ከደማቁ የምሽት ገበያ መሀል ሁሌም ከነፈገግታው ይታያል። ለእሱ ሳቅ ጨዋታ የዘወትር መለያው ነው። ያገኛቸውን ሁሉ እየቀለደ ያሳስቃል። እያጫወተ በቀልድ ከሚቀርባቸው አብዛኞቹ የእሱ ደንበኞች ሊሆኑ አይዘገዩም። ጨዋታውን ብለው ሲጠጉት የእጆቹን ዕቃ ይሰጣቸዋል። አይተው ዝም አይሉም። ይጠይቁታል። ጥራት ደረጃውን እየጠቀሰ፣ ተፈላጊነቱን እያብራራ ዋጋውን ይነግራቸዋል።
አወል ኑር ሰይድ የመንገድ ላይ ነጋዴ ነው። ጥቅም ላይ የዋሉ ጫማዎችን እያመጣ አትርፎ ይሸጣል። እሱን የሚሉ ደንበኞቹ ፈልገው አያጡትም። ከግርግር ትርምሱ መሀል በድምጹ ነጥለው ያውቁታል። ከአስፓልቱ ጠርዝ በወጉ የሚደረድራቸውን ጫማዎች ሽተው በመጡ ቁጥር ደግሞ በሳቅ ጨዋታው ይዝናናሉ።
አወል ቀልድ ጨዋታ ከዓላማው አያዘናጋውም። እየሳቀ በዓይኖቹ ያማትራል። እየቀለደ ከሥራው ያተኩራል። ይህ ባህርይው ገበያ ለመሳብ፣ ከሰዎች ለመግባባት አግዞታል። ንግግሩ የሚማርካቸው ጫማውን ሳይጎበኙለት አያልፉም። እሱ ቢገዙትም ባይገዙትም ከጨዋታው አያጎድልም። ፈገግታ ባወዛው ፊቱ ቀልዱን ጣል ያደርጋል። ደንበኞቹ ባህርይውን አይጠሉትም። ፈገግ እንዳሉ እጃቸውን ሰደው የሻቱትን ጫማ ይመርጣሉ።
ከአወል የሥራ ቦታ በስተግራ የልብስ ነጋዴው አምባቸው መሳይ ከጎኑ ተቀምጦ ያመሻል። ከእነሱ አለፍ ብሎ ቲማቲም፣ ድንች ሙዝና አቮካዶ በጋሪ የሞሉ ወጣቶች ይደረደራሉ። እምብዛም ሳይርቅ አነስ ያለ የጉልት ሸቀጥ የያዙ ሴቶች ከሥፍራው አይጠፉም።
ሁሉም ከቀኑ ይልቅ ሥፍራውን በምሽት ይሹታል። ይህን መመረጣቸው ለደንበኞቻቸውን እንደልብ ለማግኘት ነው። ሲመሽ ጠያቂዎች ይበዛሉ፣ ሲመሽ፣ እግረኞች ይበረክታሉ። በዚህ ሰዓት የጎዳና ነጋዴዎቹ የጀሞን መንገድ ያጨናንቁታል። ከጫፍ እስከጫፍ በእነሱና በያዟቸው ዕቃዎች የሚዘጋው መስመር ሁሌም ለእግረኞች ፈተና ነው።
ማንም ደርሶ ‹‹አሳልፉኝ፣ ተጠጉልኝ›› ቢላቸው አይሰሙትም። ንፋስ አያሳልፍ በሚመስለው ርቀት ተጠጋግተው ማለፊያ መራመጃ ያሳጣሉ። አብዛኞቹ በዚህ ጉዳይ ግድ የሚሰጣቸው አይመስልም። ጥቂቶች ግን ደንጋጦች ናቸው። ከመንገደኛው እሰጥ እገባ አይገጥሙም። የዘረጉትን ሰብስበው በትህትና መንገድ ይለቃሉ።
በዚህ አጋጣሚ ደንቦች ከደረሱ እነሱን አለማየት ነው። በሰው የተሞላው መንገድ ትርምሱ ይወጣል። ዕቃዎቻቸውን የተሸከሙ፣ መደበቂያ ጥግ የሚፈልጉ በየቦታው ይሮጣሉ። ጉዳዩ ሲረጋጋ አፍታ አይቆይም። ኮሽታ የሚያስደነግጣቸው ነጋዴዎች ተመልሰው ቦታ ለመያዝ ይራኮታሉ። የያዙትን ለመዘርጋት ሥፍራውን ለመሻመት ይጋፋሉ።
