እሥራኤላውያን አንዲት ጠጠር ብትሆንም ወደግንባታው ከወረወርክ ለሕንፃው መሠረት መጠናከር አስተዋጽኦ አድርገሃል የሚል አባባል አላቸው። አንዳንድ አስተዋጽኦዎች ደግሞ ከግለሰብ አልፈው ለሀገር፤ ከሀገርም አልፈው ለትውልድ የሚተርፉ ናቸው፡፡ በተለይም ዘመን ተሻጋሪ የሆኑና ከዛሬ አልፈው ለነገ የሚተርፉ ሥራዎች ለአንድ ሀገር ህልውና የማዕዘን ድንጋይ ሆነው ያገለግላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም በ«ስለኢትዮጵያ» መድረኮቹ በሀገር ግንባታ ሂደት እና ህልውና ዙሪያ የበኩሉን እየተወጣ ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ።
የውይይት ባህልን የሚያሳድጉ ስለኢትዮጵያ መድረኮችን በማዘጋጀት ዐሻራውን እያኖረ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም ስለመሆኑ የተለያዩ ርዕሳነ መስተዳድሮችና ከንቲባዎች ጭምር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ለዚህ ሃሳብ መነሻ የሆነው ደግሞ በአዲስ አበባ የተካሄደው 14ኛው የስለኢትዮጵያ መድረክና በፓናል ውይይቱ የተነሱ ሃሳቦች ናቸው።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተሰናዱት 13 የ«ስለኢትዮጵያ» መድረኮች በተለያዩ የሀገሪቷ በከተሞች ተካሂደዋል። የመጀመሪያው ዙር ማጠቃለያና የአዲስ ምዕራፍ መጀመሪያ መድረክ ደግሞ «አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ተምሳሌት» በሚል ርዕስ በሳይንስ ሙዚያም ተካሂዷል።
14ኛው የስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለፖለቲካ ዘርፍና ለፖሊሲ አውጪዎች፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚ ዘርፎች እንዲሁም ለዲፕሎማሲው መስክ የሚሆኑ ግብዓቶች የተገኘበት መሆኑን የተለያዩ ታዳሚዎች የገለጹት ጉዳይ ነው።
የፓናል ውይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢፕድ የሚያዘጋጃቸው የስለኢትዮጵያ መድረኮች የውይይት ልምዳችንን ከማሳደግ ባለፈ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራዎች ግብዓት የሚሆኑ ሃሳብ የተገኘባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ኢፕድ የውይይት መድረኩን የኢትዮጵያ ተምሳሌት በሆነችው አዲስ አበባ በማዘጋጀት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያቀርባቸው ትንታኔዎች በጋራ ለመሥራት የሚረዱ መሆናቸውንም ከንቲባዋ አንስተዋል።
በመዲናዋ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ላይ በጋራ መሥራት ይገባል፤ አስተዳደሩም የአዲስ አበባን የኢትዮጵያ ተምሳሌትነት ከፍ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል ያሉት ወይዘሮ አዳነች፤ ነዋሪዎቿ በጋራ ከፍ ለማለት እየጣሩ ናቸው። ይህን ስኬት የአሁኑ ብቻ ሳይሆን የቀጣዩ ትውልድም የሚጋራው ነው። እኛም አዲስ አበባን በተለያዩ መስኮች ከፍ ለማድረግ ከሚዲያውና ከተለያዩ ምሁራን ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ማዕከልነት አጉልቶ የሚያሳዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው፤ ይህም በዲፕሎማሲው፣ በፖለቲካውና በተለያዩ መስኮች ያላትን የስበት ኃይል እንደሚያሳድገው አመላክተዋል።
ወይዘሮ አዳነች ካነሷቸው ሃሳቦች በተጨማሪ በመድረኩ የመወያያ ጽሑፍ ያቀረቡ ምሁራንና የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ያነሷቸው ሃሳቦች ሰፋ ባለ መልኩ ሊተነተኑ የሚችሉ ናቸው።
እኛም አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ማጠናከር ስለሚገባበት ጉዳይ እንዲሁም በፖለቲካውና ኢኮኖሚው ዘርፎች የተከናወኑና መሬት ላይ ያሉ ዕውነታዎችን መሠረት በማድረግ የቀረቡ ጥልቅ ሃሳቦችን ልናቀርብላችሁ ወደናል።
አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት
በአዲስ አበባ 123 ኤምባሲዎችና 67 የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደሚገኙና በተጨማሪም ከተማዋ ከ600 በላይ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗን አንስተው፤ ይህ መዲናዋ የዲፕሎማሲ ስበት ማዕከልነቷን ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል የሚሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ተቋማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ልዑልሰገድ አበበ ናቸው።
አዲስ አበባ ከቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ጀምሮ በተሠሩ ክንውኖች አማካኝነት የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ መጥቷል። መዲናዋ ከኒውዮርክና ከጄኔቫ ቀጥሎ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል የመሆኗ ጉዳይ የብዙ ጥረትና የረጅም ጊዜ ሥራ ውጤት ነው ይላሉ በፓናል ውይይቱ ላይ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት አቶ ልዑልሰገድ።
ከዓድዋ ድል ጀምሮ የሀገራችንን ክብር ከፍ በማድረግ የመዲናችን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እንዲፈነጥቅ ተሠርቷል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከአፍሪካውያን ሁሉ ቀድማ በሉዓላዊነት የዓለም አቀፉ ቴሌኮም ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ ፖስታ አገልግሎትና የሊግ ኦፍ ኔሽን እንዲሁም መሰል የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ተቋማት አባል ሆናለች ሲሉ አስረድተዋል።
የቀደመ ታሪካችንን ብንመለከት ኢትዮጵያ በፀረ-አፓርታይድና ፀረ-ቅኝ ግዛት ወቅቶች ድምጿን ከማሰማት ባለፈ ዓለም አቀፍ ችግሮች ዓለም አቀፍ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል በሚል ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ አከናውናለች። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን በባለብዙ ወገን መድረኮች ድምጽ ለመሆን ወሳኝ ድርሻ እንድትይዝ አድርጓታል ይላሉ።
በኋላም አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረትና የኢሲኤ መቀመጫ ሆናለች። አልፎ ተርፎም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በብቃት አከናውናለች። ይህ የሆነው ግን ከአዲስ አበባ የተሻለ ከተሞች ስላልነበሩ ሳይሆን አየር ንብረታችን፣ ሆቴሎቻችን፣ እንግዳ ተቀባይነታችንና ሌሎች የዲፕሎማሲ ሥራዎቻችን የስበት ማዕከልነቷን በማጎልበታቸው ነው ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።
አንድ ሀገር ግዙፍ መሰብሰቢያ አዳራሽ ስላለው ብቻ የዲፕሎማሲ ማዕከል አይሆንም ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፤ ይህ በአንድ ወገን ሥራ ብቻ የተገኘ አይደለም፤ ይልቁንም ባለብዙ ወገን ጥረቶች በተለይም አየር መንገዳችን ምቹ በመሆኑ፣ በከተማዋ ከደህንነት አንጻር ማንም መጥቶ የመግባባትና እንደባይተዋር የሚታይበት ሁኔታ ባለመኖሩ የተፈጠረ ነው ይላሉ።
