አምርቱ ፤ አትርፉ ፤ አትዝረፉ !

“ጳጉሜን ለኢትዮጵያi”፤

13ኛዋ ጭማሪ ንዑስ ወራችን “ጳጉሚት” በጣት በሚቆጠሩ ዕለታቷ “ልዩ ልዩ” መታሰቢያዎች እየተሰየመላቸው በድምቀትና በልዩ ትኩረት መዘከር የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ ግን በሀገሪቱ የሚገኙ የክርስትና እምነት ቤተ እምነቶችና ምዕመናን የጳጉሚትን ቀናት በልዩ መንፈሳዊ ዝክርና እምነታቸው በሚፈቅድላቸው ቀኖናና ዶግማ መሠረት በጾም፣ በጸሎትና በመንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች ለዘመናት ሲያስታወሱ መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡

የ2015 ዓ.ምን እና የ2016ን ሂያጅና “አዲሱን” ዓመታት በማሰነባበት እርሷም ጭምር ፋይሏን የምትዘጋው የዘንድሮዋ “ጳጉሚት” ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በተለየ ሁኔታ መዘከሯን አስታውሰን መንደርደሩ ተገቢ ይመስለናል፡፡ እንዴታውን በአጭሩ አብራርተን ወደ ዋናው ሃሳባችን እናቀናለን፡፡ በመንግሥት በኩል የተወሰኑት ስድስቱ የዘንድሮ የጳጉሜን ልጆች እያንዳንዳቸው ሳቢ መልዕክት ተቀርጾላቸው መተግበሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የክርስትናንና የእስልምናን እምነቶች የሚከተሉ ቤተ እምነቶች (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት፣ የኢትዮጵያ እስልምና መጂሊስ፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ ኢየሱስ እና የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን ‹አድቬንቲስት›” በጋራ የንስሃ አዋጅ አውጀው ምእምናኖቻቸውን ለጾም፣ ለጸሎትና ለዱዓ ማዘዛቸው ይህቺን ተሰናባች “ጳጉሚት” ለየት ያደርጋታል፡፡

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ሁሉም ቤተ እምነቶች በተስማሙባቸው የጋራና የግል መርሃ ግብሮች መሠረት በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚናበብ አኳኋን ለምዕመናኖቻቸው የጾም፣ የጸሎትና የዱዓ አዋጅ ያወጁት አማንያኑ “ኢትዮጵያን በልባቸውና በመንፈሳቸው ተሸክመው” እየቃተቱ በእንባና በተሰበረ ልብ ወደ ፈጣሪ እንዲቀርቡ በማስተማር ጭምር ነው፡፡ የምዕመኑ ጸሎት፣ ምህላና ዱዓ ተሰምቶ ፈጣሪ ከመከራችንና ከዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ፈተናዎቻችን እንደሚታደገን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች ካውንስልም በአባልነት ባቀፋቸው በሺህዎች በሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያናት በኩል ተመሳሳይ መርሃ ግብር ነድፎ ምእመናን በምልጃ ጾምና ጸሎት በታከለበት ንስሃ የፈጣሪን ርህሩህ ፊት እንዲፈልጉ ጥሪ ቀርቦላቸው እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ይህ አስመስጋኝ መንፈሳዊ ተግባር ወደፊትም ተጠናክሮ ቢቀጥል የፈጣሪን ልብ የሚያራራና የመከራችንን ቀናት ሊያሳጥር እንደሚችል እናምናለን፡፡

ሀገራዊው የጳጉሜን ንቅናቄ፤

ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም በዕለተ ረቡዕ “የአገልጋይነት ቀን” ተብሎ በተሰየመ የመጀመሪያው ዕለት መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት በሰንደቅ ዓላማ ውጭ ውስጣቸው አሸብርቆና ተውቦ ቀኑን አክበረው ውለዋል፡፡ የየተቋማቱ ሠራተኞችም በልዩ ልዩ ባህላዊ ልብሶች አጊጠው፣ ቄጤማ ጎዝጉዘው፣ ቡና ተፈልቶ ሸብ እረብ እየተባለ ተገልጋዮች ሲስተናገዱ መመልከት ምነው የወራቱ ስያሜ በሙሉ ወደ ጳጉሜን በተለወጠ አሰኝቶ ያስመኛል፡፡ ችግሩ አንድ ቀን ብቻ መሆኑ ከፋ እንጂ፡፡

“የአገልጋይነት ቀን” በተከበረበት ጳጉሜ አንድ ቀን ይህ ጸሐፊ የራሱን ጉዳይ ለማስፈጸም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሁለት ክፍለ ከተሞችና በአንድ ከፍ ያለ መንግሥታዊ ተቋም ቢሮዎች ውስጥ ተገኝቶ ነበር፡፡ የዕለቱ የአከባበር ድምቀት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም በመንግሥታዊ ተቋሙ በራፍ ላይ የተሰየሙት የጥበቃ ባለሙያዎች “ዛሬ የአገልጋይነት ቀን ስለሆነ ሠራተኞች በሙሉ ስብሰባ ላይ ስለሆኑ አገልግሎት ማግኘት አይቻልም” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥተው ባለጉዳዮች እየተማረሩ ሲመለሱ ለማየት ተችሏል፡፡ በአንጻሩ በኮልፌ ቀራኒዮና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ቀኑን በእርግጥም “በአገልጋይነት መንፈስ” እያከበሩ ባለጉዳዮችን ሲያስተናግዱ መዋላቸውን ማድነቅ ተገቢ ይሆናል፡፡

የጳጉሜን ሽር ጉድ የቀናት አከባበር ወደፊት እንደ ባህል ሆኖ ሥር መስደዱ እንደማይቀር ተስፋ ማድረግ ቢቻልም አንዳንድ የተለመዱ፣ የተወላገዱና ያልታሰቡባቸው መፈክሮች ግን አስፈላጊነታቸውም ሆነ መልእክታቸው ግራ ማጋባቱ አልቀረም፡፡ ከላይ ለንዑስ ርዕስነት የተጠቀምኩበትን “ጳጉሜን ለኢትዮጵያ!” የሚለውን አንዱን መፈክር ብቻ ማስታወስ ይቻላል፡፡ መፈክሩና ጥቅሱ በጉልህ ተጽፎ የተሰቀለው በአንድ “አንቱ በተሰኘ ጎምቱ መንግሥታዊ ተቋም” በራፍ ላይ ነበር፡፡

ለመሆኑ ቀናት ለኢትዮጵያ የሚሰየሙት በአምስቱ ወይንም በስድስቱ የጳጉሜን ቀናት ብቻ ነውን? የተቀሩት 360 ቀናትስ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ አያስፈልጉምን? መፈክር አመንጭዎቹ ከዚህን መሰሉ የይድረስ ይድረስ “የግብር ይውጣ” ውሳኔ ደርሰው አላስፈላጊ ትርጉም የሚያስተላልፉ መልእክቶች እንዳይቀርጹ ለወደፊቱ ተገቢው ጥንቃቄ ቢደረግ ይበጅ ይመስለናል፡፡

በመንግሥት ደረጃ ለአራት አሠርት ዓመታትና ከዚያ በላይ አገልግሎት ለሰጡ ሠራተኞች ምሥጋና ቀርቧል የሚል ዜናም አንብበናል፡፡ ይህን መሰሉ ማበረታቻ ትርጉሙ ከፍ ያለና ፋይዳውም የላቀ ስለሆነ ሊበረታታ ይገባል፡፡ ነገር ግን በሚገባ ታስቦበት፣ ቀደም ብሎ ተዋውቆና እጩዎችም ታውቀው በግልጽ ምርጫ ቢመሰገኑ ውጤቱ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡ ዕድሜውን ካደለን የቀጣዩዋ ጳጉሚት ቀናት የተሻለ ሥራ እንደሚከወንባቸው እምነት አለን፡፡

“ዛሬ የአምራችነት ቀን ነው፡፡ እናስ?”

መቼም ለዕለት ጉርሱና ለወር ቀለቡ ሸመታ ወደ ባህላዊ ገበያዎች ጎራ ሳይል የማይውል ሰው ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግታል፡፡ መርካቶ የሚርመሰመሰው፣ ሾላ ገበያ የሚተረማመሰው፣ አማኑኤል መሳለሚያ የሚራኮተውን ወገን ብቻ በመመልከት እውነታነቱን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ ጸሐፊም እንደማናቸውም አባወራ ወደ እነዚህ ገበያዎች ሄዶ ከእማወራው ጋር ራሽን መሸመቱን የሚያዘወትረው ከባህላዊ ገበያ ጋር ቁርኝቱ የጠበቀ ስለሆነ ነው፡፡

ዳሩ “እምዬ መርካቶ” እየተባለ በታደገበት ሀገርና ባህል የኖረ ትውልድ ፈጥኖና ቀልጥፎ ከዘመናዊው የምግብ ግሮሰሪ ወይንም ከሱፐር ማርኬት ጋር ብቻ መቆራኘቱ እንኳን ለእኛ መሰሉ ዕድሜውን ላደለው ዜጋ ቀርቶ አዲስ ጉልቻ ለጎለቱት ወጣት ባለትዳሮችም ገና ጸድቆ ወደ ባህል ደረጃ ሊሸጋገር አልቻለም፡፡