የአወል አጎራባች አምባቸው ከፊት ከኋላው በሌሎች ነጋዴዎች የታጀበ ነው። አብዛኞቹ የሚይዙት ዕቃ ይለያያል። የልጅ የአዋቂ ልብሶች፣ የቤት ዕቃዎች፣ የመገልገያ ቁሳቁሶች የመብራት ሶኬቶችና ሌላም ዕቃዎቹን ለመሽጥ ከእያንዳንዱ ሰው የሚሰማው ጩኸት አንዳንዴ ናላ ያዞራል። ቀጭን፣ ወፍራም፣ ጎርናና ፣ ሰላላ፣ የታነቀ፣ የታመቀ ድምጽ በአንዴ ሲቀናጅ የራሱን ኃይል ይፈጥራል።
አብዛኞቹ ነጋዴዎች ይህን ሥፍራ ለመምረጥ የግል ምክንያት አላቸው። ገበያውን፣ ግርግሩን የሰውን ብዛት ይፈልጉታል። ጥቂት የማይባሉት የመኖሪያ ቤታቸው ከአካባቢው የራቀ ነው። ምሽቱን ተጋፍተው ከቦታው ለመቆም ከርቀት ይነሳሉ። ሥራቸውን ጨርሰው ተመልሰው ሲሄዱ የያዙትን ተሸክመው አይደለም።
ነጋዴዎቹ የሸጡትን ሸጠው ቀሪውን ለማኖር ማስቀመጫ ቦታ ይፈልጋሉ። ይህ ቦታ በአደራ የሚያሳድሩበት ብቻ አይደለም። ዕቃዎቻቸውን ባሳረፉ ቁጥር በቀን የሚሰላ ክፍያ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ቆጥረው አስልተው ይከፍላሉ። ይህ የአከራዮቹ መብት የአብዛኛው ነጋዴ ግዴታ ነው።
አምባቸው ተወልዶ ያደገው ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ነው። አዲስ አበባ የመጣው ከዛሬ አስራ ስምንት ዓመት በፊት ነበር። ከተማ ለመግባት ምክንያቱ ሌላ አይደለም የተሻለ ሕይወት ፍለጋ እንጂ። ቢያድግም ከተሜ ለመሆን አልዘገየም።
አይተው ከተጠጉት እሱም ከቀረባቸው ጋር ተወዳጅቶ መግባባትን ፈጠረ። ይህ አጋጣሚ እንጀራውን አሰፋለት። በውሎው ሰርቶ ከሚገባበት የቀን ሥራ ተገናኘ። ከሥራ በኋላ ከባልንጀሮቹ ተጋርቶ በተከራየው ጠባብ ክፍል ጎኑን ያሳርፋል።
አምባቸው ሰውነቱ የጠረቃ፣ አቅሙ የጎለበተ አይደለም። ሲደክም ውሎ ቤት ሲገባ በድካም ይናውዛል። ሌሊቱን በወጉ የማይጠግበው ዕንቅልፍም ሲነጋ በወፎቹ ድምጽ ይቋጫል። ቀጣዩ ቀን ሌላ ሥራ አክሎ ይቆየዋል። ግዴታውን አያጣውም። ጎንበስ ቀና ብሎ ትዕዛዙን ይፈጽማል።
እሱ ከባልንጀሮቹ በዕድሜ ለዓይን ቢያንስም ለሥራው አልሰነፈም። የታዘዘውን በወጉ እየከወነ፣ በጥንካሬ ቀናትን አለፈ። ውሎ አድሮ ከፍ ካለ ሥራ እየገባ ጉልበቱን ፈተሸ። ያዩት እንደገመቱት አልሆነም። አልወደቀም፣ አልተሰበረም። ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ በብርታቱ ጸንቶ ቀጠለ።
ዛሬ አምባቸው እንደትናንቱ አይደለም። ቤተሰቡን ቢናፍቅም በየሰበቡ ሆድ አይብሰውም። አሁን ልጅነቱ አልፏል። ከወጣትነቱ ዕድሜ ሲቆም ጥሩ የሚባል መተዳደሪያ ነበረው። ይህ ጊዜ ዓይኖቹ እንዲያማትሩ፣ አማራጮች እንዲፈልግ ዕድል ሰጠው። የቀን ሥራውን ትቶ ከሌላ መግባት ፈለገ። ያሰበውን አላጣም ።
