ለሀገራዊ ብልጽግና ለሰላም ለሚከፈልመስዋዕትነት ራሳችንን እናዘጋጅ!

 መስዋዕትነት ከእውነተኛ ፍቅር የሚመነጭ የራስን ሕይወት አሳልፎ እስከመስጠት የሚደርስ ማህበራዊ እሴት ነው። በዚህ እሴት የሚገራ ትውልድ እና ማሕበረሰብ ዘመናትን የሚሻገር ራስን የመሆን ነጻነት፤ በራስ የመተማመን ስነልቦናዊ ምሉዕነት ባለቤት ነው።

እኛ ኢትዮጵውያን ታሪካችን ስለ ነጻነታችን እና ብሔራዊ ክብራችን በተከፈሉ መስዋዕትነቶች የደመቀ ነው። ይህ ከትውልድ ትውልድ ሲቀባበል የመጣ የማንነታችን እሴት ዛሬ ላይ ላለው ትውልድ የማንነት ሰንደቅ ከመሆን ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ መገለጫችን ከሆነ ዘመናት ተቆጥረዋል።

በየዘመኑ በተከፈሉ መስዋዕትነቶች የተገነባው ሀገራዊ የነጻነት ትርክታችን፣ እንደ ሀገር የነጻነት ተምሳሌት አድርጎናል፤ በየዘመኑ ለተደረጉና አሁንም ለሚደረጉ የነጻነት የመስዋዕትነት ትግሎች የስነ ልቦና አቅም በመሆን ለስኬታማነታቸው ጉልበት ሆኖ አገልግሏል፤ እያገለገለም ይገኛል።

ከአባቶቻችን የሀገር ፍቅር እና ለነጻነት ካላቸው ቀናኢነት የሚመነጨው ይህ የመስዋዕትነት ትርክታችን፤ በየዘመኑ ስለሀገራቸው መሞትን እንደ ክብር የሚቆጥሩ ትውልዶችን ማፍራት አስችሏል። ከዚያም በላይ አስተሳሰቡ በትውልዶች የአዕምሮ ውቅር ውስጥ ሰፊ ቦታ አግኝቶ ስጋና ደም እንዲለብስ ረድቷል።

እንደ ሀገር በየዘመኑ ጦር ሰብቀው የመጡ ወራሪ ኃይሎችን ከፍ ባለ ተጋድሎና መስዋዕትነት አሳፍሮ በመመለስ ነጻነት የትውልዶች ሰንደቅ የሚሆንበትን መንፈሳዊ ልእልና በትውልዶች ማንነት ላይ መትከል ተችሏል።

ይህ በመስዋዕትነት በትውልዶች ላይ የተገነባ የአዕምሮ ውቅር እና መንፈሳዊ ልዕልና አሁን ያለችውን፣ የነጻነት ሰንደቅ የሆነችውን፣ ኢትዮጵያን ፈጥሯል። በሀገሩ ነፃነት በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ የማይደራደር ትውልድ መፍጠር አስችሏል።

በቀጣይም ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚሆነው ይህ የመስዋዕትነት ትርክታችን፣ ዛሬ ላይ ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ ሊገራ እንደሚገባ፣ ለዚህ የሚሆን ስነ ልቦናዊ ሆነ መንፈሳዊ ዝግጁነት መፍጠር የዚህ ትውልድ ኃላፊነት እንደሆነ ይታመናል።

ያለንበት ዘመን ነጻነት እንደ ቀደሙት ዘመናት ከሀገር ሉአላዊነት እያለፈ መገለጫው እየበዛ ነው። እያንዳንዱ ዜጋ ይህንን እውነታ በአግባቡ መረዳት፣ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ በተጨባጭ መንገድ መግለጽ ይጠበቅበታል።

በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የቀደሙት አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት ያስረከቡንን ሀገር፣ ነጻነቷን ምሉዕ አድርጎ ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ዛሬ ላይ ቀናብለን እንድንሄድ ያስቻለንን የብዙ መስዋዕትነት ፍሬ የሆነውን ነፃነታችንን የሚሸከም ኢኮኖሚያዊ አቅም መገንባት፤ ለዚህ የሚሆን የመስዋዕትነት ዝግጁነት መፍጠር ይጠበቅብናል።

እንደ ትውልድ ለሀገር ያለን ፍቅርም ሆነ ለነጻነት ያለን ቀናኢነት የሀገርን ሉአላዊነት ከማስከበሩ ጎን ለጎን ሀገር በኢኮኖሚው ከፍታ አግኝታ፤ በዓለም አቀፍ አደባባዮች በተሟላ ነጻነት ቀና ብላ የምትራመድበትን፤ በዚህም የዜጎች የማንነት ክብር ልዕልና የሚገዝፍበትን አዲስ የመስዋዕትነት ትርክት ልንፈጥር ይገባል።

እያንዳንዱ ዜጋ በራስ ወዳድነት ላይ ከተዋቀረ የማንነት ግንባታ መጥቶ ሀገርንና ሕዝብን ታሳቢ ወደሚያደርግ፤ ሀገራዊ ነጻነት እና ከዚህ የሚመነጭ ብሄራዊ ክብር/ኩራት ሊፈጥር ወደሚችል አዲስ ሀገራዊ ትርክት ግንባታ ሁለንተናውን ማዞር ይኖርበታል።

ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ ለኢኮኖሚ ልዕልናቸው መሰረት ለሆነው ሰላም የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ለመክፈል መንፈሳዊ፣ አዕምሯዊና ስነ ልቡናዊ ዝግጁነት መፍጠር ያስፈልጋል፤ ሰላም በሁለንተናዊ መገለጫው የቀጣይ ትውልዶች ብሔራዊ እሴት ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል መሰረት መጣልም ያስፈልጋል።

ይህን ማድረግ መቻል የነጻነትን ሙሉ ጣዕም ማጣጣም፤ በመስዋዕትነት ለደመቀው ሀገራዊ ትርክታችን ተጨማሪ ሞገስና ክብር ማጎናጸፍ ነው። የዛሬዋን ቀን የመስዋዕትነት ቀን ብለን ሰይመን በአዲስ ቀለም ስናከብራትም ይህንን እውነታ ታሳቢ በማድረግ ነው !

አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You