ትውልድ ሆይ ጥላቻንና ጽንፈኝነትን እናስወግድ!

 አንዳንድ ጊዜ ስብከቱ፣ ወንጌሉ፣ መዝሙሩ፣ ዘፈኑ፣ ንግግሩ፣ ሥነ ግጥሙ ፣ መጣጥፉ ፣ ቃለ መጠይቁ፣ ገጠመኙ ፣ ወዘተረፈ በተለይ ለእናንተ ተብሎ የተሰበከ፣ የተዘመረ ፣ የተዘፈነ ፣ የተነገረ፣ ቅኔ የተዘረፈ፣ የተጻፈ፣ የተነገረ አይመስላችሁም ። እኔን ግን ብዙ ጊዜ ዛሬ ድረስ ለእኔ ወይም ስለእኔ የተባለ ይመስለኛል ። የ2ኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ ፍቅር ባልተወለደ አንጀቱ ይደቋቁሰኝና ፍቅሯን ሳትነፍገኝ መሸከም አቅቶኝ በገዛ ጥፋቴ የተለየችኝ የመጀመሪያ አይኑካየን ያጣሁ ሰሞን የወጣው የተፈራ ነጋሽ አልበም፤ በተለይ “ደህና ሁኝ ልበልሽ “ የሚለው ዘፈን ለእኔ የተዘፈነ ይመስለኝ ነበር ። ዛሬ ድረስ በእዝነ ህሊናዬ ይታውሰኛል ።

“…ደህና ሁኝ ልበልሽ ፣ በእንባ እየታጠብኩኝ፤

ፍቅርን ለመጨረሽ፣ መቼም አልታደልሁኝ፤…”

እንዲህ እንደኔ ፍቅርን መሸከም ተስኗችሁ በየሕይወት ፌርማታችሁ ያንጠባጠባችሁ ግለሰቦች፣ መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌላም አላችሁ ። ፍቅር እየተለገሳችሁ እንደኔ ማስተናገድና ማስተዳደር አቅቷችሁ አፍቃሪዎቻችሁን ያጣችሁ የትየለሌ ናቸው። ጉድ እኮ ፍቅርን መሸከም ባለመቻል አፍቃሪን፣ ተከታይን፣ አክባሪን ማጣት። አይንህን ለአፈር መባል። ከዚህ ይሰውራችሁ።

ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ ሰሞኑን ለንባብ የበቃው የ”The Economist “መጽሔት፤” How paranoid nationalism corrupts” በሚል ርዕስ ይዞት የወጣው ርዕሰ አንቀጽ የሀገራችን፣ የሕዝባችንን፣ የመሪዎቻችንን፣ የፖለቲከኞቻችንን፣ የሚዲያዎቻችንን፣ የአክቲቪስቶቻችንን፣ ወዘተረፈ አከራረምና ሰሞነኛ አኳኋን የዋጀ ለእኛ ተብሎ በሀገራችን ጋዜጣ ባንዱ የተጻፈ ርዕሰ አንቀጽ እስኪመስለኝ አስገርሞኛል። በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነትን መሪዎች ተከታዮቻቸውን ለማስፈራራት በመጠቀም ሥልጣንን በአቋራጭ ለማግኘትና ካገኙ በኋላም አላግባብ መጠቀም የዓለማችን ፈተና መሆኑን በዋናነት ያትታል።

ግነትና ውሸት ደግሞ በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ብሔርተኝነት ምስ ናቸው ይለናል ። ይሄን ምሱን አግኝቶ ሲደነድን ደግሞ የሕግ አውጭውን፣ የተርጓሚውንና የአስፈጻሚውን ሥልጣንና ተግባር ይቀላቅላል። ያጣርሳል። ጠቅልሎ ይይዛል። ከዚያ ተጠያቂነትንና መልካም አስተዳደር ያጠፋል። ገለልተኛ ተቋማትን ያሽመደምድና አራጊ ፈጣሪ ይሆናል። ሙስናና ብልሹ አሰራር ግብሩ ይሆናል። በመጨረሻም በሀገር ህልውና ላይ አደጋ ይደቅናል።