በተጨማሪ የሆቴል አቅርቦትና የአየር ንብረት አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል እንድትሆን ካስቻሏት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። የአየር ንብረቱ የሚመቻቸውና ለስብሰባዎች የሚመርጧት ብዙዎች ናቸውና ጉዳዩን አቃለን ማየት የለብንም ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፤ አንድ ሆቴል ውስጥ የገባ ሰው የአየር ማቀዝቀዣ አሊያም ማሞቂያ ቴክኖሎጂ ሳያስፈልገው ጉዳዩን ጨርሶ ወደሀገሩ የሚመለስባት ከተማ ናት ሲሉ ገልጸዋታል።
ትውስታቸውን ሲያጋሩም ከዓመታት በፊት በታዳጊ ሀገሮችና በበለጸጉ ሀገሮች መካከል መፍትሔ በሚያሻው ጉዳይ ላይ በአንድ ስሙን መጥቀስ በማያስፈልግ ሀገር ከተማ ላይ ውይይት ሲደረግ እስከ ሌሊቱ 10 ሰዓት ስምምነት መድረስ አልተቻለም ነበር። በዚያን ወቅት ተሰብሳቢዎቹ ያነሱት ሃሳብ አዲስ አበባ የስብሰባ መግባቢያ መንፈስ ያላትና የምትመች ከተማ በመሆኗ ቀጣዩን ስብሰባችንን በመዲናዋ እናድርግ የሚል ነበር።
ይህ የሚያሳየው መዲናዋ የዲፕሎማሲ የስበት ማዕከልነቷ መሠረት እንደያዘ ነው። ዋናው ጉዳይ የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት እሙን መሆኑ ከታወቀ አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ የምክክር መድረክነትና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ክንውኖችን ለማጠናከር ምን መደረግ አለበት? የሚለው ላይ ማተኮር እንደሚገባ አቶ ልዑልሰገድ አሳስበዋል።
አዲስ አበባ የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እንድታጠናክር ዘመኑን የዋጀ ሥራ መሥራት ይገባል። በተለይም በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ሥርዓት ውስጥ ተለዋዋጭ ነገሮችን በመረዳት አካሄድን መቀየር የሚጠይቅበት ወቅት ላይ ነን፤ አሁን ላይ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ አውድ እየተቀየረ መጥቷል ብለዋል።
አቶ ልዑልሰገድ እንዳመለከቱት፤ የኮቪድ ወረርሽኝና ሌሎች ወረርሽኞችን ተከትሎ የቴክኖሎጂው ፍላጎት ማደግ፣ የሌሎች ሀገራት የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ጥያቄና ተጨማሪ ጉዳዮች ይበልጥ እንድንሠራ ያስገድዱናል።
አሁን ላይ ዲፕሎማሲው አዲስ አውድ ውስጥ እየገባ ነው፤ ፈተናው እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም የደቡብ ሀገራት ከፍተኛ ብልጽግና ውስጥ ናቸው። የደቡብ ሀገራት ፈጣን ዕድገት ሲያስመዘግቡ ደግሞ እኛስ መቼ ነው የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የምንሆነው የሚል ጥያቄ በማንሳት ላይ ናቸው። በመሆኑም ተፎካካሪ ስለበዛ አዲስ አበባችንን ተወዳዳሪ የማድረጉ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።
በተጨማሪ ኮቪድ ከመጣ በኋላ በተፈለገው ወቅት ስብሰባ ማድረግ አልተቻለም። ከዚያ ይልቅ በኢንተርኔት አማራጭና በሌሎች ሁኔታዎች ስብሰባዎች የመካሄድ ዕድላቸው ተስፋፍቷል። በመሆኑም በዲጂታል መንገድ ስብሰባዎችን የምናካሂድበትን መንገድ ማጠናከር እንደሚገባ አመላክዋል።
አሁን ላይ ከምናስተናግዳቸው ሰዎችና ተቋማት ባለፈ በተለየ ሁኔታ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ወደአዲስ አበባ ማምጣትና የቴክኖሎጂ ማዕከልነቷን ማጠናከር ይገባል የሚሉት አቶ ልዑል ሰገድ፤ ይህ ለዲፕሎማሲው ማዕከልነት ዘለቄታዊ ሥራ ይረዳል ይላሉ።
በተለይ በቀጣይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኩል የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም መቋቋሙ አይቀርምና ይህን መሰል ተቋማት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ስብሰባዎቻቸውን እዚሁ እንዲያከናውኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባችንን የምክክር ማዕከል በማድረግ ግጭቶችን ሁሉ መፍታት ይጠበቅብናል፤ ሰላምና ዲፕሎማሲ ወሳኝ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ ስለምክክርና መግባባት ይበልጥ መሥራት ይገባል።
ለዚህ ሁሉ የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ማስቀጠያ ሥራ ስትራቴጂ ሰነድ አዘጋጅቶ መሥራት ይገባል፤ በተጨማሪ አዲስ የዲፕሎማሲ ክለብ በማቋቋም ሥራዎችን ዘለቄታዊና ውጤታማ ሥራ ማከናወን ይገባል ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
አካታች ፖለቲካና አዲስ አበባ
መዲናዋ ከዲፕሎማሲውና ከኢኮኖሚው ባለፈ በፖለቲካው መስክ አካታችነቷ እየተጠናከረ ነው፤ ይበልጥ መጠናከርም አለበት ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአማካሪ ኮሚቴ አባልና የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባል አቶ አሽኔ አስቲን ናቸው።
«አካታች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሥርዓት» በሚል ርዕስ መወያያ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ አሽኔ፤ እኔ ከመጣሁበት ጋምቤላ ተወክሎ የመጣ ሰው በመዲናዋ ምክር ቤት አባልም ሆኗል፤ ይህ የሚያሳየው ከተማዋ አካታች መሆኗን ነው ብለዋል።
መዲናዋ አካታች ፖለቲካን ትከተል እንጂ በተለያዩ ጊዜያት ዴሞክራሲያዊ ሃሳብን ባለመቀበል ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች ሲከሰቱ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ነገሥታት ኢትዮጵያን አንድ የማድረግና አሁን ያላትን ቅርጽ እንድትይዝ ያደረጉት ጥረት አለ። በዚህ ሂደት ውስጥ የአካታችነት ጉዳይ ሲነሳ አንዱ አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል መንግሥታቱ ትኩረታቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሆኖ በመከናወኑ አንዳንዶች ትችት ያቀርቡበታል።
በተለይ የመንግሥት የመሬት አስተዳደር ሥርዓት ላይ ቅሬታ ይቀርብ ነበር፤ በኋላም በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የመሬት ላራሹና የተማሪዎች ንቅናቄ አመጽ የተነሳበት ወቅት እንደነበር አንስተዋል።
የቀደሙት መንግሥታት ከወደቁ በኋላ የደርግ መንግሥት መጣ፤ የደርግ የኢሠፓ ሥርዓት ደግሞ ሀገር በቀል ሳይሆን የውጭ ሃሳብ ላይ ትኩረት በማድረግ የሌኒንና ማርክሲስት ሃሳብን ያነገበ ያደረገ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ብዝሃነትን ያላገናዘበና የሚነሱ ጥያቄዎችን በኃይል የመደፍጠጥ ሁኔታ ያለው ነው። በዚህ ሂደት በርካታ ታጣቂ ኃይሎች በመነሳታቸው የደርግ መንግሥት ሊወድቅ ችሏል።
ኢህአዴግም በብሔር መልኩ የተደራጀ ስለነበር አካታችነትን ሊመልስ አልቻለም ያሉት አቶ አሽኔ፤ የአጋርና የመሪ ፓርቲ አደረጃጀቱ በእራሱ ትልቅ ችግር የነበረው ነው። በጊዜ ሂደት የሥነልቦና ጫና በመፍጠር ሰዎች በብሔራቸው ብቻ በመለየት በፖለቲካ ተሳትፏቸው እንዲገደቡ ያደረገ መሆኑን አውስተዋል።
ጥያቄዎች ሲነሱ በቀጥታ ሳይንሳዊና ቀና በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ፤ በኃይል የመፍታት ሂደት ነበር። ይህ ሂደት እኔ የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ወይ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ያደርጋል። ሀገረ መንግሥትና ብሔረ መንግሥትን ባለመለየት ብሔር ላይ ያተኮረ ሂደት ለመፍጠር ተሞክሯል ሲሉ አስረድተዋል።
አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ሐረሪና ሌሎችም በአጋርነት ተገድበው በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዳይሰጡ ያደረገ ሥርዓት እንደነበር አንስተው፤ አሁን ላይ ብልጽግና ከዚህ በተለየ አካታችነትን ባማከለ ሁኔታ አጋር የተባሉትንም ጨምሮ ሁሉንም ያካተተ ሂደትን እየተከተለ መሆኑን አድንቀዋል።