አምባቸው ስለ ቀጣይ ሕይወቱ ጊዜ ወስዶ አሰበ። አሁን ዓመታትን ከገፋበት የቀን ሥራ የተሻለ መተዳደሪያ ይፈልጋል። ከአንድ ሆቴል የመስተንግዶ ሥራ ሲገኝለት ዓይኑን አላሸም። በደስታ ወደ ሙያው ገባ። ቀልጣፋነቱ፣ ከሰው መግባባቱ አግዞት ሁሉን ተላመደ። ‹‹አቤት ! ወዴት›› ን አወቀ።
አምባቸውና የሆቴሉ ሥራ ከልብ ተዋደዋል። ከደሞዙ በላይ የሚያገኘው ጉርሻ ኑሮውን እየደገፈው ነው። ከነበረበት ለቆ ወደ ሌላ ሲዛወር ልምድን ከችሎታ ጨምሮ ነበር። መስተንግዶው መተዳደሪያው ሲሆን አርቆ ማሰብ ያዘ። የራሱን ቤት በአቅሙ ተከራይቶ መኖር ሲጀምር ብቸኝነቱን የምታስረሳ የትዳር አጋር አገኘ።
አሁን አምባቸው እንደ ቀድሞ ስለራሱ ብቻ የሚያድር አልሆነም። ውሎ ሲገባ ቤት ጎጆውን ያስባል። ስለ ነገ ብዙ ዓላማ ያለው ወጣት ከአንድ ሁለት ሲሆን ዕቅዱ በረከተ። ገንዘብ መያዝ ቁጠባን መልመድ አወቀ። እንዲያም ሆኖ ኑሮ በዋዛ አልሞላም። አንዱ ሲሳካ ከሌላው እየጎደለ ሕይወት እንደነገሩ ቀጠለ።
ጥንዶቹ በ ‹‹አንተ ትብስ፣ አንቺ ›› ያቆሙት ጎጆ አንድ ነፍስ አክሏል። ቤተሰቡም ከሁለት ሶስት ሆኗል። እማወራዋ የልጅ አሳዳጊ የቤት እመቤት ናት። ዘንድሮ ኑሮ እንደአምናው አይደለም። ለከርሞ ሕይወት በነበረበት አይቆምም።
አሁን የቤት ኪራዩ፣ የዕለት ወጪው፣ የቀለብና የሌላም ፍላጎት ማሻቀብ ይዟል። ይህ እውነት አምባቸውን በየቀኑ እያስጨነቀ ያስተክዘዋል። ሲሰራ ውሎ ይዞ የሚገባው ገንዘብ ዋጋ እያጣ ነው። የመስተንግዶ ሥራው ለዚህ ሁሉ ቀዳዳ ሊበቃው አይችልም። ውሎውን መቀየር ገቢውን ማሳደግ አለበት።
አምባቸው በየቀኑ ያስባል፣ አንዱን ቋጥሮ ሌላውን ይፈታል። አሁን ካለበት በተሻለ ቤቱን የሚመራበት ልጁን የሚያሳድግበት ገቢ ያሻዋል። እንደፈለገ ገብቶ የሚወጣበት፣ የራሱ አለቃ የሚሆንበትን ቀን ተመኘው። ‹‹አቤት! ወዴት›› የሚልበት የሆቴል ሥራ እየሰለቸው ነው።
አምባቸው እንደሱ ሮጠው ከሚያድሩ አቻዎቹ መከረ። ሁሉም በየራሳቸው ዓለም የሚባክኑ ናቸው። ከነዚህ መሀል የጥቂቶቹን ሥራ ልቡ ፈቀደው። የቦንዳ ልብስ ገዝቶ መሸጥ እንደሚያወጣ ሲያወሩ ሰምቷል። መኖሪያውን ወደ ኮልፌ ቀይሮ እሱን ሊሞከርው ቆረጠ። ዛሬ ከጎዳና ጥግ አቁሞ ከደንቦች የሚያሯሩጠውን የልብስ ሽያጭ።
ወደ አወል ኑር ተመልሻለሁ። የቦንዳ ጫማዎችን ወደሚሸጠው ሳቂታ ወጣት። ከሰሞኑ አወል ደስታ ፈገግታው ከገጽታው የለም። ፊቱ ገርጥቷል፣ ድምጹ ቀንሷል፣ እንደቀድሞው ደንበኞቹን በጨዋታ እያዋዛ አይደለም። የእጁን ጫማዎች ከፍ አድርጎ ‹‹ይቺ የአሜሪካ፣ ይሄ የጣልያን፣ ያኛው የሜክሲኮ›› ሲል አይጣራም። አወል ጥቂት ጫማዎችን ከወለል ዘርግቶ አላፊ አግዳሚውን በዝምታ ይቃኛል።
