የግንቦት ወር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚገኙ ወጣቶች ለየት ያለ መሆኑ ይነገራል፡፡ ቅጠላቸውን አርግፈው የተንጨፈረረ የቅርንጫፍ ዘለላ የተሸከሙ ረዣዥም ዛፎች፤ ለምለም አረንጓዴ ቅጠል ማልበስ ይጀምራሉ፡፡ ሲረግጡት ከሥፖንጅ ባልተናነሰ ትንቡክ ፣ትንቡክ የሚለው ለም አፈር (መሬት) የሚያካፋበትን ብናኝ ዝናብ ተቀብሎ ፈጣን ምላሽ ይሰጣል ። ከሰደድ እሳት የተረፉ የሳር ጉቶዎች ጨሌ ያበቅላሉ፡፡ የተለያዩ የሀረግና የዛፍ ቁጥቋጦዎች ለጋ የቅጠል ዘለላዎች (ቀንበጦች) አዝለው እዚህም እዚያም እይታን ይስባሉ፤ ውብ ስሜትም ይፈጥራሉ፡፡
በዚህ ወቅት ኧረ የወጣት ያለህ? ተብሎ ቢታሰስ ከአካባቢው (ከሰፈሩ) ወጣት ማግኘት አይታሰብም:: ጤናው ያልታወከና ለአቅመ እርፍ መጨበጥ የደረሰ ጎረምሳ ከግንቦት ልደታ ማግስት ከቤት አይውልም:: ነውር መሆኑንም ወጣቶች ይናገራሉ::
ከመኖሪያ ቀያቸው ርቆ የሚገኘውን የእርሻ ማሳቸውን በሬ ጠምዶ ለማረስ በሚያስችል ደረጃ አሰናድተው የሚጨርሱበት መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ አልፎ አልፎም በቆሎ፣ ዘንጋዳ (በአካባቢው አጠራር ቦቤ) በመዝራት ላይ የሚጠመዱበት ጊዜ ነው ባሳለፏቸው አመታት ፡፡
ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በክልሉ በተለይም በመተከል ዞን በቅርቡ ከተነሱ ግጭቶች ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከላይ ያነሳሁላቸው መደበኛ የእርሻ ሥራዎችን ማከናወን ቀርቶ ወጥቶ መግባት ስጋት እየሆነባቸው እንደሆነ ወጣቶች ይናገራሉ፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአካባቢው የሚኖሩ ወጣቶች አስተያየት ምን እንደሆነ ጠይቀናቸው የሰጡንን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል? ለችግሮቹ መፍትሄ ከማፈላለግ አንጻር በግጭቱ ምክንያት ቂምና በቀል እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ፣ የሕዝቦቹን የበፊት አንድነት በመመለስ በኩል፣ የነበረው ሰላም ተመልሶ መደበኛ ሥራና መደበኛ ሕይወት መቀጠል እንዲቻል በማድረግ ዙሪያ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ወጣቶቹ ይናገራሉ፡፡
ወጣት አየነው ደምሴ ተወልዶ ያደገውና የሚኖረው በዳንጉር ወረዳ ነው፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር በእርሻ ሥ ራ የ ሚ ተ ዳ ደ ር ነበር፡፡ ዘንድሮ በአካባቢው በተፈጠረው ችግር ምክንያት ከቤተሰቦቹ ጋር ቀዬውን ለቋል፡፡ በዚህ ምክንያት ዘንድሮ አርሶ መብላት ከባድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ እስከ አሁን የሚስተዋለው ሁኔታም የመፈራራትና የሥጋት ድባብ ነው፡፡
ወጣቶች ከመንግስት ጋር ሆነው ሰው (ማህበረሰቡ) የሚተማመንበት ሰላም እንዲመጣ በተገቢው መስራት አለባቸው፡፡ አሁን በካምፕ ለተጠለለው ሕዝብ የሚደረገው ድጋፍም ከርሃብ የሚያድን አይደለም፡፡ ሥለዚህ ወደ ቀየው ተመልሶ እንዲሰራ መደረግ አለበት፡፡ የአካባቢውን ሰላም ሕብረተሰቡ ራሱ ማስጠበቅ አለበት፡፡ መንግስትም ማገዝ ግዴታው ነው፡፡ ይህ ካልተደረገ ከዚህ የከፋ ችግር ቀጣይ ይመጣል የሚል ሥጋት አለኝ ሲል ተናግሯል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የፓዊ ልዩ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ጌታቸው ሀይሌ እንደገለጸው የተፈጠረውን ችግር በሕዝቦች መካከል የተፈጠረ እንዲመስል ሰፊ የተንኮል ሥራ ተሰርቷል:: ምንም በማያውቁት የጉሙዝ ብሔረሰብ ሕጻናትና እናቶች በግፍ ሕይወታቸው ጠፍቷል:: በርካታ የሚያሳዝኑ ድርጊቶች ተፈጽመዋል፡፡ ማንሳት አልፈልግም፡፡ መጠኑ በውል የማይታወቅ ሐብትና ንብረት ወድሟል፡፡ በዚህ የተነሳም አሁን በርካታ ሕዝብ አካባቢውን ለቆ ለችግር ተጋልጦ ቁራሽ እንጀራ አጥቷል፡፡
አሁን በ አ ገ ር ሽማግሌዎች እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ከፌዴራል እስከ ክልል ባለስልጣናት በአካል እየመጡ ሕዝብ በማወያየት ላይ ናቸው፡፡ ሥለዚህ በአማራ ብሄር በኩል የተወከሉ የአገር ሽማግሌዎች በደንብ ከወጣት እስከ አዛውንት ድረስ ማግባባትና ማሳመን አለባቸው፡፡ በሆዱ ቂም ማሳደር የለበትም፡፡
በጉሙዝ ማህበረሰብ በኩል የተመረጡትም ወጣቶችን ለብቻ አወያይተው ማሳመን አለባቸው ። እናቶችና አዛውንቶችም በተገቢው ሐሳባቸውን ገልጸው እንዲወያዩ ካልተደረገ ዘላቂ ሰላም አይመጣም፡፡
የጉሙዝ ወጣቶችም ይሄ ችግር በቀል በበቀል እየተተካ የሚቀጥል ከሆነ ሄዶ ሄዶ ለከፋ ችግር የሚጋለጠው ወጣቱ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ወጣቱ ተስፋ ሊኖረው ይገባል፡፡ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ፣ሕብረተሰቡም ወደ ቦታው ተመልሶ አብሮ ተከባብሮ እንዲኖር ከፍተኛ ሥራ መሰራት አለበት፤ዘላቂ በሆነ መንገድ ሲልም ወጣት ጌታቸው ይናገራል፡፡
በዚህ ደረጃ እየተለየ ከተወያየና ወጣቱ ሐሳቡን እንዲሰነዝር ከተደረገ የተሻለ ሰላም ሊፈጠር ይችላል፡፡ የተወናበደው አስተሳሰብም እየጠራ ይሄዳል ብሏል፡፡
አሁን እኮ በርካታው ወጣት ሆን ብለው ጥቅም የሚፈልጉ አካላት ሕይወቱን ለምስቅልቅል
እንደዳረጉት ያስባል፡፡ ወንድሙን፣እህቱን፣ልጁንና ቤተሰቡን ያጣው አካል ደግሞ የሚያስበው በጣም የተለየ ነው የሚሆነው፡፡ ሥለዚህ በባህላዊ እርቅና ምህላ የአገር ሽማግሌዎች ቁስሉና ቂሙ እንዲሽር ማስታረቅ አለባቸው፡፡ መንግስትም በንጹሃን ደምና ሕይወት የቀለዱትን ወንጀለኞች በአፋጣኝ ለሕግ አቅርቦ ማሳየት አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ሕብረተሰቡም ወጣቱም ይረጋጋል የሚል እምነት እንዳለው ወጣት ጌታቸው ገልጿል፡፡
በመተከል ዞን የማንዱራ ወረዳ ነዋሪው ወጣት አሰፋ አያኖ በበኩሉ፤ እንደ ወጣት ብዙ ነገር መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ምክንያቱም ቀላልና ውሀ የማያነሳው የሁለት ሰው ጠብ ለዚህ ሁሉ ጥፋትና ሞት አያደርስም፡፡ ከዚህ በፊት እኮ ከዚህ የባሱ ችግሮች እየተፈጠሩ ወዲያው ሲፈቱ አይተናል፡፡ ይሄ ሕዝብ በጣም ተዋድዶና ተከባብሮ የተፈጠረና እየኖረ ያለ ነው፡፡ አሁን በዚህ አይነት ሕይወቱ ውስጥ መርዝ የረጨ የጥፋት ኃይል አለ ይላል ወጣት አሰፋ፡፡
‹‹ከህዝቡ በላይ እኔ አውቅልሃለሁ፣እኔ አስብልሃለሁ እያሉ የሚያዋጉ እሾህ የፖለቲካ ሰዎች እጃቸውንና ጭምብላቸውን ከሕዝቡ ላይ እንዲያነሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወጣቱ ከፍተኛ ሚና መጫወት አለበት፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር እኩል ሰላም እንዲመጣ መጣር ያስፈልጋል፡፡ ሁላችንም ዘግናኝ ግፍ ተፈጽሞብናል፡፡ የጉሙዝ ማህበረሰብ የግፍ ጭፍጨፋም ይዘገንናል፤ያሳዝናል፡፡
‹‹ነገር ግን ከሰላም በስተቀር ሌላ ምን አማራጭ አለ? አርቆ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ቂምና በቀል የሚቆምበት ቦታና ጫፍ የለውም፡፡ በፈጣሪም በጣም የተከለከለ ጉዳይ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ በዚህ ዘመን በቀል አያስፈልግም ባይ ነኝ፡፡ በጋራ የሺናሻ፣ የአማራ፣ የጉሙዝና ሌሎችም ብሔር ወጣቶች አንድ ሆነን የተሰነዘረብንን ችግር መመከት አለብን::›› ሲልም ወጣት አሰፋ አመልክቷል፡፡
ከጥንት ጀምሮ የማህበረሰባቸውን ሰላም የአገር ሽማግሌዎች ያስጠብቃሉ፡፡ አሁንም ያደርጋሉ:: እኔ አሁን 28 ዓመቴ ነው፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከአገር ሽማግሌ በላይ የሆነና መፍታት ያልቻሉት ጠብ አይቼም፤ ሰምቼም አላውቅም፡፡ መንግስት የራሱን ሥራና ኃላፊነት ለይቶ መስራትና መወጣት አለበት፡፡ ከሁሉም ብሔር የምንገኝ ወጣቶች መድረክ ፈጥረን መወያየት ይገባናል፡፡ አካባቢው ሰላም ሆኖ መደበኛ ሥራችንን ያለመሳቀቅ መስራት እንድንችል ርብርብ እንድናደርግ ጥሪየን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ሲል ወጣቱ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ወጣት አያንቱ በከሬ በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ነዋሪ ናት፡፡ በዞኑ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር በቀላሉ መታለፍ የለበትም፡፡ በሕዝቡ መካከል የሌለ ሥሜት እየፈጠሩ ሰላም ማደፍረስ መቆም አለበት፡፡ በሕዝቡ በውይይት ያነሳውን በሚገባ መስማቷን ታስታውሳለች፡፡
“ሰው ዥንጉርጉር ሆኖ የተፈጠረው ዛሬ አይደለም፤ ይህ የፈጣሪ ስራ ነው፡፡ ቀይ ጥቁር እየተባባልን ልንፋጅ አይገባም!” ነበር ያሉት የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች፤
‹‹እኛ ተከባብረን፣ተቻችለን እና ጥቁር ቀይ ሳንል አብረን በልተን፣አብረን ጠጥተን የኖርን ሕዝቦች ነን፡፡ ለእኛ አብሮ መኖር አስተማሪ ፖለቲከኛ አያስፈልገንም፡፡ ሥለዚህ እባካችሁ የፖለቲካችሁን ጦስ እዚያው ያዙልን፡፡ እዚህ የምስኪኑን ገበሬ ልጅ የፈላ ጥይት ማብረጃ አታድርጉት›› የሚል በሕብረተሰቡ በምሬት መነሳቱንም ተናግራለች፡፡
እኛ እንደ ወጣት የሚከናወኑ የሰላምና የእርቅ ሂደቶች መደገፍ አለብን፡፡ መንግስትም አጥፊዎችን (ተጠርጣሪዎችን) በቤኒሻንጉልና በጃዊ ከ63 ሰዎች በላይ ለይቻለሁ ማለቱን ገልጻለች፡፡ ይህ በራሱ በቂ አይደለም፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር ተፈልፍለው እያደሩ በሕዝብ ደም የሚነግዱ ፖለቲካ ፓርቲ ነን ባዮችን መፈተሽ አለበት፡፡ በራሱ በመንግስት መዋቅሩ ውስጥ በየደረጃው በተዋረድ ያሉ አመራሮች ሊበጠሩ ይገባል፡፡
ማህበረሰቡም ከለመደው የተለየ ነገር በሚያስተውልበት ጊዜ መጠራጠርና ለሚመለከተው በማሳወቅ ማጣራት ተገቢ ነው፡፡ ወጣቶች ነቅተን የማንታገል ከሆነ፣ለሰላማችን ዘብ ካልቆምን ለነገ ተስፋ አይኖረንም፡፡ ሥለዚህ ያለፉት አይነት አሰቃቂና አሳፋሪ ድርጊቶች በመካከላችን በምንም አይነት መንገድ መከሰት ቀርቶ መታሰብ የለባቸውም:: ወጣቶች ሥለ ሰላም መወያየት ይኖርብናል፡፡ በአገር ሽማግሌዎች የተጀመሩ የሽምግልና ሂደቶች እንደ የባህሉ በዳይ ለተበዳይ የሚደረገውን ሁሉ ፈጽሞ ቂምና በቀልን የሚሽር ዘላቂ ሰላም የሚፈጥር እርቅ እንደሚገለፅም ሙሉ እምነት አለኝ ሥትል ወጣት አያንቱ አስተያየቷን አጋርታለች፡፡
በአጠቃላይ ወጣቶቹ የአካባቢው የሰላም ሁኔታ አስተማማኝ እንዲሆን፤ ከፍርሃትና ከሥጋት ሕብረተሰቡ ተላቆ ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ መመለስ አለበት፡፡ ለዚህም ወጣቶች ሰላማችን ተረጋግጦ እርሻችንን እንድናከናውን የድርሻችንን ማበርከት ይኖርብናል በማለት አስተያየታቸውን አካፍለዋል::
አዲስ ዘመን ግንቦት 8/2011
ሙሐመድ ሁሴን