አካታችነት ወሳኝ ጉዳይ ነው የሚሉት አቶ አሽኔ፤ የተሳትፎና የአካታችነት ጉዳይንም መለየት እንደሚገባ ነው የሚያሳስቡት።
አካታችነት የባለቤትነት ስሜት ያለው ሲሆን ተሳትፎ ግን ጥሪ ሲደረግላቸው የመካፈል እንጂ ሂደቱ ውስጥ የሚሳተፉበትና ባለቤት የሆኑበት አካሄድ አይደለም። በአካታችነት መርህ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያውያንን ባሳተፈ መልኩ በሀገራችን ጉዳይ ላይ የመወሰን አቅም ይኖራል ይላሉ።
ይሁንና ያለፉ ታሪኮች ክፉም ይሁኑ በጎ ልንማርባቸው እንጂ ሊያጣሉን አካታችነታችንንም ሊያጎድሉት አይገባም፤ የተለያዩ ሀገራት ያጸኑት በላብና በሥራቸው ነው፤ ያለፈው ታሪክ የሚገድበን መሆን የለበትም የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል።
አካታች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሁኔታ በኢትዮጵያ ሥርዓት ለማጠናከር ሕዝቦች ይበልጥ እንዲቀራረቡ መሥራት አለብን ያሉት አቶ አሽኔ፤ ስለኢትዮጵያ ስናነሳ በአብዛኛው የምናወራው ስለተራሮቿና ስለዛፎቿ በመሆኑ ይህን ሃሳብ መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ትኩረት ማድረግ ያለብን ኢትዮጵያን የቀየሩ ሰዎች ላይ ነው፤ ተራሮቹን ታሪካዊ ወንዞቿን ታዋቂ ያደረጓትን ሰዎች በመለየት ትውልዱ እንዲያውቅ ማድረግ ይገባል ሲሉም ሃሳብ ሰጥተዋል።
አቶ አሽኔ ትውስታቸውን ሲያጋሩም፤ ብዙዎች ስለጋምቤላ ሲጠይቁኝ የሚያውቁት ስለባሮ ወንዝና ስለተፈጥሮዋ ነው እንጂ በጋምቤላ ስለሚኖሩ አኙዋክ፣ ኑዌርና በጋምቤላ ስላሉ ዜጎች አይደለም። እኔም ጎጃም በኖርኩበት ወቅት ስለጢስ ዓባይ ፏፏቴ እንጂ ስለአካባቢው ነዋሪዎች ብዙም አልሰማሁም። ይህ የሚያሳየው ሰው ላይ ሳይሆን ሲነገረን የኖርነው ስለተፈጥሮው ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት የምንፈልገውን አካታችነት ማምጣት አልቻልንም ብለዋል።
አቶ አሽኔ እንደሚገልጹት፤ ታላላቅ ሰዎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለብን፤ ስለሰዎች እየተነጋገርን ሀገራችንን በአካታችነት መምራት ይኖርብናል። በዚህ መንገድ የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ከተሞችንም አካታችነት ማሳደግ ይቻላል።
ሀገር የሚገነባው በመጀመሪያ በሀሳብ ነው ያሉት አቶ አሽኔ፤ ያለው ችግር የአስተሳሰብ ችግር ስለሆነ ከማስተማር ከተነሳን ብዙ ነገሮችን ማስተካከል እንችላለን ሲሉ አስረድተዋል።
አንዳንዶች ዘረኝነት ነው አካታች እንዳንሆን ያደረገን፤ ችግራችን እሱ ነው ይላሉ። እኔ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው በዘረኝነት ስም ወይም በሰፈር ስም የሚቀነቀን የፖለቲካ ሽኩቻ ነው ባይ ነኝ። ዘረኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ በእኔ እይታ እርግጠኛ አይደለሁም ሲሉም ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።
የፖለቲካ ፍላጎቴ አልተሟላም የሚል አካል ሃይማኖትን፣ ጎጠኝነትን፣ ቋንቋን ያነሳል ያሉት አቶ አሽኔ፤ ሰው የዘራውን ያጭዳል ነውና ሰላምና አንድነትን በመዝራት የምንፈልገውን እንድናገኝ መሥራት አለብን። መልካም ነገር ለማግኘት መልካም ነገር መዝራት ይኖርብናል፤ ሰላም ለማግኘት አንድነትን መዝራት ይኖርብናል ብለዋል።
በመሆኑም መጽሐፉም እንደሚለው ሰሚዎች ብቻ ሳይሆን አድራጊዎች እንሁን ነውና እያንዳንዳችን ከእራሳችን መጀመር አለብን። በጎረቤት ከጀመርንና በጋራ ተግባብተን ከተፈቃቀርን ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።
ትውልዱ ኢትዮጵያ ማለት አምላክ በአምሳሉ የፈጠረው በአጠገባቸው ያለው ጎረቤታቸው መሆኑን እንዲረዱ ካደረግን ሀገራችንን ወደፊት ማጽናት አያቅተንም፤ ይህን ሃሳብ ካጠናከርን አዲስ አበባን ይበልጥ አካታች ማድረግ ከቻልን እንደሀገርም ተጨማሪ ስኬት ማስመዝገብ እንችላለን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሶሺዮ- ኢኮኖሚ መናኸሪያ
ስለኢትዮጵያ ስናስብ በዋናነት ስለአዲስ አበባ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ልናስብ እንገደዳለን። ኢኮኖሚውም በቀጥታ ከፖለቲካው ጋር የተገናኘ በመሆኑ የከተማዋን ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንዘብ ወሳኝ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ናቸው።
የአዲስ አበባ ኢኮኖሚ ግዙፍ መሆኑን ለማወቅ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን መረዳት ይገባል፤ አዲስ አበባ ከፖለቲካው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በተለይ የፋይናንስ ተቋማት አሏት። በአዲስ አበባ የሚገኙ የንግድ፣ የፋይናንስና የኢንሹራንስ ተቋማት ከመላ ሀገሪቷ አንጻር ሰፊ ድርሻን ይይዛሉ ብለዋል።
የመዲናዋ ኢኮኖሚ ደግሞ ጤነኛ በመሆኑ የፖለቲካና መሰል ዘርፎችን ሁናቴ እንዳይረበሽ ይረዳል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ማሳያው የመዲናዋ ኢኮኖሚ 80 በመቶው የሚንቀሳቀሰው በግሉ ዘርፍ ተዋንያን መሆኑ እንዲሁም 85 በመቶው የከተማዋ ኢንቨስትመንት የሚመጣው ከግሉ ዘርፍ መሆኑ ዋነኛ ምክንያት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የአንድ ከተማ ኢኮኖሚ በአብዛኛው በግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ጤናማ ነው፤ ዘላቂም ይሆናል። ሌላው ኢኮኖሚው ጤነኛ ነው የሚያስብለው ጉዳይ ቁጠባ ነው። አዲስ አበባ ከሀገር ውስጥ ምርትና አገልግሎቷ አንጻር የቁጠባ ልምዷ 40 በመቶ ደርሷል። ይህ የነዋሪዎቿ የቁጠባ ባህል ማደጉንና የተረጋጋ ሶሺዮ-ኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች መሆኑን እንደሚያሳይ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ከተማዋ የትራንስፖርት ኔትወርክ ማዕከልም ናት፤ ምክንያቱን ከየአካባቢው የሚጓጓዝ ሰው አዲስ አበባን መርገጥ ይኖርበታል፤ በሀገር ውስጥ ጉዞ ብቻ ሳይሆን በአየር መንገድ አገልግሎት ዘርፍም በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች መዲናዋን አይተው ይመለሳሉ፤ ይህ ኢኮኖሚውን ብቻ ሳይሆን የዲፕሎማሲና ለፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውጤታማነት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በዚሁ ልክ መዲናዋ የሀገሪቷ የትምህርት ማዕከልና አፍሪካዊ ስሜት ያላት የቱሪዝም ማዕከል ነች። በተጨማሪ አዲስ አበባ የምገባ ማዕከላትን በመገንባት ትውልዱ በተስፋ እንዲማርና ወላጆችም ሃሳባቸው እንዲረጋጋ አድርጋለች ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ የሕፃናት ትምህርት ቤቶች ላይ የተሠራው ሥራ ለሌሎች ክልሎችም አርዓያ መሆን የሚችል ተግባር መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በአንጻሩ ግን ለመዲናዋ ፈታኝ የሆኑ ጉዳዮች የሥራ አጥነት ቁጥር፣ ሕጋዊ መስመር ያልያዙ የንግድ እንቅስቃሴዎችና ፍልሰት መሆናቸውን አመላክተው፤ ችግሮቹን በጋራ መከላከል ከተቻለ የመዲናዋን ሶሺዮ ኢኮኖሚ ብሎም ፖለቲካዊ ማዕከልነት ማጠናከር እንደሚቻል ሃሳብ ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው እንደገለጹት፤ ከአዲስ አበባ ኢኮኖሚ አራት በመቶ የሚሆነው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዘ ንግድ ነው። ይህም ዘመናዊና ሕጋዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ስለሚሆን ማስተካከል ይጠይቅ ነበርና እንዲቀንስ ተደርጓል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ባወጣው መረጃ መሠረት በሥራ ዕድል ቁጥር 10 በመቶ በየዓመቱ እያደገ ነው። ነገር ግን የሥራ አጥ ቁጥሩ 23 በመቶ ይደርሳል፤ ይህ ቁጥር ከሌሎች ከተሞች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው። ይህ አንዱ የመዲናዋ ተግዳሮት ነውና ማስተካከል ይጠይቃል።
የከተማው እንቅስቃሴ ስቧቸው የሚመጡና ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ወደአዲስ አበባ የሚገቡ ሰዎች በመብዛታቸው በከተማዋ ድህነትን፣ ሥራ አጥነትንና ተያይዘው የሚከሰቱ ፖለቲካዊ ምክንያቶችን መቀነስ አስቸጋሪ አድርጎታል ባይ ናቸው።
ይህ ግን የሌሎች ከተሞችን ጫና የተሸከመ ከመሆኑ የተነሳ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ጫናውን ሌሎች ከተሞችም ሊጋሩትና የመዲናዋን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያግዙ ይገባል ሲሉ ሃሳብ ሰጥተዋል።
በከተማዋ ከ10 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ለሥራ ፈጣሪዎች ብድር መዘጋጀቱና የዋጋ ግሽበቱን ለመከላከል የሚከናወኑ ሥራዎች መልካም ናቸው። ይሁንና የገበያ ዕድሎችን በመጠቀም፣ የኢንቨስትመንት ጥረቶችን ማጠናከር፣ ችግሮችን የጋራ ማድረግና በጋራ መሥራት ለተሻለው የከተማችን ለውጥ ወሳኝነት አለው ብለዋል።
የአዲስ አበባን ሶሺዮ-ኢኮኖሚያዊ ውቅር ለማጠናከርና ፖለቲካዊ አንድምታዋንም ይበልጥ የተረጋጋ ለማድረግ ነዋሪዎቿ ይበልጥ መትጋት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
በፈተና ያለፉ ፕሮጀክቶች
በአሁኑ ወቅት ሜጋ ፕሮጀክቶች ኢኮኖሚያዊ ይዘት ብቻ ያላቸው ፖለቲካዊ ጥያቄንም የሚያስነሱ ጉዳዮች ሆነዋል ያሉት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ናቸው።
በአንድ ወቅት በፈረንሳይ ፓሪስ «አይፍል ታወር» የተሰኘው ግዙፍ በብረት የተሠራ ሐውልት ለመሥራት ስትነሳ ትልቅ ተቃውሞ ገጥሟት እንደነበር አንስተው፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሁራኖች ፕሮጀክቱ መሠራት የለበትም ብለው በመፈራረም የብረት አስክሬን የመሰለ ሐውልት ለፓሪስ አይመጥናትም በሚል ሲከራከሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በስተመጨረሻም ፓሪስ ያንን ሁሉ ጫና በመቋቋም አሁን ላይ መገለጫዋ የሆነውን ያማረና ግዙፍ የሆነውን አይፍል ታወርን ተክላለች። ፓሪስን ሲያስቡ ያለ አይፍል አይታሰብም፤ በማንኛውም ወደከተማዋ ያቀና ቱሪስት በኪነ ሕንፃው ውበትና በታሪካዊ ዳራው የፈረንሣይ ብሔራዊ አርማ ተደርጐ የሚቆጠረው ሐውልት ስር ሆኖ ፎቶ መነሳትና መዝናናት ያስደስተዋል። ይህ ደግሞ ለከተማዋ ከፍተኛ ገቢ እያስገኘ ያለ ፕሮጀክታቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል።
እኛም ሀገር ስንመጣ የመስቀል አደባባይ ሜጋ ፕሮጀክት ላይ የተነሳውን ግርግር ማስታወስ እንችላለን ያሉት ዶክተር እዮብ፤ በወቅቱ ስፈራው እንዳይለማ የተፈጠረውን ውዥንብር ማስታወስ ከተቻለ ጠንካራ አመራር ባይኖር ፕሮጀክቱ ተቋርጦ ሊቀር ይችል እንደነበር አንስተዋል።
ይሁንና ጥራትና ጊዜ እንዲሁም በተቀመጠው ወጪ መሠረት ትኩረት አድርጎ መሥራት ስለተቻለ ግርግሩ ረገበ፤ ሥራው ግን ለትውልድ ዘላቂ ነው። ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ ተቃውሞ ቢነሳም የግንባታ ፈተና ቢመጣም ያንን ተቋቁሞ ሠርቶ ማሳየት በመቻሉ አሁን ላይ አልፈናቸው ስለሌላ ሥራ እያሰብን ነው።
በተመሳሳይ አንድ ሌላ ሜጋ ፕሮጀክት ሲነደፍ ተቃውሞ አይጠፋውም። ዋናው ጉዳይ ግን ቁርጠኛ አመራርና ክትትል ማድረግ ነው። በአንድ በኩል በዘላቂነት የመከታተልን፣ ምንም ዓይነት ፈተና ቢመጣ ተቋቁሞ የመቀጠልን ሂደት እያስለመዱን ያሉ ሥራዎች ሜጋ ፕሮጀክቶች ናቸው ይላሉ።
