ የሹፌር ደመወዝና የተሽከርካሪ መለዋወጫ ወጪዎችን የሚሸፍን አለመሆኑን አመላክተዋል።
ዛሬ ላይ ያለው የነዳጅና የመለዋወጫ ዕቃ ዋጋ ጨምሯል ያሉት አቶ አዳነ፤ ድርጅቱ ጊዜ ወስዶ ጥናት በማድረግ የዋጋ ማሻሻያውን ማድረጉን አስታውቀዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለመደበኛው ትራንስፖርት እንጂ በተለየ መልኩ ለተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት የሚውል ድጎማ እንደማያደርግ ጠቁመው፤ ወቅቱን ያገናዘበ ጭማሪ በመደረጉ ወላጆች ቅሬታ ሊሰማቸው እንደማይገባ አስረድተዋል።
ድርጅቱ የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ የተለያዩ መጠን ያላቸው 100 አውቶብሶች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ አሁን ላይ 82 አውቶብሶች አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛል ብለዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2016 ዓ.ም