በብሔራቸው ተከልለው ሕዝብ ይዘርፋሉ፣ ያጉላላሉ፣ ያሰቃያሉ። ፈላጭ ቆራጭ አምባገነን ይሆናሉ። መጣብህ፣ ተነሳብህ፣ ሊውጥህ ነው እያሉ ፍርሀት እየጎነቆሉ የልባቸውን ይሰራሉ። ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትን ከጥላቻ ጋር ተጃሎ ሀገራችንን ወደለየለት ቀውስ እያንደረደሯት ነው። ላለፉት 50 ዓመታት ተቋማዊና መዋቅራዊ ሆኖ የተለፈፈው ልዩነትና ሀሰተኛ ትርክት መንታ አሳቅፎናል። እነሱም ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትንና ጥላቻ የተባሉ ዲቃላዎችን። የእነዚህ ዲቃላዎች ተስቦ ደግሞ በአንድም በሌላ መልኩ ሁላችንንም ታማሚ አድርጎናል።

አንዳንዶቻችን መታመማችንንም አምኖ መቀበል ተስኖን ሌሎች በሽተኞች ላይ ጣት እንቀስራለን። እንደጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ብለን እጃችንን ለመታጠብ ይዳዳናል። ቁርጣችሁን ልንገራችሁ ይህ ተስቦ ያልገባበት የለም። በገዢው ፓርቲ በለው በተቃዋሚውና በአክቲቪስቱም ሆነ በዩቲውበሩ ። ምን አልባት ደረጃው ይለያይ

 ይሆናል እንጂ ሁላችንም ወይም አብዛኞቻችን ጥላቻን ጽንፍ ከረገጠ ብሔርተኝነት እያጃመልን በሕዝብ መካከል የባቢሎንን ግንብ ከመገንባት አልፈን አንዱን በአንዱ ላይ እያነሳሳን ነው።

ቆም ሰከን ብለን የተያያዝነውን አደገኛ የጥፋት መንገድ ትተን መጀመሪያ ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትንና የጥላቻን ጋብቻ 80 ካልቀደድን፤ በማስከተል ደግሞ ጥላቻን በሀቀኛ ፍቅር ካላሸነፍን ጽንፍ የረገጠ ብሔርተኝነትን የሚቀፈቅፍ መዋቅርንና ተቋምን ካላፈራረስን እንደ ሀገር የመቀጠላችን ነገር ያሰጋል። ይህ ሟርት አይደለም። መሬት ላይ ያለ ሀቅ እንጂ። ስለሆነም ኑ በአዲስ ዓመት መጀመሪያ ጥላቻንና አክራሪ ብሔርተኝነት እናፋታ እላለሁ። በማስከተል መዋቅራቸውንና ተቋማቸውን ማፍረስ እንጀምር ስል ጥሪ አቀርባለሁ።

እንደ ግሪኳ አማልክት ካሳንድራ በአፓሎ አትደመጭ ተብላ እንደተረገመችው ተረግሜ እንጂ ላለፉት አምስት ዓመታት ጉሮሮዬ እስኪነቃ ለፍልፌ ነበር። አባ ከና ሚለኝ አጣሁ እንጂ። ዛሬም ብንዘገይም አልረፈደምና የቀድሞው የጀርመን መራሔ መንግሥት ዊሊ ብራንት፣” የሁላችን የሆነ አብሮ ማደግ ይችላል፤” በሚል ዕምነት ስስትን፣ ሴራንና መጠላለፍን ትተን በእውነተኛ አንድነት ከቆምን የተቀረው እዳው ገብስ ነው። ሀገራችን ከበቂ በላይ ናት። ጥላቻንና አክራሪ ብሔርተኝነት ነጣጥሎ ለመምታት ያብቃን እንጂ ባህላዊ ወረቶቻችን ከበቂ በላይ ናቸው። ለመሆኑ ባህል፣ ባህላዊ ንብረትስ ምንድን ነው የሚለውን ለመግባቢያ ያህል በአለፍ ገደም እንመልከት።

ባህል ሁሉንም የሚያስማማ የሚያግባባ ወጥ የሆነ ትርጉም ብያኔ ባይኖረውም የአንድ ማህብረሰብ ወይም ህዝብ እምነት ፣ ልማድ ፣ ወግ በኪነ ጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተዳውሮ፣ ተሸምኖ፣ ተንሰላስሎ የመገኘት፣ የመገለጥ ዥጉርጉር ሕብራዊ ቀለም ነው። በደስታ፣ በኀዘን፣ በስራ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት፣ ወዘተ… የሕይወት ገጾች ይገለጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባህልን፦ የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት፣ …። በማለት ሲተረጉመው። የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በበኩሉ ባህል፦ ልማድ፣ ደንብ ሲል ይፈታዋል።

ባህላዊ ወረት (cultural capital) የሚለው ሀረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የሥነ ህብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ። ባህላዊ ወረት በማህበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ እውቀትን፣ ፀባይና ክህሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው። ባህላዊ ንብረት ወይም ወረት በግለሰብ፣ በማህበረሰብ ከፍ ሲልም በህዝብ በሀገር ይሰላል። የበለፀገ ባህላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባህላዊ ንብረት ያለው ማህበረሰብ ህዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል።

ባህል ማለትም የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት፣ ወዘተ. በሂደት በእውቀትና በክህሎት እየበለፀገ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ባህል በእውቀት፣ በክህሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማህበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የእለት ተእለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል። ባህላዊ ንብረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ንብረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ እርቅን፣ መነጋገርን፣ መቀባበልን፣ መከባበርን፣ መተባበርን፣ አንድነትን፣ ወዘተ. እውን ማድረግ ካልቻል እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል።

ሀገርን ህዝብን ከግጭት፣ ከቀውስ፣ ከመፈናቀል፣ ከመጠራጠር፣ ከጥላቻ፣ ከበቀል፣ ወዘተ. መታደግ አልቻለማ። እስኪ ለአንድ አፍታ ባህሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባህላዊ ንብረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው። ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ስራ

ላይ ውለዋል !? አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባህላዊ ንብረቶቻችንን እንደ ጦር እቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት፣ መመላለስ ለምን ተሳነን? መልሱ ቀላል ነው።

ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጂ አንኖራቸውም። በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም። በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንሯሯጣለን እንጂ አንኖራቸውም። በሥርዓተ ትምህርታችን አካተን ትውልድን ለማነጽ አላዋልናቸውም። ለብሔራዊ መግባባት፣ እርቅ፣ አንድነትና ሰላም ካላቸው ፋይዳ ይልቅ ስለሚስቡት ጎብኝና ቱሪስት እንጨነቃለን። ወደ ተራ ሸቀጥ እናወርዳቸዋለን። ይህ የተንሸዋረር እይታ ሊስተካከል ይገባል።

“ባለንጀራህን፣ ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ ”የሚሉ አብርሃማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን!? በአንድ አምላክ እያመን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን? መልሱን ለማግኘት ሚስጥሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም። መልሱ ቀላል ነው። እሱም ባህላዊ ንብረቶቻችንን በካዝና ቆልፈን አስቀመጥን እንጂ ስራ ላይ ስላላዋልናቸው (ኢንቨስት) ስላላደረግናቸው ነው። ሀገራዊ ሰላምና አንድነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከካዝና አውጥቶ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ በፍጥነት ማፍሰስ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል።

በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ባህል ከተፈጥሮ፣ ከሰውና ከአካላዊ፣ ቁስ አካላዊ (physical) ቀጥሎ 4ኛው ንብረት ሆኖ መጠናት፣ መተንተን ከጀመረ ከራርሟል። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሀገር እድገትና ለዘላቂ ሰላም አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሰላም በሌለበት ኢኮኖሚያዊ እድገትም ሆነ ብልፅግና ሊታሰብ አይችልምና። ለሀገር ግንባታ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ወሳኝ ሚና ከሚጫወተው ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ሥርዓት በተጨማሪ ለዘመናት እንደ ህዝብ፣ እንደ ሀገር አጋምዶ ያቆየን ባህላዊ ንብረታችን ነው።