አቶ እዮብ እንዳመለከቱት፤ 24 ሰዓት ክትትል በሚደረግባቸውና በሳምንት ሰባት ቀናት ሥራ በሚከናወንባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ደግሞ በዲፕሎማሲውና በቱሪዝሙ ጭምር ድል ማስመዝገብ እንደሚቻል ማወቅ ይገባል።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሥራዎች ውስጥ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች አሉ፤ የሜጋ ፕሮጀክቶች ሥራ ከዚህ ውስጥ አንዱ ክንውን ነው። ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ ግንባታዎችን ጀምሮ መጨረስ ሳይሆን አስቀድሞ ጨርሶ መጀመርን ያሳዩ መሆናቸውን አቶ እዮብ ተናግረዋል።
የ10 ዓመት ትልም፤ በ30 ዓመት ውስጥ የት መድረስ እንደምንችል ግልጽ ውጥን አለ። የከተማዋ ሜጋ ፕሮጀክቶች ደግሞ የእነዚህ ሀገራዊ ትልሞች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የሜጋ ፕሮጀክቶች ሥራ የአንድ ሰሞን የሆይ ሆይታ ጉዳይ ሳይሆን በተምሳሌትነት የተሠሩና ሀገራዊ እይታ ያላቸው የመዲናዋን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ከፍ የሚያደርጉ እንዲሁም ለዜጎች ምቹ አካባቢን የፈጠሩና የሥራና የፖለቲካ ባህልን ያሳደጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አሁን ላይ ክልሎችም ይህን ልምድ እየተገበሩት ነው። በሶማሌ ክልል ደገሃቡር እንዲሁም ጎዴ አካባቢ በሸበሌ ወንዝ ዳርቻ የተሠሩ ፕሮጀክቶች የአዲስ አበባ ሜጋ ፕሮጀክቶች የፈጠሩት የፖለቲካና የሥራ ልምድ ማሳያዎች ናቸው። በተባለው ጊዜና ጥራት ጀምሮ የመጨረስ ልምድ እየታየ ስለመሆኑ በግልጽ መናገር ይቻላል ብለዋል።
ፈጠራ በተሞላበት መንገድ የፋይናንስ አቅምን በማጠናከር በእንጦጦና በመሃል ከተማ የተሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ያነሱት አቶ እዮብ፤ የኢኮኖሚ ጫናንና የገንዘብ እጥረትን በመቋቋም የተከናወኑ መሆናቸውን አመላክተዋል።
መንግሥት ገቢ ሰብስቤ ሜጋ ፕሮጀክቶችን አከናውናለሁ ቢል ሥራው ፈቅ አይልም ነበር፤ ይሁንና ባለሀብቶችን በማሰባሰብ ልዩ እራት በማዘጋጀትና ድጋፍ በማሰባሰብ ሜጋ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል። ይህ ፈጠራ የተሞላበት የፋይናንስ አጠቃቀም ለሌሎችም ተምሳሌት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ከግንባታዎች ባለፈ ለተማሪዎችና ለአቅመደካሞች የሚደረጉ የምገባና የቤት ዕድሳት ፕሮግራሞች የሜጋ ፕሮጀክቶች አካል ናቸው። በእነዚያ ልጆችና እናቶች ጀርባ ስንት ሰው እየተረዳ መገንዘብ ከቻልን የሜጋ ፕሮጀክቶችን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አስተዋጽኦ መረዳትና መደገፍ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ዋናው ነገር ይህንን የሜጋ ፕሮጀክቶች ሥራ ውጤታማነት ማስቀጠሉ ላይ ነው፤ በጫና ውስጥም ቢሆን ሜጋ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ አንድም ፖለቲካውን ለማርገብ በሌላ በኩልም ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ይረዳል ሲሉ አቶ እዮብ አመላክተዋል።
ምሁራኑና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎቹ እንዳሳሰቡት ከሆነ፤ የአዲስ አበባን የዲፕሎማሲና የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ ማዕከልነት ለማሳደግ አካታች የፖለቲካ ልምድን ማጎልበት፣ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከርና የፕሮጀክቶችን የቁጥጥር ባህል እያሳደጉ መሄድ ይገባል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም