አዲስ የምንሆንበት አዲስ ዓመት

 አሮጌውን ዓመት ሸኝተን አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ የምንቀበልበት የዓመቱ የበኩር ወር መስከረም። የወራቶች ንጉሥ የሆነው ወርሃ መስከረም ለእኛ ኢትዮጵያውያን ልዩ ወር ነው። በአሮጌው ዓመት የቱንም ያህል ባይደላን፣ ሞልቶ የማያውቀው የኑሮ ሽንቁሩ አብዝቶ ቢያጎድልብን፣ መከራና ኀዘን ቢፈራረቅብን፣ ብናዝን፣ ብንከፋም አዲስ ዓመትን ተስፋ አድርገን እንጠባበቃለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም። ይህ የኖረ ልማዳችን ነው። እኛ ኢትጵያውያን እንኳንስ ኑሮ ጎድሎብን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ አሸወይና አይነት ዓመት ብናሳልፍ እንኳ፤ አዲስ የነበረውን አሮጌ ብለን ሸኝተን አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ በአዲስ ተስፋ መጠበቅና መናፈቃችን አይቀሬ ነው።

በአዲስ ዓመት የጎደለው እንዲሞላ፤ የራቀው እንዲቀርብ፣ የጠፋው እንዲገኝ ከመመኘት ባለፈ የሞላውም ሞልቶ እንዲትረፈረፍ በአዲስ ዓመት ተስፋ የምንሰንቀውም ለዚሁ ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን በአሮጌው ዓመት በብዙ ብንፈተንም በፈጠርናቸው ችግሮች እግር ከወርች ተይዘን መከራ ተፈራርቆብን ይሆናል። ያም ቢሆን ታዲያ ችግሮቻችን ሁሉ በሐምሌና ነሐሴ ጎርፍ ተጠራርገው እንደሚሄዱ እናምናለን እንጂ ከአሮጌው ዓመት ጋር አሮጌ አንሆንም። ይህ ደግሞ የብዙዎቻችን እምነት ነው። ‹‹እምነት ያድናል›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ እምነታችን ዕውነት ሆኖ ዝናቡ ጋብ ሲል አዲስ ዓመትን በብዙ ተስፋና በአዲስ መንፈስ በአበቦች መዓዛ ለመቀበል እንጓጓለን ጓግተናልም።

ጉጉታችን ዕውን ሆኖም ለወትሮው አዲስ ብለን የተቀበልናቸውን ብዙ ሺ አዲስ ዓመታት አሮጌ ብለን ሸኝተናል። በተመሳሳይ አዲስ ዓመትን በወርሃ መስከረም ከሚፈኩ አበቦች ጋር ፈክተን ተቀብለናል። ይኸው ዛሬም መጣሁ መጣሁ የሚለውን 2016ን አዲስ ብለን ለመቀበል ስንዱ እመቤት ሆነን ከላይ ታች እንላለን። አዲስ ዓመት ሲነሳ ታዲያ ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የጥበብ ሥራዎች መነሳታቸው የግድ መሆኑ ዕሙን ነው። ለዚህ ደግሞ አንጋፋው ድምጻዊ የክብር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን የሚቀድመው ባይኖርም የተከተሉት ድምጻውያን በርካቶች ናቸው። እንዳለ አሮጌ ሆኖ ከሚሰናበተው ዓመት ጋር በሽታና ችግር ተጠራርገው እንዲወገዱ ድምጻዊው በምኞቱ ሲያዜም…

‹‹ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ፤

አሮጌው ዓመት አልፎ፣ አዲሱ ሲገባ፤

በአበቦች መአዛ ረክቷል ልባችሁ፤

ህዝቦች ሁሉ በጣም እንኳን ደስ አላችሁ፤

የበሽታን አይነት በሙሉ ጠራርጎ፤

ከቆሻሻ ጋራ ጎርፉ ሙልጭ አድርጎ፤

ፈሳሽ የወንዝ ውሃ ተውሳኩን ይውሰደው፤

ጤና መሆኑን ነው እኛ የምንወደው…››

እርግጥ ነው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ለሀገራችን ሰላምን፤ ለዜጎቿ ስኬትና ብልጽግናን አጥብቀን የምንመኝበት የአዲስ አመት ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ታድያ እንዳለፉት ብዙ ሺ ዓመታት ሁሉ 2015 ዓ.ም አሮጌ ብለን ስናሰናብተው አብረን ተባብረን የምናሰናብታቸው እግር ከወርች የያዙን አንድ ሺ አንድ ችግሮች ስለመኖራቸው ለአፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም። ሀገር ሰላም ውላ እንዳታድር ከውስጥም ከውጭም ሲጎነትሉን የኖሩ እሾህ አሜኬላዎች እንዲነቀሉና ተጠራገው እንዲወገዱ፤ ህዝብ ለህዝብ ተባብሮና ተከባብሮ መኖር የሚችልበትንና ኢትዮጵያዊ አንድነቱን የሚያጠናክርበት አዲስ ዓመት እንዲሆን አጥብቀን ልንመኝ ይገባል፡፡

