አምራችነት ለተሻለና ለላቀ ግብይት

በአንድ ሀገር ነገዎች ብሩህነት የአምራች ዘርፉ አስተዋጽኦ መተኪያ አይኖረውም ። በተለይም እንደኛ ባሉ ለማደግ እየተውረተረተሩ ላሉ ህዝቦች ምርትን በብዛትና በጥራት አምርቶ ወደ ገበያ /የሀገር ውስጥ ሆነ ዓለም አቀፍ ገበያ/ ይዞ መግባት ለሚያልሙት ነገዎቻቸው እውን መሆን ትልቁ አቅማቸው ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ በ1930ዎቹ ዓ.ም መጀመሪያ አንስቶ እንደ ሀገር የአምራቹን ዘርፍ ለማዘመን ፤ ምርቶችን በጥራት እና በብዛት ወደ ገበያ ለማቅረብና በዚህ ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ስራዎች ተሰርተዋል። በተለያዩ ምክንያቶች የተሰሩትን ያህል ውጤታማ መሆን ባይቻልም በዘርፉ የተመዘገቡና እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ግን በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም።

እንደ ሀገር ያሉንን የተፈጥሮ ጸጋዎች/ሀብቶች በኢንዱስትሪው ሆነ በግብርናው ዘርፍ ወደ ምርትነት ለመለወጥ ፤ ዘመናዊ ፋብሪካዎችን ከመገንባት አንስቶ ፤ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርጉንን ምርቶች /ሸቀጦች በጥራትና በብዛት ለማቅረብ የምናደርጋቸው ጥረቶች የውጤታማነት ደረጃ እንደየወቅቱ ይለያይ እንጂ ውጤታማነታቸው ግን ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም።

በተለይም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ምርታማነትን በጥራት እና በብዛት ለማሳደግ ሰፊ ጥረቶች ተደርገዋል። ፋብሪካዎች የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች ከማሟላት ጀምሮ የተጀመሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ከዛም ባለፈ ተጨማሪ ፓርኮች በጥራትና በብዛት ለመገንባት እየተሰራ ነው። ኢትዮጵያ ታምርት በሚል ሀገራዊ ንቅናቄ የተመዘገበው ስኬትም ይህንኑ ተሳቢ ያደረገ ነው።

በግብርናው ዘርፍ ቢሆን እንደ ሀገር ያለውን አቅም በመጠቀም በዘርፉ ያለውን ምርታማነት / አምራችነት ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎችና የተገኙ ስኬቶች ሀገርን እንደ ሀገር ቀና ማድረግ ያስቻሉ ናቸው። ከዚህ አንጻር በበጋ የመስኖ ስንዴ የተገኘው ውጤት ፣ ጤፍን በመስመር በመዝራት፣ በአትክልትና ፍራፍሪ ፣ ወዘተ እየተመዘገበ ያለው ውጤታማነት ተጠቃሽ ነው። በገበታ ለሀገር እና በሌማት ትሩፋት እየታየ ያለው ስኬትም የዚሁ እውነታ አካል ነው።

በቀጣይ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን አቅም በሚፈቅደው መጠን በማስተካከል ፣ በኢንደስትሪው ሆነ በግብርናው ዘርፍ በጥራትም በብዛትም ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችን ማምረትና ለገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ተስፋ ሰጪ ጅማሮዎች አሉ፤ ጅምሮቹ ቀጣይና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ የጋራ ሃላፊነት ነው ።

ከዚህ ጎን ለጎን ለዘርፉ እድገት ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ የመጣው በቀጣይም ዋነኛ ፈተና ይሆናል ተብሎ የሚታመነው ፤ ለሀገራዊ የገበያ ሥርዓቱ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ። በተለይም የገበያ ሥርዓቱን ሕጋዊና ፍትሀዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግ ካልተቻለ በአንድም ይሁን በሌላ ሀገራዊ ምርታማነትን መገዳደሩ የማይቀር ነው።

