በቡና ላይ እሴት በመጨመር ለዓለም እያስተዋወቀ ያለው ዩኒዬን

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጳጉሜን ቀናትን በተለያዩ ስያሜዎች ማክበር እየተለመደ መጥቷል። ስያሜዎቹ መሠረት በማድረግ የሚካሄዱ ዝግጅቶችም ዜጎች በአንድነት፣ በሰላም፣ በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በመረዳዳትና በጠንካራ የሥራ ባህል መኖርን እንዲያጎለብቱና በአዲሱ ዓመት ብሩህ ተስፋ እንዲታያቸው ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩና ዕድል የሚሰጡ ተግባሮች የሚከናወንባቸው ናቸው። ዘንድሮም ከጳጉሜን ለኢትዮጵያ በሚል ከጳጉሜን አንድ እስከ ጳጉሜን ስድስት ያሉ ቀናት በተለያዩ ስያሜያዎች እየተከበሩ ይገኛሉ።

እነሆ ዛሬ ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹የአምራችነት ቀን›› ላይ እንገኛለን። በአምራችነት ቀን ደግሞ አምራቾችን በተለይም አርሶ አደሩን ማንሳትና ማስታወስ የግድ ነው። በዕለቱ የስኬት አምዳችንም የጠንካራ አርሶ አደሮች ስብስብ ከሆኑ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት መካከል አንዱ የሆነውን የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ልናነሳ ወደናል።

ዩኒዬኑ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በአምራችነት የዘለቀና የአምራችነት ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ከዓመት ዓመት ዕድገት ማስመዝገብ ችሏል። በ34 መሰረታዊ ማህበራትና በ22ሺህ በሚደርሱ አርሶ አደር አባላት የተመሰረተ ነው። ስምንት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ይዞ ነው የተነሳው።

ዩኒዬኑ በአምራችነቱ የታወቀና በገበያው ውስጥም ረጅም ጊዜን ያስቆጠረ ነው። በአሁኑ ወቅትም ዩኒዬኑ ቡናን አምርቶ ወደ ውጭ ገበያ እየላከ ይገኛል። በተለይም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ እሴት በመጨመር የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ በማስተዋወቅ የመሪነትን ሚና ይዟል።

አቶ ሰለሞን ታደለ የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን እህት ኩባንያ የሆነው የዋንኮ ቡና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት፤ ዩኒዬኑ የተመሰረተው በወቅቱ በቡና ገበያ ላይ የገጠመውን የገበያ ችግር ለመፍታት በሚል በ1991 ዓ.ም ነው። ዛሬ ላይ 407 ማህበራትና 557ሺህ አባል አርሶ አደሮችን ይዟል። ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዝገብም ችሏል።

በቡና ገበያ ላይ የነበረውን ችግር ለመፍታት ኩባንያው/ዋንኮ/ መቋቋሙን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ አርሶ አደሩ የራሱን ምርት በራሱ ካምፓኒ ወደ ገበያ ማቅረብ ቢችል የልፋቱን ውጤት ማግኘት ያስችለዋል የሚል ዕምነት በማሳደሩም ዩኒዩኑ ተቋቁሟል ይላሉ።

ዩኒዬኑን ለማቋቋም በወቅቱ ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ አሁን ላይ ግን የሀገሪቱ ቡና በዓለም ገበያ የበለጠ እንዲተዋወቅና ስም እንዲያገኝ ሆኗል። የተደራጀው በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫዎች በሚገኙ የኦሮሚያ አካባቢዎች በመሆኑም ሁሉም አይነት ቡና በኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ውስጥ እንዲገኝ እንዳደረገውም ያነሳሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁሉም ዓይነት ቡና በዩኒዬኑ ይገኛል። ይህ መሆኑ ደግሞ ዩኒዬኑን ከሌሎች ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል። ከዚህ በተጨማሪም በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ መዝለቅ እንዲችል እድል ሰጥቶታል። ምርቶቹንም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ባዛሮች ላይ በመሳተፍ 27 በሚደርሱ ዓለም አቀፍ ሀገራት ላይ ቡናውን መሸጥ እንዲችልም አድርጎታል። በየዓመቱም ወደ እነዚሁ ሀገራት ጥሬ ቡናው እየተላከ ሀገር የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስችሏል።

