ስለ ሰላም መስዋዕት በመሆን ዘመኑንእንዋጅ !

 ኢትዮጵያ የእልፍ ልጆቿ አጥንት ተከስክሶና እንደ ዱቄት ልሞ በደማቸው ተቦክቶ የተጋገረች ሀገር ናት። በየዘመናቱ ልጆቿ በከፈሉላት መራራ የሕይወት መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ዛሬ ላይ ደርሳለች። የየዘመናቱ የታሪክ ምዕራፏ ሲገለጥም የቆሰሉላት፣ የደከሙላት፣ የሞቱላት፣ እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡላት እጅግ በርካታ ጀግኖችን እንዳፈራች ያስረዳናል። አንድነቷ ተጠብቆ ዳርድንበሯ ሳይሸራረፍ፣ ክብሯ ሳይጓደል ለትውልድ እንድትተላለፍ በአራቱም ማዕዘን እስከ እስትንፋሳቸው ህቅታ ድረስ የተጋደሉላት ብዙዎች ናቸው።

በጠላት እጅ ወድቆ ሀገሩ ተዋርዳ ላለማየትና ክብሯን ላለማስደፈር ሲል፤ አፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ባሩዱን ጠጥቶላታል። አፄ ዮሐንስ ዳር ድንበሯ እንዳይሸራረፍ መተማ ላይ አንገቱን ሰውቶላታል። አፄ ሚኒልክ የክተት ዘመቻ አውጀው ሕዝቡን በአንድነት አስተባብረው አድዋ ላይ ወራሪው የጣሊያንን ጦር ወደ መጣበት አንገቱን አስደፍተው መልሰዋል። በዚህ አውደውጊያ አባቶቻችን በፈጸሙት መራራ መስዋዕትነት እኛ ልጆቻቸው በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ከማድረጋቸው ባሻገር በዓለም ዙሪያ ላለ ጥቁር ሕዝብ የነጻነት ችቦ አቀጣጥለዋል።

ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ሁሌም ለሀገራቸው ሕልውና መስዋዕትነት መክፈልን እንደ ጽድቅ የሚቆጥሩ፤ ድንበሯን ጥሶ የመጣን ጠላት በአንድነት “ቀፎው እንደተነካ ንብ ግልብጥ” ብሎ ወጥቶ አይቀጡ ቅጣት መቅጣትን የሚያውቁ ናቸው። በደርግ ዘመነ መንግሥት በሀገሪቱ ውስጥ በነበረው ፖለቲካዊ ሽኩቻና የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ፤ “ሀገሪቱ ክንዷ ዝሏል” በሚል እሳቤ በእብሪት ተወጥሮ ድንበሯን ዘልቆ የገባውንና እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የዚያድ ባሬን ጦር ጀግኖች አባቶቻችን ዋጋውን ሰጥተው ወደ መጣበት በመመለስ ዳርድንበሯን አስከብረዋል።

በጥቅሉ ታሪክ የሚያስረዳን፤ በልጆቿ የተባበረ የመስዋዕትነት ክንድ ድንበሯን አልፎ የመጣባት ሁሉ ዶጋ አመድ ሆኗል። ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ በተከፈለ መስዋዕትነት ዳር ድንበሯ ሳይደፈር፤ ባህል፣ ወጓ፣ ኃይማኖቷ… ወዘተ ተከብሮ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ዛሬም ጸንታ እንድትቆም እልፎች መስዋዕት ሆነውላታል። እየሆኑላትም ይገኛሉ።

ኢትዮጵያ በህዝቧ መስዋዕትነትና አብሮነት በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባች ጠንካራ ሀገር ናት። የጥንካሬዋ ሚስጥሯ፤ የዘመናት አልበገር ባይነት መሰረቷ፤ ታፍራና ተከብራ የመኖሯም ሚስጥር ይኸው ነው። “እሾህን በእሾህ” እንዲሉ፤ ፊት ለፊት ገጥመው ሊያንበረክኳት ያልቻሏት ታሪካዊ ጠላቶቿ፤ የኃይሏ ሚስጥር የሆነውን የሕዝቧን አንድነት ለመበጣጠስና ለመናድ በብዙ ሴራዎች በየዘመኑ ተገልጠዋል።

ይህ ደግሞ ከመሬት በታች የተቀበረ ሳይሆን በግሀድ ከመሬት በላይ እየታየ ያለ ሀቅ ነው። ትናንት ለአንድ ሀገር ዳር ድንበር አብሮ የተዋደቀ፤ ስለክብሯ በአንድ ጉድጓድ የተቀበረ ማሕበረሰብ ዛሬ “አንተ ከየት ነህ? ከየት መጣህ?” በመባባል መገፋፋቱ፣ ወንድም በወንድሙ ላይ ጨክኖ እጁን ማሳረፉ፤ ከትናንት አዳፋ ታሪካችን መማር ተስኖን ዛሬም ከእርስ በእርስ የጦርነት አዙሪት አለመውጣታችን የዚሁ እውነታ አንድ አካል ነው።

ኢትዮጵያ ሀገራችን እንደ ትናንት ዛሬም ታፍራና ተከብራ እንድትኖር፣ ነገም ዳር ድንበሯ ተከብሮ ለትውልድ እንድትተላለፍ እንደ አባቶቻችን ሁሉ ዘመኑ የሚሻውን መስዋዕትነት ሁሉም ዜጋ ሊከፍል ይገባል። ትናንት አባቶቻችን በዱር በገደሉ ደማቸውን አዝርተው አጥንታቸውን ከስክሰው የሀገራቸውን ዳር ድንበር፣ ጥቅም በጋሻና በጦር ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው አስከብረዋል።

ጠላቶቻችን ዛሬ ላይ እንደትናንቱ ፊት ለፊት መጥተው በነፍጥ ሊገጥሙን ሞራሉም አቅሙም የላቸውም፤ ከዛ ይልቅ የእጅ አዙር ጦርነት እየከፈቱ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉን ነው። ይህን ተረድቶ የጠላቶቻችን የእጅ አዙር ጥቃት ለመመከትና ምኞታቸውን ለማክሸፍ እንደ ትናንት አባቶቻችን ጋሻና ጦር ይዞ በዱር በገደል በመዋደቅ መስዋዕትነት መክፈልን አይጠይቅም።

ይልቁንም የኃይላችን ሚስጥር የሆነውን አንድነታችን መጠበቅ፤ እርስ በእርስ መዋደድ፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ አንተ ትብስ አንቺ ተባብሎ ተሳስቦ መኖር… ወዘተ ዛሬ ላይ ትውልዱ ሊከፍለው የሚገባ መስዋዕትነት ነው።

አይደለም በአንድ ሀገር የሚኖር ህዝብ ይቅርና በመንትያማቾች መካከል ፍጭት፣ ግጭት፣ አለመግባባት… ወዘተ የሀሳብ ልዩነት የሚጠበቅ ነው። እንደ ሀገር በርካታ አለመግባባቶች፣ የሀሳብ ልዩነቶች.. ወዘተ አሉብን። ልዩነት የሚጠበቅ ነው። ሆኖም ችግርና አለመግባባቱን ዛሬም እንደትናንቱ ባለፈበት ፋሽን በነፍጥ እንፍታ የሚለው አያስኬድም። ማንም አትራፊ እንደማይሆንም ከትናንት ታሪካችን አይተነዋል። ከትናንት ታሪካችን ዛሬም ለመማር ግን አልረፈደም።

ታዲያ ከትናንት ተምረን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት በሰጥቶ መቀበል መርህ ለመፍታት ሁሉም ከልብ ቀናኢ ሊሆን ይገባል። ያኮረፈ፤ በዚህም፣ ነፍጥ ያነገበውን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ የሰላም አርአያ ሊሆን ይገባል። ዘመኑ የሚፈልገው መስዋዕትነት ይህ ነው። በዚህ ነው ልክ እንደ አባቶቻችን ዛሬም እኛ ልጆቻቸው ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዳግም አሸንፈን መቆምና ወደፊት መራመድ የምንችለው።

ሁላችንም ሀገራዊ ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ዛሬውኑ በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ለመነጋገር መወሰን አለብን። መንግሥትም ልክ እንደ ትናንቱ በሆደ ሰፊነት ያኮረፉና ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ ከግማሽ በላይ እርቀት መሄድ ይጠበቅበታል።

መላው ሕዝብም ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ በሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይገባል። ኢትዮጵያውያን ከመቼውም በላይ አንድነታችን ጠብቀን በጋራ በመቆም ለሰላም የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሁሉ የምንከፍልበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ይህንን መስዋዕትነት ለመክፈል ሁሉም ቆርጦ መነሳት ይኖርበታል።

በማህበራዊ ሚዲያ “የሞቀ ቤቱ ቁጭ” ብሎ በለው፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው፣ …እያለ የእርስ በእርስ ግጭት የሚጠምቁ የጦርነት ነጋዴዎችን ኀብረተሰቡ “ጆሮ ዳባ ልበስ” ሊላቸው ይገባል። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያው ተዋናይ የሆነው ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል የነዚህ የጦርነት ነጋዴዎች መሣሪያ እንዳይሆን እራሱን ሀሰተኛ፣ የጥላቻ፣ ግጭት ቀስቃሽ ሀሳቦችንና ምስሎችን ከማጋራት በመቆጠብ ዘመኑ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለሀገሩ መክፈል ይኖርበታል። ማህበራዊ ሚዲያውን ለበጎ ነገር ሊያውል ይገባል። ጠንክሮ ተምሮና ተመራምሮ ሀገሩን በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ ወዘተ ማዘመን ከወጣቱ የሚጠበቅ የዘመኑ መስዋዕትነት ነው።

ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሀገሩንና ወገኑን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል፣ ለሰላሙ ዘብ መቆም፣ የኃይላችን ሚስጥር የሆነውን አንድነታችን መጠበቅ፣ ችግሮቻችን በሰላማዊ መንገድ በድርድር በውይይት በመፍታት የሰላም ሀዋሪያ መሆን፤ እንዲሁም እጅ ለእጅ ተያይዞ በማልማት ሀገሩን ወደ ብልጽግና ማማ ማውጣት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ ዘመኑ የሚፈልገው መስዋዕትነት ነው።

ዛሬ ጳግሜን ሁለት የመስዋዕትነት ቀንን በማስመልከት መስዋዕትነት ከፍለው ይቺን ለምለም ሀገር ለትውልድ ያሻገሩ አባቶቻችን በማመስገን እንዲሁም ለሠራዊቱ እና የፀጥታ አካላት ክብር በመስጠት ቀኑን አስቦ ከመዋል ባለፉ፤ ሁሉም ዜጋ ዘመኑ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነቱን በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅበታል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You