አምራችነትን ማሳደግ ሀገርን ማሳደግ ነው!

 አምራችነት የመኖር መሰረት፣ የዕድገት ምንጭ ነው። ለኢትዮጵያ ደግሞ ከምንም በላይ ወሳኝ ነው። የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት ሲባል ብቻ አይደለም አምራችነት ወሳኝ የሚሆነው። በአጠቃላይ በምጣኔ ሀብት የላቀ ደረጃ ለመድረስ፣ ከርዳታና መሰል ተግባሮች ጥገኝነት ፈጽሞ ለመላቀቅ፣ ለራስም ፣ ለብሄራዊ ኩራትም ጭምር ወሳኝ ነው። እንደ ዜጋ ቀና ብሎ ለመጓዝም በአምራችነት ላይ መስራቱ ለኢትዮጵያ እጅጉን ወሳኝ ነው።

ለዚህም ነው መንግሥት በሁሉም የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ላይ በትኩረት የሚሠራው። በግብርናውና አምራች ኢንዱስትሪው ዘርፎች ላይ በተጠናከረ መልኩ እየተሰራ ካለበት ሁኔታ መገንዘብ የሚቻለውም ይህንኑ ነው።

በግብርናው ዘርፍ በሚከናወኑ ተግባሮች ምርትና ምርታማነት በየጊዜው እየጨመረ ነው። ጨመረ የሚባለው ምርትና ምርታማነት ከዚህም በላይ እንዲጨምር ይጠበቃል፤ ምክንያቱ ደግሞ መጨመር የሚችልባቸው ምክንያቶች በርካታ በመሆናቸው ነው። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ፣ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን መተካት፣ ከምክንያቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

ሀገሪቱ የኢኮኖሚዋ መሰረት የሆነውን ግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራዕይ ሰንቃ እየሠራች ትገኛለች፤ ለዚህ ደግሞ ግብርናው ጠንክሮ ለኢንዱስትሪው መሠረት ከሚሆኑት መካከል አንዲሆን ይጠበቃል። ኢንዱስትሪው ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ፣ ግብዓት፣ ማሸነሪዎችንና የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶች መገንባትን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ሀገሪቱ ያላት አንዱ ዋና አቅም ግብርና እንደመሆኑ በግብርና አምራችነት ላይ በትኩረት መሥራት የግድ ይሆናል።

በዘርፉ እንዲሠራ የሚጠበቀውም ለዚህ በሚሆን መልኩ ነው። በመኸርና በበልግ ወቅት እርሻ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች፣ የበጋ ስንዴ መስኖ ልማቱ፣ ሜካናይዜሽንን ለማስፋፋት እንዲቻል እየተስፋፋ ያለው ኩታ ገጠም እርሻ፤ በሩዝ፣ በአቮካዶና በሌሎችም ልማቶች ወደፊት ለመራመድ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባሮችና የታዩ ለውጦች በግብርናው ዘርፍ ለአምራችነት የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታሉ። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የተገኙት ለውጦች ለእዚህ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

በመስኖ ስንዴ ልማቱ የሚሸፈነው ማሳ ብዛት፣ የሚገኘው ምርትም በየዓመቱ እየጨመረ ነው፤ ምርቱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 47 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል። ይህ ምርት ከመኸርና ከበልግ ምርት ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱን ዓመታዊ የስንዴ ምርት አሳድጎታል። በዚህም ስንዴ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ደረጃ ላይ ተደርሷል። የአምራችነት ጉዳይ ሲነሳ ግብርና መጠቀስ ያለበት በዘርፉ እየተከናወኑ ካሉ ግዙፍ ስራዎችና እየገተኙ ካሉት ውጤቶች በመነጨ ነው። የውጭ ምንዛሬ ሲገፈገፍበት የነበረው ስንዴ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆን ጀምሯል።

ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ራዕይ ተሰንቆ እየተሰራ መሆኑ ይታወቃል። የግሉ ዘርፍ በራሱ የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶችን እየገነባ ከሚያከናውናቸው የማምረት ሥራዎች በተጨማሪ ሀገሪቱ በዘርፉ የተያዘውን ራእይ ለማሳካት በተለይ ለውጭ ባለሀብቶች ሊውሉ የሚችሉ 13 ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከነሙሉ መሰረተ ልማታቸው ገንብታ ወደ ስራ አስገብታለች። ኢንዱስትሪዎቹ ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡም ይገኛሉ። ለብዙ ሺ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

የኢንዱስትሪ ልማቱ ግን በተለያዩ ፈተናዎች ሳቢያ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ አጋጥሟል። ኮቪድና ዓለም አቀፍ ጫና እንዲሁም ጦርነትና ግጭት፣ የኃይል አቅርቦት ውስንነት፣ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ በተከሰተ የግብዓት እጥረት ሲፈተን ቆይቷል። ከጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ በጦርነቱ ቀጣና አካባቢ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሥራ ያቆሙቡት ሁኔታም ታይቷል። ከማምረት አቅማቸው በታች እንዲያመርቱ የተገደዱበት ሁኔታም አለ።

መንግሥት እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ ሰርቷል፤ እየሰራም ነው። እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት በአምራች ዘርፉ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመተግበር ዘርፉ እንዲነቃቃ ሰርቷል። በዚህም ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ የተመለሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በቀጣይም በዘርፉ በርካታ ተግባሮችን በማከናወን ለውጦችን ለማምጣት ይሠራል። ሀገሪቱ ባሏት 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ 100 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባትም አቅዳለች። ይህ ደግሞ የግሉ ዘርፍ በራሱ ከሚገነባቸው የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማቶች በተጨማሪ የሚገነባ ነው።

በአሁኑ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ከሰባት በመቶ ያልበለጠ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህን አስተዋጽኦውን በቀጣይ 10 ዓመታት ወደ 17 ነጥብ ሁለት በመቶ ለማሳደግ ታቅዷል። አሁን ያለውን 50 በመቶ የኢንዱስትሪዎች የምርታማነት አቅም ወደ 85 በመቶ የማድረስ ዕቅድም ተይዟል።

የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ ወጪን ለማዳን፣ የግብርናውን ዘርፍ ምርቶች በግብአትነት በስፋት ለመጠቀም፣ ወዘተ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል። ለዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ዘርፉን የማስተዋወቅ፣ ማበረታቻ የመስጠት፣ የህግ ማዕቀፎችን የማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው።

ይህ ሁሉ መንግስት ለአምራች ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያመለክታል። አምራች ዘርፉም ይህን የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም በሚገባ ለመጠቀም፣ ያለውን ሀብት በዘርፉ በማዋል የዘርፉ እቅድና ራዕይ እንዲሳካ መስራት ይኖርበታል። አምራችነትን ማሳደግ ሀገርን ማሳደግ እንደመሆኑ የዛሬውን የአምራችነት ቀንንም የዘርፉ ለውጦች፣ ችግሮችና መፍትሄዎች የሚመላከቱበትና ለቀጣይ ስራ የሚመከርበት፣ ግብዓት የሚሰበሰብበት አርጎ መጠቀም ይገባል!

አዲስ ዘመን    ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You