በጎነት ለራስ ነው፣ መልሶ ይከፍላል !

 

የወሮች ሁሉ በኩር፣ የዘመን ካባ ቀዳማይት ጳጉሜ እንሆ ሦስተኛ ቀኗን ከስሞች ሁሉ ባማረው በበጎነት/በመልካምነት ተሰይማ ከተፍ ብላለች። በጎነት የሁሉም የሰው ልጅ የጋራ መጠሪያው ነው። ፈጣሪ በአርአያና በአምሳሉ የሰውን ልጅ ለመፍጠር ሲነሳ መጀመሪያ ላይ ታሳቢ ያደረገው በጎነትን ነበር። ይሄን እውነት አስመልክቶ በኤፌሶን መልዕክት ላይ ‹መልካሙን ሥራ እንድንሠራ በክርስቶስ እየሱስ ተፈጠርን› የሚል ጥቅስ እናገኛለን።

ሰውነት መነሻው በጎነት ነው። እንዴትም ብንኖር በጎነትን እስካልተላበስን ድረስ ሙሉነት አይጎበኘንም። ከሁሉም ትልቁ ፈጣሪ ወደሰው ልጅ ሕይወት የሚመጣው በጎነት በሚሉት የጽድቅ መንገድ ነው። ምን ያክል ጠቢብ፣ ምን ያክል የተሳካለት፣ ምን ያክል ጀግና እና ብርቱ እንደሆንን ከምናሳይበት መንገድ አንዱ የሌሎችን ጉድለት በመሙላት እንዲሁም ተስፋቸውን በማስቀጠል ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን እየተረዳዳንና እየተሳሰብን የመጣን ሕዝቦች ነን። በደቦና በማኅበራዊ ቁርኝት በመደጋገፍ ቀን የወጣን ሕዝቦች ነን። በጋራ ሠርተን፣ በጋራ አስበን በጋራ ሀገርና ሕዝብ የሆንን ነን። በዙሪያችን ያሉ ችግረኞችን መርዳት ከኢትዮጵያዊነት የተማርነው እንጂ ከአውሮፓና ከምዕራባውያን የወረስነው እውቀት አይደለም።

በጎነት ለእኛ አዲስ ነገራችን አይደለም። በጋራ በልተን፣ በጋራ ኖረን፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ቀን የወጣን ነን። ድንበር ተሻግሮ የመጣን የወራሪ ምርኮኛ እንኳን አብልተንና አጠጥተን ወደሀገራቸው ስንልክ ነው ዓለም የሚያውቀን። ይሄ ትውልድ እናቱ ገበያ ስትሄድ የጎረቤት ጡት ጠብቶ ያደገ ነው። ይሄ ትውልድ በያገባኛል ስም በሰፈር ሰዎች እየተቆነጠጠ እና እየተቀጣ ያደገ ነው።

አሁን ላይ በጎነት መልኩን እያጣ እኔነት እየገነነ የመጣበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው። ከመስጠት ይልቅ መንጠቅ፣ ከማካፈል ይልቅ መስረቅ እንደዘመናዊነት ቀደምት የበጎነት ታሪካችንን እያደበዘዘብን ነው። በወቅታዊው የኑሮ ውድነት እንኳን ባልጠፋ ምርትና ባልታጣ ሸቀጥ ምርት በመደበቅና ዋጋ በማናር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆኑ አንዳንድ ነጋዴዎች እየተስተዋሉ ነው።

ከሰሞኑ እንኳን በከተማ አስተዳደሩ በኩል በርካታ የንግድ ተቋማት ሕገ ወጥ በሆነ አገልግሎት መዘጋታቸውን ሰምተናል። በማስጠንቀቂያ የታለፉ እንዳሉ ሁሉ የንግድ ፍቃዳቸውም የተቀማ ብልሹ ተቋማት እንዳሉ እያየን ነው። በጎነት መገልገል ሳይሆን ማገልገል ነው። መልካምነት መነሻው ሀገርና ሕዝብ ነው። ከሀገርና ሕዝብ በልጦ ራስወዳድነት ባይዘን ኖሮ የኑሮ ውድነቱ በዚህ ልክ ባላስተከዘን ነበር።

አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ሳቢያ ካልተጋገዝን ለብቻ የምንዘልቀው አይደለም። ጊዜው ከመቼውም በላይ የእኛን አብሮነት የሚፈልግበት ነው። በብዙ ማኅበራዊ ተግዳሮት ብዙዎች ካለረዳት ብቻቸውን የሆኑበት ጊዜ ላይ ነን። በእኛ በጎነት ሌሎች ቀና እንዲሉና አዲስ ተስፋን እንዲሰንቁ ማድረግ ከኢትዮጵያዊነት የወረስነው የአባቶቻችን ውርስ ነው።

የሚያምርብን መረዳዳት ነው። አምሮብን ሌሎች እንዲያምርባቸው አድርገናል። በቸርነታችን ብዙዎችን ቀና አድርገናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ስለበጎነት ብዙ ጥቅሶች ተጠቅሰዋል። መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 3 ከቁጥር 27 ላይ ‹ለተቸገረ ሰው በጎ ነገርን ማድረግ አትከልክል› የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን።

በዚያው በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 6 ቁጥር 30 ላይ ‹ለሚለምንህ ሁሉ ስጥ› የሚል ለተነሳንበት የበጎነት አላማ ብርታት የሚሆን ጥቅስ እናገኛለን። ሌላው በዚያው ምዕራፍ ላይ የምናገኘው ‹ስጥ ይሰጥሀል› የሚለው ቅዱስ ቃል ነው። በዚህና በመሳሰለው ማስረጃ በጎነት ምን ያክል ጠቃሚ እንደሆነ መረዳት እንችላለን።

ነብዩ መሐመድ በሃዲስ፤ ስለ በጎነት እንደተናገሩት፤ መመጽወት /ለሌላው በጎ ማድረግ የእያንዳንዱ ሙስሊም ግዴታ ነው:: ሰውየው ምንም ባይኖረው እንኳን በራሱ እጅ ለራሱ ጥቅም መሥራት እና ከደመወዙ መጥኖ መመጽወት /በጎ ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል::

መሥራት የማይችል ቢሆን እንኳን ድሆችን እና ረዳት የሚሹትን መርዳት እንደሚኖርበት፣ ይህንን ማድረግ ካልቻለ፣ ሌሎች መልካም ያደርጉ ዘንድ ማነሳሳት እንዳለበት፣ ይህን ማድረግ ከተሳነው ራሱን ከእርኩሰት መጠበቅ እንደሚገባው፣ ይህም ራሱ ልግስና /በጎነት እንደሆ ነ አስተምረዋል::

በጎነት መንፈሳዊ ብቻ አይደለም። ከዚህ በራቀ መልኩ ሰው ለሆነ ሁሉ ተፈጥሮአዊ ማንነት ነው። ሃይማኖት የለሽ እንኳን ከሞት በኋላ የሚደርሱበት መጨረሻ እንደሌለ እያመኑ ጥሩ መሆንን የሚመርጡ ናቸው። ይሄ ማለት በጎነት ሰብአዊ ነው ማለት ነው። በሀገራችን የምንሰማቸው እና የምናያቸው ብቻነትን ያነገቡ አንዳንድ ማኅበራዊ መደብዘዞች ይሄን ተፈጥሮ ከመሳት የሆኑና ኢትዮጵያዊነትን ከመርሳት የተፈጠሩ እንደሆኑ መገመት አይከብድም።

ስቃዮቻችን እንዲያበቁ በፊተኝነት ባራመዱን የበጎነት አውድ ስር መሰባሰብ ይኖርብናል። ዓለም በሚያውቀን አንተ ትብስ አንተ በሚለው ጥንተ በኩር ወጋችን እናውጋ። ልባችን ለበጎነት ከተከፈተ ብዙ የምንሰጠው አለን። ለአፍሪካ ነፃነትን፣ ለዓለም ሥልጣኔን የቸርን ሕዝቦች ነን። ፍትህና እውነትን ባስቀደመ ማንነት ለጥቁሮች ቀና ማለትን ለኃያላኖች ደግሞ ዝቅታን የፈጠርን ክንደ ብርቱዎች ነን። ለመስጠት ከተዘጋጀን የምንሰጠው ብዙ አለን። በመስጠት የከበርን እንደሆንን ታሪኮቻችን ምስክሮች ናቸው።

የዚህ ዓለም ታላቁ ጥበብ በበጎነት በኩል የሚታይ ነው። ኦስትራዊቷ ማዘር ተሬዛ ሞተውም በበጎነታቸው ዓለም ይዘክራቸዋል። ሌላኛዋ አፍሪካዊት ማዘር ተሬዛ በመባል የሚታወቁት ኢትዮጵያዊቷ አበበች ጎበና፤ በበጎነታቸው የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህልም፣ የብዙ ወጣቶችን ራዕይ፣ የብዙ ሕፃናትን ነገ ብሩህ ያደረጉ የበጎነት ተምሳሌት ናቸው። ይህ ምግባራቸው ትውልድ ሲዘከረው የሚኖር ነው ።

የአንድ ዜጋ ጉስቁልና፤ የአንድ ዜጋ ማጣት፣ የአንድ ዜጋ እንግልት የሀገር ፈተና ነው። በዚያው ልክ ሀገር ማቅናት፣ ሕዝብ ማጽናት፤ ካለን ማካፈል ኢትዮጵያዊነትን ማስቀጠል፤ የተፈጠርንበትን አላማ መፈጸም ነው። ከዚህ ውጪ ባለጸግነት መስጠት ካልሆነ ዋጋ የለውም። አለው መባል ማካፈል ካልሆነ ትርጉም የለሽ ነው።

በሀገራችን የእኛን እጅ የሚጠብቁ ብዙ ችግረኞች አሉ። መማር እየፈለጉ ያልቻሉ፣ መሥራት እየፈለጉ ዕድል ያጡ፣ መኖር እየሻቱ ተስፋ ያጡ። የእነዚህን ሰዎች የመኖር ተስፋ ማስቀጠል ዋጋው በምንም አይተመንም። በጎነት ዙሪያን መቃኘት፣ አካባቢን ማስተዋል ነው። በዙሪያችን የሚያነሳቸው እጅ የሚጠብቁ ብዙዎች አሉና።

በእኛ በጎነት የሚከፈቱ እልፍ የተዘጉ ቤቶች አሉ። ለሀገራችንና ለሕዝባችን ዋጋ ያለው ዜጋ ሆነን ለመኖር በበጎነት መበርታት አማራጭ የሌለው ግዴታችን ነው። በጎነት ኪስን ገልቦ መስጠት ብቻ አይደለም። ከልብ የሚወጣ ራሮትን መሳይ፣ አለሁልህን ዓይነት በጎነትም አለ። ከሃሳብ፣ ከጊዜ፣ ከጉልበት የሚጀምር፣ አብሮነትን ያስቀደመ፣ በመደጋገፍና በመተባበር የሠለጠነም ነው።

በጎነት ክፍያ አለው። በእኛ መልካምነት ውስጥ ፈጣሪ መንገዳችንን እያቀናልን፤ በእኛ በጎነት ውስጥ አምላክ ነጋችንን እየሠራልን፤ በእኛ ጥሩነት ቤተሰቦቻችን፣ ሕይወታችን፣ ሥራችን፣ ትዳራችን፣ ዘመናችን እየተጠበቀ ነው። በእያንዳንዷ መልካም ሥራችን ልክ የምትከፈል መልካም ዋጋ አለችን።

