‹‹የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ለየት ያሉ ባህርያት አሉት›› -አባ ገብረሃና ገብረጻድቅ

ሊቀ ኅሩያን አባ ገብረሃና ገብረጻድቅ ይባላሉ። የቤተክርስቲያኑን ትምህርት ከዘመናዊው ጋር አዋህደው የተማሩ ናቸው። ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋትን የዘመን አቆጣጠር ጭምር አብጠርጥረው ያጠኑ ናቸው። በቴኦሎጂ ወይም የነገረ መለኮት ትምህርት የሁለተኛ ዲግሪ አላቸው። በዘመናዊው ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል ኮሚዩኒኬሽን ኢንጂነሪግ ተመርቀዋል። በእነዚህ ትምህርቶቻቸው ደግሞ በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ መሥሪያ ቤቶች የሰሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የርቀትና የኦንላይን ትምህርት ኮሌጅ ዲን እና የፓስቶራል ቴኦሎጂ መምህር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ከእኚሁ ምሁር ጋር ቆይታ አድርጓል፤ መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለመነሻ ያህል ስለእርስዎ የትምህርት ሁኔታ እስኪ ጥቂት ይበሉን?

አባ ገብረሃና፡- በቤተክርስቲያን ትምህርት ቅዳሴ ከደብረ ዓባይ ምስክር፣ ቅኔ ደራ ሐሙሲት ከየኔታ ጥበቡ፥ የባሕረ ሐሳብ ከዬኔታ ቀለመወርቅና አቡሻህርን ከዬኔታ ብርሃነ መስቀል ጉንድ ተክለሃይማኖት ገዳም እንዲሁም በነገረ መለኮት ትምህርት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተምሬያለው። በዘመናዊው ትምህርት ደግሞ ቤት ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ጎን ለጎን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በጎንደር እድገት ፈለግ ትምህርት ቤት፣ የመሰናዶ ትምህርቴን አዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ። ከዚያ ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በማምጣት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛው ትምህርትም በኤሌክትሪካል ኮሚዩኒኬሽን ኢንጂነሪግ ተመርቄያለሁ፡፡

አዲስ ዘመን፡- በሥራው ዓለም በሃይማኖቱም ሆነ በዘመናዊው ትምህርት የት የት ሰሩ?

አባ ገብረሃና፡- በምንኩስናው ዓለም ውስጥ ሆኜ በግልም በመንግሥትም እንዲሁም መንግሥታዊ ባልሆኑ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሰርቻለሁ። ለአብነት በንግድ ሚኒስቴር ውስጥ በሁለት የሥራ ዘርፍ ሰርቻለሁ። ይህም የኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ውስጥ የኳሊቲ አሹራንስ ኢንስፔክሽን ቁጥጥር ባለሙያ እና በአይሲቲ ዳሬክቶሬት የኔትዎርክና ሲስተም አድሚን ባለሙያ ሆኜ ሰርቻለሁ።

በተጨማሪ ደግሞ በልማት ባንክ በICT በኔትዎርክ ሲስተም ዝርጋታ ሰርቻለሁ። ከአንድ የቻይና ድርጅት በገጠር ሶላር ኢነርጂ ተከላ ሱፐርቫይዘር በመሆን አገልግያለሁ። በመንፈሳዊው ዓለም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ በልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን በአቅም ግንባታ ፕሮጀክት አስተባባሪነት፥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን መገናኛ ብዙኃን ሥርጭት ውስጥ በአይቲና በሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊነት አገልግያለሁ። በአሁኑ ወቅት በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የርቀትና ኦንላይን ትምህርት ዘርፍ የኮሌጅ ዲን እና የፓስቶራል ቲኦሎጂ መምህር ነኝ፡፡

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በርካታ አማኞች እና ዕሴቶች ያላት ሀገር ናት እያልን ከዛ በተጻራሪ የሚሰሩ ነገሮች ለምን ተበራከቱ ?

አባ ገብረሃና፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አማኞች እና እምነት የለም ብዬ አላምንም። እምነቱም አማኞችም አሉ። ከተሰራብን አንጻር ልንሆን ከምንችለው፣ የመጣብን ብዙ ቢሆንም አሁን እየሆነብን ያለው ግን ጥቂቱን ነው። ይህ ደግሞ ያለ እምነት አይመለስም ነበር። ቅዱሳንና እውነተኛ አማኞች ስላሉ ከብዙ ነገር ተጠብቀናል። የእነሱ እውነትና ፀሎት ከመጣብን ትልቅ ችግር ታድጎናል። በእነርሱ እውነትና ፀሎት ዛሬን አይተናል።

ስብራታችን የቱ ጋር ተፈጠረ ከተባለ መልከ ብዙ ነው። አንዱን ብናነሳ የተሰራብንና እኛነታችንን ያስተወን ነገር ነው። ፋይዳውን ሳናስብና ሳንመረምር መግባታችን እውነታዎቻችንን ወስዶብናል። ያ እውነት ደግሞ ማህበረሰብን ከእሴቱ ከእምነቱ ከእውነቱ ጋር በመጠኑ ለያይቶታል ብሎ መውሰድ ይቻላል። የኢትዮጵያዊነት እውነትን የሚሸረሽሩ ብዙ ነገሮች እንዲፈጠሩ አድርጓልም።

አንዱ የሚፈለገው እውነት አምላካዊ ማንነትን፤ መንፈሳዊ ሕይወትን ጥሎ ዓለማዊነትን፤ የሥጋዊ ፍላጎቶችንና ምኞቶችን ማሳኪያ መንገድን የሚያመቻች በጀት ነው። ሌላው ደግሞ ጉልበት ኃይል ሲሆን፤ ገንዘብ አለ አይዶሎጂ አብረው ይተባበራሉ። ይሁን እንጂ እነኚህ ሁሉ ተዳምረው እስካሁን እምነትን መጣል አልቻሉም፤ አማኒያንን ከእምነታቸው ማላቀቅ አልሆነላቸውም። በእርግጥ በዚህ መካከል ሰዎች ከእምነት አልወጡም ማለት ያስቸግራል። ብዙዎች ወርደዋል፤ ብዙዎች ተንጠባጥበዋል፤ ብዙዎች ከኋላ ቀርተዋል። እናም መወሰድ ያለበት የአማኒያንና የእምነት ችግር በሀገሪቱ ላይ ኖሮ ሳይሆን የተሳሳቱ እሳቤዎች ጎልተው መታየታቸው ነው ከጠንካራው እምነት ይልቅ ውድቀታችን ገዝፎ የታየው።

እኛ በእምነትም ለዓለም የምንተርፍ ምሳሌ ልንሆን የምንችል፤ እምነት ባፈራው እውቀት፤ እውነት በሰጠን ኃይል፤ እምነት በሰጠን ፀጋ ዓለምን የምናጠግብ ነን። ሆኖም የምናየው ሌሎችን መሆን ስብራታችንን እንዳንለየው አድርጎናል። ለእኛነታችን ፍላጎትና ስሜት ቅርብ የሆኑ ጥበቦችና ፍልስፍናዎች ቢኖሩንም ምርጫችን ግን አይደሉም። ሁሌ ታላቆቹ የአውሮፓውያን አስተሳሰብና ፍልስፍና ናቸው። የእነርሱ ባህል ባህላችን እንዲሆን እንደክማለን። ይህም የረቀቀ እውቀትም ኃይልም ከኢትዮጵያ ውጭና ውስጥ በሆነ በተቆራኘው ሕይወት ሕዝብና ሀገር ላይ ይሰራል። እናም ያንን በራስ ማንነት ማከም ካልተቻለ የስብራቱን ቦታ በቀላሉ ማወቅ አዳጋች ነው።

አዲስ ዘመን፡- ታዲያ ከዚህ አንጻር እንዴት ማህበረሰቡን ወደነበረበት ልንመልሰው እንችላለን ?

አባ ገብረሃና፡- ለዚህ መፍትሔው አራት የእርቅ መርሆች ናቸው። የመጀመሪያው እንደ ሕዝብ ከፈጣሪ ጋር መታረቅ አለበት። ለሥራው በደል ይቅርታ የሚጠይቅ፤ ይቅርታ ለጠየቀው ይቅር የሚል፥ በጎ የሰራውን በአደባባይ በእውነት መግለጥ ይገባል። ሁለተኛው ሰው ከራሱ መታረቅ አለበት። ማለትም እንደ ሕዝብ ውስጡ ካለበት በቡድንም ሆነ በግል ከሰራው መጥፎ ነገር፤ ከክፋትና ከጥፋት ድርጊቱ መመለስ አለበት።

ሦስተኛው እርቅ ሕዝብ ከማንኛውም ፍጥረታት ጋር መታረቅ ይኖርበታል። ተፈጥሮን አክባሪና ተንከባካቢ መሆን ይገባዋል። የመጨረሻው ሕዝብ ከመሪ ጋር መታረቅ አለበት። እናም እነዚህን ካደረግንና በዚህ እሳቤ ውስጥ የምንጓዝ ከሆነ የምፈልገው ስኬት ላይ እንደርሳለን። ይህንን ውጤታማ ለማድረግ ሀገር በቀል ኃይላችንን እውቀታችንን ጥበባችንን መጠቀም ይኖርብናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ዛሬ በጎ ሰዎች ያስፈልጉናል፤ ሀገርን የሚያድኑ እና የሚያሻግሩ ሰዎች ያሻናል። እነኛን ሰዎች እንዴት ማግኘት እንችላለን?