በርግጥ አምራችነት ከሁሉም በላይ ሰጥቶ መቀበል የገበያ ሂደት ነው። ሂደቱን ልክ የሚያደርገው ደግሞ በእውነት እና በሀቀኝነት ህዝብ ተኮር የግብይት ሥርዓት ሲታከልበት ነው። የግብይቱን ሂደት በተመለከተ በሀገራችን በተለይም በተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙ ቅሬታዎች ይነሳሉ። ከዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ እስከምርት መደበቅ ድረስ ያሉ ቅሬታዎች። ይሄ አይነቱ የግብይት ሥርዓት ገበያውን ከማናጋቱ ጎን ለጎን ብዙ ማህበራዊ ምስቅልቅሎችን የሚፈጥር ነው።

አምራችነት ሀቀኝነት ነው። ለፍተንና ተግተን ያመረትነውን ወይም ደግሞ ለትርፍ የገዛንውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ የማህበረሰቡን አቅም ባገናዘበ መልኩ ለገበያ ማቅረብ ተገቢ ከመሆኑም በተጨማሪ ሊያስመሰግነን የሚችል ነው። ባለው ነባራዊ የገበያ ሥርዓት ግን እንዲህ አይነት ህዝብ ተኮር የሰጥቶ መቀበል ግብይት እየተስተዋለ አይደለም። ለምን ብለን ስንጠየቅ ገበያው የህዝብ ፍላጎት፣ አቅምና ምቾት ያልተካተተበት በተወሰኑ ሰዎች ስግብግብ ፍላጎት ውስጥ በመውደቁና እየተዘወረ በመሆኑ ነው ።

አምራችነት ትስስር ነው። የምናመርተውን ምርት ወደገበያ ይዘን ስንመጣ ህዝብ ይገዛናል ብለን ነው። ሥርዓቱ የተሳሰረ ነው። ሸማችን ሳናከብርና ለህዝብ ፍላጎት ቅድሚያ ሳንሰጥ የምንፈጥረው የገበያ የበላይነት የለም። የተሻሉ ምርቶች ከተሻሉ ዋጋዎች ጋር ሁልጊዜም ተመራጮች ናቸው። እንዲህ አይነቱ በዳይም ተበዳይም የሌሉባቸው የገበያ ሥርዓቶች ያስፈልጉናል። ገበያውን ከማረጋጋት፣ ፍላጎትን አሟልተው፣ የኑሮ ጫናን ከመቀነስ አኳያ ሚናቸው የጎላ ነው።

ከምርት መላሸቅ እና ከዋጋ መናር ጋር በተያያዘ አሁን አሁን ጥራቱ እንዴት ነው? ሳይሆን ዋጋው ምን ያህል ነው? ወደማለት መጥተናል። ለጥራት ቅድሚያ የሚሰጠው ማህበረሰብ ወደ ብዛት ወርዷል። ከብዛት ጥራት ድሮ ቀረ። ይሄን የፈጠረው ከአምራችነት ጋር ተያይዞ የመጣው የገበያ ሁኔታ ነው። ራሳችንን ብቻ ለመጥቀም የምናደርገው የብልጠት ርምጃ ፍትህን ከማጓደል በላይ በድሃው ማህበረሰው ላይ ይሄ ነው የማይባል ጫናን እየፈጠረ ነው።

ግብይት ጠቅመን የምንጠቀምበት፣ ለህዝብ ፍላጎት ቅድሚያ የምንሰጥበት ነው። ራስ ወዳድነት ካልታከለበት ሁሉም ነገር በቂ ነው። ምርቶቻችን አጥግበውን ሌላን ማጥገብ የሚችሉ ናቸው። በፖለቲካም ይሁን በዓለም አቀፍ ቀውስ በተከፈተች ትንሽ መንገድ እንሄድና ሁሉንም ነገር ቅጥ ያጣ እናደርገዋለን። አምራችነት ዋጋ ባያጣና ራስ ተኮር ባይሆን ጠግበን ከማደር ባለፈ የኑሮ ውድነቱ መስመር ይይዝ ነበር።

እስካሁን ድረስ አመርቂ ምላሽ ያላገኙ ከአምራችነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ብዙ ቅሬታዎች አሉ። ነጋዴው በህዝብ ላይ ተመሳጥሮ በመሰል አፈ ቀላጤ ደላሎች በኩል ከአርሶ አደሩ ምርት ይረከባል። በርካሽ የተረከበውን ምርት ተጠያቂ እንዳይሆን ለሚያደርጉ አካላት እጅ መንሻ እየሰጠ በውድ ዋጋ ለማህበረሰቡ ያቀርባል። ሂደቱ ይሄን መሰል ነው።