ካለ በጎነት ኢትዮጵያዊነት ልክ አይመጣም። ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ስማችን በመልካምነት በኩል የተዋወቅነው ስም ነው። አብሮነታችንን የምናጠነክርበት፣ የምንመልስበት ጥሩው መንገድ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የመረዳዳት ሥርዓታችን በኩል ነው። ከተለማመድነውና ሀገር ከሠራ በጎ ትውፊታችን በቀር ኢትዮጵያዊነትን የምናስቀጥልበት የተሻለ አማራጭ የለንም።

በዚህ ሁለት አመት ውስጥ በተለይም ከሰሜኑ ጦርነት ወዲህ በሀገራችን በተለየ መልኩ የተፈናቃይና የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በሌላ መንገድ ከተማዋን የሞላት የችግረኛ ብዛት የትዬ ለሌ እየሆነ ነው ። እኚህ ሁሉ ማኅበራዊ ምስቅልቅሎች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ሰላም ተኮር እሳቤ ከማስፈለጉ ጎን ለጎን የበጎነት (የመደጋገፍ) ባህላችን መጠንከር አለበት።

የዚህ ዓለም ትልቁ ሥልጣኔ በመልካምነት በኩል የሚጎበኘን ሥልጣኔ ነው። ሀገር ወይም ዜጋ ምንም ያክል ችግር ቢገጥመው ያ ማኅበረሰብ የመረዳዳት ባህል ያለው ከሆነ ችግሩን አያሸንፈውም። እኛ ደግሞ በዚህ መሰሉ ባህል ውስጥ ተወልደን ያደግን ነን። እጆቻችንን መዘርጋት፣ ልቦቻችንን መክፈት ከቻልን ችግሮቻችን አይበልጡንም።

አዲስ አመት የሚያምረው ከበጎነት ጋር ነው። በጎነት ወቅት ባይኖረውም ከአዲስ አመት ጋር ግን ልዩ ነው። በዙሪያችን የተቸገሩን በመርዳት፣ ለጎደላቸው በመሙላት በአዲስ መንፈስ አዲስ አመትን መቀበል ይቻላል። ልክ የሚሆነውም እንዲህ ስናከብረው ነው። ወትሮም የሚያምርብን ተጠራርተን በአንድ ማዕድ ፊት ስንቀርብ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከሚታወቅባቸው መገለጫዎቹ አንዱ አብሮነት ነው። አብሮነት ደግሞ አብሮ በመብላት፣ አብሮ በመኖር፣ በመደጋገፍና በመያያዝ የሚገለጽ ነው። በሁላችንም ልብ ውስጥ ስለኢትዮጵያዊነት የተጻፈ አንድ እውነት አለ እርሱም ‹ኢትዮጵያዊነት መልካምነት› የሚለው አባባል ነው። ይህ እውነት አባባል ብቻ ሳይሆን የእኛነታችን ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ከብዙ ቀለማት፣ ከብዙ ማንነቶች፣ ከብዙ ባህልና ሥርዓቶች ተበጥብጦ አንድ ስብዕናን ያበጀ ስም ነው። ይሄ ስም በአብሮነት የጠበቀ፣ በኢትዮጵያዊነት የጠነከረ በጎነትና ጥሩነትን ፊተኛ ያደረገ ቀደምት ማንነት ነው። ይሄ ማንነታችን ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ የገናና ስምና የገናና ነፃነት ባለቤት ያደረገን። ተያይዘንና ተደጋግፈን ባንመጣ ኖሮ በዚህ ልክ ባለታሪክ ባልሆንን ነበር። በጎነት ከየትኛውም ጥበብ የላቀ ፊተኛ የማኅበረሰብ ትውፊት ነው።

እጸሳቤቅ (በማርያም)

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You