እንደ ሀገር ያሉን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶቻችን በዋንኛነት በበጎነት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። እናም ለኢትዮጵያውያን ስለ በጎነት ለመስበክ/ለመንገር መነሳት ለቀባሪው የማርዳት ያህል ለትዝብት የሚዳርግ ሁነት ነው።
የቀደሙት አባቶቻችን ለፍጥረታዊ ማንነታቸው / ሰውነታቸው ቅርብ ከመሆናቸው የተነሳ ሕይወታቸው በበጎነት የተሞላ፤ እያንዳንዷ የሕይወት እንቅስቃሴያቸው በበጎነት የተቃኘ ለዚሁ እሴታቸውም የተገዛ ነው። እንደሀገርም በጎነት የብሔራዊ ማንነታችን አንዱ መገለጫ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ይህንን ማኅበራዊ እሴት በትውልዶች መካከል ለማስቀጠል የተሠሩ ዘመን የሚዋጁ ሥራዎች አሁን ላይ ትውልዱ ለበጎነት እንግዳ እንዳይሆን አድርገውታል፤ በራሱ የዘመን እሳቤ በበጎነት የተቃኘ ማኅበራዊ መነቃቃት ያለው እንዲሆን አስችሎታል።
በጎነትን በሚያጠይሙ ተግዳሮቶች በየዘመኑ እየተፈተነ የመጣው ይህ ማኅበራዊ እሴታችን፣ ዛሬም ቢሆን እንደ ሀገር ያለን ትልቁ ሀብታችን፤ ነገን ተስፋ የምናደርግበት መንፈሳዊ እና ሥነ ልቦናዊ መመኪያችን ነው። ከሁሉም በላይ ትውልድ የምንቀርጽበት የጽናታችን መሠረት ነው።
እንደ ሀገር የፈተና ወቅት የመሻገሪያ አቅማችን በብዙ መንገድ የሚገለጸው በያንዳንዱ ዜጋ ውስጥ ያለው በጎነትና በበጎነት የሚቃኘው አስተሳሰባችን ነው። ስለ ራሳችን፣ ቤተሰባችን ፣ ጎረቤታችን ፣ መንደራችን ፣ ሰፈራችን እና ሀገራችን ያለን በጎነት ፣ በጎነቱ የሚፈጥረው ጠረን ዘመናትን ላስቆጠረው ሀገራዊ ማንነታችን ሀውልት ነው።
የዛሬዪቱ ኢትዮጵያም በዚሁ የበጎነት እሴታችን በብዙ ተምጣ የተወለደች፤ የነገ ተስፋዋም በዚሁ እሴት ቀጣይነት ላይ የተመሠረተና ተስፋ ያደረገ ነው። በጎነት የዛሬ ፈተናችን መሻገሪያ ፤ እንደሀገርም ድህነትን አሸንፈን ለመጪዎቹ ትውልዶች የተሻለች ሀገር ለመፍጠር ለጀመርነው አዲስ የታሪክ ጉዞ ስኬት ትልቁ አቅማችን ነው ።
አባቶቻችን በበጎ ቀናት የተለማመዱት በጎነታቸው፤ ማንነታቸው አድርገው የተቀበሉት ማኅበረሰባዊ ስብእናቸው መንፈሳዊ እና ስነልቦናዊ አቅም ሆኖ ክፉ ቀናትን ተደጋግፈው እንዲሻገሩ አስችሏቸዋል። በዚህም በቀጣይ ትውልዶች መንፈስና ልብ ውስጥ የበጎነት ሐዋርያ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ይህም ትውልድ የአባቶቹ የባህሪ ልጅ ከመሆኑ አንጻር፤ በአባቶቹ በተግባር የተሰበከው በጎነት ፤ የዛሬ ሕይወቱ ስኬት ፤ የነገ ተስፋው መሠረት መሆኑን በአግባቡ ተረድቶ፤ በውስጡ አቧራ እየለበሰ የመጣውን ይህንን የማንነቱን እሴት ከዘመኑ የአቧራ ቡናኝ ሊያጸዳ፤ ውስጡ ያለውን የበጎነት እሴት ሊያነቃቃ ይገባል።
ዛሬም ቢሆን በተለይም አሁን እያጋጠሙን ላሉት ብሔራዊ ፈተናዎች /ችግሮች መሻገሪያ ዋነኛ መንገዱ በጎነትን በሁለንተናዊ መልኩ መለማመድ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር፤ በጎነትን በተጨባጭ በያንዳንዱ ማኅበራዊ ማስተጋብሮቹ በማስቀደም የቀደመውን የበጎነት የታሪክ ምዕራፍ ማደስ ይጠበቅበታል።
ስለ ራሱ፤ ቤተሰብ ፣ ጎረቤቶቹ ፣ መንደር ፣ ሰፈር፣ ሀገሩ ዛሬና ነገዎች በጎ በማሰብ፤ የራሱን ነገዎች ብሩህና በተስፋ የተሞሉ ማድረግ፤ ለራሱና ለትውልዶቹ የተመቸች ሀገር የመፍጠር ትውልዳዊ ኃላፊነቱን ዘመኑን በሚዋጅ የበጎነት አስተሳሰብ መሠረት ላይ ቆሞ ማዋቀር ይኖርበታል።
አባቶቻችን በበጎ ቀናት በጎነትን ተደግፈው ክፉ ቀናትን መሻገር የሚያስችል መንፈሳዊና ሥነ ልቦናዊ መሠረት መፍጠር እንደቻሉ፤ እኛ የአባቶቻችን ልጆች በዚህ ክፉ ቀን አባቶቻችን በውስጣችን የማንነታችን ተቀዳሚ እሴት አድርገው የሠሩትን በጎነት ከውስጣችን አምጠን በመውለድ ይህንን ክፉ ጊዜ ልንሻገር ይገባል።
የዛሬዋን ቀን የበጎነት ቀን አድርገን ስናስባትም፤ በውስጣችን ያለውን የበጎነት ዘር የፈተና መሻገሪያ ድልድይ አድርገን መጠቀም እንድንችል፤ ውስጣዊ መነቃቃት በመፍጠር፤ በጎነትን በዕለት ተዕለት የሕይወት መስተጋብራችን ተጨባጭ እውነት ለማድረግ ቃል እየገባን ነው።
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም