በጎነት ብሔር፤ ሃይማኖት ሳይለይ የሚከወን መልካም ተግባር ነው። የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰው ልጅ ምንም አይነት ክፍያ ሳይገኝበት ይበጃል፣ ይሆናል፣ ያስደስታልና የህሊና እርካታ ያስገኛል ብሎ ያለማንም ቀስቃሽና ጎትጓች በእራስ ተነሳሽነት የሚፈጸም ተግባር ነው፡፡
ይህ ተግባር ማንኛውንም ዜጋ የሚያሳትፍ ቢሆንም በዋናነት ግን ወጣቶችን በስፋት የሚመለከት ተግባር ነው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ትስስርን፣ አንድነትንና ፍቅርን የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግ ማስቻሉ ደግሞ ሌላኛው መልካም ጎኑ ነው፡፡ መንግሥታትን ከከፍተኛ የገንዘብ ወጪ በማዳን የአገራትን ኢኮኖሚ ማጎልበትም ከሚሰጠው ፋይዳ ጋር ይደመራል፡፡ በዚህ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በበርካታ ሚሊዮን ብር ሊሰራ የማይችል ተግባር በየዓመቱ ሲከናወን ይስተዋላል፡፡
የበጎ አድራጎት ሥራ እርስ በእርስ ትስስር አንድነት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሚሰጠው ሰዋዊ ማህበራዊ መስተጋብር የጎላ እንደሆነ ብዙዎች ያነሳሉ።
ወጣት ተካልኝ ልጅዓለም የዘንድሮ ዓመትን በበጎነት ከተሰለፉ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ እርሱ እንደሚናገረው በጎ ፍቃድ ቃሉ እንደሚናገረው ከራስ ተነሳሽነት ያለ ምንም የጥቅም ፍላጎት የሚደረግ ተግባር ነው ይላል። እንዴት ወደ በጎ ፍቃድ ሥራ እንደገባ ሲናገርም የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ክበባት ነበሩ። በእነዚህ ክበባት በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚቸገሩ ምግብ እና ደብተር ማግኘት ለማይችሉ ልጆች ለመድረስ ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ይህ እያደገ መጥቶ ነው ዛሬ ላይ ከፍ ባለ ደረጃ በበጎ ፍቃድ ተሳታፊ እንዳደረገው ይናገራል።
አሁን ላይ እየተሻሻለ ቢመጣም ከጓደኛ ከቤተሰብ በጎ ፍቃደኝነትን በተመለከተ የሚሰጡ አስተያየቶች ጥሩ አልነበሩም የሚለው ወጣት ተካልኝ ‹‹ሥራህን አትሰራም ወይ?›› በሚል ብዙ አሉታዊ አስተያየቶች ይሰጡ ነበር፡፡ አንድ ሰው በበጎ ፍቃድ ሥራ ውስጥ ሲሳተፍ ጊዜውን እንዳባከነ ይቆጠር ነበር ይላል።
የበጎነት ሥራ እንደሚታወቀው ሌሎችን አስተባብሮ በግብዓት፣ በገንዘብ፤ በጉልበትና በዕውቀት የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ እንደመሆኑ ማንኛውም ሰው በአለው አቅም ሁሉ ሊሳተፍበት የሚችል መሆኑን ወጣቱ ያስረዳል፡፡ ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ እስካለ ድረስ ይህ ጎድሎኛል ሳይባል ሁሉም የአቅሙን ያህል አስተዋጽኦ የሚያበረክትበት መስክ መሆኑን ይናገራል፡፡
ከዚህ ቀደም በዚህ የበጎነት ተግባር ተጠቃሚ ነበርኩ የሚለው ወጣት ተካልኝ በአንድ ወቅት ትምህርቱን መማር የማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እንደነበርና ለበጎነት በተዘረጉ እጆች አሁን ያለበት ደረጃ ስለመድረሱ ተናግሮ እነዛ ድጋፎች በጊዜው ተደርገውለት ባይሆን ኖሮ ዛሬ ላይ እዚህ ደረጃ ላይ መገኘት እንደማይችል ይናገራል።
ወጣት ተካልኝ እንደሚናገረው በ2015 ዓ.ም በተለያዩ የበጎ ፍቃድ ሥራዎች ላይ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል፣ የሚኖርበት ሰፈር በአዲስ አበባ አውቶብስ ተራ ሰባተኛ አካባቢ እንደመሆኑ በርካታ መንገደኞች የሚተላለፉበት ነው። በዚህ አጋጣሚ በርካታ የሌብነት ድርጊቶችና ዘረፋዎች ይከሰታሉ፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ሲከሰት እዛው አካባቢ ያለውን የነጋዴ ህብረተሰብ በማስተባበር ለማደሪያ፣ ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ አስተባብሮ በመሰብሰብ ባለሰቡት አጋጣሚ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ በማድረግ የተዘረፉት ሰዎች ለበለጠ ማህበራዊ ችግሮች እንዳይጋለጡ ሲያደርግ እንደቆየ ይገልፃል።
ከ2015 መስከረም ጀምሮ አቅመ ደካሞችን በመለየት ማዕድ ማጋራትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር እርሱ በጉልበት ሌሎች ባላቸው አቅምና ገንዘብ አቅመ ደካሞች የመደገፍ ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል። ለክርስቲያን እና ሙስሊም በዓላት እገዛ ከማድረግ በተጨማሪ በደም ልገሳ ተግባር በርካታ ዩኒት ደም የማሰባሰብና በሰላም ሠራዊትም አካባቢን በመጠበቅ ሰፊ ተሳትፎ ሲያደርግ እንደቆየ ይናገራል።
አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባ ወጣት ለበጎ ፍቃድ ያለው እይታ እየተሻሻለ እየመጠ እንደሆነ የሚናገረው ወጣት ተካልኝ በየሰፈሩ ወጣቶች በተለያየ መንገድ ለበጎነት እጃቸውን እየዘረጉ ነው። መንግሥትን ሳይጠብቅ በራስ ተነሳሽነት የሚሰሩ ወጣቶች እየተበራከቱ ነው፤ ይህም ተስፋ ሰጪ ነው ይላል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸውም በርካታ ሰዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያገኙ እንደሆነ የሚናገረው ተካልኝ ከዚህ በተጨማሪ ማህበረሰቡ እርስ በእርስ መደጋገፉ ትልቅ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ እያስገኘ መሆኑን ይናገራል፡፡
‹‹ድጋፍ በሚሰጠው እና ድጋፉን በሚያገኘው ሰው መካከል መደጋገፍና መቀራረብን በመፍጠር የሰዎችን ግንኙነት በማጠናከር ረገድ አበርክቶው ከፍተኛ ነው። ሶስት እና አራት ልጆችን ይዛ አይደለም በዓል ሲመጣ ለወትሮ ልጆቿን ለመመገብ የምትቸገርን እናት መደገፍ ማለት ትልቅ ሥነ ልቦናዊ ሕክምና ነው ብዬ አስበለሁ›› ይላል።
በ2016ዓ.ም ላይም ይህንን ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚፈልግ የሚናገረው ወጣት ተካልኝ በጎነትን እንደ ሥራዬ ስለያዝኩት በሚመጣው ዓመት ላይ ከአምናው በበለጠ ያለውን ጊዜና ገንዘብ በመስጠት ተሳትፎውን በይበልጥ ለማጠናከር እንዳሰበ ተናግሯል።
ሃና ሃምዛ ሌላኛዋ የ2015ዓ.ም የበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ወጣት ሴት ናት፡፡ እርሷ እንደምትናገረው፣ በበጎ ፍቃድ ፅህፈት ቤት አማካኝነት በተለያዩ የበጎ ፍቃድ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገች እንደቆየች ትገልፃለች። በቦሌ ክፍለ ከተማ ስር በደም ልገሳ፤ በአረጋዊያን ቤት እድሳት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ በችግኝ ተከላ ሰፊ ሥራዎችን ስትሰራ እንደቆየች ሥራውንም በውጤታማነት ማከናወን እንደቻለች ትናገራለች።
በበጎ ፍቃዱ ተሳታፊ ለመሆን ምን እንዳነሳሳት የምትናገረው ሃና ለሰዎች ያለ ክፍያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስገኘው የህሊና እርካታ ከፍተኛ በመሆኑ ማንንም ሳትጠብቅ በበጎ ሥራ ውስጥ መሳተፍ መጀመሯን ታስረዳለች፡፡ ያለ ክፍያ ለአገር ለወገኔ በማለት የአካባቢ ወጣቶችን በማስተባበር በ2015 የተለያዩ ፋይዳ ያላቸውን ሥራዎች እንደሠራች ትናገራለች።
በአካባቢያችን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ማንም ቀስቀሽ ሳያስፈልግ ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደምትፈልግ ለወረዳ በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ አካለት በመግለፅና የአካባቢ ወጣቶችን በማስተባበር ወደ ሥራው ገባሁ የምትለው ሃና፣ የተለያዩ ጫናዎች ቢኖሩም ለፈተናዎች እጅ ባለመስጠት ስኬታማ ሥራዎችን ማሠራት እንደቻለች ትናገራለች።
