ዶክተር አጥላው ዓለሙ ይባላሉ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህንድ አገር ካልካታ ሜሪን ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ በኢንጅነሪንግ ይዘዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ አግኝተዋል፡፡ አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት መሥሪያ ቤት ባህርተኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚያም 15 ዓመታት በተለያዩ ፋብሪካዎች ሠርተዋል፡፡ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር አጥላው በአሁኑ ጊዜም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ኃላፊም ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተስፋና ተግዳሮት ዙሪያ ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡
የኢንዱስትሪው ጉዞ
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪው ዕድገት አዝጋሚ ነው፡፡ ይህም የፖሊሲው ውጤት ሲሆን፤ ቀደም ብለን ጀምረነው ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ጊዜ የኢንዱስትሪ ዕድገት ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ያለፈው 21 ዓመታት በከንቱ የጠፋ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እስኪቀረጽ ድረስ ኢንዱስትሪን በዝቅተኛ ደረጃ የሚያይና እንዲያውም እኔ ግብርና ነው ትኩረቴ ስለ ኢንዱስትሪ አታውሩብኝ የሚል መንግሥት ነበር፡፡
ግብርና መር ኢኮኖሚ ፖሊሲ ግብርና ኢንዱስትሪን እንዲመራው የሚፈለግበት አካሄድ ነው፡፡ ሆኖም ግብርና ሊያድግ ከተፈለገ ኢንዱስትሪው ሊረዳው ይገባል፡፡ ለምን ብትል ግብርናው ግብዓቶችን ከኢንዱስትሪ ማግኘት አለበት፡፡ ምርቱን ደግሞ ኢንዱስትሪው ወስዶ እሴት ጨምሮ ለገበያ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ማዳበሪያ ከውጭ እየተገዛ ግብርናውን ካሳደግን በኋላ ወደ ኢንዱስትሪ እንገባለን የሚል የተበላሸ ፖሊሲ ስለነበር ኢንዱስትሪው ሊያድግ አልቻለም፡፡ ሥልጣን የያዘው መንግሥትም ከእኔ በስተቀር ሌላ የሚያውቅ የለም ስለሚል ባለሙያዎች የሚመክሩትንም አስተያየት አይቀበልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ማደግ የምትችልበትን ጊዜዋን አጥፍቶባታል፡፡ ምክንያቱም በፖሊሲ ችግር ምክንያት በኢንዱስትሪ ሳናድግ ቀርተናል፡፡
መሰረታዊ የአቅጣጫ ችግሮች
ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገቡ በብዛት የሚጠሩት ገንዘብ፣ እውቀት ያልቸገራቸው የውጭ ባለሀብቶች ናቸው፡፡ ግን ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዋናነት መግባት ያለባቸው አቅም የሌላቸው፣ ቦታ፣ መሰረተ ልማት፣ ለማግኘት ለቸገራቸው ኢንቨስተሮች መሆን አለበት፡፡ አሁን ግን ለውጭ ገበያ (ለኤክስፖርት) በሚል በተሳሳተ አቅጣጫ የውጭ ኢንቨስተሮችን ነው ለመሳብ የሚፈለገው፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮችማ ገንዘባቸውንና እውቀታቸውን ይዘው እንዲመጡ የሥራ ሁኔታን ነው ማስተካከል የሚያስፈልገው፡፡ ስለዚህ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በዋናነት መያዝ ያለባቸው በአገሬው ባለሀብት እንጂ በውጭ ባለሀብት መሆን አልነበረበትም፡፡ ሆኖም አልፎ አልፎ በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ከውጭው ገበያ ጋር የሚያስተሳስሩ መልህቅ (አንከር) የሆኑ የውጭ ኩባንያዎች ያስፈልጋሉ፡፡
ግን አብዛኛውን የውጭ ባለሀብት ነው መግባት ያለባቸው ብሎ በዚህ ልክ እጅን ታጥቦ መጠበቅ ተገቢና ትክክልም አይደለም፡፡ በብዛት አቅም የጎደለው የአገሬው ባለሀብት ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን ለማበረታታት እንጂ የውጭ ባለሀብት እንዲቆጣጠሩን መፈቀድ የለብንም፡፡
የውጭ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉት ቴክኖሎጂውን፣ የገበያ ትስስሩን አሸጋግረው በመጨረሻ ላይ አገሬው እንዲሠራው እንጂ እነሱ አምርተው ሽጠው ገንዘቡ ወደ ውጭ ይዘው የሚሄዱበት መሆን የለበትም፡፡ ካልሆነ ግን ጉልበት ብቻ ኤክስፖርት ማድረግ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ የአቅጣጫ ችግር እንዳለ ነው የሚታየው፡፡
ሌላው የአቅጣጫ ችግር መንግሥት ኤክስፖርት እንደ ዋና ግብ መውሰዱ ነው፡፡ ከውጭ የምናስገባውን እዚሁ አገር ውስጥ ማምረት አለብን፡፡ ይህም ሥራ ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ያስችላል፡፡ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ትልቁ ዓላማው እኮ ለአገሬው ህዝብ ሥራና ገቢ መፍጠር ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ከውጭ በምናመጣበት ጊዜ ግን የሚጠቀመው ምርቱ የሚመረትበት አገር ሠራተኛና ባለሀብት ነው፡፡
ስለዚህ ሥራ አጥ በበዛበትና አዳዲስ ሥራ በሚያስፈልግበት አገር ከውጭ የሚገቡትን ምርቶች እዚሁ በማምረት ሥራ መፍጠር ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪን ፍላጎትም መቀነስ አለብን፡፡ የምሥራቅ እስያ አገሮችም መጀመሪያ ያደረጉት ከውጭ የሚያስገቡትን ምርት የመተካት ሥራ ነው፡፡ ይህ ግን ኤክስፖርቱን ይተውታል ማለት ሳይሆን ሁለቱንም ጎን ለጎን ነው የሚያስኬዱት፡፡ እኛ አገርም እንዲሁ ነው ማድረግ ያለብን፡፡
ለምሳሌ ብስኩት፣ ጭማቂ፣ ማዳበሪያ፣ ጨርቃ ጨርቅና መሰል ምርቶችን እዚሁ አገር ውስጥ ማምረት አለብን፡፡ ምክንያቱም ለኤክስፖርት ብቻ ብለን የአገር ውስጥ ገበያውን መዘንጋት የለብንም፡፡ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰውን ገንዘብ የሚጠይቀን ከውጭ የምናመጣው ዕቃ ነው፡፡ ወደ ውጭ ከምንሸጠው ምርት የምናገኘው ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም፡፡ በተወሰኑ ዓመታት ከ17 ቢሊዮን ዶላሩ ገሚሱን እንኳ ብንቀንስ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ማቃለል ይቻላል፡፡
እርግጥ ነው የተወሰኑ የሞባይል፣ የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳና መሰል አምራች ኩባንያዎች ተቋቁመዋል፤ ጥሩ ነው መስፋት አለበት፡፡ ሌሎችንም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን አስመስሎ በመሥራት የውጭ ምንዛሪን የማዳን ሥራ በስፋት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ግዥና ሌሎችም የግል ኩባንያዎች ከአገር ውጭ ከመግዛት ይልቅ በአገር ውስጥ ምርት ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ሲቻል ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉና እያደጉ ይሄዳሉ፡፡
ሁለተኛ እዚህ አገር የተወሰነ አካባቢ ብቻ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ ሌላው አካባቢ ደግሞ ገበሬ ሆኖ እንዲቆይ የሚመስል ሁኔታ ይታያል፡፡ መንግሥት ይህን አይነት መንገድ ስለተከተለ ኢንዱስትሪው መስፋፋት አልቻለም፡፡ እንቅፋቶቹም ብዙ ናቸው፡፡ የመሬትና የፈቃድ አሰጣጥ፣ የኤሌክትሪክና የውሃ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ እንዲሁም የታክስ ሥርዓቱም ውስብስብ ነው፡፡
ችግሮቹን ለመፍታት ምን ይደረግ?
ኢንዱስትሪው በስም እንጂ የተደገፈው በተግባር አይደለም፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ደግሞ የአገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ባለቤቶችን ወደ ኢንዱስትሪ ውስጥ መግባት ቀላል ወይንስ ከባድ ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎች ከኢንዱስትሪ ይልቅ ወደ ሸቀጣሸቀጥ ንግድ የሚገቡት በኢንዱስትሪ መሰማራት ውስብስብ ሂደቶች በመኖራቸው ነው፡፡ ማኑፋክቸሪንግ ውጤቱን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ስለሚፈጅ ባለሀብቱ ቀላል ወደ ሆነው ጅምላና ችርቻሮ ንግድ ያዘነብላል፡፡
ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ከውጭ ማስመጣት፤ ሠራተኞችን ማሠልጠን፣ ማስተዳደር፣ የመንግሥትን የተቀላጠፈ አገልግሎት ይፈልጋል፡፡ እናም በኢንዱስትሪ መሰማራት ብዙ ሂደቶችና ስጋቶች ያሉበት በመሆኑ እንቅፋቶቹን በቀላሉ ማስወገድ ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አንደኛ ያሉት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ ማድረግ፣ ያልገቡ እንዲገቡ መደገፍ አለበት፡፡
መንግሥት ለግብሩ ሳይሆን መጨነቅ ያለበት በራሱ ማምረት ሥራ የሚፈጥር መሆኑን በመረዳት ማበረታታት ነው የሚጠበቅበት፡፡ ኢንዱስትሪዎች ሲስፋፉ የመንግሥትን ራስ ምታት የሆነውን የሥራ አጥ ችግር ያቃልላሉ፡፡ ለወደፊቱ አቅም ይገነባል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ማምረት ያልቻለ ወደፊት ጥራትና ተወዳዳሪ ምርት ማምረት አዳጋች ነው የሚሆነው፡፡
የኢንዱስትሪዎች የምርት ጥራት ችግር
ጥራት እንዲመጣ ውድድር ያስፈልጋል፡፡ ለሠራተኞችም በየጊዜው ማሠልጠን ይገባል፡፡ መርዳትና ተሞክሮ እንዲቀስሙ ማድረግም ተገቢ ይሆናል፡፡ መንግሥትም የምርት ጥራታቸው እንዲያሻሽሉ መቆጣጠርና መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ፍትሀዊ የንግድ ውድድር ካለ በራሱ ጥራት ያመጣል፡፡ ስለዚህ ምቹ ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ ሳይጀመር ግን ወዲያውኑ ጥራት ማምጣት አይቻልም፡፡ በሂደት ግን ጥራቱ የተጠበቀ ምርት የሚያመርቱ ይሆናል፡፡
የተሻለ አማራጭ ፖሊሲ
ግብርናውን እንደ ገበያው የሚቆጥር ኢንዱስትሪ ማስፋፋት አማራጭ የፖሊሲ ሀሳብ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ግብርናውን እንደ ገበያ የሚቆጥርበት በብዙ መንገድ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ገበያ የሚያገኘው ግብርናው ላይ ቢያተኩር ነው፡፡ ለምሳሌ የማዳበሪያ፣ የፀረ ተባይ፣ አረም ማጥፊያዎች፣ የግብርና መሳሪያዎች (በእጅ የሚገፉ ማረሻዎች፣ ምርት መሰብሰቢያ አነስተኛ ኮባይነሮች፣ ማጓጓዥ ጋሪዎች ወይንም ሞተሮች)፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በስፋት ማቋቋም ግብርናውን እንደ ገበያ የሚቆጥር ኢንዱስትሪ ማስፋፋት ተመራጭ ሀሳብ ነው፡፡ ሌላኛው ከግብርናው ጥሬ ዕቃ እየወሰደ እሴት ጨምሮ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከግብርናው ጎን ለጎን መካሄድ ነበረባቸው፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ኋላ ቀር ነው ከተባለ የኢንዱስትሪ ግብዓት ሳያገኝ ሊያድግ አይችልም፡፡ ስለዚህ ለሱ የሚሆኑ ግብዓቶች የሚገኙት ኢንዱስትሪውን በማስፋፋት ነው፡፡ መጀመሪያ ግብርናውን አሻሽዬ ከዛ በኋላ ሀብት ሲኖረኝ ወደ ኢንዱስትሪው እገባለሁ የሚለው የተሳሳተ ፖሊሲ ነው፡፡
