በአብሮነት – ሀገርን ማጽናት

 አሮጌውን ዓመት ደህና ሰንብት ብለን አዲሱን ለመቀበል እንሆ የመጨረሻ በሆነችው ጳጉሜን 6 ላይ ከተመን፡፡ ከጥበብ ሁሉ በላቀችው የአብሮነት መንፈስ ውስጥ ሆነን ሀጂውን ሸኝተን መጪውን ልንቀበል ሽርግዱ እያልን ነው። ዘመን እንደሸማኔ መወርወሪያ ነው… እየሄደ የሚመጣ።በዚህ የጊዜ ሀዲድ ውስጥ ራስን ዋጋ ባለው የአብሮነትና የወንድማማች መንፈስ ውስጥ ማኖር ደግሞ ትልቁ ጥበብ ነው፡፡

የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ተከባብሮና ተቻችሎ ለመኖር ከየትኛውም በላይ የአብሮነት እሴቱ ትልቅ ነው፡፡ ይህ እውነታ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ነገራችን አይደለም። ከትላንት እስከ ዛሬ እንደ ባህልና ሥርዓት ይዘነው የመጣነው ነው፡፡ እንደ ሀገርም ረጅም ዘመን የዘለቅነው አብሮነት በሚወልደው መተሳሳብ ነው።

ለእኛ ኢትዮጵያውያን አብሮነት የሥርዓት መነሻችን ነው፡፡ ገናና ሀገርና ታሪክ የጻፍነው በዚህ እውነት ውስጥ ተመላልሰን ነው፡፡ ደምቀው ያሱዋቡን ወግና ባህሎቻችን አብሮነታችንን ታከው የቆሙ ስለመሆናቸው አያሌ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እዛም እዚም ባሉ የብዙኃንነት መገለጫችን ውስጥ አብሮነት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዝ የማንነታችን ዋልታና ማገር ነው። ያቆመና ያጸናን ትልቁ መገለጫችን አብሮነት ነው፡፡

አብሮነት እንደ ሀገር ትልቁ ውበታችን ነው። ስናብር የሚደፍረን የለም፡፡ በአንድ ስንቆም አስፈሪዎች ነን፡፡ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ የታሪኮቻችን ገድሎች በተያያዙ እጆች፣ በተጣመሩ ክንዶች የተጻፉ ናቸው፡፡ ሀገር ካቆምንበት፣ ትውልድ ካነጽንበት ከአብሮነት ማዕድ ፊት በጋራ ስንቆም ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ ታሪክ አይኖሩንም፡፡

አብሮነት በአንድ ሀሳብ፣ በአንድ እምነት መቆም ብቻ አይደለም፡፡ አብሮነት በአንድ ኃይል የበላይነት ተጽዕኖ ውስጥ መሆንም አይደለም። አብሮነት ስለሀገርና ሕዝብ ክብር ሲባል ልዩነቶችን አጥቦ አንድ መሆን ነው፡፡ አብሮነት በምክክርና በውይይት፣ በፍቅርና በይቅርታ የጋራ ቤት የምንሰራበትን ሃሳብና እውነት ማዋጣት ነው፡፡

ይህንን እውነታ ሥጋና ደም የሚያላብሱ አያሌ ሥነ ቃሎችን አሉን ‹ድር ቢያብር አንበሳን ያስር፡፡ ለአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ› አይነት አባባሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንበሳን ያህል ብርቱና ሀይለኛ ፍጡር ምንም በማይረባ ድር ሲታሰር አስባችሁታል? ሚስጢሩ የድሩ አለመርባት ሳይሆን የአንድነት ጥበብ ነው፡፡ ብዙ ድሮች አንድ ላይ ሆነው ጠብቀውና ጠንክረው አንበሳን ያስራሉ፡፡