ወጣት ሃና እንደምትገልጸው፣ ወጣቶች በፍላጎትና በራስ ተነሳሽነት በሚሰሩት ሥራ የሚያገኙት የህሊና እርካታ ነው። ገንዘብ ለማግኘት አይደለም የሚሰሩት። ይህ ትልቅ ትርጉም ያለው እንደመሆኑ ገንዘብ እንኳ ባይኖራቸው በጉልበታቸው፤ በዕውቀታቸው በአጠቃላይ በሚችሉት ሁሉ ለማህበረሰቡ መልካም አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ሁሉም ወጣት በየአካባቢው ባለው ነገር ሁሉ ለበጎነት የፈጠነ መሆን አለበት ትላለች።
ወጣት ሰላሙ ደግነት ሌላኛው የበጎ ፍቃድ ተሳታፊ ነው። ወጣቱ እንደሚናገረው በጎ መሥራት በየትኛውም ሃይማኖት ከፈጣሪ ጽድቅ የሚገኝበት በመሆኑ እርሱም በዚህ ስለሚያምን ለበጎ ፍቃድ ሥራው እንደተነሳሳ ይናገራል። በተጨማሪም በጎ በመሥራት መሬት ላይ የወደቁትን በማንሳት፤ አቅመ ደካሞች በመጋዝ፤ በደም ልገሳ፤ በመኪና አደጋና መሰል ሁኔታዎች የተጎዱ ሰዎች በበጎ ፈቃደኞች ሲረዱ ማየቱ ውስጡ ተነሳስቶ የበጎ ፍቃድ ሥራውን እንደተቀላቀለ ይገልፃል።
በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች በደም ልገሳ፣ በትራፊክ ማስተናበር፣ በክረምት ችግኝ ተከላ፤ በዓመቱ መግቢያ ላይ ደግሞ ደብተርና እስክርብቶ በመግዛት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ያስረዳል፡፡
በጎነት ምንም ዓይነት ክፍያና ውዳሴ ከማንም ባለመጠበቅ ዘር፤ ሃይማኖት፤ ብሔር ሳይለይ የሚሰራ ሥራ ነው የሚለው ወጣት ሰላሙ፣ ይህንኑ ግንዛቤ በስፋት ሰዎች እየተገነዘቡት ስለመጡ ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ በ2015 የበጎ ሥራ ተግባራት የተከናወኑበት ዓመት ነበር ይላል።
መልካም መሥራት ለራስ እንደሆነ ወጣቱ እየተረደ እየመጣ እንደሆነ የሚናገረው ሰላሙ ምላሹን ከፈጣሪ ለማግኘት የየትኛውም ፖለቲካና ሃይማኖት ተከታይ ቢሆንም በጎነት የሚገድበው ነገር እንደሌለ አውቆ ለህሊናው መሥራት እንደሚገባው ያስረዳል። ይህ ሲሆን የጋራ አገር፤ የጋራ ርዕይ እና የጋራ አስተሳሰብ ይኖረናል ይላል፡፡
2015 ዓ.ም በተለያየ መስክ እጅግ ፋይዳቸው የጎላ የበጎነት ተግባራት እንደተከናወኑ የሚናገረው ወጣት ሰላሙ፣ በልቶ ማደር ለሚቸገሩ ወገኖች ማዕድ ማጋራት እና ለዕለትም ችግር መድረስ መቻል ትልቅ ነገር ነው ይላል።
ወጣቱ እንደሚናገረው በበጎነት በአንድ ጊዜ ለሁሉም መድረስ ባይቻልም ለከፋ ችግር የተዳረጉ ዜጎች እፎይታ እንዲያገኙ ማስቻል ትርጉሙ ብዙ ነው። በጎ ሥራ ማንም ሰው ሲሰራ ለህሊና እርካታ እንጂ ጊዜያዊ ጥቅምን መሠረት አድርጎ መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ የትኛውም ወጣት ወደ በጎ ፈቃድ ሲገባ ይህንን ተገንዝቦ መሥራት አለበት ይላል።
ወጣቶቹ እንደተናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከራስ ተነሳሽነት የሚመነጭ ነው፡፡ በጎ ፈቃድ ከቅን ልቦች የሚመነጭ፤ ከበጎ እጆች የሚዘረጋ መልካምነት ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችሉት ርህሩህ ልብ ያላቸውና ከራሳቸው ይልቅ ለሌሎች መኖርን የሚመርጡ ብቻ ናቸው፡፡ “በጎ ፈቃድ” የሚለው ቃል ትርጉሙ በራሱ እንደሚያመለክተው የሰው ልጆች ያለ ክፍያ ማንም ሳያስገድዳቸውና ሳያነሳሳቸው በራሳቸው ህሊና ቀስቃሽነት ከውስጣቸው በሚመነጭ መልካም ስሜት ተነሳስተው ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ አገልግሎቶችን የሚሰሩበት ተግባር ነው፡፡
እንዲሁም በጊዜና በሁኔታዎች የማይገደብ አገልግሎት መሆኑ ከሌሎች አገልግሎቶች በዓይነቱ የተለየ ያደርገዋል። ስለዚህ ሁሉም ወጣቶች በየአካባቢያቸው ለማህበረሰብ የሚጠቅም ሥራ በመሥራት የወጣትነት ጊዜያቸውን በበጎ ተግባር ላይ በመሳተፍ ለሀገራቸው መልካም አበርክቶ ሊያኖሩ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም
ክብረአብ በላቸው