ይህ ጸሐፊ የአምራችነት ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከበርበት በዚህ ዕለት እጅግ የተገረመበትን አንድ ጉዳይ ማስታወስ ወቅቱ የሚፈቅድ ይመስለናል፡፡ ቀደም ሲል በተጠቃቀሱትና መሰል ባህላዊ ገበያዎችና ጉልቶች ውስጥ አንድ ሸማች ነጭም ይሁን ቀይ ሽንኩርት እንደ አቅሙ ለመግዛት ሲፈልግ ለምርጫ የሚቀርቡለት የሀገር ውስጥ ነው ወይንስ የውጭው ወይንስ የሱዳኑ? የበርበሬ ዛላም እንዲሁ ከማረቆው የሀገራችን ምርት ጋር ተመሳስሎ የሚቀርበው “የቻይና” በመባል ከሚታወቀው መጤ ዓይነት ጋር ነው፡፡ ድፍን ምስርም እንዲሁ በኢምፖርትም ይሁን በኮንትሮባንድ ብቻ በፈለገው መልኩ ሀገር ውስጥ ሲቸበቸብ ማስተዋል በእጅጉ ከራስ ጋር ያስተዛዝባል፡፡

በጠቢባኑ የጋሞ ልጆች እጅ የሚመረቱት የባህል አልባሳት በቻይና አርቴፊሻል ምርት ከገበያ ሊወጡ ቋፍ ላይ በደረሱበት አንድ ወቅት “ላለመሞት መወዳደር ይበጃል” የሚል ምላሽ የሰጠን አንድ የሀገር ሹም ባሰብኩ ቁጥር ምን ያህል ከራስ ጋር ጠበኞች እንደሆንን ለማረጋገጥ አያስቸግርም፡፡

ዛሬ የአምራችነት ቀን በሚከበርበት የጳጉሚት አራተኛ ቀን ውይይቶችና ንግግሮች በሙሉ ተገቢው ትኩረት በተነፈጋቸው ለዕለት ጉሮሯችን ማስታገሻነት በሚውሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ቢሆን ይህ ጸሐፊ ፈቃዱ ነው፡፡ ያለመታደል ሆኖ አምራችነት ሲነሳ ቶሎ ወደ አእምሯችን ከተፍ የሚለው በትልልቅ ፋብሪካዎች የሚመረቱ ምርቶች እንጂ በውሎ አምሽቷችን ለሚያስፈልጉን መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች እጅግም “አባ ከና” የሚላቸው ያለ አይመስለንም፡፡

የአምራችነት ሕጋዊ ሠርቲፊኬት ግድግዳቸው ላይ ሰቅለው በተልከሰከሰ የማምረቻ ጓዳቸው ውስጥ ተሸሽገው ባዕድ ነገር እየደባለቁ ሕዝብን ለክፉ ደዌና ሞት የሚዳርጉት “የክፋት አምራቾች” ስለመገሰጻቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

“ጳጉሜን” የሚለው የባዕድ ቋንቋ ወደ ራሳችን ትርጉም ሲመለስ “ተጨማሪ” የሚል ፍቺ እንዳለው መዛግብተ ቃላት ይደነግጉልናል፡፡ የቃሉን ሥርወ መሠረት መተንተኑ ለጊዜው የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ስላይደለ እጅግም ጫን ብለን በመጥለቅ “የጳጉሚትን” የትመጣነት በስፋት አንዳስስም፡፡ ይልቅስ የሚበጀው “የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል” እንዲሉ በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ ከቀን ወደ ቀን “ጭማሪ” እያሳየ ናላችንን ባዞረው ብሔራዊ ችግራችን ላይ መፍትሔ እንዲፈለግ መወትወቱና መጠቋቆሙ ይበጅ ይመስለናል፡፡

የሀገራችን አምራች ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በርግጡ የሚመሩት በሥነ ምግባር መርህ ነው? ለምርታቸው ጥራትና ውበትስ ይጨነቃሉ? የአገልግሎታቸው ዋና ግብ የራስን ሕዝብ በቅንነት፣ በታማኝነትና በአክብሮት በማገልገል የህሊና እርካታ ለማግኘት ወይንስ የባህር ማዶውን “ዶላር” እያሰቡ ለራስ ሀገር ጓዳ ባዕድ መሆን?

“ጥያቄ አቅርቤያለሁ መልስ ብትሰጡኝ” ያለውን ድምጻዊ ከአሁን ቀደም አስታውሼ የዜማውን አንድ ስንኝም ስለ መዋሴ ማመስገኔን አስታውሳለሁ፡፡ ዛሬም ይህንኑ አባባል ልጥቀስና በዚህ “የአምራችነት ቀን” ላይ በዋነኛነት እንዲታወስ የተፈለገው ዋና መልእክት ወይንም ጉዳይ ምንድን ነው? ለመሆኑ ከቀን ወደ ቀን ለመሠረታዊ ህልውናችን ሳይቀር አደጋ የተጋረጠበት ኑሯችን እንዲፈወስ ምን መላ ተዘይዶለታል? መልስ ሰጭ ኖረም አልኖረ ጥያቄ ከመጠየቅ ግን አንቦዝንም፡፡

“ድንግሉና ጦም አደሩ” የሀገሬ ማሳ ተጠቀሙብኝ እያለ ሲወተወት፤ ሀገሬ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላ ከውጭ ሀገራት ሽንኩርት ሲገባ፣ ምስር ሲጋዝ፣ በርበሬ ገበያውን ሲያጥለቀልቅ፣ በሀገራችን የኢንዱስትሪ መንደሮች የሚመረቱ “ኳሊቲ” አልባሳትና ጨርቃ ጨርቆች” ዶላር እየጎመጁ ወደ ውጭ ሀገራቱ ሲጋዙ የትኛው መንግሥታዊ ክፍል ነው “ሚዛን” አስጠብቆ “ከምኞትና ከቅልውጥና” ደዌ የሚፈውሰን፡፡ እርግጥ ነው ሀገሬ ያለባት የውጭ ምንዛሬ ችግር እንደ አንድ ዜጋ ለማንም ሰው ይጠፋዋል ተብሎ አይገመትም፡፡

ግን ጨከን ብለን የአምራቹን ዘርፍ እንሞግት ብንል ከመስከረም እስከ ነሐሴ ሸቀጦች “ወደ ዶላር ገበያ” መክነፋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ምናለ በጳጉሚት አምስትና ስድስት ቀናት ብቻ እነዚያ ምርታቸውን ወደ ውጭ ኤክስፖርት የሚያደረጉ የባዕዳን ፋብሪካዎች ጥቂቱን ቆንጥረው ለሀገር ወስጥ ገበያ ቢያቀርቡ? መቼም ምኞት ስለማይከለከል ቢያንስ “የአምራችነት” ቀን ተብሎ በተሰየመው በዚህ ቀን “ሆድ ያባውን ብዕር ቢያወጣው” ልንገሰጽ አይገባም፡፡

ባዕዳን አምራቾቹ በዘመነ ኮቪድ ወደ ውጭ የሚልኩት ምርታቸው ሲቀርባቸው ያካካሱት ለእኛ ለምስኪን ዜጎች “የፊት መሸፈኛ ማስክን የመሳሰሉ” ምርቶችን አምርቶ በሀገር ውስጥ በማከፋፈል እንደነበር አንዘነጋም፡፡ ታዲያ አሁን “በዘመነ መረጋጋት” ምናለ ወደ ውጭ ከሚልኩት ምርቶች ጥቂቱን ቆንጥረው ለሀገር ውስጥ ገበያ ቢያቀርቡ?

የዚህ ጽሐፍ አቅራቢ በመላዋ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢንዱስትሪ መንደሮችን የአጀማመር ታሪክና እንቅስቃሴ ዶኪዩመንት ለማድረግ ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በተንቀሳቀሰበት አንድ ወቅት “ስለምን የተወሰነ ምርት እንኳን ለሀገር ውስጥ ገበያ አታቀርቡም?” ብሎ አምራቾቹን በመጠየቁ የደረሰበትን ግልምጫና ፌዝ ምን ጊዜም አይረሳውም፡፡ አንዳንድ አምራቾችም ይህንኑ ጥያቄ በመጠየቃቸው ስለ ሥራቸው መረጃ አንሰጥም እስከ ማለትም ደርሰው ነበር፡፡

ዛሬ የሚከበረው “የአምራችነት ቀን” ከትናንትናው “የበጎነት ቀን” ጋር ተጣምሮና ከጳጉሜን ሁለቱ “የመስዋዕትነት” ቀን ጋር ተሸርቦ ለመሠረታዊ የሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦታችን አምራቹና አከፋፋዩ ርህራሄ ማድረግ ቢቻል ትርፉ ብር ብቻ ሳይሆን አንድም የሕዝብ እርካታ ያስገኛል፣ አንድም የህሊና እረፍት ይሰጣል፣ አንድም በፈጣሪ ዘንድ የሚያስመሰገን ተግባር ሆኖ “በሰማያዊ መዝገብ ላይ ይመዘገባል”፡፡ አምርቱ! ግን በሕዝብ ድህነት አትሳለቁ፡፡ አትርፉ ነገር ግን አትዝረፉ፡፡ ይህ ነው የጳጉሜን አራቱ “የአምራችነት ቀን” የሕዝብ ምኞት፡፡ ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You