አባ ገብረሃና፡– ሁልጊዜ ከግል እሳቤ ወጥተን ወደ ቡድን፤ ከቡድን እሳቤ ወጥተን ወደ ማህበረሰብ ከማህበረሰብ እሳቤ ወጥተን ደግሞ ወደ ሀገር መሻገር አለብን። ሀገር የሚለውን እሳቤ ለማምጣት ትንሹ ግለሰብ ነው። ትልቁ ደግሞ ሀገር ነው። እናም ትልቁን ሀገር እንገንባ ካልን ተፈቃቅደን፤ ተዋደን መኖር አለብን። ዓለም አንዱ ጠግቦ የሚተፋባት ሌላው ደግሞ ተርቦ የሚያድርባት መሆን የለባትም። በጎ ነገር ከግለሰብ ሊነሳ ይችላል። በጎ ሃሳብ ከአንድ ቦታ ሊመነጭ ይችላል። ግን ትልቁ ነገር ያ በጎነት ሀገር እስካልተቀበለው፣ የማህበረሰብ እስካልሆነ፣ በጋራ የማያቆምን ከሆነ እሱ መመርመር አለበት።

በጎነትን የሚጠላ መንግሥትና ግለሰብ አለ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። በበጎነት ስም ክፋቶች ስለበዙ በጎነት ሰጥቶ መቀበል ሆነ፤ በጎነት ምድራዊ ዋጋን ፈለገ። ነገር ግን መሆን ያለበት የምናደርገው በጎነት ስለነጋችን መሆን ይጠበቅበታል። በጎነት ከእኔ የመነጨ ሳይሆን እኔ ጋ የነበረ የእሱ የሆነ ነገር ነው የምሰጠው የሚለውን እሳቤ የያዘ መሆን ይገባዋል። በጎነት ስንል ሀገር፤ ማህበረሰብንና ግለሰብን ይጨምራል። ከየትኛውም ይነሳ ከየት ዓላማ እና ግቡ ግን አንድ ነው። የአንድ ሰውን ከችግር ስናወጣ ከአካላችን መካከል ታማ የነበረችን ጣት ማከም እንደማለት ነው።

በጎነት ከቅድስውና እና ከንጽህናው ውጭ ለሌላ ዓላማ፤ ከማንነቱ ውጭ ለሌላ ተግባር ሲውል በጎነት ራሱ የነበረው እሴት እና ዋጋ ያጣል። በጎነት እሴቱን ካጣ ደግሞ በጎነት የሚለው ቃል ይጠፋል። በጎነት እንደግለሰብም ከሃይማኖት አባት፤ እንደ ማህበረሰብም ከአንድ ማህበረሰብ ይጀምራል በየደረጃው ሃይማኖት እና የሀገር መሪ ኃላፊነት አለበት። ስለዚህ በጎነት መነሻው በውስጣችን ባለችን የሕሊናችን መንፈሳዊ ኃይል ነው። ዋናው ቁም ነገሩ ከየት መነጨ ሳይሆን የት ላይ ደረሰ፤ ዋጋው እንዴት ተተመነ የሚለው ነው።

አዲስ ዘመን፡- መከባበር ፤መዋደድ፤ አብሮነት እና የመሳሰሉት እሴቶች መሸርሸር እንደ ሀገር ዋጋ አያስከፍለንም?

አባ ገብረሃና፡- እያስከፈለን ነው እንጂ። አሁን እኮ የኃይማኖት አባቶች አይደመጡም፤ መሪዎች አይሰሙም፤ ወላጆች በልጆቻቸው ክብር ያጡበት ጊዜ ነው። መምህራን በተማሪዎቻቸው ዘንድ ዋጋ የላቸውም። ሃይማኖትም የማህበረሰቡ አንዱ ነጸብራቅ ሊሆን ይችላል። መሪም የማህበረሰብ ነጸብራቅ ነው። ግን ሁሉም በንቀት ሲታዩ ይስተዋላል። እናም እንዳንሰማማ፤ እንዳንከባበር፤ እንዳንደማመጥ፤ እንዳንተባበር ያደረገን ነገር ምንድነው የሚለው መመርመር ይኖርበታል። አንዱ ሁላችንም ከእራሳችን እሴት ለመውጣት ከምናደርገው ትግል የመነጨ ይመስላል።

መከባበር የእኛ እሴት ነው። እሱን አንፍልግም ብለን የሌላው እሴት እና የሌላውን ማንነት ይዘን በዚያ ማንነት ውስጥ እኛን ስንፈልግ ደግሞ እንዲህ አይነት ነገሮች መከሰታቸው የግድ ይላል። ስለዚህ ይህንን ችግር እልባት እንስጠው ከተባለ እኛነታችንን መፈለግ ያለብን እኛ ውስጥ ብቻ ነው። ማንነት እና እሴታችን ውስጥ እኛን ማየት ይገባናል።

የሌላው እሴት እና የሌላው ማንነት ይዘን በዚያ ማንነት ውስጥ እኛን እንፈልጋለን ማለት የጠፋብን እቃ ሌላ ቦታ ነው የምንፈልግበት ቦታ ደግሞ ሌላ ቦታ ነው እንደማለት ነው። እውነት ለመናገር የሃይማኖት አባቶቻችንን የማክበር ሥርዓታችን ጠፍቷል በሚባልበት ደረጃ አይደለም ቀንሷል እንጂ። ስለሆነም ያለውን ማቅናት ከምንም በላይ ያስፈልጋል።

አባቶቻችን አርዓያዎቻችን ናቸው። እንደ አርዓያም የመከተል ልምድ ነበረን። አሁን ግን ያንን የአርዓያነትን ትርጉም ዘመኑ ወደ ሌላ ወስዶታል። አሁን ላይ ከኃይማኖት አርዓያነት ውጭ ነው ትውልዱን እያኖርነው ያለነው። እነሜሲ የኢትዮጵያ ወጣቶች አርዓያዎች ናቸው። ቡድኖቻችን እነአርሴናል እና ማንቸስተር ሆነዋል። እምነቶቻችን እና ፍልስፋናዎቻችንም ምንጮቻቸው አውሮፖዊያን ናቸው። ሀገር በቀሉ፤ ያስተሳሰሰረን፤ በአንድ የጠበቀን እርስ በእርሳችን ልንነጋጋርበት እና ልንወያይበት የምንችለውን እሴት እና ወግ ተትቷል። አይጠቅምም ወደሚለው ደረጃ ደርሷል። ስለዚህ መከባበራችን ተሸርሽሮ እንዳናቀናው ሆነናል።

አዲስ ዘመን ፡- ወደ ራሳችን ለመመለስ ምን ማድረግ አለብን?

አባ ገብረሃና፡ – የቀደመውን በቅንነት እና በእውነት እንመርምር። የምንመረምረው ስህተትን ለማውጣት ሳይሆን የበለጠ በጎነታችንን ለማሳየት ነው። በትናንቱ ማንነቶቻችን ውስጥ የነበሩ በጎ ያልሆኑ ስብራቶቻችን እንኳን ቢኖሩ ዛሬም እንዳንደግማቸው ይጠቅሙናል። የትላንት መልካምነቶች ደግሞ ለዛሬው መሰረቶቻችን ይሆናሉ። ከሌላው ዓለም ከምናመጣው ይልቅ የራሳችን ከእኛም አልፎ ለዓለም የሚተርፉ እሴቶች አሉን። እነዚህን እሴቶች መጠበቅ ያስፈልጋል።

በእርግጥ የውጭውም ሙሉ ለሙሉ አይጠቅምም ማለት አያስፈልግም። መመርምርና ለእኛ በሚጠቅም መልኩ ወደራሳችን ማምጣት አለብን። እውቀት ጥበብ የአንድ ሀገር ብቻ አይደሉም፤ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ነው።

 ከእነሱ ክፉውን አስቀርተን የእኛን በጎውን ጨምረን እሴቶቻችን ማጎልበት አለብን። የውጭ አያስፍልግም የሚል ፍልስፍና የለም። ሁሉም ጥሩ ነው የሚል አለመካከትም ሊኖር አይችልም። የትናንት አይጠቅምም የሚለው ነገር ትክክል አይደለም። የትናንቱ ጥበብ ነው፤ የዛሬው ደግሞ ማንነታችን ነው።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ከሌሎች ሀገራት የተለየ ነው። ታሪካዊ አመጣጡ ምን ይመስላል?

አባ ገብረሃና፡- ዘመን ረቂቅ አኃዝ ሲሆን ሥራውን እውነት ነው። እውነት ደግሞ የእኛን የምድራዊ ሕይወት ትርጓሜ የምንሰጥበት፥ ሁኔታዎች ማወቅና መረዳት የምንችልበት እንዲሁም ነገሮችን የምንተነትንበትና የምንለካበት መሣሪያ ነው። የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ሁለት መሠረታዊ ምንጮች አሉት። አንደኛው ተፈጥሯዊ ነው። ሁለተኛው ሃይማኖታዊ ነው። ተፈጥሯዊ ምንጭ ስንመለከት የሰው ልጅ የሕይወት ክንዋኔና የሥርዓተ አምልኮቱን አፈፃፀም ያለ ጊዜ እና ያለ ቦታ ማከናወን፥ መግለፅና ማሰብ አይችልም። ስለሆነም በተፈጥሮ የሚከናወኑ ዑደቶችን ተከትሎ የድርጊት፥ የሁኔታዎችና የእሳቤ መለኪያዎች ናቸው። አሁንም በጊዜ ውስጥ ሆነን እየተነጋገር ነው። በዚህም ኢትዮጵያ ለየት የሚያደርገው አንደኛው የዘመን መስፈሪያና መቁጠሪያ ስልት ብዛቶች ናቸው። ምዕራባውያን መስፈሪያ የሚያደርጓቸው ሶስት ዑደቶች ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ሰባት አዕዋዳት መሆናቸው ነው። በዚህም ሀገራችን መጥቅዕ ጠቅሳ ጊዜያት አዕዋዳትን ቀምራ፥ በዘመን አቆጣጠር የዘመን መለወጫ ዕለት ወስና፥ ባሕረ ሃሳብን አስልታ አዲስ ዘመንን ታከብራለች።

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ሥርዓተ ትምህርት ወይም ኃይማኖታዊ መልኩን ስናየው የአንድ ዓመት ልኬት መስከረም መባቻው በማድረግ በፀሐይ 365 ከሩብ ቀን ይዘልቃል። አመዳደቡም 12ቱ ወር እያንዳንዱ ወር 30 ቀናት እንዲሁም ጳጉሜን ተብለው የሚታወቁ ሦስቱን ዓመታት 5 በአራተኛ ዓመት 6 ቀናትን የያዘ ነው። የአውሮፓውያን አቆጣጠር የሚባለው ጎርጎርዮሳዊው ቀመር ግን ከእርሱ በፊት የነበረው የጁሊየስ ቀመርን ጨምሮ ዓመቱን መጀመሪያቸው ጃንዋሪ በማድረግ በ12 ወሮች ሲመደቡ የእያንዳንዱ ወር የቀን ብዛት 28፣ 30 እና 31 በማድረግ ይቀምራሉ።

አዲስ ዘመን፡- አበባዮሽ እና አዲስ ዓመት ያላቸው ግንኙነት ምንድን ነው፤ የእንቁጣጣሽ ትርጓሜስ ምንድን ነው?

አባ ገብረሃና፡- አበባዮሽ የሴት ልጆች የአዲስ ዓመት ብቻ የደስታ መግለጫ ጨዋታ ነው። ለዚህም ማሳያው በዘመን መለወጫ በዓመት አንድ ጊዜ በወርሐ መስከረም የምትታብበውን አበባ ወይም እንቁጣጣሽ ወይም ደግሞ አደይ አበባን በመያዝ ልጆች መጫወታቸው ነው። ተስፋችንን እንዲያለመልመው መመኘታቸውም ነው። ልጆች የዛሬ አበቦች ናቸው፤ እንደ አበባ የሚታዩ። ነገ ደግሞ ወላጆች፣ ፍሬዎች የሚሆኑበት ጊዜ ነው። እናም ያንን እንድናስብ ያደርጉናል።

እንቁ ለብቻው ሲታይ ደግሞ አንድምታውን ወይም ታሪካዊ አመጣጡ በመጽሐፈ ነገስት አንደኛ 11 ላይ እናገኘዋለን። ይህም የኢትዮጵያ ንግስት ማክዳ ወይም ንግስት አዜብ ከሰሎሞን እውቀት እና ጥበብን ሽታ በሄደችብት ጊዜ እንቁ ተሰጥቷት እንደነበር ይነግረናል። ያንን እንቁ ለአንዳድን ጣቷችሽ ሲል የሰጣትን በመያዝም እንቁ ለጣትሽ እንድንለው ሆነናል የሚሉ አሉ።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዓመት አዲስ ዘመን እንደሆነ ይገለጻል። ይህ እንዴት ይብራራል?

አባ ገብረሃና፡– የአዲስ ዘመን መባቻ ዋንኛ ትርጉም የሚሰጠው በቀድሞው ዘመን በመንገድና በስልጣኔ እጥረት የተነሳ ለሁለት የክረምት ወራት የሰው ግንኙት የለውም። ምክንያቱም ታቹም ላዩም ውኃ በመሆኑ የተነሳ ወገን ከወገኑ ዘመድ ከዘመዱ ይለያያል። በአዲስ ዘመን ግን ይህ የተለያየ ሰው የሚገናኝበት፤ የራቁት የሚቀራረቡበት ልዩ የደስታ ዕለት ነው።

እንደ ሀገር አዲስ ዓመት የደስታ ጨዋታ የሚጫወቱበት፣ በአዲስ ዓመት አበባ መገለጫ የምትገለጥበት፤ ሁሉም ሰው ያለፈውን በመተው አዲስ ተስፋ እና ምኞት የሚሰንቅብት በመሆኑ በገጠር በከተማ፣ ባለው በሌለው ሰው፣ በተማረው ባልተማረው፣ በሚያምነው በማያምነው ዘንድ ሁሉ ለአንድ አይነት የሕይወት መርህ እና የተግባር ለውጥ የሚነሳበትና በአንድ አይነት መዝሙር የሚደሰትበት ጊዜ ነው።

የዘመን መለወጫ በዓል አሮጊው አልፎ አዲሱ ሲተካ፥ የክረምት ጨለማው አልፎ ብርሃን ሲመጣ፥ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላ መሻገሩን ሁላችን በምናከብርባት መስከረምን መባቻ ዕለት ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትጎላበት ወንዞች የጠራ ውኃ የሚፈሱበት፣ ምንጮች የሚፈልቁበት የተዘሩት ማበብ የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎች፥ ተራራዎችና ሸለቆዎች በአበባ የሚያጌጡበት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተለዩ እምነቶች አሉ። ይሁን እንጂ አዲስ ዓመትን አብረው ያከብራሉ አብረው እንዲያከብሩ ያስተሳሰራቸው ምንድን ነው?

አባ ገብረሃና፡– በሀገራችን የተለያዩ የሃሳብ፣ የእምነት፣ የፍልስፍና እና የባህል ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ግን አራት ነገሮች አንድ ያደርጋቸዋል ብዬ አስባለሁ። አንደኛው ባህላችን በዓሉን የሕይወታችን የኑሮ ዘይቤን በጋራ ደስታ አንድ አድርጎ መግለፅ በመቻሉ። ሁለተኛ ልጆቻችን በአንድነት መዝሙር አበባዮሽ ጨዋታን እንዲጫወቱ ማስቻሉ። ሶስተኛው ስለሀገራቸው፤ ስለቤተሰቦቻቸው ስለወደፊት ዕጣ ፈንታችን የጋራ ተስፋና ምኞት እንዲኖራቸው የሚያደርግ በመሆኑ። አራተኛው ብዙ አብረን የማናከብራቸው በዓላት በብዛት ቢሆኑም ይህ የጋራ ክብረ በዓላችን መሆኑ ትልቅና የተለየ ያደርገዋል፡፡

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን ሲመጣ መልካም ምኞት የምንገልጽበት መሆኑ ይታወቃል፤ መጭውን ተስፋ በማሰብ እቅድም የምንይዝበት ጊዜ ነው። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

አባ ገብረሃና፡- እንደ ግልም እንደ ሃይማኖትም እቅዶች ይኖራሉ። በዋናነት በኃይማኖት እሳቤ ውስጥ በቡድንም ይሁን በግል እቅድ ስናወጣ በደል፣ ኃጢያት፣ ክፋት ያለበትን ሕይወት ማስወገድ ነው። በአዲስ ዘመን ንስሐ ያልገባ ወደ ንስሐ ሕይወት እንዲገባ፣ የበደለው እንዲክስ፤ የቀማው እንዲመልስ፤ የተቸገረው እንዲገኝ ስለዚህ ከልብ የሆነ መጸጸት ይፈልጋል። ይህን ስናደርግ እቅዶቻችን የሰመሩ እና የተስተካከሉ ይሆናሉ፡፡

እንደማንኛውም ማኅበረሰብ ለሚያምነውም ለማያምነውም ግን ያለፈውን ነገር በሀቀኝነት መገምገም አለበት። ምን አቅም ኖሮኝ ነው ምን ያቀድኩት፤ የእኔ አቅም ምንድን ነው? የምችለው ነገር ምንድን ነው? የማልችላቸው ነገሮችስ ምንድን ናቸው? የሚሉት መመለስ አለባቸው። በአጠቃላይ ሰዎች በእውነተኛ ማንነታቸው ላይ ተመስርተው እቅድ ማወጣት አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች ቢኖሩም ሁሉም እንደየእምነቱ የራሱን ይዞና የሌሎችንም አክብሮ የመሄድ ባህሉ ከፍተኛ ነው፤ ከዚህ አንጻር የሀገራችንን የመቻቻልና የመተሳሰብ ባህል እንዴት ይገልፁታል?

አባ ገብረሃና፡- ይህ እንደሰዎች አስተሳሰብ የሚወሰን ነው።፡ በአመለካከት፣ በሃይማኖት እንዲሁም በአካል እንለያያለን። አንድ ያደረገን ነገር ቢኖር የመሥሪያ ቤቱ ሕግና ሥርዓት ብቻ ነው። በግድም ቢሆን አንድ የሚያደርገን የተቋሙ ዓላማና ራዕይ ነው። ይህ ደግሞ በማህበረሰባችንም ውስጥ እንዲሁ ነው ያለው። ማህበረሰቡን አንድ የሚያደርገው የጋራ የሆነ እሳቤ አለው። የጋራ ህልምና የጋራ ራዕይ አለው። እነዚህ ከሌሉ ሀገር ሊኖር አይችልም። የጋራ ማንነት ከሌለ አንድ የሚያደርገን እሴት የለም ማለት ነው። ስለዚህም አንድ ያልሆነ ቤተሰብ እንደሌለ ሁሉ አንድ ያልሆነ ሀገር ሊኖር አይችልም። እናም ሀገር የምትኖረው በጋራ መሰረቶች ላይ ተመስርታ ነው።

መቻቻል በሀገር እሳቤ ውስጥ ትክክል አይመስለኝም። ምክንያቱም ቅራኔን ይዞ አንድነትን፣ ፍቅርንና ተስፋን ማምጣት አይቻልም። ስለዚህም የቋንቋው አገባብ የተለየ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም መቻቻል መባል ያለበት ከሀገርና ከማኅበረሰብ ውጭ ባለ ጉዳይ ነው። ለአብነት እንደ ኢትዮጵያ ስናስብ ክርስትና ለእስልምና ጠላትም ሥጋትም አይደለም። እንዲሁ እስልምናው ለክርስትናው ጠላቱም ሥጋቱም አይደለም። በውስጥ ተደብቆ ሌላ አላማ ይዞ የሚሰራ አካል ከሌለ በስተቀር። ፈጣሪን የሚያመልኩና ለእርሱ የሚገዙ እስከሆነ ድረስ አንዱ ለአንዱ የሕልውና ጉዳይ ናቸው። የአንዱ መኖር ለሌላው ተስፋና ሕይወት ነው። ስለዚህም በዚህ እሳቤ ውስጥ ካለን ደግሞ አንዱ አንዱን ይንከባከባል እንጂ አያጠቃውም። ስለሆነም መቻቻል ሳይሆን መደጋገፍና ነገን ማሳመር ነው።

አዲስ ዘመን፡- መቻቻልን የሚለው ትርጓሜ ስህተት አለበት ብለው ያምናሉ፤ ቋንቋውን እርስዎ እንዴት ያዩታል?

አባ ገብረሃና፡- አዎ። የቋንቋ ትርጉም ልዩነቶች የሚከሰቱት የምንጠቀምበትና የማንጠቀምበትን አውድ መለየት ሳንችል ስንቀር ነው። አብሮ ለመኖር፤ ለመግባባት፣ ለአንድነት መጠቀም ያለብን መቻል የሚባለው ቃል ሳይሆን ከዚህ የተሻሉ ህብረትን የሚፈጥሩ ቃላት አሉ። ምክንያቱም መቻቻል ማለት በደልና ቅራኔን በውስጡ ያዘለ ነው። እስከመቼ የሚለውንም ያመጣል። የጊዜ ገደብን በውስጡ የያዘም ነው። የሚበድለኝን ሰው ልሸከመውና ዛሬን ልለፈው እንደ ማለትም ነው። ይህ ደግሞ አብሮ በሚኖር ሰዎች መካከል የሚሆን አይደለም። የአንዱ መኖር ለሌላው ሕልውናም እድገትም ነውና በምክንያታዊነት ይራመዳል እንጂ መቻል የሚለውን ነገር አያስገባም።

አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዓመት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ባህላዊና ታሪካዊ እንዲሁም ኃይማኖታዊ በዓላት አሉ። እነዚህ ዓመታዊ በዓላት በትውልድ ቀረጻ ላይ የሚኖራቸው አንድምታ እንዴት ይብራራል? ይህ እንዲቀጥልስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?

አባ ገብረሃና፡- በዓላት ምንም ዓይነት መልክ ቢኖራቸውም በትውልድ ቀረጻ ላይ ትልቅ አቅም ፈጥረው የሚጓዙ ናቸው። ምክንያቱም እነርሱ የነበረውን ትናንት በስሜትም በኑሮም የሚያሳዩ ናቸው። ትናንትን ከእነሙሉ ክብሩ የሚያስረክቡ ናቸው። እነርሱ ላይ ስንሆን ግን ቅድሚያ ማህበረሰብ የሚለው ይጎላል። ሕብረት ይጎላል። በብዛት ጥልቅ ፍቅር እንጂ ጥላቻ አይስተናገድም። በሰላም መለያየት እንጂ መከፋፋት አይታይበትም። ድብድብ እንኳን ኖሮ ‹‹ አይቆጡም ጌታ›› ተብሎ ነው የሚታለፈው። ስለዚህም ለሰላምና ለጸጥታው፤ ለአንድነትና ለአብሮነት የሚሰጠው ግምት ከፍ ያለ ነውና ትውልዱ ያንን እያወቀ ማደጉ ደግሞ ሁሌም ሰላማዊና ሰውን አፍቃሪ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ትውልድ የሚቀረጸው በባህልና በታሪክ ውስጥ ነው። ከሌላ ሳይሆን ከእምነቱ፣ ከባህሉ የሚመነጨውን ተቀበል ሲባልም ነው በቀላሉ ወደመተግበሩ የሚገባው። ይህም ቢሆን ጥንቃቄን ይፈልጋል። በተሳሳቱ ትርክቶች ከሞላነው ጥላቻን አንግቦ የማይሆን ሕይወት ውስጥ ይገባል። ስለዚህም እምነት እና ባህል ውስጥ ያለውን እምቅ ጥበብ በእውነቱ ልናስረዳው ይገባል። የማያግባቡን ትርክቶችን እንደእውነት እያደረግን መንገርን ከአሁኑ ልናስወግድ ይገባል።

አዲስ ዘመን፡- ለኢትዮጵያውያንና ለመላው የዓለም ሕዝብ አዲሱን ዓመት መሠረት በማድረግ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ ቢገልጹልን?

አባ ገብረሃና፡- የማይነጋ ሌሊት እንደሌለ ሁሉ የማያልፍ መከራም ሆነ ችግር የለም። በኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ አለ። መከራዎቿ ተስፋዎቿን ትልቅ ያደርጉታል። አሁን ብዙ መከራ ውስጥ ነን። ለመሪም ለሕዝብም ብዙ ያልተመቹ ነገሮች አሉ። ጦርነቱ፣ መፈናቀሉ፣ መሰደዱና መራቡ እንዳለ እየተገለጠ ነው። እነኚህ ችግሮች ግን ሊወለድ ላለው ትልቁ ተስፋ መሠረቶች ናቸው። ከዚህ መከራ ጀርባ ትልቅ እውነት፤ ትልቅ ስኬትና ድል ይኖራል ብዬ አስባለሁ። እንደ ግለሰብም ሀገርም ከዚያ ችግራቸው በኋላ ነው የሚቆሙትም የሚጸኑትም። ስለዚህ ግን ሥራዎች ይፈልጋሉ።

አንዱ ጎልተው የሚደመጡት ነገሮች በጎነትን፣ አብሮነትን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የያዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ለልዩነት እስካሁን ደከምን ያፈራነው ነገር አሁን እያየነው ነው። እናም ከችግሮቻችን ለመዳን መፍትሔው ለአንድነት መድከም ነውና የዛሬው ሥራችን ይህ መሆን አለበት። ከሚለያየን ትርክት ይልቅ የሚያስተሳስበንና የሚያስተሳስረን አዲስ ትርክት እንፍጠርለት። ከመሪ እስከተመሪ ድረስ ያለው አካል በግለሰብ ማንነቱ ራሱን ይፈትሽ። ለለውጥ እንደሚተጋ እርግጠኛ ይሁን። ከዚያ ያንን ወደ ቡድን ያምጣው። ይህ ሲሆን ደግሞ ሀገርን መሥራት ይቻላል።

ለማጥፋት ካልሰራን ለበጎነት ከተጋን በጎ ነገር የማያስማማው ግለሰብ አይኖርም። እናም እንደሀገር ከትናንትናው ስብራቶቻችን፣ ውድቀቶቻችን ይበልጥ የሚመጣው ተስፋዎቻችን ላይ እንመርኮዝ። እነርሱ የአዲስ ዓመት አበባዎቻችን ናቸው። በቀጣይ ፍሬን የምንለቅምባቸው። በባለፉት መከራዎቻችን በዓመተ ፍዳ፣ በዓመተ ኩነኔ ውስጥ ከሆንን እድገትን ሳይሆን ውድቀትን ነውና የምንጠራው እርሱን ለአለፈው ዘመን እንተውለት። ማህበራዊ ፍልስፍናዎቻችን፣ ማህበራዊ ጥበባችን፣ እውነተኛ የኃይማኖት ማንነቶቻችን ላይ ተመርኩዘን በጎ በጎውን ብቻ ይዘን እንሻገር። በጸሎት ማንነት ከፈጣሪ ጋ ከተጋመድን ደግሞ ተስፋችን ቅርብ ይሆናልና እርሱን እናድርግ። መልካም አዲስ ዓመት።

አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ ከልብ እናመሰግናለን።

አባ ገብረሃና፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You