‹‹ፍርድ ቤቶች ለሕገወጥ መሬት ወራሪዎች የሚሰጡት ዕግድ ለሥራችን እንቅፋት ሆኖብናል››ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ

ለአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በሕግ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል ሕገ ወጥ ግንባታ መከላከል፣ ሕግ ወጥ የጎዳ ላይ ንግዶችን መቆጣጠርና ማስቆም ብሎም ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ከሕግ ያፈነገጡ አሠሮራችን መከላከል ዋና ዋና ሥራዎቹ ናቸው። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በዛሬው የተጠየቅ ዓምድ ዕትማችን ባለሥልጣኑ እነዚህን ኃላፊነቶቹን ከመወጣት አኳያ ምን እየሠራ ነው? ምን ምን ጉዳዮችስ እየፈተኑት ነው? ቀጣይስ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን በምን መልኩ እየሠራ ነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል።

 አዲስ ዘመን፡- የባለሥልጣኑ ከተሰጠው ተቋማዊ ተልዕኮ አንጻር የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በአዲስ አበባ እንደሚገኝ እንደማንኛውም አገልግሎት ሰጭ ተቋም በተለይ በ2015 ዓ.ም በከተማዋ ውስጥ የሚታዩትን የደንብ ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ለማረም፣ ለማስተካከል እና እርምጃ ለመውሰድ በርካታ እቅዶችን በማቀድ ወደ ስራ ገብቶ ነበር።

የ2015 ዓ.ም በጀት ዓመትን እቅድ ከመውጣታችን በፊት በ2014 ዓ.ም ያቀድናቸውን እቅዶች በዝግጅት ምዕራፋችን በደንብ ተመልከተናል። በዚህም በ2014 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ በሰጠን የሥራ ኃላፊነት ምን ሰርተናል? ምን ቀረን? የሚሉትን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖቻችንን ገምግመናል።

በዚህም ለ2015 ዓ.ም ሥራዎቻችን ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን ጨምረን እና ቀንሰን የተሻለ ሊያሠራ የሚችል የተቋሙን መሪ እቅድ አውጥተን ወደ ሥራ ገብተን ነበር። ከመሪ እቅዱም ባሻገር ከአስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች ባህሪ እና አቀማመጥ ጋር አያይዘን እቅድ አውጥተን አገልግሎት የሰጠንበት፤ ይህም ብቻ ሳይሆን 23 ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት በርካታ ሥራዎች ሠርተናል።

በከተማዋ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ መፍታት እንደየተቋሞች እና እንደየቢሮዎች በአዋጅ የተሰጡ የሥራ ኃላፊነቶች መሠረት ያደረገ በመሆኑ የደንብ ማስከበር ከ23ቱ ተቋማት ጋር ለመሥራት የሚያስችሉ እቅዶችን አውጥተን ወደ ስራ ገብተን ነበር። በእቅዱ ዙሪያ ከህብረተሰቡ እና ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተወያይተናል።

ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ጋር በምንሠራበት ጊዜ ምንድን ነው ተጋግዘን መሥራት ያለብን? ተቋሙስ የተሰጠው ተልዕኮ እንዴት ሊወጣ ይችላል? በሚሉት ላይ አትኩሮት ሰጥተን ሰርተናል። በዚህ መልኩም ወደ ትግበራ በመግባቱ ተቋሙ በ2014 አመርቂ ሥራዎችን መስራት ችሏል። ይህን የተሻለ አፈጻጸም ደግሞ በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ማስቀጠል አለብን ብለን ገምግመናል። በግምገማው መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሻለ እንደነበር ማሳያዎቹ ምንድን ናቸው? ከዚህ በፊት ከነበሩት አሰራሮቻችን ምን የተለወጠ ነገር አለ? የሚለውን በደንብ አይተናል።

አንድ ተቋም ደግሞ በአዋጅ እና መመሪያ ተቆጥሮ የሚሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም የተቋም ግንባታ እና አደረጃጀት ወሳኝነት አለው። ከዚህ አኳያ ባለሥልጣኑ የተቋም ግንባታው ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ከሙያተኞች እና ከአመራሮች ጋር በመቀናጀት ተቋማችንን ለመገንባት በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

በዚህ መሠረት በመጀመሪያ ደረጃ በተቋሙ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል የተሰጡንን ኃላፊነቶችን ለመወጣት የሚያስችል ደንብ ማርቀቅ ነው። ከዚህ አንጻር በ2015 ዓ.ም ደንብ አርቅቀን በሕዝብ በማስተቸት እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት አዋጅ 74/2014 የሚያጠናክር የደንብ ቁጥር 150/2015ን አጸድቀን ወደ ሥራ ገበተናል።

ደንቡን ሊያሠራ የሚያችሉ ሦስት የሥራ መመሪያዎችን አውጥተናል። ደንብ እና ሕግ የተሻሻለ እና የጠነከረ ከሆነ ተጠያቂነትም ይኖራል፤ ፍትሐዊነትን ማስፈን ይቻላል። ከዚህ አንጻር ባልስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በትክክል እንዲወጣ የሚያስችሉ ደንብ እና መመሪያዎችን አውጥቷል።

ሌላው በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተሠሩ ዐብይ ጉዳዮች መካከል ከፐብሊክ ሰርቪስ ጋር በመሆን በቢፒአር ጥናት መሻሻል ያለባቸውን ሥራዎች አሻሽለን ወደ ሥራ ገብተናል። በተቋሙ በርካታ የሲቪል ሠራተኞች አሉ። እነኝህ የሲቪል ሠራተኞች በፍላጎት እና በሞራል እንዲሠሩ የደረጃ እድገት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተለይም ከዚህ ቀደም የፓራ ሚሊቴሪ የተቋሙ ሠራተኞች የደመወዝ የዕድገት ደረጃ ለውጥ የሌለው እና በነበረበት የቆመ ነበር። ይህንን ለማሻሻል በማሰብ፤ ሰው በየችሎታው እና በአገልግሎቱ ልክ ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኝ ኃላፊነቱ እና ተጠያቂነቱም እንዲጨምር ለማድረግ በሚል ከፐብሊክ ሰርቪስ ጋር በመተባበር የኦፊሰሩን የሥራ እድገት እንዲያገኙ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል።

ከዚህ ባሻገር ፓራ ሚሊቴሪው ራሱን ችሎ ከከተማ ጀምሮ እስከወረዳ ድረስ የሚገኙ በመከላከል፣ በቁጥጥር እና እርምጃ ዘርፉ ውስጥ ያሉ የሥራ ሂደት እና አመራሮች በተቀናጀ ሁኔታ ከላይ እስከታች የዕዝ ሰንሰለቱ እየተሻሻለ እና ለግዳጅ አወጣጥ በሚያመች መልኩ እንዲደራጅ ያደረግንበት አሠራር አንዱ የተቋሙ ስኬት ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚስተዋለውን የከተማ እድገትና የወንጀል መበራከት ተገንዝቦ ከመስራት አኳያ ምን ሠርታችኋል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- ከተማችን እየሰፋች ከመሄዷ ጋር ተያይዞ የወንጀል አይነቶችም እየተበራከቱ መጥተዋል። እነኝህ ወንጀሎችን ለመከላከል እና ለመቀልበስ የሚያስችል ኃይል ማደራጀት በማስፈለጉ ከዚህ ቀደም ከነበሩን 5ሺ325 ነባር ኦፊሰሮች በተጨማሪ በዘንድሮው ዓመት ወደ 1ሺ110 ኦፊሰሮችን ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች መልምለን ወደ ሥራ ለማስገባት በሂደት ላይ ነን። በቅርቡ ተመርቀው ወደ ሥራ ይገባሉ። ይህ ኃይል ስልጠናውን ጨርሶ ወደ ነባሩ ሲቀላቀል የተሻለ የማስፈጸም አቅም ይፈጥርልናል።

ሁለተኛው ደግም ሥራችን ነው። በተቋሙ ከተሠሩ ሥራዎች አንዱ የሪፎርም ሥራ ነው። በዚህም የአገልግሎት አሰጣጣችን፣ የመልካም አስተዳደር፣ የብልሹ አሰራር እና የሌብነት እንቅስቃሴ ሥራዎችን በመቀልበስ እና የተሻለ ተቋም ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ ሥራዎች ተሰርተዋል። በዚህም በ11 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ አመራሮችን ቀያይረናል። ከ60 በላይ የሚገመቱ የወረዳ አመራሮችን ለውጠናል። ከአንድ ሺህ በላይ ኦፊሰሮችንም ከነበሩበት ቦታ እየቀያየርን እንዲሰሩ አድርገናል።

በአባሎቻችን ላይ ከኅብረተሰቡ ዘንድ ሰፋ ያለ ቅሬታ በመኖሩ ይህን ቅሬታ ለመፍታት የኅብረተሰቡን ሃሳብ በመሰብሰብ እና በመጭመቅ እንደ ግብዓት በመጠቀም ለአባሎቻችን ስልጠና በማዘጋጀት በጥሩ ሥነ-ምግባር ኅብረተሰቡን እንዲያገልግሉ ለማድረግ ተችሏል። ይሁን እንጂ አሁንም አልፎ አልፎ የሚታዩ የሌብነት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ።

አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ በግልጽ ተለይተው የተሰጡት ሥራዎች አሉ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዘጠኝ የሥራ መደቦች እንዲያከናወን ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል። አንደኛው ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው። እንደሚታወቀው መሬት የሀገር ሀብት ነው። ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር በከተማዋ ውስጥ የሚታዩ ባዶ ቦታዎችን እንዲጠብቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በዚህ መሰረት የመንግሥትን መሬት ለግል ጥቅማቸው ሊያውሉ የተንቀሰቀሱ አካላት ላይ እርምጃ ወስዷል።

በዚህም 15ሺ 749 የሚሆኑ የተወረሩ መሬቶችን (ቦታዎችን) ለመንግሥት ማስልመስ ችሏል። የመሬት ወረራ ችግር በሁሉም የከተማ አስተዳደሩ ክፍለ ከተሞች የሚስተዋል ቢሆንም ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ቦሌ፣ ለሚ ኩራ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ላይ ግን የበረታ ነው።

ሁለተኛው ተቋሙ ቁጥጥር ከሚያደርግባቸው ዘርፎች መካከል ሕገ ወጥ ግንባታ ነው። ከዚህ አንጻር በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ከተሰጣቸው ይዞታ ውጭ ግንባታ ባከናወኑ 8ሺ235 ሕገ ወጦች ላይ ተቋሙ እርምጃ ወስዷል። ሦስተኛው ከሕገወጥ የመሬት መስፋፋት ጋር የተገናኘ ነው። በዚህም ከተሰጣቸው ቦታ ውጪ ትርፍ ቦታ በመጨመር ለመገንባት የሞክሩ 2ሺ198 ሰዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

አራተኛው የጎዳና ንግድ ነው። ሕገ ወጥ የጎዳና ንግድ ስንል በእግረኛ መንገድ፣ በአደባባዮች፣ በተሽከርካሪ መንገዶች፣ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ምርት የሚከናወን ንግድ ነው። ከዚህ አንጻር በተለይ በዘንድሮው ዓመት ወደ 82ሺ 824 የሚገመቱ ሕገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ተቋሙም ውጤት ካገኘባቸው የሥራ ዘርፎች አንዱ ይሄ ነው።

አምስተኛው ደግሞ የእርጥብ እና ደረቅ ቆሻሻን መከላከል ነው። ከግለሰብ፣ ከተቋማት፣ ከኢንዱስትሪዎች ወዘተ የሚወጡ ደረቅ እና ፈሳሽ ቆሻሻዎች ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ የሚለቁ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አድርገናል። በዚህም 9ሺ933 ሕገወጦች ላይ እርምጃ ወስደናል።

ሕገ ወጥ እርድ እና የእንስሳት ዝውውርን በተመለከተም፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዚህ ዓመት 2ሺህ ዘጠኝ በሚሆኑ ሕገ ወጥ እርድ በፈጸሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ሕገ ወጥ የመንገድ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም በተለይም የግንባታ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው አካባቢዎች በእግረኛ እና በተሽከርካሪ መንገዶች ላይ አሸዋ፣ ብረታ ብረት እና ድንጋይ የማከማችት ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል። በዚህም 20ሺ 543 ግለሰቦች ላይ እርምጃ ወስደናል።

ስምንተኛው እና ሌላው ኃላፊነት ደግሞ አዋኪ ተግባርን መቆጣጠር ነው። ከትልልቅ ባለኮኮብ ሆቴሎች እስከ በመኖሪያ ቤቶች፤ ከሬስቶራንቶች እስከ ማሳጅ ድረስ ከኢትዮጵያዊነት ባህሪ ያፈነገጡ እና የአምራች ኃይሉን ሥነ አዕምሮ የሚያበላሹ ተግባራት ይከናወናሉ። ‹‹ኒኮቲን›› ያላቸው መርዛማ ሆኑ አደንዛዥ ዕጾችን ይጠቀልላሉ፤ይሸጣሉ። ከዚህ በመነሳት 3ሺ792 ሕገ ወጦች ቤቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል።

ሌላው ቁጥጥር እንድናደርግ ኃላፊነት የተሰጠን በሕገወጥ ማስታወቂያ ላይ ነው። በዚህም 392ሺ646 ሕገ ወጥ ማስታወቂያዎች እንዲነሱ ተደርጓል። በድምሩ በበጀት ዓመቱ 125 ሺህ 827 ሕገወጦች ላይ እርምጃ ወስደናል። ወደ ሕግ ከምናቀርባው ውጪ በገንዘብ ከ32 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት ምን ተግዳሮቶች አጋጣማችሁ? እንዴትስ ፈታችሁ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- በ2015 ዓ.ም በርካታ ችገሮች አጋጥመዋል። በተለይ በሥራ ላይ በነበሩ ኦፊሰሮች ላይ ሕገወጦች በፈፀሙት ተግባር ከህይወት ማጣት እስከ አካል ጉዳት አጋጥሟል። በዚህም አንድ አባላችን በመኪና ተገጭቶ ሲሞት ከ10 በላይ የሚሆኑ ኦፊሰሮች ደግሞ የዓይን መጥፋት፣ የጥርስ መሰበር እና የአካል ጉዳት አጋጥሟቸዋል።

ሁለተኛ ከመሬት ጋር ተያይዞ አሁንም ቢሆን ሊሻሻል እና ሊስተካከል ያልቻለ በባዶ መሬት ወይም ባንክ በገቡ፤ በአርሶ አደር ወይም ግሪነሪ ቦታዎች ላይ አንድ ሕገ ወጥ ሥራ የሚሰራ ሰው ሕገወጥ ተግባሩን ከማከነወኑ በፊት ከሚመለከተው የፍትህ አካል ወይም ፍርድ ቤት እግድ ያወጣል። በዚህም ማታ ባዶ የነበረ ቦታ ጠዋት ስትነሳ በቆርቆሮ ታጥሮ እግድ ተለጥፎበት ታገኘዋለህ።

በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች ለሕገወጥ መሬት ወራሪዎች የሚሰጡት እግድ ለሥራችን እንቅፋት ሆኖብናል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አባሎቻችን ሕገ ወጥ ተግባሩ እንዴት ይፈጸማል? ሲሉ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፋችኋል እየተባሉ አባሎቻችን እንዲታሰሩ እና እንዲንገላቱ እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ ያልተፈቱ እና በቀጣይ ትኩረት ሰጥታችሁ ልትሰሩባቸው የለያችኋቸው ችግሮች አሉ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- ትልቁ ያልተፈታ ችግር ብለን የገመገምነው ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው። በእርግጥ አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ የወሰዳቸው እርምጃዎች አሉ። እያንዳንዱ መሬት እንዲቆጠር ተደርጓል። እንዳንዱ ባዶ መሬት የመንግሥት የሆነ፣ የአርሶ አደር የሆነ፣ ተቆጥሮ ለደንብ ተላልፏል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን በመሬት ላይ ያለው ፍላጎት በጣም ከባድ ነው። ከባድ እንደመሆኑ መጠን አሁንም አንዱ የከተማችን ችግር ወይም ተግዳሮት ከመሬት ጋር የተያዘ ችግር ነው።

ሌላው የተቋሙ ፈተና እና አሁን መቅረፍ አስቸጋሪ የሆነው የጎዳና ላይ ንግድ ነው። በጎዳና ላይ የሚነገዱ ንግዶች በከተማችን እንደ ባህል ተቆጥረዋል። ይህ ደግሞ ከከተማዋ ስታንዳርድ አኳያ ተገቢ እና ትክክል ያልሆነ ተግባር ነው ።

አዲስ ዘመን፡- በ2016 በልዩ ትኩረት ልትሰሩት ያሰባችሁት ምን አለ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- በ2016 ዓ.ም ለመስራት ከታቀዱ ሥራዎች መካከል የአባሎቻችን የሥነ ምግባር ሁኔታ በማሻሻል ዘጠኙን የደንብ ጥሰቶች በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚለው ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት ነው። ይህ ድርድር የሌለው ማድረግ የሚገባን ነገር ነው። በተቋማችን የሚታዩ የሥነ ምግባር ችግሮች፣ የሌብነት እና የብልሹ አሰራሮች ምንድን ናቸው የሚሉትን ለይተን እየሰራን ነው።

በዚህም በጣም ጫፍ የወጡትን ከተቋሙ እንዲቀነሱ ይደረጋል። መማር የሚችሉትን ደግሞ እናስተምራለን። ይህን ሥራ ከሠራን ሁሉ ነገር ቀላል ይሆናል። ፍትሐዊ አገልግሎት እና ለሕዝብ የሚኖር የአገልጋይነት ስሜት እያደገ ይሄዳል። በዚህም የተቋም ግባችንን ማሳካት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- የተጠቀሱትን የተቋሙ ዓላማ ለማሳካት ከሰው ኃይል አኳያ ያላችሁ አደረጃጀት በቂ ነው ብለው ያስባሉ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡– በተቋሙ ውስጥ በርካታ የሰው ኃይል አለ። የፓራ ሚሊታሪው ክንፍ አንደኛው ነው። በዚህም 5ሺ 325 የሚደርስ የሰው ኃይል የያዘ ነው። ይህ ክንፍ የተሻለ ሥራ እንዲሰራ ከአንድ ሺህ በላይ ሠራዊት አሰልጥነናል። በቅርብ ቀን ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል። ሌላው የሲቪል ክንፍ ነው። ይህ ክፍል በአብዛኛው በከተማ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ይገኛል። ካለን የሰው ኃይል ከ60 እከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው። ስምሪት ላይ ለሚገኘው ኃይል ድጋፍ የሚሰጥ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- ከሰው ኃይል ምልመላ አንፃር የምትከተሉት መስፈርት ምንድን ነው? ማስታወቂያው ለሕዝብ ግልጽ አይደለም ይባላል። እርስዎ ምን ይላሉ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- እኛ የሰው ኃይላችንን ስናደራጅ ግልጽ የሆነ ማስታወቂያ እናወጣለን። መስፈርቶችም ኢትዮጵያዊ፣ ከወንጀል ነጻ፣ ለሕዝብ ታማኝ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተወላጅ ወይም በከተማዋ ውስጥ ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ የኖረ ወዘተ የሚሉ ናቸው። ስብጥሩም ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ነው። በአጠቃላይ የቅጥር ማስታወቂያዎች በተመለከተ በየክፍለ ከተማዎች ለሕዝብ ግልጽ በሆኑ ቦታዎች እንዲለጠፉ ይደረጋል።

በሲቪል ክንፉ ደግሞ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሰረት ቅጥር ይከናወናል። ከትምህርት ዝግጅት አንጻር በተለይ በአሁኑ ዓመት ዲግሪ እና ከዚያ በላይ የሆነ ነው። ከጾታ አንጻር የሴቶችን ተሳትፎ ከወንዶች እኩል ለማደረግ እየተሠራ ነው። በዚህ ዓመት በተከናወኑ ምልመላዎች 48 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው ። በቀጣይ እኩል ለማድረግ ይሠራል።

አዲስ ዘመን፡- ከሕገወጦች ከሚወረሱ ንብረት አያያዝ እና አስተዳደር ጋር ግልጽነት ይጎድላል የሚል ቅሬታ ከኅብረተሰቡ ይሰማል፤ በተጨማሪም ጉዳዩን ለሕዝብ እና ለሚዲያዎች ከማሳወቅ አንጻር ምን ያህል ተባባሪ ናችሁ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- የሠራናቸውን ሥራዎች ለሕዝብ እና ለሚዲያ ከማሳወቅ አንጻር በአዲስ አበባ ከሚገኙ ተቋማት የደንብ ማስከበር ግንባር ቀደም ነው። አብዛኛው ሥራችን በሚዲያ የተደገፈ ነው። በተቋሙ የተደረጉ የሥራ ክንውኖችን ለሚዲያ ያላሳወቅንበት ጊዜ የለም። በዚህም ሥራችንን ለሕዝብ ግልጽ እያደረግን መጥተናል። በዚህም በእኛ ተቋም ተሠርተው ሕዝብ የማያውቃቸው ሥራዎች የሉም።

ከሚወረሱ ንብረቶች ጋር ተያይዞ ንብረቶች ሁለት አይነት ናቸው። ለአብነት፣ በፍጥነት የሚበላሹ አትክልት እና መሰል ንብረቶች ይገኛሉ። ይህ በአፋጣኝ ይወገዳል። ኤሌክትሮኒክስ እና ጨርቃ ጨርቅ የመሰሉ ደግሞ ሲወረሱ ገቢ የሚደረግበት የራሱ መመሪያ አለው። በዚያ መሰረት ገቢ ይደረጋል።

በወረዳ ደረጃ በዋና ሥራ አስፈጻሚው የሚመራ የጨረታ ኮሚቴ አለ። የደንብ ማስከበር ከኮሚቴው ውስጥ አንዱ አባል ነው። ሻጭ ግን አይደለም። የተወረሱ ንብረቶችም በወረዳ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሪነት በጨረታ ሕግ እና ደንብ መሰረት በግልጽ ጨረታ ተሸጦ ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የደንብ ማስከበር ፈተናዎች አሉበት። ከእነዚህም መካከል የሚወረሱ ንብረቶችን ማስቀመጫ ቦታዎች ማጣት አንዱ ነው። ይህ ደግሞ ለሌብነትም ሆነ ለብልሹ አሰራር ክፍት ያደርገዋል። እንደዚህ አይነት ችግሮችን ለማረም በ2016 የበጀት ዓመት ከፍተኛ ሥራዎችን ለመስራት እቅዶች ተዘጋጅተዋል።

አዲስ ዘመን፡- ከደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች ጋር ተያይዞ የሥነ ምግባር ችግር መኖሩን የተለያዩ አካላት ያነሳሉ። በዚህ ላይ የእርስዎ እይታ ምንድን ነው?

ሻለቃ ዘሪሁን ፡- ከኦፊሰሮቻችን ጋር በተያያዘ ከኅብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ ሃሳቦች ፣ጥቆማዎች አሉ። እንደ ተቋም ከኅብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ ሃሳቦች፣ ጥቆማዎች ትክክል ነው ብለን እናምናለን። ምክንቱም ሕዝብ ስለማይሳሳት። እኛ የማናያቸውን በተለይ ኦፊሰሮቻችን ከሕዝቡ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንደመሆኑ መጠን የተቋሙ አመራሮች ከሚቆጣጠሩት በላይ ሕዝቡ በደንብ ያያቸዋል።

ከሕዝብ በሚሰጠን ጥቆማ እና አመራሩ በሚያደርገው ክትትል መሰረት በ2014 ዓ.ም የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች የሥነ ምግባር ችግር ጎልቶ የወጣበት እና አስቸጋሪ የሆነበት ዓመት ነበር። በዚህም ተቋሙ በከፍተኛ ደረጃ የተፈተነበት ነበር። ይህን ለማስተካከል በ2015 ዓ.ም በጣም በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል። ይሁን እንጂ አሁንም የሚታዩ ችግሮች አሉ።

በደረሰን ጥቆማ መሰረት ከሦስት በላይ የሚሆኑ አመራሮች እና ስድስት ኦፊሰሮች ከሌብነት እና ከብልሹ አሰራር ጋር በተጨባጭ ተገኝተዋል። እነዚህ ወደ ሕግ ቀርበው ከሥራም እንዲታገዱ ተደርጓል። ከእነኝህ በተጨማሪ በሕግ ጉዳያቸው እየታየ የሚገኝም አለ።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ ኦፊሰሮቻችሁን የሥራ ላይ ሥነምግባር የምትከታተሉበት አካሄድ አላችሁ? ከሆነስ በከተማዋ የደንብ ጥሰቶች ለምን ተበራከቱ የሚለውን ጉዳይ ገምግማችሁ ለይታችኋል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- በከተማ ውስጥ የደንብ ጥሰቶች ለምን ይበዛሉ? የሚለውን በየጊዜው ይገመገማል። ሳይገመገም የታለፈበት ጊዜ የለም። ለምን ይበዛሉ? ለሚለው መልሱ ከተማ ስለሆነ ነው። ነገር ግን ይህን ችግር ለመቀልበስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብረን እየሰራን እንገኛለን።

የኦፊሰሮቻንን እና አመራሮችን የሥነ ምግባር ሁኔታ የምንከታተልበት የዲሲፕሊን ኮሚቴ በየደረጃው አለ። የሥነ ምግባር እና የፀረ ሙስና ዳይሬክተርም አለ። ይህ ዳይሬክተር በወረዳ እና በክፍለ ከተማ የራሱን ፈጻሚ አካል በማደራጀት ከሕዝብ ከሚሰጡ ጥቆማዎች በመነሳት እና ራሱም በሚያደርገው ክትትል የሕግ ጥሰት በፈጸሙ ኦፊሰሮች ላይ እርምጃ ይወሰዳል።

አዲስ ዘመን ፡- በከተማዋ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ከሕዝብ ጋር ተባብሮ እና ተናብቦ የመስራቱ ነገር ምን ይመስላል ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- ከዚህ በፊት ተቋሙ ከኅብረተሰቡ ጋር ግንኙነት ከማድረግ ጋር ክፍተቶች ይታዩበት ነበር። በ2015 ዓ.ም የበጀት ዓመት ከተቀረፉ ችግሮች መካከል አንዱ ከኅብረተሰብ ጋር ተባብሮ ችግሮችን የመፍታት አሰራሩን በስፋት ማከናወን ነው። በወረዳ ደረጃ በ120 ወረዳዎች ለሁለት ጊዜያት ከኅብረተሰቡ ጋር ተገናኝተናል።

የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ኅብረተሰቡ በሚኖርበት ወረዳዎች ወርዶ ችግሮችን መፍታት እና በጋራ ለመስራት ውይይት አድርጓል። በክፍለ ከተማ እና በከተማ ደረጃ ከማኅበረሰቡ ጋር በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል። እነኚህ የሕዝብ ውይይቶች በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረን አስችለዋል።

አዲስ ዘመን፡- ፍራፍሬ እና መድኃኒት የመሰሉ በቀላሉ የሚበላሹ ንብረቶች በሚወረሱ ጊዜ እንዴት ታስቀምጣላችሁ? እንዴትስ ታስወግዳላችሁ?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- እንደ ፍራፍሬ ዓይነት ንብረቶች ከመወረሳቸው በፊት ቢቻል ቢቻል በእንደዚህ ዓይነት ተግባር ላይ እንዳይሳተፉ ምክር ተሰጥቷቸው የሚለቀቁ አሉ። ነገር ግን የተደረገውን ምክር ተላልፈው በሕገወጥነት የሚቀጥሉ ከሆኑ እንዲወረሱ ይደረጋል። ለጨረታም ቀርቦ ይሸጣል። መድኃኒትን በተመለከተ መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያስወግድበት አሰራር አለ።

አዲስ ዘመን ፡- ከጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አሉ። ከዚህ አንጻር የደንብ ማስከበር ምን ያደርጋል የሚሉ ሰዎች አሉ። ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ አንጻር ይህን የሰዎች አስተያየት እንዴት ይመለከቱታል?

ሻለቃ ዘሪሁን፡- የደንብ ማስከበር ከተቋቋመለት ዓላማ አንጻር የፌዴራል ፖሊስን ወይም የአዲስ አበባ ፖሊስን ተክቶ የሚሠራ ተቋም አይደለም። ራሱን የቻለ በአዋጅ የተሰጡት ኃላፊነቶች አሉት። ነገር ግን የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከጸጥታ ችግር ጋር የሚታዩ ችግሮችን ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ችግሮችን ለማስወገድ ሥራዎችን ይሠራል።

አዲስ ዘመን ፡- ለቃለ ምልልስ ስለተባበሩን እናመሰግናለን።

ሻለቃ ዘሪሁን ፡– እኔም አመሰግናለሁ።

ከሚወረሱ ንብረቶች ጋር ተያይዞ ንብረቶች ሁለት አይነት ናቸው። ለአብነት፣ በፍጥነት የሚበላሹ አትክልት እና መሰል ንብረቶች ይገኛሉ። ይህ በአፋጣኝ ይወገዳል። ኤሌክትሮኒክስ እና ጨርቃ ጨርቅ የመሰሉ ደግሞ ሲወረሱ ገቢ የሚደረግበት የራሱ መመሪያ አለው። በዚያ መሰረት ገቢ ይደረጋል

 ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን    ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም

Recommended For You