ዩኒዬኑ ቡና ከሚሸጥላቸው 27 የዓለም ሀገራት በተጨማሪ 96 የሚደርሱ ዓለም አቀፍ ቡና ገዢ የካምፓኒ ደንበኞች አሉት። ይሁንና ዩኒዬኑ በቡና ንግድ ላለፉት 25 ዓመታት እንደመሰማራቱ የአርሶ አደሩን ሕይወት በሚፈለገው ልክ መለወጥ አልተቻለም የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ለዚህም ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው። ዋናው ግን ቡናን በጥሬው ብቻ ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ነው። ስለዚህ ቡናን በጥሬው ብቻ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ እሴት ጨምሮ ማቅረብ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል። አርሶ አደሩን የተሻለ ተጠቃሚ ለማድረግም ወደ ተግባር መቀየሩን ያስረዳሉ።

የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒዬን ቡናን እሴት በመጨመር ወደ ገበያው ለመግባትና አርሶ አደሩንም የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ባደረገው ጥረት ዋንኮ ቡናን መስርቷል። ዋንኮ ቡናም ፋብሪካውን ገንብቶ ወደ ምርት ከገባ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። በአሁኑ ወቅት የዋንኮ ቡና ምርት በስፋት ወደ ገበያው እየገባ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ገላን ከተማ በሚገኘው ግዙፍ ፋብሪካ ውስጥ ጥሬ ቡናውን ለውጭ ገበያ ከማዘጋጀት ባለፈ ቡናውን ቆልቶ የሚፈጭ ዘመናዊ ማሽንም በዚሁ ፋብሪካ ይገኛል።

ዩኒዬኑ የቡናን ዱካ በመከተል ፈረንጆቹ የሚፈልጉትን የቡናን አመጣጥ ታሪክ ለማወቅና ለማሳወቅ ያመቸው ዘንድ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሶስት ትላልቅ ቡና ማበጠሪያና ደረጃ መስጫ ፋብሪካዎችን ገንብቷል። ፋብሪካዎቹ የሚገኙት ቃሊቲ፣ ድሬዳዋና ገላን ከተማ ሲሆን፤ ገላን ከተማ ላይ የሚገኘው የጥሬ ቡና ማበጠሪያ ፋብሪካ አጠቃላይ 30ሺህ ካሬ ሜትር ስፋት ቦታ ላይ አርፏል። እዚህ ውስጥ ደግሞ 1800 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ቡናን እሴት ጨምሮ ተቆልቶና ተፈጭቶ ይዘጋጃል ነው ያሉት።

እሳቸው እንዳሉት፤ በምዕራብ በኩል የጅማ፣ የኢሉባቦርና የወለጋ ቡና ቃሊቲ በሚገኘው ፋብሪካ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ ከጉጂ፣ ከአርሲና ከባሌ የሚመጣውን ቡና ደግሞ ገላን በሚገኘው ፋብሪካ ይዘጋጃል። የሀረርን ቡናም እንዲሁ ድሬዳዋ ላይ በሚገኘው ፋብሪካ ተዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ይሆናል። ይህም ዩኒዬኑን በዓለም ገበያ ልዩና ተመራጭ አድርጎታል።

የውጭ ገዢዎች የቡናውን ታሪክና ቀጣይነት የሚፈልጉት በመሆኑ ትክክለኛና ያልተበረዘውን ቡና ከዩኒዬኑ ያገኛሉ። ለዚህም የተለያዩ ሰርተፊኬቶችን እና ዕውቅናዎችን ማግኘት መቻሉን ያስረዳሉ። ከቡናው ዋጋ በተጨማሪም ለዕውቅናው የሚያገኙት ተጫማሪ ገቢ ስለመኖሩም ይናገራሉ።

በአሁን ወቅት ዩኒዬኑ ቡናን እሴት ጨምሮ ወደ ገበያው ለማስገባት ባደረገው ጥረት ‹‹ዋንኮ ቡና›› በሚል የራሱን ብራንድ ወይም መለያ ይዞ ወደ ገበያው በመግባት ቡናውን በሁለት አይነት መንገድ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ እያደረገ ይገኛል። የተቆላ እና የተፈጨ ቡና በተለያየ መጠን ለተጠቃሚው እየደረሰ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ የተቆላው ቡና በግማሽ፣ በአንድና በሁለት ኪሎ ታሽጎ የሚቀርብ ሲሆን፤ ተቆልቶ የተፈጨ ቡና ደግሞ በሩብ፣ በግማሽና በአንድ ኪሎ ተዘጋጅቶ ለገበያ ይቀርባል ብለዋል።

የዋንኮ ቡና ፋብሪካ ከ15 እስከ 20 ደቂቃ በሚፈጅ ጊዜ ውስጥ በአንድ ጊዜ 120 ኪሎ ግራም ቡና መቁላት የሚችል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ መፍጨትና ማሸጉ ብዙ ጊዜ የማይወስድ ነው። ለዚህ ደግሞ ፋብሪካው የአውሮፓን ደረጃ ያሟላና አሁን ያለውን የቡና መቁላት ቴክኖሎጂ በሙሉ የሚጠቀም መሆኑ አግዞታል። እናም አሁን ቡናውን ማንም ቢቆላው ከቴክኖሎጂው ውጭ አይሆንም ነው ያሉት።

‹‹ዩኒዬኑ ቡናን በስኒ ለመሸጥ ሲነሳ ዓላማው ትክክለኛውን የቡና ጣዕም ለዓለም ማስተዋወቅና በተለይም ፈጣሪ ለኢትዮጵያ አድልቶ የሰጠውን ጸጋ ሰው እንዲረዳ ለማስቻል ነው›› የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ አሁን ላይ ትክክለኛ የቡናን ጣዕም ማጣጣም አስቸጋሪ እየሆነ ስለመምጣቱ አንስተው፤ ለዚህም መፍትሔ ይሆን ዘንድ የዋንኮ ቡናን የመጀመሪያውን ካፌ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ መክፈት እንደቻሉ ያስረዳሉ። ዋንኮ ቡና በአየር መንገድ ውስጥ ሁለት ቦታዎች ማለትም በውጭ ሀገር ተጓዦች ተርሚናል እና በሀገር ውስጥ ተጓዦች ተርሚናል ተከፍቶ አገልግሎት እየሰጠም እንደሆነ ይናገራሉ።

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጨማሪም ዋንኮ ቡና በከተማ ውስጥ ሁለት ካፌዎችን መክፈት የተቻለ ሲሆን፤ ወደፊት የጥራት ደረጃቸውን ከፍ በማድረግ ካፌዎቹን ማስፋፋት ለሚፈልጉ ሌሎች ደንበኞች ስሙን የመሸጥ ዕቅድ እንዳለው የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፤ ዩኒዬኑ ከፍተኛ እውቀት ያለው ቡና አፍልቶ በመሸጥ ሳይሆን ቡናን ማምረት ላይ በመሆኑ ከዚህ ሥራው ይወጣል። አሁን እየሠራ ያለው ተግባር የማስተዋወቁን ኃላፊነት ለመወጣት ነው። ያም ቢሆን ትልቅ ውጤት ያገኙበት መሆኑን ያስረዳሉ።

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን ያህል ሰው በአየር መንገድ ውስጥ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ዋንኮ ቡናን የማጣጣም ዕድል እንዳገኙ የሚያነሱት አቶ ሰለሞን፤ አሁን ላይ ሰፊ ቁጥር ያላቸው የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ደንበኞችን ማግኘትና ገበያውን ማስፋፋት እንደቻሉ ይገልጻሉ። የውጤታማነት መገለጫቸውም በ2015 ዓ.ም ብቻ መቶ 12ሺህ ኪሎ የተቆላና የተፈጨ ቡና ለገበያ በማቅረብ 123 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻላቸው መሆኑን በማስረጃነት ይጠቅሳሉ። ይህ እንደ ጀማሪ የሚያበረታታ ውጤት ቢሆንም በቀጣይ ሀገር ውስጥ የተጀመረውን ሥራ በሌሎች ሀገራትም ዋንኮ ቡና በስፋት እንዲቀርብ የሚሠራ ይሆናልም ነው ያሉት።

ዩኒዬኑ የሚያመርተው ቡና 30በመቶ ያህሉ የአሜሪካ ገበያ ውስጥ የሚገባ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ 20 በመቶ ደግሞ አውሮፓ ገበያ ውስጥ የሚሸጥ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ቀሪው በአረብ ሀገራትና አሁን ደግሞ ቻይና እና ኮሪያ እንዲሁም ጃፓን ገበያ ውስጥ እየገቡ የሚሸጡት እንደሆነ ያብራራሉ። ከእነዚህ መካከል ትልቁ ገዢ ስታር ባግስ ሲሆን፤ በዓመት እስከ መቶ ኮንቲነር ቡና ከዩኒዬኑ በመግዛት ይታወቃልም ይላሉ።

ሮያል ኮፊ ትልቁና የረጅም ጊዜ ታማኝ ደንበኞች መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ ዩኒዬኑ እስካሁን ባለው የጥሬ ቡና ሽያጭ የጠራ ችግር ገጥሞት እንደማያውቅና ከረጅም ጊዜ ደንበኞቹ የደረሰው ቅሬታ አለመኖሩን ያስረዳሉ። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የቡና ምርት በመጠን እየቀነሰ የመጣ ቢሆንም በ2015 በጀት ዓመት ብቻ 250 ኮንቴነር ጥሬ ቡና ወደ ውጭ በመላክ ከ19 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማምጣት እንደቻሉም ይናገራሉ።

የቡና ዋጋ በዓለም ገበያ ተለዋዋጭ ቢሆንም ዩኒዬኑ ቡናውን በከፍተኛ ጥራት አዘጋጅቶ በትልቁ ዋጋ ይወዳደራል። ይሁንና ከውጭ ገበያ የሚገኘውን ትርፍ መጠነኛ በማድረግ ምርቶቹን በሰርተፊኬት እንዲሸጡ እያደረገ ተለዋዋጭ የሆነውን ገበያ መቋቋም እንደተቻለ አቶ ሰለሞን ጠቅሰው፤ በአሁን ወቅትም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በተወሰነ ትርፍ ማስገባት መጀመራቸውን ያስረዳሉ። በተለይም የማህበሩ አባላትን ሊጠቅሙ የሚችሉ እንደ ደብተር፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ምርቶችን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ በማቅረብ አባላቱንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ማገዝ ተችሏልም ይላሉ።

ቡናን በጥሬው ወደ ውጭ ገበያ መላክ ቀላል ቢሆንም እሴት ጨምሮ ቆልቶና ፈጭቶ መላክ ግን ፈታኝና አስቸጋሪ ነው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ያም ቢሆን ግን መጀመር እንዳለበት በማመን በብዙ ውጣ ውረድም ቢሆን ዋንኮ ቡና ሥራውን መጀመሩን ያስረዳሉ። በቅርቡም አሜሪካን ሀገር አንድ ሺህ ኪሎ ግራም የተቆላ ቡና ልከው ቡናው በእጅጉ ስለመወደዱ መስማታቸውን ነው የገለጹት። ይሁንና የተቆላ ቡናን በሚፈለገው ልክ ወደ ውጭ ገበያ ለማስገባት ብዙ እንቅፋቶች አሉ። እነሱን ለማለፍ ደግሞ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል። ለአብነትም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ቡናውን ወስደው እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ ካፌ ያላቸውም በካፌያቸውና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም ቡናው ገበያ ውስጥ እንዲገባ ማስቻል የሚሉት ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ያነሳሉ።

እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ ቡናው እሴት ተጨምሮበት ሲሸጥ የሚያስገኘው ገቢ ከፍተኛ ነው። ከዚህም ባለፈ የሚፈጥረው የሥራ ዕድል በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ለዚህም መንግሥትን ጨምሮ ዕድሉ ያለው እያንዳንዱ ዜጋ በተለይም የአርሶ አደር ጉዳይ ያገባኛል የሚልና በየደረጃው የሚገኝ ሁሉ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

ዩኒዬኑ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ከ300 በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ሠርቶ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ችሏል። ከእነዚህ መካከልም ትምህርት ቤቶች፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃና የገጠር መንገዶች ይገኙበታል። ለማህበረሰቡ አገልግሎት የሚውሉ ተግባራትንም በየዓመቱ በዕቅድ ይዞ በየአካባቢው የተለያዩ ሥራዎችን ያከናውናልም ነው ያሉት አቶ ሰለሞን።

በመጨረሻም አዲስ ዓመት ሲመጣ መልካም ምኞት መመኘት የተለመደ ነውና እኛም ከሁሉ አስቀድመን ለሀገራችን ሰላምን፤ ለዜጎች ፍቅርና አንድነትን፤ ስኬትና ብልጽግናን እየተመኘን አበቃን።

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You