አብሮነት – ኢትዮጵያዊ ማንነት

አብሮነት ለሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብር ወሳኝ ሚና ያለው መርህ ነው። አብሮነት የተለየ ማንነትን፣ ባህልን ወይም ሃሳብን የሚያከብርና የሚያስተናግድ በሰላም አብሮ የመኖር መሠረት ነው።

ዩኔስኮ የአብሮነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ያደረገው በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት ያለውን ልዩነት በመቀበል የሰው ልጆች ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን እንዲያጠናክሩ ለማድረግ በማሰብ ነው።

በልዩነቶች ምክንያት በየጊዜው የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መጠነ ሰፊ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን ለማስገንዘብና አብሮነት ለሰው ልጆች ተሳስበው መኖር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ነው። አንዱ የሌላውን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር ለዓለማችን ሕዝቦች ወሳኝ መሆኑን ግንዛቤ ለማስረፅ ጭምርም ነው።

ሰዎች በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በማንነት ወዘተ የተለያዩ እንደመሆናቸው አብሮ የመኖር ህልውና የሚረጋገጠው በአብሮነት ብቻ ነው። ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም የምንለይበትን የጳጉሜን ወር ስናከብር የዛሬዋን ዕለት በአብሮነት መሰየም ብቻ ሳይሆን አብሮነታችንን በማጠናከር ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያ የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የመልክአ ምድር ብዝሀነትን የተላበሰች ኅብረ ብሔራዊት ሀገር ከመሆኗም ባሻገር ሕዝቦቿ በአንድነት የሚቆሙበትና የሚተባበሩበት በርካታ ሀገራዊ እሴቶች አሏት። በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሟትን የውጭ ወራሪዎች ለመመከት ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በባህልና በሃይማኖት ሳይለያዩ አብረው ተዋግተው ነፃነቷን አስጠብቀዋል።

ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ትግል የመተባበርና አብሮ የመፋለም እሴት ዛሬም ጎልቶ ይታያል። ለዚህም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና ገበታ ለሀገር በመሳሰሉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሁሉም ዜጋ በጋራ መሳተፉ ጉልህ ማሳያ ነው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሕዝቦችን የሰላምና የአብሮነት ፍላጎት የማይመጥኑ፣ ትብብርና ወንድማማችነታቸውን ከማጠናከር ይልቅ የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያሻክሩ፤ በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት ከማጉላት ይልቅ ልዩነት ላይ የሚያተኩሩ፤ አብሮነታችንን ወደ ገደል አፋፍ የሚገፈትሩ ክስተቶች አጋጥመዋል፣ ፈትነውናልም።

በተከሰቱ ግጭቶቹ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመት እንዲሁም ዜጎች ለዓመታት ከኖሩባቸው ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች ምክንያት ከተወለዱበት፣ ካደጉበት እና ለዓመታት ከኖሩበት ስፍራ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያን ቁጥርም ቀላል የሚባል አይደለም።

ቀደም ባሉ ዓመታት የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴቶች ከማጎልበት ይልቅ ልዩነቶች ላይ የተሠራው ሥራ በዝቶ እንደነበር የሚታወስ ነው። በተለይ በማንነት እና በሃይማኖቶች መካከል ጥርጣሬ እንዲነግስ በር በመክፈት አንደኛው ወገን ሌላኛውን እንዲጠራጠር ብሎም የበዳይና ተበዳይ ትርክት እንዲፈጠር ተደርጎ ቆይቷል። የፖለቲካ ልሂቃን፣ የአክቲቪስቶች እና የአንዳንድ ምሁራን ትርክቶች ጥላቻ እንዲነግስ በር ከፍቷል። ይህም በጠነከረ አለት የተገነባ አብሮነታችንን ለመሸንቆር እየታገለ ይገኛል፡፡ ይሁንና በለውጡ ዘመን የተፈጠረውና አብቦ በመሄድ ላይ ያለው የወንድማማችነትና እህትማማችነት የአንድነት ትርክት በአሁኑ ወቅት መሠረቱን እያሰፋ በመሄድ ላይ በመሆኑ ለአብሮነታችን ያለው ፋይዳ ትልቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር የምትሆነው ሕዝቦቿ በአብሮነት መቆም ሲችሉ ነው። እንደ ሀገር በመጣችበት መንገድ ክፍተቶች አልነበሩም ባይባልም፣ የነበሩ ጉድለቶችን በማረም ለነገው ትውልድ የሚሻገር ሠላም፣ አብሮነትና አንድነትን ማረጋገጥ ከዛሬው ትውልድ የሚጠበቅ ነው።

የሀገራችን ሕዝቦች ለዘመናት የገነቡት ትስስር፣ መስተጋብርና የአብሮነት እሴቶች ለመለያየት የማያስችሉና የተሳሰሩ መሆናቸውን ማንም የሚገነዘበው እውነታ ነው። የአብሮነት እሴቶች የጎለበቱባቸው ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና ሥነልቦናዊ ሁነቶች ጠንካራ ናቸው። እንደ አሜሪካ ያሉ ሀገራት የዓለማችን ልዕለ ኃያል ያደረጋቸው አብሮነታቸው ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ሃይማኖቶች እና ልማዶች ቢኖሩም በእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ የሚያመሳስላቸው ኢትዮጵያዊ ማንነት አላቸው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የእርስ በርስ የትብብርና የአብሮነት ታሪክ ያላቸው በመሆኑ ብዙዎቹ ማኅበራዊ ግንኙነቶችና ልማዶች ተወራርሰዋል። ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያቆዩትን እሴት ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት በአብሮነት ብቻ ነው። አብሮነት ከሌለ ወይም ከተሸረሸረ ውስጥ ለእርስ በርስ ግጭት ከውጭ ደግሞ ለብሔራዊ ደህንነታችን ስጋት የሚሆኑ አደጋዎችን ያስከትላል። ስለሆነም ጠንካራ ሀገር እንዲኖረን የአብሮነት እሴቶቻችንን ልንንከባከብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አብረን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር ናት፡፡ አብረን ኖረናል አሁንም አብረን እየኖርን ነው፣ ወደ ፊትም አብረን እንኖራለን!

 የሰዎችን ጤናማ ግንኙነት ጠቀሜታን ማሳወቅና ማስፋፋት (promoting the importance of human relationships) አጠቃላይ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ መስተጋብሮችን ባልተዛባና ወደ አንድ ጎን ባላዘመመ ትስስር ማስተናገድ የሚችል ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር እንደሚያስችል የማኅበራዊ ሳይንስ በተለይም የሶሲዮሎጂ፣ የሳይኮሎጂና የሶሻል ወርክ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

የሰዎችን ጤናማ ግንኙነቶችን ለማሳለጥ ከሚረዱ እሴት አዘል ተግባራት ውስጥ ደግሞ የወል(የጋራ) መተማመንንና መከባበርን፣ አብሮነት መገንባት ከዋነኞቹ ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በርካታ የራሷ መገለጫዎች አሏት። ከብርቅዬ ኢትዮጵያዊ ማንነቶች መካከልም ዘመናትን የተሻገረው የውድ ልጆቿ በደግም በክፉም የመተባበር የአብሮነት መስተጋብር በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ በሺዎች ዘመን ታሪኳ ብዙ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ብዙ ማንነቶችንም በአብሮነት አቅፋ ያኖረች ሀገር ናት።

የአክሱምን ሐውልት ያቆመ፣ የፋሲልን ሕንፃ ያነጸ፣ ላሊበላን ከአንድ ወጥ ድንጋይ የቀረጸ፣ የሐረርን ግንብ የገነባው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ተሳትፎ የገነባው የአብሮነት ግንብም እጅጉን በጸና መሠረት ላይ የታነፀ ነው፡፡

ተደጋግሞ እንደሚነገረው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ስናወራ አንድ ቀለም ስለለበሰች ኢትዮጵያ ሳይሆን፤ ከዚያ በላይ የተለያዩ ማንነቶች፤ ቋንቋ ፣ባህል፣ ሃይማኖት ወዘተ ያላቸው ዜጎች በሰላም በፍቅር ሀገር መስርተው የሚኖሩበት፤ እየኖሩባት ስላለችው ባለ ብዙ ቀለሟ ኢትዮጵያ ማለታችን ነው።

ሁላችንም እንደምንረዳው የአብሮነት መጀመሪያው ጉርብትና ነው። ጉርብትና አካባቢን/ መልክአ ምድርን ታሳቢ ያደረገ ነው። በአንድ ሰፈር ውስጥ ከሚኖሩ የአጥር ተዋሳኞች እስከ ቀበሌ ወረዳ ዞንና ክልል ሕዝቦች በጉርብትና ይኖራሉ። እነዚህ የድንበር፣ የወንዝና የተራራ ወሰኖች ግን ሕዝቡን ከአብሮነት ፈቀቅ አድርገውት አያውቁም። ሊያደርጉትም አቅም የላቸውም።

ኢትዮጵያም እንደ ሀገር ድንበርን በተመለከተ በውስጥም ሆነ ከውጭ ኃይሎች /ሀገራት ጋር በየዘመኑ የተለያየ አከላለልን ስታስተናግድ ኖራለች። ይህም ሆኖ ግን አንዳቸውም የልጆቿን አብሮነት አቆራርጠውት አያውቁም። ይልቁንም ድንበር ተሻጋሪ አድርገውት ቆይተዋል።

ስደተኞች እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ ባላቸው ቆይታ የባይተዋርነት ስሜት የማይሰማቸው፤ በቀላሉ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚግባቡና ተስማምተው እንዲኖሩ የሚያስችላቸው የኢትዮጵያውያን የአብሮነት እሴት የታሰረበት ገመድ ድንበር የማይበጥሰውና ጠንካራ በመሆኑ ነው፡፡

«ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል እንዲሉ» እንዲህ ዓይነቱን መሠረት የጣለ የአብሮነት ድርና ማግ ለመበጣጠስ አንዳንዶች ሲውተረተሩ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ተስፋ ያልቆረጡ ከፋፋዮች በቀቢጸ ተስፋ ከውስጥም ከውጭም ሆነው የኢትዮጵያውያንን የአንድነት ገመድ ለመበጠስ መውተርተራቸውን አላቋረጡም፡፡

የእነዚህ የከፋፍለህ ግዛ እሳቤ አራማጅ የእፉኝት ልጆች ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከሚራመዱባቸው መንገዶች አንደኛው የመልክአ ምድር ሰው ሠራሽ አርቴፊሻል ድንበርን በመጠቀም ማንነትን መነሻ ያደረገ ነው።

በዚህ ተግባር ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች ከፊሎች የየራሳቸው ጥቅም የማግኘት ህልም ያላቸው፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ካለማወቅ ነገ ከነገ ወዲያ የሚለበልባቸውን እሳት የሚጭሩና የሚያባብሱ ናቸው።

እነዚህ ሁለቱም ደግሞ መቼም ቢሆን ሊጠፉ አይችሉም። ምክንያቱም በመለያየት ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ያሰበ ክፍተት ያገኘ ሲመስለው መሞከሩ፤ አላዋቂም እስኪያውቅ ድረስ በስህተት መንገድ መጓዙ አይቀርም።

ቀን እና ወቅት እየጠበቁ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለመበጠስ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩም አንድ መታወቅ ያለበት እውነት ቢኖር ግን የኢትዮጵያውያንን የአብሮነት ገመድ መበጠስ የሚችል አንዳችም ምድራዊ ኃይል እንደሌለ ነው፡፡

ከቅርብ አመታት ወዲህ ጽንፈኛ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት አክራሪዎች የሚሞከሩት የመከፋፈል፤ የመለያየትና የማቃቃር ሙከራም ብልጭ ድርግም እያለ ለነፋስ የተሰጠ አመድ ሲሆን እያየን ነው።

በቅርቡ እያየነው ያለውም ክፍተት በሕዝቦች መካከል ተዘርቶ ያቆጠቆጠ የመለያየት ስጋት ኖሮ ሳይሆን ዘመን አመጣሹ ማኅበራዊ ሚዲያ ለማንም ክፍት በመሆኑ ተስፋ ባልቆረጡ ተስፋ ቢሶች አጋጣሚውን በመጠቀም የተፈጠረ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡

እንዲህ ያለው በሳል ስብዕና እንደ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ፣ የሀገር ሕዝብ በጋራ ስንኖር ለሚኖሩን ግንኙነቶች የተግባቦት ጤናማነት መሠረት በመሆኑ ግንኙነቶቻችንን ሁሉ ሰላማዊ በማድረግ ጠንካራ ሀገርና ሕዝብ ለመመስረት ዋስትና ይሆናል፡፡

ሁሉም ዜጋ ሀገሩን እንዲወድ በዚህ ምግባርና ተግባሩም ምን ያህል አትራፊ እንደሚሆን ማስገንዘብ ካልተቻለ፣ በተለይ የባዕዳን ፍርፍሪ ተካፋዮች ‹‹እንደ ተመኘኋት አገኘኋት›› ፣ «እንደ አቀድንላት በታተናት» የሚሉበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።-

የኢትዮጵያውያን ዘመናትን የተሻገረ አንጸባራቂ የአብሮነት ጉዞ ያለው ፋይዳው ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ተዘርዝሮ የሚያልቅ ባለመሆኑ እንዳይበረዝም እንዳይሸረሸርም ከሁላችንም የሚጠበቅ ሥራ ይኖራል።

ለዚህም የመጀመሪያውን ድርሻ መውሰድ ያለበት መንግሥት ነው። በተለይም እንደ ባክቴሪያ ምቹ ሁኔታ ባገኙ ቁጥር እዚህም እዛም እሳት ለመጫር የሚሞክሩትን አደብ ማስገዛት ይጠበቅበታል።

በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖት ሽፋን በአደባ ባይ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያቋስሉ ነገሮችን የሚያስተላልፉ ግለሰቦችን ጊዜ ሳይሰጥና ነገሮች ሳይባባሱ አደብ የማስገዛት ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት ግድ ይለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የሚጠበቀው ሕዝብ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ሳይሆን መንግሥት ከሕዝብ ጎን እንዲቆም ነው። ይህንን ያልኩበት ዋናው መነሻዬ አብዛኛውን የአብሮነት አፍራሽ ተግባራት በመጋፈጥ እየተከላከለና እያከሸፈ ያለው እራሱ ሕዝቡ በመሆኑ ነው። ይህንን የሚያደርጉ ዜጎችን የመደገፍ፤ በርቱ የማለትና የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ሊሆን ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።

ብዙ ተከታይ አላቸው ተብሎ የሚገመቱ አዋቂ ሳይሆን ታዋቂ ግለሰቦች ዛሬም ድረስ በየማኅበራዊ ሚዲያው አንዳንድ ጊዜም በመደበኛ ሚዲያዎች ጨምሮ እየቀረቡ የሚረጯቸው መርዞች ሀይ ባይ ካላገኙ ለዘመናት የዘለቀውን የሕዝባችንን አብሮነት አደጋ ውስጥ እንደሚከተው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በተደጋጋሚ የምንሰማት መንግሥት ቻይና ሆደ ሰፊ መሆን አለበት የሚባል አካሄድ በዚሁ ከቀጠለ ብዙ የሚያስከፍለን ይሆናል የሚል ስጋት አለኝ።

የሃይማኖት ተቋማትም ቢሆኑ በሀገሪቱ በየደረጃው ተሰሚነትና ተቀባይነት ያላቸው በርካታ የሃይማኖት አባቶችና ሰባኪያን እንዳላቸው ይታወቃል። ተቋማቱ በሥራቸው ያሉትን፤ ወይንም በየስማቸው የሚንቀሳቀሱትን የሃይማኖት አባቶች ምእመኖቻቸውን እንዴት መምራት እንዳለባቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለባቸው።

ለመጪው ዘመን ሁለንተናዊ እድገት የአሁኗንና የወደፊቷን ኢትዮጵያ በእኩልነት፣ መከባበር እና በአንድነት መንገድ ላይ እንድትራመድ ለማድረግ የሚደረገውን ርብርብ ላይ ሁላችንም በቅንነት ልንሳተፍ ግድ ይለናል፡፡

በጋዜጣው ሪፖርተር

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ሰኞ ጳጉሜን 6 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You