ለሁሉም ነገር ተጠያቂው ገበያውን የሚመራው አካል እንደሆነ አጠያያቂ ባይሆንም በእንዲህ አይነት ብልሹ ግብይት ላይ የተሳተፉ አካላት ደግሞ ቀጣዩን እርከን ይይዛሉ።

እኚህን ሕገወጥ ነጋዴዎች በተጠያቂነት ለሌሎች አስተማሪ በሆነ መንገድ መቅጣት ገበያውን የሚያረጋጋ ፍቱን መፍትሄ ነው ።

ችግሩ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር.. ግን አያበቃም። ባልተገባ ዋጋ የተገዙ ምርቶች ለአገልግሎት ብቁ አለመሆናቸው ሌላው ጥያቄ ነው። ምርትን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀየጥ በማህበረሰቡ ላይ ጉዳት የሚፈጥሩ አካላት ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚነሱ የግብይቱ ሌላው ተግዳሮቶች ናቸው። ገል እየፈጩ ከበርበሬ ጋር በመደባለቅ፣ ሙዝና ቅቤን ቀላቅለው በመሸጥ እንዲሁም እንደእንጀራ ያሉ ምግቦች ላይ ባዕድ ነገሮችን በመቀየጥ ከሥነምግባር ያፈነገጡ ጥቂቶች አይደሉም።

በእንዲህ አይነቱ የግብይት ሥርዓት ስር በሰደደ ራስን የማፍቀር አባዜ ማህበረሰቡን ለሌላ ችግርና ወጪ የሚዳርጉ ነጋዴዎች የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል። እንዲህ አይነቱ ከሥነምግባር ያፈነገጠ አሰራር ከዝርፊያ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ኑሮ በእንቅርት ላይ ለሆነበት ህዝብ፣ ጥራት በሌለው ምርት፣ ባልተገባ ዋጋ፣ አማራጭ የላቸውም በማለት ብቻ ህዝብን መበዝበዝ ይቅር የማያሰኝ በደል ነው።

በዛው ልክ ከህዝብ ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ምርትና አቅርቦት በማቅረብ የህዝብን ርካታ ያስቀደሙም አልጠፉም። የበዓል ሰሞን እንደመሆኑ እንዲህ አይነት የምርት መደበቅና የአቅርቦት ውስንነት ከፍ ሲልም ለጤና ጠንቅ የሆኑ ምርቶች በስፋት የሚታዩበት ነው። ምርታማነት ሻጭ ሳይጎዳ ገዥም ሳይበደል በመተማመንና በጋራ እርካታ የሚደረግ ግብይት ነው።

እንደሀገራችን የምርት አቅርቦት የሚያንስና የሚያጥር ምርት የለም። ምርት እንዲያንስ የሚያደርገው ራስ ወዳድነትን የቀየጠው የገበያ ሁኔታ ነው። ብዙ የንግድ ተቋማት ኢፍትሀዊ በሆነ አሰራር ታሽገዋል። በእንዲህ አይነቱ ያልተገባ አሰራር ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችም ጥቂት አይደሉም። በአግባቡና በሥርዓት ከሆነ ጠቅመን መጠቀም የምንችልበት እድል ሰፊ ነው።

ሀገራችን ለምለም ሀገር ናት። መሬቶቿም ለምና ለምርት ምቹ የሆኑ ናቸው። ምንም እንኳን በባህላዊ መንገድ አምርተን የምናቀርብ ቢሆንም ካለን ሰፊ መሬትና የምርት ብዛት አንጻር ለተጠቃሚ የሚያንስ አይደለም። ምርታማነት በታመነና በሀቀኝነት ከህዝብ ለህዝብ የምናደርሰው ምርት ነው።

የዓለም ሥርዓት ሰጥቶ የመቀበል ሥርዓት ነው ታማኝ በሆንን ቁጥር ይበልጥ እየተገለገልን ነው የምንሄደው። ከህዝብ ደብቀን እና ህዝብ ዋሽተን ያከማቸንውም ሆነ ያተረፍነው ትርፍ አይጠቅመንም። ዋናውና ትልቁ የሰብዓዊነት ግዴታችን ባለን ነገር ህዝብን በታማኘነት ማገልገል ነው።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You