አሁን የቀድሞ ልማዱ ከእሱ የለም። ደንበኞችም ስለመኖሩ ያወቁ አይመስልም። ከዚህ በፊት እንዲህ ሆኖ አያውቅም። የሚገዙትን ጨምሮ ሳይገዙ በጥያቄ የሚያደክሙትን ሁሉ ያለመሰልቸት በፈገግታ ያስተናግዳል። በዚህ መሀል ብዙ ክፉ ገጠመኞችን አስተናግዷል። አንዳንዶቹ ብዙ የፈተኑት ኑሮውን ጭምር ያናጉበት ናቸው።
ከቀናት በአንዱ አንድ ተለቅ ያለ ሰው ቀረብ ብሎ ጫማዎች እንደሚፈልግ ሹክ ይለዋል። ግርማ ሞገሱን ያስተዋለው አወል ደንገጥ ብሎ ፍላጎቱን ሊሞላለት ፈቃደኛ ይሆናል። አጋጣሚ ሆኖ ምርጥ የሚባሉ ጫማዎችን ያስገባበት ጊዜ ነበር። ሰውዬው ተረጋግቶ እየቃኘ ዓይኖቹ ያረፈባቸውን ጫማዎች መምረጥ ይጀምራል።
ሰውዬው አንድ ሁለት እያለ ከግማሽ ማዳበሪያ የማያንስ ጫማዎች ይሰበስባል። ይህን ያስተዋለው አወል የምሽቱን ገበያ እያሰበ ልቡ መደለቅ ይጀምራል። ለእያንዳንዱ ሂሳብ አውጥቶ ሲያስበው ደግሞ ደስታው በእጥፍ ጨመረ። በአንድ ቀን ይህን ቁጥር የሚያህል ጫማ ሸጦ አያውቅም። ደስ አለው። ደጋግሞ ፈጣሪውን አመሰገነና ወደ ገዢው አተኮረ።
ሰውየው ጫማዎቹን የሚገዛው ለባለቤቱ እንደሆነ ነግሮታል። ለዛሬ ግን በቂ ገንዘብ ኪሱ የለም። ቢሆንም ለሚስቱ ለማስመረጥ አንድ አንድ እግሩን ነጥሎ ይወስዳል። አወል የሞቀው ልቡ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሲቸለስ ተሰማው። በዓይኑ ሲዞር የቆየው ገንዘብ ወዲያውኑ ሲተን ታየው። ‹‹እምቢኝ›› ማለት ግን አልቻለም። ነገ የተሻለ እንደሚሆን ያውቃል ። ይህ ሲገባው ጥቂት አንገራግሮ በይሁንታ ተስማማ።
ሁለቱም ጥንዶቹን ጫማዎች በአንድ እየነጠሉ ከማዳበሪያው ከተቱ። የዕለቱ ጫማዎች ከወትሮው የተለዩና ምርጥ የሚባሉ ናቸው። አሁን በአወልና በሰውዬው እጆች የአንድ አንድ እግር ጫማዎች ብቻ ቀርተዋል። ስምምነታቸው በቃል ታስሮም በቀጠሮ ተለያይተዋል ።
ሰውየው ለእማኝነት የሞባይሉን ቁጥር ሰጥቶታል። አወልም ለትክክለኛነቱ እዛው ደውሎ አረጋግጧል። አወል ሰውዬው ብሩን ይዞ ሲመለስ ቀሪዎቹን ጫማዎች ሲሰጠው እያሰበ የሚይዘውን ገንዘብ ያሰላል። እንዲህ በርከት ያለ ብር ሲገኝ በኑሮው ለውጥ ይኖረዋል። ያለክፍያ ጫማዎቹን መስጠቱ ትክክል መሆኑን አመነ።
ሰውየውና አወል የተቃጠሩበት ቀን ደረሰ። በተባለው ቀን አወል በአጠገቡ በሚያልፉ ሰዎች ላይ ዓይኑን ሲፈያፈጥ አመሸ። እንዳሰበው እሱን የሚመስል ሰው ብቅ አላለም። በቀጣዩ ቀን ተስፋ ሳይቆርጥ አፍጥጦ አመሸ። ጀርባውን የሚነካው፣ እጁን የሚጨብጠው ሰው እየናፈቀ ዓይኖቹን ተከለ። አንዳች ሳይፈጠር ገበያው ተበትኖ ወደቤቱ ተመለሰ። አወል ስለ ሰውየው ቢጨነቅ ወደ ስልኩ ደወለ። መልስ የለም። ጥሪውን ደጋገመው። አሁንም መልስ የለም።
በሌላ ጊዜ ስልኩን ያለማቋረጥ ሞከረ፣ ሞከረ፣ ሞከረ… ‹‹አቤት›› የሚለው ሳያገኝ ቀናት ተቆጠሩ። አወል እጁን በራሱ ጭኖ ደጋግሞ አሰበ። የጫማዎቹ ባለ አንዳንድ እግሮች በእጆቹ ላይ ይገኛሉ። ያለአቻቸው፣ ያለግጥማቸው ለእሱም ለሰውዬውም አይጠቅሙም።
ምሽት ደርሶ ለገበያ በተቀመጠ ቁጥር ሰውየውን እያሰበ ጫማዎቹን እያስታወሰ ይናደዳል፣ ይበሳጫል። ድፍን አንድ ዓመት ያስቆጠሩት የጥንድ አልባ ጫማዎች ሚስጥር እስካሁን አልገባውም። ይህን እያሰበ የውስጡን በውስጡ አምቆ ፊቱን በፈገግታ ሲያበራ ያመሻል። እስካሁን ከእሱ ያሉት ትርጉም የለሽ ጫማዎች የሕይወት ፈተናዎቹ ምልክቶች ሆነዋል። አልጣላቸውም፣ አይጥላቸውም።
ሰሞኑን ደግሞ አወል በሌላ ፈተና ተጠለፈ። ሲሸጥ አምሽቶ ጓዙን በክፍያ ከሚያሳድርበት የአደራ ቤት ጫማዎቹ ተሰረቁበት። 150 ጥንድ የቦንዳ ጫማዎች እየተመረጡ መወሰዳቸው ቢያንገበግብ፣ ቢያናድደው ከዝምታ ተዋዶ፣ ከሀዘን ተላምዶ ሰነበተ፣ በትካዜ አንገቱን ደፋ።
የአወልን ሳቅ ነጥቆ ለድብርት የዳረገው ይህ እውነታ ባህርይውን ቀይሮታል። እንደቀድሞው ድምጹ ጎልቶ ደንበኞችን አይስብም። እንደነገሩ ተጎልቶ በሚያመሽበት ጎዳና የደንቦች ኮቴ፣ የገበያተኞች ትርምስ አያስደንቀውም። አወል በሆነበት እየተናደደ፣ ባጋጠመው እየተገረመ የነገን መንጋት መናፈቅ ይዟል። ነገ በአዲስ ፀሐይ እስኪደምቅ ተስፋው አይነጥፍም።
የቦንዳ ልብስ ነጋዴው አምባቸው ልክ እንደ አወል ብዙ ገጥሞታል። ሥራውን የጀመረ ሰሞን ብዙ የተበላሹ፣ የነተቡ ልብሶች ገዝቶ ለኪሳራ ተዳርጓል። በጎዳና ቆሞ ሲሸጥ በውድ የገዛቸው ልብሶች በአጭበርባሪዎች ተወሰድውበታል። ድንገቴዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ሳያስበው ደርሰው ሙሉ ንብረቱን ነጥቀውታል።
ይህ ዓይነቱ እውነታ የሁለቱ ወጣቶች ታሪክ ብቻ አይደለም። በየቦታው በየጊዜው ይህን ሀቅ የሚጋሩ፣ በዚህ መንገድ የሚጓዙ አምሳያዎች እልፎች ናቸው። ‹‹ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል›› እንዲሉ የሕይወት መልኩ ቢለያይም ነገ ነግቶ ፀሐይ እስክትወጣ በሻካራማ፣ በእሾሃማው መንገድ መመላለስ ግድ ይላል። እንደ ሁለቱ ነፍሶች… አወልና አምባቸው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም