አገልጋይነት  የሕዝብ እርካታ መመዘኛ

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ጳጉሜን 1ን የአገልግሎት ቀን ሲል ሰይሟል። ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ ያደረገችንን ጳጉሜን ልዩ ልዩ መልዕክት ባላቸው ሕዝባዊ መንፈሶች በማክበር አሳልፈናል። ዘንድሮም በተመሳሳይ ‹የአገልግሎት ቀን› ስንል ጀምረናል።

ጳጉሜን የአዲስ ዓመት መግቢያ በር እንደመሆኗ አዲሱን ዓመት በተለየ መንፈስ ለመቀበልና ከመጠቀም አኳያ አገልጋይነት የሚለው ቃል ጥሩ አድርጎ ይገልጻታል። ባለን ሙያና ኃላፊነት ሀገራችንን እና ሕዝባችንን ከምንጠቅምበት መንገድ አንዱ አገልጋይነት ነው።

አገልጋይነት በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል። የማኅበረሰብን እርካታ መሠረት ያደረገ መንግሥታዊም ሆነ ግለሰባዊ ግልጋሎት አንዱና ዋነኛው መገለጫው ነው፤ ከዚህ በተጓዳኝ ወደአንድነት በሚመሩን የአብሮነት መንፈሶች ውስጥ መገኘትም ሌላው ሀገርን የማገልገያ መንገዳችን ነው።

አገልጋይነት በአንድ ነጠላ እውነት ብቻ የሚቋጭ አይደለም። ከምናስበው ሃሳብ ጀምሮ አገልጋይነትን ማንጸባረቅ እንችላለን። ሃሳባችን አድጎና ጎልቶ ነው በማኅበረሰቡ ውስጥ ተግባር ሆኖ የሚታየው። እናም በጎ ሃሳብ ከማሰብ ጀምሮ የአገልግሎት አድማሳችንን ማስፋት እንችላለን።

የአገልግሎት ቀን መጪውን አስራ ሁለት ወራትና ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በሥራ ባህል፣ በሰጥቶ መቀበል ለማሳለፍ እንድንችል የተነሳሽነት መንፈስን የሚፈጥር ነው። እርካታን መሰረት ያደረጉ ውጤት ተኮር ግልጋሎቶች የተነሳሽነት አቅምን ከማጎልበት ባለፈ የሥራ ልምዳችንንም ያነቁታል። በብዙ የምንታማበት የስንፍና ፤ የመጠበቅ አባዜያችንን ያስቀርልናል።

የአገልጋይነት ጽንሰ ሃሳብ በመጠበቅ ወይም ደግሞ ራስን ብቻ ማዕከል አድርጎ በመኖር የሚገለጽ ሳይሆን ሌሎችን እያሰቡና ለሌሎች በመኖር የሚገለጽ ነው። የሀገር እድገትና ብልጽግና ዛሬ ላይ እያገለገልነው ባለው የማኅበረሰብ እርካታ የሚለካ ነው። እርካታ የእድገት መመዘኛ ነው።

ማገልገልና መገልገል የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። አንዳቸውን ከአንዳቸው ነጥለን ማየት አንችልም። ስናገለግል ነው የምንገለገለው። ስንሰጥ ነው የምንቀበለው። ሀገር ስንጠቅም ራሳችንን እየጠቀምን ነው። ማኅበረሰብ ስናገለግል ትውልዱን እያገለገልን ነው። ምንም ይሁን አሁን ላይ ለሀገራችን እየሰጠን ያለነው ነገ ላይ እኛ በእጥፍ ከሀገራችን የምንቀበለው ነው።

ብዙ ጊዜ መገልገልን የምንመርጥ ነን። ሀገራችን አገልጋያችን፣ መንግሥት አሳቢያችን እንደሆነ የምናምን ነን። እርግጥ ነው መንግሥት ጠባቂያችን ሀገር ደግሞ መጠለያ ናት። ይሄ እውነት ትርጉም የሚያገኘው ግን እኛ የአገልጋይነት ኃላፊነታችንን ስንወጣ ነው። ኃላፊነታችን ደግሞ ሀገርን በማገልገል የሕዝብን እርካታ ማረጋገጥ ነው።