ይሄ አባባል የአብሮነትን መንፈስ ለማንጸባረቅ ከእኛ ጋር ከዘመን ዘመን የተሻገረ ኢትዮጵያዊ ወግ ነው፡፡ አብሮነት ከተነሳ ሁሌም የሚታወሱ ድሮአዊና አሁናዊ ታሪኮች አሉን፡፡ የመጀመሪያው ዓድዋ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ነው፡፡ በሁለቱም አብራክ ውስጥ ባለታሪክ የሆነው በአብሮነት ስለተነሳን ነው፡፡ ሃሳብ መድገም እንዳይሆንብኝ ብዬ እንጂ በነዚህ ሁለት የታሪክ አውድ ውስጥ ያለውን የአንድነት መንፈስ በብዙ መልኩ መግለጽ ይቻል ነበር፡፡

ዛሬም እንደ እንከን ከፊታችን ቆመው ያስነወሩንን የድህነትና የኋላቀርነት ብሎም የዘረኝነት ጽንፎች ከሥራቸው መንግሎ ለመጣል አብሮነትን የመሰለ ፍቱን መድኃኒት የለንም፡፡ ዓድዋን የሚያክል በዘመናት ታሪክ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ የሰነበተን ሁነት ከፈጠርን፣ በአፍሪካ ደረጃ ከፊት የሚቀመጥን የኃይል ማመንጫ ያለማንም እገዛ ለብቻችን መገንባት ከቻልን አሁናዊ ችግሮቻችንን የማንረታበት ምንም ምክንያት የለም።

ኢትዮጵያዊነት የብቻ ማንነት ሳይሆን የጋራና የብዙሃነት መልክ ነው፡፡ አብረን ሆነን፣ አብረን አስበን፣ አብረን ሰርተን ነው ይሄን የክብር ስም የተጎናጸፍነው፡፡ መጀመሪያችን የአንድና የሁለት ቡድን አለቅነት ቢሆን ኖሮ በዚህ ልክ አንገንም ነበር። ተደባልቀንና ተዋህደን የእኔ የአንተ እንዳንባባል በሚያደርግ የአብሮነት ውህደት ውስጥ ነን፡፡ ከዚህ ሀገር ካበጀ እልፍ ቅይጥ ማንነት ውስጥ የምንመዘው የብቻ ሰበዝ የለም፡፡ አንዱ ሲመዘዝ ቤቱ እንዲፈርስ ሆኖ የታነጸ ታሪክ ነው ያለን፡፡ አንዱ ሲጎል መላው እንዲደበዝዝ ሆኖ የተሰራ እልፍኝ ነው ያለን፡፡

ዛሬ ላይ የግል ታሪክ ፈጥረን የእኔ የአንተ የምንባባለው የአንድነት ዋጋ ጠፍቶን ሳይሆን በልዩነት የምናተርፈው ትርፍ ያለ መስሎን ነው፡፡ ልዩነት ትርፍ የለውም፡፡ በዘርና በብሔር ተቧድኖ በብዙሃነት የጸናን መሠረት መነቅነቅ የሚያስወቅስ እንጂ የሚያስመሰግን ጀብድ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን የሚያስፈልጋት በጋራ ሃሳብ የአብሮነት ቤት የሚሰራ ፖለቲካና ፖለቲከኛ ነው። በአሁኑ ሰዓት ሕዝባችን የሚሻው በንግግርና በምክክር የጥንቱን ኢትዮጵያዊነት የሚመልስ እውቀትና ጥበብ ነው፡፡

እንደ አብሮነት የሚያምርብን ማንም የለም። ሰማይ በከዋክብቶቹ እንደሚያምር የእኛም ውበት ያለው አብሮነታችን ውስጥ ነው፡፡ በዚህ በምንም እንዳይላላ ሆኖ በተገመደ አንድነታችን ውስጥ መርዝ ሆነው ሊያላሉን የገቡ እሳቤዎች እምቢ ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ኋላችንን መለስ ብለን ብንመለከት በአብሮነት የተዋጁ ሆነው ነው የምናገኛቸው፡፡ ፖለቲካም የውልዳቸው ወይም ደግሞ በራስ ወዳዶች ይፈጠሩ አሁናዊ የመለያየት ቁርሾዎች ኢትዮጵያዊነትን ከማደብዘዝ ባለፈ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡

ወደፊት ለመሄድ የሰነቅንው ሕዝባዊ ተስፋችን አብሮ በመቆም ውስጥ ነው፡፡ ለአፍታ ዛሬንና ትላንትን ማሰቡ አሁንን ለመታዘብ እድል ይሰጠናል። ትላንትና አንድ ሀገር፣ አንድ ሕዝብ ነበርን፡፡ በታሪክ፣ በባህል ተጋምደን በአንድ ፎሌ እየጠጣን፣ በአንድ ገበታ እየበላን ኢትዮጵያን ያከበርን ሕዝቦች ነን፡፡ የአንዱን ችግር የእኔ ብለን፣ የአንዱ መነካት የሁላችን መነካት እንደሆነ አምነን ቅያሜ በሌለው አብሮነት ውስጥ ነበርን፡፡ ዛሬ እኚህን ውበቶቻችንን የሚያደበዝዙ ፖለቲካ ለበስ የብሔርና የማንነት ጥያቄዎች እየተነሱ ነው። ኢትዮጵያዊነትን አኮስሰው ራስ ወዳድነትን ያበረቱ ጽንፍ የረገጡ እብሪቶች እያየን ነው፡፡

እኚህ አስተሳሰቦች ልዩነትን ከማስፋትና አብሮነትን ከመሸርሸር ባለፈ ሕዝባዊ ትርፍ የላቸውም፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥም የሞትና የጉስቁልና ፍሬአቸውን አይተናል፡፡ በእውቀትና በምክር፣ በእርቅና በፍቅር ወደተውነው የአብሮነት ሥርዓታችን እስካልተመለስን ድረስ ከዚህም በላይ ዋጋ ለመክፈል እንደተሰናዳን ልናውቅ ይገባል፡፡

አላማችን ኢትዮጵያንና አብሮነታችንን ማስቀጠል ከሆነ የእልህ ፖለቲካና የእልህ እንቢተኝነት ማብቃት አለባቸው፡፡ ድህነትና ኋላቀርነት መገለጫችን ከሆኑ ዘመናት ተቆጥረዋል። በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት ሌላ ስምን እያተረፍን ያለንበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያን መውደድ የሰላም ሃሳብን ከማመንጨት የሚጀምር ነው፡፡ ችግሮቻችን ወደጦርነትና ወደአላስፈላጊ ድርጊት የሚመሩን ከሆነ የሀገር ፍቅር አልገባንም ማለት ነው፡፡

ስልጣኔ መነሻው አብሮነት ነው፡፡ አክሱምና ላሊበላን የመሰሉ ለዘመናዊው ዓለም ትንግርት የሆኑ የኪነጥበብ ንድፎች በኢትዮጵያውያን እጆች የታነጹት በአንድነት በተጣመሩ እጆችና አእምሮዎች ነው፡፡ ዓለምን በነጻነት የተጋድሎ ታሪካችን ያደመቅነው በአብሮነት መንፈስ ነው። ፍቅር የዛኛው ትውልድ ቋንቋው ነበር፡፡ ፍቅር ሰላም የሚወለድበት፣ አንድነት የሚበቅልበት ለም መሬት ነው፡፡ በዚህ ለም መሬት ላይ ተዘርተን ሰላሳና ስልሳ መቶም ያማረ ፍሬ ካላፈራን ኢትዮጵያን ከጥላቻ ልንታደጋት አንችልም፡፡ ወደክብራችን ለመመለስ ወደተውነው የአብሮነት ቀለማችን መመለስ ይኖርብናል። ተነጋግረን የምንግባባበት የሰላም መድረኮች፣ የእርቅና የአብሮነት ድምጾች ያስፈልጉናል፡፡

በውይይትና በበላጭ ሃሳብ ተሟግተን በጦርነት ሳይሆን በፍቅር፣ በጥላቻ ሳይሆን በሰላም መሸናነፍን መልመድ ያስፈልገናል፡፡ መጪው አዲስ ዓመት በሁላችንም ልብ ውስጥ የተስፋ፣ የሰላም እና የእርቅ እንዲሆን የቀደመው አብሮነታችን መመለስ አለበት፡፡

ሰላምና አብሮነትን በሚያመጡ የአዲስ ተስፋ ጅምሮች ስንነቃና ስንበረታ ጥያቄዎቻችን መልስ ያገኛሉ፡፡ መጪውን ጊዜ በጋራ ህልም እና በጋራ ንቃት እስካልተቀበልነው ድረስ ከአሮጌው እንደማይሻል ማወቁ ይበጃል፡፡ መነሻችን አብሮነት ነው… አብሮነት ደግሞ ከሰላም እና ከእርቅ የሚጀምር ነው፡፡ የጀመርናቸው የእርቅ ጎዳናዎች ፍሬ እንዲያፈሩ ሁላችንም ዋጋ መክፈል አለብን፡፡

ከየትኛውም ምድራዊ ብርታት በላይ አብሮነት ኃይል ነው፡፡ በዚህ ልክ በርትተንና ጀግነን የቆምንም አብረን ስለሆንን ነው፡፡ መለያየት ማንንም ባለታሪክ አድርጎ አያቅም፡፡ አሁን ላይ እየተንገዳገድንና እየተፍረከረክን ያለንም ከጥንቱ የአብሮነት መንፈስ ስለተንሸራተትን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ወደክብሩ እንዲመለስ፣ የጀመርናቸው የማደግና የመለወጥ ግቦች ትልማቸውን እንዲመጡ አብረን መቆም ግዴታችን ይሆናል፡፡

ክብር የጨመሩልን ሕዝባዊ ውበቶቻችን ዛሬ ላይ የብሔርና የእኔነት መልክ እየያዙ ነው፡፡ ተስተካክለን እስካላስተካከልናቸው ድረስ ከዚህም በላይ የሚቀሙን ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ እኚህ ስሜት ለበስ ፍላጎቶች በአብሮነት የጸና የጋራ ስማችንን ከማጠልሸት እና ከማደብዘዝ ውጭ ባለማዕረግ አያደርጉንም፡፡

ሀገር የክብር ዙፋን ናት፡፡ በስሟ የምንከብረውም ሆነ የምንዋረደው እኛ ነው። በእኛ ድርጊት የሚከብር እና የሚዋረድ ማንም የለም፡፡ ከውርደት ክብር እጅጉን ይሻላልና ወደከፍታ የሚወስደንን የአብሮነት ንቃት በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ላይ እንጀምር፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ላይ የድርሻችንን ማዋጣት ብንችል ድህነት በዚህ ልክ፣ አለመግባባት በዚህ መጠን ባላስጎነበሱን ነበር፡፡

ጳጉሜን 6 አሮጌውን ዓመት ተሰናብተን ወደአዲሱ ዘመን የምንሸጋገርባት የመጨረሻ ቀናችን ነው፡፡ ወደአዲሱ ዓመት ይዘነው የማንሄደውን አሮጌ አስተሳሰባችንን ሽረን ለሀገር በሚበጅ በነቃና በበቃ እሳቤ መስከረምን መጀመር አለብን፡፡ እንደ ሀገር፣ እንደ ግለሰብ የነበሩብንን ችግሮች አርመንና ነቅሰን በአዲስ ብርታት ለመነሳት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንትጋ፡፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሁም ደግሞ ተነጋግረን የምንግባባበት፣ ተግባብተን አብረን የምንኖርበት የአብሮነት እንዲሆን ከልብ እመኛለሁ፡፡

 እጸሳቤቅ (በማርያም)

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You