የትምህርት ተቋማት አብሮነትን የማስረፅ ሚና

የዛሬዋ የመጨረሻ የጳጉሜን ቀን “የአብሮነት ቀን” ተብላ ተሰይማለች። አብሮነት ደግሞ ከነጠላነትና ብቸኝነት ጋር አይስማማም። በየትኛውም መስክ አብሮነት ልክ እንደ ዓድዋ ለድል ሲያበቃ፤ ወደ ላይ ሲያወጣ፣ ዘርቶ ለመቃም፣ ወልዶ ለመሳም ሲያደርስ፤ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ዕድገትና ልማትን ሲያስቀጥል፤ እርስ በርስ መተማመንና የጋራ እድገትን ሲያፋጥን፤ ሕዝብን ለአንድ አላማ ሲያሰባስብ ነው የሚታየው፤ የሚታወቀው።

አብሮነት በየትኛውም መስክ ያለና መኖርም ያለበት ነው፡፡ በተለይ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ሲታይ የአብሮነት መሠረቱ ትምህርት ቤት ሆኖ ይገኛል፡፡ የዚህ ዐብይ ምክንያቱ ደግሞ ትምህርት የሚሰጥበት ትምህርት ቤት በባህሪው የግል ሳይሆን ማህበራዊ አገልግሎት የሚስተናገድበት ተቋም በመሆኑ ነው።

አብሮነት ማህበራዊነት ነው፡፡ አብሮነት ጋርዮሽ ነው። አብሮነት በአንድ እጅ ማጨብጨብና የሚፈለገው ውጤት ሳይመጣ ቀርቶ መና መቅረት ማለት አይደለም። በሁለት እጅ አጨብጭቦ ውጤታማ መሆን ነው። አብሮነት ከአካባቢያዊነትም የሰፋ ነው። አብሮነት ከሰውም የተሻገረ፣ እንስሳትን ሳይቀር “አንድ” የሚያደርግ የጋራ ተግባር ውጤት ነው። አብሮነት የብቸኝነት ህመም መፈወሻ መድኃኒት ነው። አብሮነት የመተማመን መገለጫ፤ የመሰማማት ማሳያ ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ከፍ ብሎ የሚታየው በትምህርት፣ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ነው፡፡ እዚህ ጋር “ዩኒቨርሲቲዎች ትንሿ ኢትዮጵያ ናቸው” የሚለውን ማስታወስ ተገቢ ይሆናል።

አብሮነት ከላይ በተጠቀሱት ማህበራዊ ዘርፎች ብቻ የሚገለፅ አይደለም። በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም ባጠቃላይ በሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ አብሮነት አለ። ፖለቲካው ከተናጠል ይልቅ በአብሮነት ሲያዝ ነው ውጤታማ የሚሆነው፡፡ ለነገሩ የአሁኑ ዘመን ያመጣው ጣጣ እንጂ ፖለቲካ፣ ሃይማኖት፣ ትምህርት ወዘተ በብሔር ወይም በጎሳ አልያም በመንደር ሆኖ አያውቅም።

ለምሳሌ፣ ከምርጫ 97 የምርጫ ዘመቻና የምረጡኝ ቅስቀሳ፤ በተለይም ቅንጅት ከተባለው ፓርቲ በኩል የታየው ይኸው ነው። ይህ ይባል እንጂ ከእድሜና ሰብእና ቀረፃ አኳያ ብሎም ከአንድ ማህበረሰብ ግንባታ አንፃር የአብሮነት መሠረቱ ትምህርት ቤት ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት በአብዛኛው አብሮነትን የሚሹ ናቸው። ከተጓዳኝ ትምህርት ጀምሮ አብሮ መሥራትን የግድ የሚሉ በርካታ ትምህርታዊ እንቅስቃሴዎች አሉ። ክፍል ውስጥ የሚደረግ ውይይት ወይም ክርክር አብሮነትን ግድ ይላል። መቀመጫና ወንበር መጋራቱ አብሮነትን የሚጋብዝ ነው። በአንድ ጣራ ስር ለአንድ አላማ መገናኘቱ በራሱ አብሮነት ነው፡፡ ይህም ተማሪዎች በሚገባ እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ እድል ይፈጥርላቸዋል።

በትምህርት ተቋማት ውስጥ አብሮነት ካለ ተማሪዎች እኩል የትምህርቱ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ፡፡ አንዳቸው ከሌላቸው ይተዋወቃሉ፡፡ የጋራ ግንዛቤ ይኖራቸዋል፡፡ አድልኦ፣ መገለልና የመሳሰሉት ፈፅሞ አይኖሩም። ተማሪዎች ወደ አንድ የትምህርት ተቋም ከአንድ አካባቢ ብቻ አይደለም የሚሰባሰቡት፡፡ ወደ አንድ የክፍል ጣራ ስር የሚሰባሰቡት የየራሳቸውን ቋንቋ፣ እምነት፣ ባህልና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ይዘው ነው፡፡ ወደ ተቋሞቻቸው ሲገቡ ግን ይህ ሁሉ ይቀርና “አንድ” ይሆናሉ። በቃ፣ “ተማሪ” ብቻ ናቸው። “እኔ” የሚለው ቀርቶ “እኛ” በሚለው ቃል ይተካል።

አብዛኛዎቹ ሰዎች አብሮነትን ለማስረፅ ሲፈልጉ ሶስት ፍጡራንን ይጠቅሳሉ፡፡ ንብ፣ ጉንዳንና ምስጥን። ይህንን ለማለታቸው ምክንያታቸው ደግሞ የእነዚህ ነፍሳት እንቅስቃሴ፣ ሥራና ውጤታቸው በአብሮነት፣ በመደጋገፍና በጋራ መሥራት ላይ የተመሰረተ፣ ቅብብሎሽ፣ ትብብርና ድጋፍ የማይለየው በመሆኑ ነው። አብሮነት ወደ ሰው ሲመጣ ደግሞ “ሰው በተፈጥሮው ማኅበራዊ እንስሳ ነው” የሚለውን አባባል ያጠናክራል፡፡

“ሰው በተፈጥሮው ማኅበራዊ እንስሳ ነው” የሚል ነገር በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ትርጓሜውም የአንዱ መኖር በሌላው ሰው ላይ የተደገፈ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ተማሪዎችም ሰዎች ናቸውና ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከታቸዋል። በትምህርት ሂደት ውስጥ አብሮነትን በተመለከተ “Inclusive education” /የአካታችነት ትምህርትን/ ጨምሮ የሕግ ማዕቀፎች ያሉ እንደመሆናቸው መጠን ለሥራ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች አያጋጥሙም ባይባል እንኳ እዚህ ግባ የሚባሉ አይሆኑም።

ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጀምሮ እነ ዩኔስኮ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የዓለም የትምህርት ፎረምና የመሳሰሉት ከትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነት መመዘኛና መስፈርቶች መካከል አንዱ አካታችነቱና አብሮነትን ከማጠናከር አኳያ የተሰሩ ሥራዎች መሆናቸው ነው።

እንደነዚህ ድርጅቶች እምነት ትምህርት ቤቶች አካታች መሆናቸው ተማሪዎች ከየአቅጣጫው፣ ከተለያዩ ባህሎች እና ቋንቋዎች ወዘተ ተሰባስበው በትምህርት ገበታ ላይ መገኘታቸው ትክክለኛና እውነቱን፣ ተጨባጩን ዓለም መሠረት ያደረገ ትምህርት ይቀስሙ ዘንድ ከማስቻሉም ባለፈ መላውን ህብረተሰብ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ያደርጋል።

በትምህርት ቤት ውስጥ የአብሮነት መኖር ግለሰቦች ማህበራዊ ግዴታዎቻቸውንና ኃላፊነቶቻቸውን በሚገባ እንዲወጡ ያስችላቸዋል። የተለያዩ አመለካከቶችን፣ አስተሳሰቦችን፣ አተያዮችን የማስተናገድ አቅማቸውን ያጎለብታሉ። ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔዎችን የማፍለቅ፣ ለጋራ ውሳኔም የመግዛት ባህልን ያዳብራለ። ይህ በበኩሉ በአንድ ሀገር ላይ የዲሞክራሲ ሥርዓት እንዲያብብ የሚያደርገው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

በእነዚሁ ተቋማት ያሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት አካታችነት ዝም ብሎ አይመጣም፤ ወይም አይገኝም። አካታችነት አካታች ሥርዓት (Inclusive system)ን ይፈልጋል። በሌላ አባባል ቀደም ሲል የነበሩትንና አካታች ያልሆኑትን ከአመለካከት ጀምሮ እስከ ፖሊሲዎች ድረስ የዘለቁ አሰራሮችን መለወጥን ሁሉ ግድ ይላል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለመለወጥ ዝግጁ የሆነ ማህበረሰብንና አጠቃላይ አመራርን ይፈልጋል እንደማለት ነው።

ትምህርት ዕውቀትንም ሆነ ሙያን የማስተማርና የመማር ሂደት ነው። ማስተማር እና መማር ደግሞ የሁለት አካላትን ማለትም የሚያስተምረውንና የሚማረውን አንድ መሆንና አብሮነታቸውን ይፈልጋል። ይህም ትምህርት በአንድ ወገን ጥረት ብቻ መሬት የሚወርድ ጉዳይ አይደለም እንደማለት ነው። ይህም በብዙ መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ ዋናው ትኩረት ግን ከትምህርት ጋር በተያያዘ ብቻ ይሆናል፡፡

ምንም እንኳን ትኩረቱ በዘመናዊ የትምህርት ተቋማት ላይ ብቻ ቢሆንም የአብነት ትምህርት የጉባዔ ቤቶች ተብለው በሚጠሩ ልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፎች አሉ፡፡ ለአብነትም ቤት፣ ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መጻሕፍት ቤት የተከፋፈሉት የአብነት ትምህርት ቤቶች “ኃይማኖታዊና ባሕላዊ እሳቤዎችን፤ እሴቶች እና ትውፊቶችን ለታዳጊዎች እንዲሁም ለአዋቂዎች” ለማስተማር የተወጠኑ የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ተቋማት ይገኙበታል፡፡ አብሮነትን ከማፅናት አኳያም ሚናቸው የጎላ መሆኑ ሲነገር ኖሯል። በደረሳውም እንደዛው።

ዘመናዊ ትምህርት በአዲስ መልክ ሲቃኝ ግን እነዚህን ሁሉ አላካተተም፡፡ በመሆኑም ለውድቀት ዳረገን የሚሉ ድምጾች ሁልጊዜ ይሰማሉ። ለመሰማታቸው አንዱ፣ ምናልባትም ዋነኛው ጉዳይ ደግሞ አብሮነት እየተሸረሸረ መምጣት መሆኑ ይነገራል። የትምህርት ፖሊሲያችን ሀገር በቀል እውቀታችንን አሽቀንጥሮ ጥሎታል፡፡ በመጣሉም ዋጋ አስከፍሎናል ነው እየተባለ ያለው። ከዚህ አኳያ ካየነው ወቀሳው ምላሽ እያገኘ ያለ ይመስላል።

ባለፈው ዓመት የግብረ ገብ፣ የዜግነትና የሰላም ዕሴቶችን ያካተተ ሥርዓተ ትምህርት ለማዘጋጀት እየተሰራ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቆ እንደ ነበር ይታወሳል፡፡ ተጠናቅቆና ወደ ሥራ ገብቶ ከሆነ አብሮነትን በተማሪዎች አእምሮ ውስጥ ለማስረፅ አንድ ርምጃ ወደፊት የሚያራምድ በመሆኑ ተቋሙ ሊመሰገን ይገባል። ካልሆነም በቅርቡ፣ ቢያንስ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ለጉዳዩ እንድንጓጓና ትምህርት ሚኒስቴር ቢያንስ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ያስገባቸው ዘንድ ያስጨነቀን “የግብረ ገብ፣ የዜግነትና የሰላም ዕሴቶች” የሚሉ ትምህርቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ ፅንሰ ሃሳቦች ከአብሮነት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤቶች ውስጥ አብሮነትን ከማዳበር አኳያ የሚኖራቸው ሚና በቀላሉ የማይታይ በመሆኑ ነው።

ይህንኑ፣ በትምህርት ገበታም ሆነ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ የተማሪዎችን አብሮነት በተመለከተ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በልማትና የተማሪዎች የመማር መብትን አስመልክቶ ባዘጋጀው ሰነድ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ ጉዳዩ መምህራንንም በቀጥታ የሚመለከት ነው።

የድርጅቱ ሰነድ እንዳሰፈረው መምህራን የማስተማር ተግባራቸው ይህንኑ የተማሪዎችን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ መሆን እንደሚገባውና ለዚህም የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ ራሳቸውን ከሁኔታዎች ጋር በሚገባ ማዋሀድ ይገባቸዋል። የትምህርት ተቋማት ምድረ ጊቢም በዛው ልክ ያማረና የተዋበ፤ አብሮነትን በሚጋብዝና በሚያስተናግድ መልኩ ሊገነባ ይገባል። አብሮነትን ከሚሸረሽሩት መሰናክሎች አንዱ “እኩል ተጠቃሚ አለመሆን” ነውና የመማሪያ-ማስተማሪያ ቁሶችም ያለ ምንም አድልኦ ለሁሉም እኩል ተደራሽ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

እንደ ድርጅቱ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ከላይ የተዘረዘሩት ብቻቸውን በቂ አይደሉም። የየሀገራቱ መሪዎች በትምህርት ተቋማት ውስጥ አብሮነትን ሊያዳብሩ የሚችሉ አሰሪ የሕግ ማእቀፎችን ሊያዘጋጁ ወይም ሊኖራቸው ይገባል። አብሮነት ምን ያህል እየተጠናከረ እየሄደ እንደሆነም በየጊዜው ለማወቅ ያስችል ዘንድ የቁጥጥር፣ የክትትልና የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓት ሊኖራቸው፤ የሙያና የቴክኒክ ድጋፍም ሊያደርጉ ይገባል። የሀገራት ልምድንም መቅሰም አስፈላጊ ነው።

በመርህ ደረጃ፣ የትምህርት ተቋማት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና በሂደትም ባህል መሆን ከፍተኛ ድርሻ ብቻ ሳይሆን ሚናም አላቸው። በመርህ ደረጃ በአንድ ሀገር ላይ የትምህርት ተቋማት ብዙ ማለት ካልበዙባቸው ሀገራት በተሻለ ደረጃ እዛ ሀገር ዲሞክራሲ አለ ማለት ነው። በተሻለ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ አሰራር አለ ማለት ነው። በተሻለ ደረጃ ፍትህና ርትእ ነግሷል ማለት ነው። የእነዚህ ሁሉ እሴቶች ባለቤት መሆን ደግሞ አብሮነትን አያካትትም ማለት አይሆንምና የትምህርት ተቋማት ሚና ከዚህ መለስ የሚባል አይደለም።

የትምህርት ፍልስፍናን በተመለከተ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሊቃውንት እንደሚሉት ተግባራዊ አልተደረገም እንጂ በኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲና ማስፈፀሚያ ሰነዶች ላይም ሰፍሮ እንደሚገኘው ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ብቁና በምክንያታዊ ትንተናና በውይይት የሚያምኑ፤ በሙያቸው ብቃት ያላቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ አድርጎ አጠቃላይ ሰብዕናቸውን መገንባት “ብዝሃነትን ላካተተ ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ” ይገባል የሚለው የትምህርት ፍልስፍና ቁልፍ መልእክት ነው። ለዚህ ሁሉ ስኬት ደግሞ መሠረቱ አብሮነት ነው።

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You