ዓለም አቀፉ የኢኮኒሚስቶች ማኅበር ሀገርና ማኅበረሰብ የተዋሃዱበትን መነሻ ጽንሰ ሃሳብ ሲተነትን ከሁሉም ልክ ሆኖ ያገኘው እውነት አገልጋይነት የሚለውን ነው። በአገልጋይነት ውስጥ አሁናዊ የማኅበረሰቡን ፍላጎት ከማሟላትና የትውልዱን ጥያቄ ከመመለስ አንጻር ይሄ ነው የማይባል ሚናውን ማየት እንችላለን።

ትላልቅ የስኬት በሮች በማኅበረሰብ እርካታ በኩል የሚከፈቱ ናቸው። እንደሀገር ያስቀመጥናቸው የማደግና የመለወጥ ግቦች አገልጋይነትን ታከው የሚመጡ ናቸው። እውነትና ፍትህን በተጋራ አእምሮና ልብ የምንሠራው፣ የምናስበው ሃሳብና ምግባር ከድህነትና ከኋላቀርነት ሊያወጣን አቅም አለው።

በአዲስ ዓመት መግቢያ በጳጉሜን ደጃፍ ላይ ቆመን በጋራ የምንከብርበትን የአገልጋይነት ቀን፤ ሀገራችንን ብሎም ራሳችንን ከዛም አልፈን ትውልዶችን ተጠቃሚ ለሚያደርገው የአገልጋይነት መንፈስ ራሳችንን የምናነቃቃበትና የምናድስበት ነው።

ሀገራችንን ለማገልገል የሚያንስ እውቀት፣ የሚያንስ ተፈጥሮ የለም። እኛ ሰፊ ሕዝብ፣ ሰፊ መሬት፣ ሰፊ ወጣት፣ ሰፊ ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን። ሁሉ ኖሮን አይደለም ለሌላ ለራሳችን መብቃት አልቻልንም። ለዚህ የእኔነት መንፈሶች ተግዳሮቶች ሆነው ይዘውናል። ከእኔነት በጸዳ የአገልጋይነት መንፈስ እስካልመጣን ድረስ ነገም ስንዴ ለማኝ እንደሆንን መቀጠላችን የማይቀር ነው።

ተያይዘንና ተግባብተን በአንድነት መቆም ከቻልን እንደጥንቱ ጊዜ ዓለምን የሚያስገርም ኃይል መፍጠር እንችላለን። ከራሳችን አልፈን በነጻነት አፍሪካን፣ በሰላም ደግሞ ዓለምን አገልግለናል። እነዛን ወንዝ ተሻጋሪ የአገልጋይነት መንፈሶች መልሰን ከድህነት እና ከተረጂነት ለመውጣት ጊዜው አሁን ነው።

ባለን ነገር ሁሉ ሕዝባችንን ማገልገል እንችላለን። በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን የእኛን እርዳታ የምትፈልግበት ጊዜ ላይ ናት። በኑሮ ውድነት፣ በሰላም እጦት በብዙ ማኅበራዊ ቀውሶች ውስጥ ነች። እነኚህ ሀገራዊ ውጥንቅጦች እልባት እንዲያገኙ በአገልጋይነት መንፈስ መታደስ አለብን።

አሁናዊ ችግሮቻችንን ለማሸነፍ ሁሉን አቃፊ የአገልጋይነት ስነልቦና ያስፈልገናል። ሰላምን ሊያመጣ በሚችል፣ አንድነትን ሊፈጥሩ በሚችሉ ሀገራዊ ትብብሮች ላይ በንቃት መሳተፍ አንዱ የአገልጋይነት መገለጫ ነው። ሰላም ስናመጣ፣ ለሰላም ስንለፋ ሀገር አገልግለናል ማለት ነው። ተነጋግረን ስንግባባ፣ ተግባብተን አብረን ስንቆም በሰላም እጦት የሚደርሱ ማኅበራዊ ቀውሶችን ተከላክለናል ማለት ነው።

ሀገር ለማገልገል ካለንበት መጀመር እንችላለን። ምርጡ አገልጋይነት ከቅርብ ጀምሮ ወደሩቅ መሄድ ነው። ከቤት ወደጎረቤት፣ ከጎረቤት ወደአካባቢ ከዛም ወደሀገር። በጽኑ ፍላጎት ውስጥ ከቆምን ሀገር ለማገልገል መንገድ አናጣም። ባለን እውቀት፣ ባለን ጸጋ፣ በተሰማራንበት ዘርፍ በቅንነትና በታማኝነት በመቆም ሀገር ማገልገል እንችላለን። እንዲህ አይነቱ የአገልግሎት መንፈስ ነው በማኅበረሰብ እርካታ ተለክቶ ሀገርን ወደፊት የሚያራምዳት።

ብዙዎቻችን እያወቅን የምንስት ነን። ባለን ኃላፊነት ሀገር ከማገልገል ይልቅ ራሳችንን ወይም ደግሞ ጥቂት በማገልገል የምንደክም ነን። እንዲህ ዓይነቱ ኢ- ፍትሐዊ ግልጋሎት ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የለም። አገልጋይነት በእርካታ የሚመዘን የብዙኃኑ ቅቡልነት ነው።

ከሕዝብ ላይ እየሰረቅን፣ በሙስናና በብልሹ አሠራር ተጨማልቀን የምንፈጥራት ኢትዮጵያ የለችም። በእኔነትና በጎጠኝነት ተጠፍረን በግራ እየተቀበልን በቀኝ የምንሰጥ ከሆነ የሀገር ፍቅር አልገባንም። ቢሯችንን ለፀሐፊ ትተን፣ ባለጉዳይ እያጉላላንና በቀን ለሃምሳ ጊዜ የሻይ እረፍት እያልን ሥራ የምንበድል ከሆነ የአገልጋይነት ጽንሰ ሃሳብ ገና አልገባንም። ስልጣንን ተገን አድርገን የሀገርን ሀብት ለግል ጥቅማችን የምናውል ከሆነ ከተጠያቂነት ባለፈ ባለእዳ ነን።

ንጹህና ነውር የሌለበት አገልጋይነት ታማኝነትን ያስቀደመ፣ እውነትና ፍትሕን ያስከተለ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለማኅበረሰብ መልፋትን መርህ ያደረገ ነው። በእንዲህ ባለው ብዙኃኑን ባስቀደመ አቃፊ ሥርዓት ስንራመድ ብቻ ነው ሀገር የምንለውጠው። ሀገር የድርጊት ውጤት ናት። የዛሬዋ ኢትዮጵያ በትናንት ድርጊታችን ተፈጥራለች። የነገዋን ኢትዮጵያ በአዲስ መንፈስ እንድትፈጠር ሀገር የቀደመበት፣ ሕዝብ የለጠቀበት እውቀትና ሥርዓት ያስፈልገናል።

አገልጋይነትን ሽራ ሀገሬን ባዶ ያስቀረች ‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል› የምትል አንድ ነውረኛ አባባል አለች። ባለስልጣናትን ከኃላፊነት የምታጎል፣ ከእውነት የምታርቅ ጸያፍ አባባል። እንዲህ ያሉ ከጨዋነትና ከሥነምግባር ያፈነገጡ አባባሎች ሕዝባዊ ሳይሆኑ ግለሰባዊ ናቸው። የሆኑ ሆዳም ቡድኖች ሌብነትን ለማበረታታት እና እኔነትን ለማራመድ ሲሉ የሚፈጥሯቸው ናቸው።

እውነተኛ ሹም ሀገር ይጠቅማል፣ ሕዝብ ያገለግላል እንጂ ከድሀ ሀገር ላይ አይሰርቅም። ሀገር ጠቅሞ የተሻረ ባለስልጣን በዓለም ታሪክ የለም። የሚሻሩ፣ የሚገለሉ አገልጋይነትን የማያውቁ ሌቦች ናቸው። ራስን ከመጥቀም አኳያ የሚታዩ አንዳንድ ክፍተቶች ተስተካክለው ሕዝብ ተኮር በሆነ የአገልጋይነት ስሜት ቢተኩ የምንሻትን ኢትዮጵያ ይሰጡናል።

የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የማኅበረሰቡን ጥያቄ ከመመለስ ጎን ለጎን በበረታ አመራርና ንቃት የአገልግሎቱን ዘርፍ ሕዝብ ተኮር፣ ውጤት ተኮር እንዲሆን መሥራት ነው። እንዲህ ባለው ጠንካራ አሠራር ውስጥ አገልጋይነት አብቦ ሀገር ፍሬ ታፈራለች፤ ሕዝብም ርካታውን በይበልጥ ይገልጻል። ሌቦች ቢኖሩ እንኳን ለሌላው ማስተማሪያ በሚሆን ቅጣት ከስህተቶቻቸው ተምረው ወደአገልጋይነት እንዲመለሱ ይደረጋል።

በአንዲት ‹አገልጋይነት› በምትል ትንሽ ቃል ሁለንተናዊነትን ሥርዓት መግለጽ ይቻላል። በፖለቲካው በማኅበራዊው ያለው እንቅስቃሴ ሁሉ በዚህ ቃል ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። ጳጉሜን በዚህ ስሜት ስንጀምር አዲሱን ዓመት ሀገር ተኮር በሆነ የአገልጋይነት ንቅናቄ እንድንጀምር፤ ጀምረንም እንድንቀጥል እድል ይሰጠናል።

ከሁሉም ትልቁ ሉዓላዊነት እንኳን ከአገልጋይነት የሚነሳ ነው። ውጤት እና እርካታ ተኮር የሆነው ይሄ እሳቤ ችግሮቻችንን እየቀረፍን በበረታው እንድንቀጥል የጎላ ድርሻ አለው። ብዙኃነት መታወቂያ የሆነች ሀገር ሁሉንም በአንድ ለማስተናገድ ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ አያስፈልጋትም።

በማገልገል መገልገል የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳይ ነው። ከዚህ ባለፈም የሀገር ፍቅር ከሚገለጽባቸው መንገዶች ውስጥ የመጀመሪያው ነው። ሀገር ማለት ሰው ነው ስንልና ሰው ማለት ሀገር ነው ስንል መገለጫው አገልጋይነት ነው። አገልጋይነት በሌለበት ወይም ባልተካተተበት ወይም ሙሉ ባልሆነበት ሥርዓት ውስጥ የሚመጣ ለውጥ የለም።

የለውጥ ፍልስፍና ከሕዝብ በሕዝብ ለሕዝብ ነው። ይሄ ማለት ሁላችንም ያለንበት፣ ሁላችንም የተሳተፍንበት ማለት ነው። ጋን በጠጠር እንደሚቆም ሀገርም የምትቆመው ዛሬ ላይ እኔ እና እናተ በምናዋጣው ሃሳብ እና ሥነ ምግባር ነው። ይሄ ሁሉ በአንድነት አገልጋይነት ተብሎ ይጠራል። አገልጋይነት መንግሥትና ሕዝብ ያሉበት፣ የእኔ የአንተ የሁላችን ትብብር ነው።

አዲሱን ዓመት ሀገር ተኮር ለማድረግ ሕዝብ የቀደመበት አገልጋይነት ሚናው ላቅ ያለ ነው። ታሪኮቻችንን ለመቀየር፣ ችግሮቻችንን ለመፍታት የትብብር መንፈስ ዋጋው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በእኔ ውስጥ እናንተ፣ በእናንተ ውስጥ እኔ በሌላው ውስጥም እንዲሁ በስተመጨረሻም የረካችና የበቃች ኢትዮጵያን መውለድ እንችላለን።

ሀገር በማቆም ሂደት ውስጥ የሕዝብ ርካታ ቀዳሚው ነው። ዛፍ በስሩ እንደሚጸና ሁሉ የሀገር ጽናትም በአገልጋይነት በኩል የሚንጸባረቀው የሕዝብ ርካታ ነው። በሥራችን ሕዝብን ማስደሰት በየትኛውም ሙያ ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ኃላፊነት ነው።

በአንድ ሀገር ውስጥ የሕዝብ ይሁንታ የምንም ነገር መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። አንድን መንግሥት፣ አንድን የመንግሥት ባለስልጣን፣ አንድን ዜጋ ምን ሠራ ብሎ ሊመዝነው የሚችለው የሕዝብ ርካታ ነው።

በጳጉሜን አፋፍ ላይ አሮጌውን ዓመት ወደ ኋላ ጥለን፣ በሐምሌና በነሐሴ ጭጋግ ላይ ተንጠራርተን ወደአዲሱ የብስራት ዓመት አሻቅበናል። ቸር እንድናይ፣ ቸር እንድንሰማ ፤በአገልጋይነት፣ ከኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ…በእኛ ከእኛ ለእኛ በሆነ የአብሮነት መንፈስ ወደአዲሱ ዓመት ጉዞ ጀምረናል።

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን    ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም

Recommended For You