ክረምትና በጋ የሚፈራረቅባት ለምለሟ ኢትዮጵያ ሳትጠብ የጠበበ አመላችንን አስፍተን እርስ በእርስ የምናደርገውን መገፋፋትና መጠላለፍ፤ ጥላቻና ኤኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ያልተገባ ፉክክርን እንዲሁም ዘረኝነትን ከውስጣችን አስወግደን የሁላችን በሆነችው አንዲት ሀገር በአንድነትና በመተሳሰብ በጋራ ተረዳድተንና ተከባብረን ለመኖር አዲሱ ዓመት መነሻ ይሁነን። መገፋፋትና መከፋፈልን በጽኑ አውግዘን ‹‹…ፈሳሽ የወንዝ ውሃ ተውሳኩን ይውሰደው ጤና መሆኑን ነው እኛ የምንወደው…›› እንዳለው ድምጻዊው በ2015 ዓ.ም የደረሰብን የሰላም ዕጦት፣ ችግር መከራ፣ ስደት ጉስቁልና፣ ጦርነትና መፈናቀሉን አጠቃላይ የተፈጥሮ አደጋውና ተውሳኩን በሙሉ ፈሳሽ የወንዝ ውሃው ጠራርጎ እንዲወስድልን አጥብቀን እንሻለን።

ዛሬ ከተሰናባቹ 2015 ዓ.ም የመጨረሻ ጠርዝ ላይ እንዲሁም ከአዲሱ ዓመት ዋዜማ ደጃፍ ላይ ሆነን ለሀገራችን ሰላምን ከመመኘት ባለፈ ለሰላም ዘብ በመቆም ሙሉ አቅማችንን አሟጠን መጠቀም የግድ ይለናል። ምክንያቱም የሰፈረብን የጥላቻና የዘረኝነት ዛር እንዲህ በቀላሉ የሚለቀን እና እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በአዲስ ዓመት “ማጨስ አቆማለሁ…” “መጠጥ አቆማለሁ…” “ማምሸት አቆማለሁ…” “ትምህርቴን እጨርሳለሁ…” “መሥሪያ ቤት እቀይራለሁ…” “የግል ሥራ እጀምራለሁ…” ወዘት… በማለት ለግል ሕይወታችን ቃል ገብተን የምናልፈው ጉዳይ አይደለም። በእውነት ስለዕውነት ስለሀገራችን ሰላም ቃል የምንገባበት እንጂ፤ በግል ሕይወታችን ልናሳካ ያሰብነውና ያቀድነው ሁሉ ከሀገር ሰላም ውጭ የሚታሰቡ አይደሉምና ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በአዲሱ ዓመት ቃል እንግባ፡፡

የሰላም አስፈላጊነት ከማንኛውም የግል ጥቅም፣ ፍላጎት እና የጦር መሳሪያ ኃይል የሚበልጥ ሆኖ ሳለ ብዙዎች በሰላም ስም ጦር መዘው ቃታ ይስባሉ። እርግጥ ነው ብዙ ሀገራት ለሰላማቸው መደፍረስ አይነተኛ ምክንያት ቢኖራቸውም ሰላማቸውን የማረጋጋጥ ኃላፊነትም በእጆቻቸው መዳፍ ላይ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ለሰላም ዋጋ ሲከፍሉና ቅድሚያ ሲሰጡ አይስተዋልም።

እንደሌሎች ሀገራት ሁሉ ታዲያ ኢትዮጵያም ሰላሟን ያደፈረሱና እያደፈረሱ ያሉ ለቁጥር የበዙ ችግሮቿን ከአሮጌው ዓመት ጋር አራግፋ ወደ አዲስ ዓመት ለመሸጋገር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተዋታል። አንዱን ችግር ተሻገርኩ ስትል ሌላው እየተከተለ ከልማት ጉዞዋ ብቻ ሳይሆን ክቡር ከሆነው ከሰብዓዊነት ጎዳና ጭምር ሊያወጣት ሲፈታተናት መቆየቱ ገና ትዝታ አልሆነም። ታዲያ ለመውደቅ ጫፍ ያደረሷትን ችግር በአሮጌው ዓመት አሮጌ በማድረግ ጠራርጎ ማስወገድ የግድ ይሆናልና ለዚሁ ክንዳችንን እናበርታ።

አሮጌ ያልነውን 2015 ዓ.ም ስናሰናብት አብረን ልናሰናብታቸው የሚገቡ ለቁጥር የበዙ ህመሞችና ተውሳኮች አሉ። እነዚህ ተውሳኮች በፈሳሽ የወንዝ ውሃ ተጠራርገው አንዲወሰዱና ሀገር ሰላም እንድትሆን ዜጎች በጤና፣ በፍቅርና በደስታ እንዲኖሩ አጥብቀን እንመኛለን። በተለይም በአዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ሆነን በአዲስ ተስፋ ተሞልተን ሁሉም ጥሩ እንደሚሆን እንመኛለን። ከምኞት ባለፈም ታዲያ አጥብቀን ለምንሻው ለሀገር ሰላምና ለዜጎች ስኬትና ብልጽግና ከእያዳንዳችን የሚጠበቅ የቤት ሥራ ስለመኖሩ ለአፍታም መዘንጋት አይገባንም።

አዲስ ዓመት አሮጌነትን አውልቀን አዲስ የምንሆንበት እንጂ ሲያለያየንና ሲከፋፍለን የነበረ ማንኛውም ችግር ከትናንቱ አሮጌው ማንነታችን ወደ አዲሱ ተስፋችን አምጥተን ተስፋችንን የምናጨልምበት አይሆንም። ከሁሉም በላይ ግን በሀገር ደረጃ የሚያወዛግቡንን ጉዳዮች በመለየትና በመወያየት እንደ ሀገር ከግጭትና ቀውስ አዙሪት ውስጥ ለመውጣት የሚያስችለንን ሰላማዊና ሁሉን አቀፍ የሆነ ትጥቅ ታጥቀን ከአሮጌው ጋር አሮጌ ሳንሆን አዲሱ ዓመትን በአዲስ መንፈስ በብዙ ተስፋ እንቀበለው።

ፍሬሕይወት አወቀ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ መስከረም 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You