ሁነቱን፣ ክዋኔውን፣ መንፈሱን ጠብቆ ተንከባክቦና አልምቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ፣ ማስቀጠል፣ ማክበርና ማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነትም አደራም ነው። ሆኖም የመጨረሻ ግብ ሆኖ ግን ሊወሰድ አይገባም። ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል። አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ፣ የሚዋጅና የሚቤዥ መሆን አለበት።

ዘረኝነትን፣ ጥላቻን፣ ቂም በቀልን፣ ደባን፣ መከፋፈልን፣ ወዘተ. መቤዥ፣ መዋጀት አለበት። ባህላዊ ንብረታችንን ይበልጥ በማጎልበት፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን፣ ለነገ ተስፋችን፣ ለእርቅ፣ ለሰላም፣ ለአንድነት፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና፣ ለመደመር ወዘተ. ልናውለው ይገባል። ስኬቶቻችንን የምናወድስበት፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አበክረን ማሰብ ያስፈልጋል።

የፍቅር፣ የእርቅ፣ የሰላም፣ የአብሮነት፣ የማካፈል፣ የመተባበር፣ የመተጋገዝ፣ የመረዳዳት፣ የምስጋና፣ ወዘተ. ባህሎች፣ ልማዶች፣ እምነቶች፣ ሃይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ንብረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን፣ ፍቅር ከጎደለን፣ እርቅ ከገፋን፣ ሰላም ከራቀን፣ አብሮነትን በቀዬአዊት ከተካን፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን፣ ወዘተ . ምኑን ሙሉኡ ሆነው?።

ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው? በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሂሳብ እናወራርድ።

ፍቼ ጨምበለላ፣ ቡሔ፣ ሻደይ፣ አሸንዳ፣ ሶለል አይነ ዋሬ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ መስቀላዮ፣ አጋመ፣ ጊፋታ፣ ኢ ሬቻን፣ ጋሮ፣ ቺሜሪ፣ ወዘተ. በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች የሚከበሩ ሃይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን፣ ፍቅርን፣ ነፃነትን፣ አብሮነትን፣ ምስጋናን፣ እርቅን፣ ይቅርታን፣ ወዘተ. የሚያውጁ፣ የሚለፍፉ ናቸው። ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየአመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም። አንለማመዳቸውም።

ከገጠሙን ቀውሶች፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፊ እንጥፍጣፊ በባህላዊ ንብረቶቻችን ነው። በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት ቀን ከሌት እንደ ተሰብከው ልዩነት፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል። ተጨራርሰናል። ለዚህ ነው መዳኛችን፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ንብረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው።

ባህላዊ ንብረታችን ለበጎ ዓላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል። ቁጣ አብራጁ ይህ የጋሞ አባቶች ልመና (ጋሞ ወጋ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ንብረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው።

ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን ለማነፅ፣ ለመገንባት ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ አይነት የሽምግልና፣ የእርቅ ባህላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መስራት ይጠበቅብናል። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል ፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባህላዊ ንብረቶቻችን ጥንስስ ፣ ወረት የማይተካ ሚና አላቸው። ትውልድ የተለያዩ ባህላዊ ንብረቶች ባለፀጋ ስለሆነ የየራሱን መዋጮ ማበርከትና ወደ ስራ መግባት ይጠበቅበታል።

በየአካባቢያችን፣ በየቀዬአችን የምናንፀው፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል።

ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ። አይደለም ዘውጌአዊ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ፣ የሚመኝ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል። ለዚህም ትውልዱ ዛሬ ላይ እንደ ትውልድ ተግዳሮት የሆኑበትንና ዋጋ እያስከፈሉት ያሉትን እውነታዎች በሰከነ መንፈስ፤ በሃላፊነት ሊያጤናቸው ይገባል።

ፈጣሪ በአዲሱ ዓመት ሀገራችንን ሰላም ያርግልን !!!

አሜን ።

 ቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን     ጳጉሜን  5 ቀን  2015 ዓ.ም

Recommended For You