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ የሆነን ግብርና ለማቆየትና የተወሰነ አካባቢን ኢንዱስትሪያላይዝድ ለማድረግ የታሰበ ይመስላል፡፡ ግብርና ግብዓትና ገበያ ሲያገኝ ሊያድግ አይችልም፡፡ ገበያውም ግብዓቱም የሚገኘው ደግሞ ከኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ሳያድግ ግብርና አያድግም፡፡ ስለዚህ ፖሊሲው መጀመሪያ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት አለበት፡፡ ይህ ኢንዱስትሪ ደግሞ ግብርናውን ላይ ያተኮረ መሆን አለበት፡፡
አሁንም ጊዜያችንን ሳናጠፋ ገጠሩ ምን ይፈልጋል የሚለውን ማወቅ አለብን፡፡ የሚፈልገውን የቴክኖሎጂ አገር ውስጥ በዝቅተኛ ዋጋ እንዴት እናምርትለት የሚል የኢንዱስትሪ አቅጣጫ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ኢንዱስትሪውን ከግብርናው ጋር ማስተሳሰር ይገባል፡፡ አሁን ከውጭ እየገቡ የሚገኙትን በአነስተኛና በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች የሚመረቱ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እዚሁ አገር ውስጥ መመረት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰሊጥ፣ ኑግና ተልባ ምርቶች እያሉ ዘይት ከውጭ ማስገባት ማቆም አለብን፡፡
ምክንያቱም መንግሥት ይህን ሁሉ ሙያና ቴክኒክ ኮሌጆችን፣ የኢንጅነሪንግ ዩኒቨርሲቲዎችን ከፍቶና ባለሙያዎችን እያመረተ ቴክኒካሊ ከውጭ የሚገቡትን ምርቶችን እያስመሰሉ መሥራት የማይችሉ ዜጋ ማፍራቱ ዕዳ ነው የሚሆነው፡፡
ማነቆውን መፍታት
አሁን ካለንበት ጊዜ ጀምሮ እንድንፈናጠር ካስፈለገ ኢንዱስትሪ ትኩረት ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ትኩረት ይሰጠው ሲባል ሌላ ነገር አይደለም ለግል ባለሀብቱ እንደልቡ እንዲሠራ መንገድ ይከፈትለት ማለት ነው፡፡ መንገድ ይከፈትለት ሲባል ብዙ ጊዜ መንግሥት ይደግፋል፣ ምንድነው ችግሩ ይኸው የኢንዱስትሪ ፓርክ እያቋቋመ አይደለም ወይ? ብዙ ድጋፍ እያደረገ ነው መንግሥት ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪው እንዲገቡ ይፈልጋል ግን የሚገባ ጠፋ ነው የሚባለው፡፡ ሆኖም ወደ ኢንዱስትሪው የሚገባው ባለሀብት አነስተኛ የሆነበት ምክንያት መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ማነቆ ስላስቀመጠበት ነው፡፡ ብዙ ሥራ አጥነት ባለበት አገር ሠርቶ ሀብት ለማፍራት በሚፈለግበት አገር ውስጥ በጣም ብዙ ምርት ከውጭ አገር በሚመጣበት አገር ውስጥ እንዴት ነው ኢንዱስትሪ መቋቋም የሚፈልግ ሰው የሚጠፋው፡፡ መልሱ ማነቆው ብዙ ስለሆነ ነው፡፡ችግሩን ማቃለልና ማነቆውን መፍታት የመንግሥት የቤት ሥራ ይሆናል፡፡
ለውጡና ኢኮኖሚው
ኢኮኖሚው ገና ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ፖለቲካው ሳይስተካከል ኢኮኖሚውን ማስተካከል ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ፖለቲካው ነው ለኢኮኖሚው አቅጣጫ የሚሰጠው፡፡ አሁን የ100ቀናት ዕቅድ በሚል ትኩረታቸውን አሳይተዋል፡፡ በቀጣይም በግብርና በኢንዱስትሪ ያለውን ትስስር በቅጡ መታሰብ አለበት፡፡ ኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት መደረግ ይኖርበታል፡፡የንግድ ማነቆዎችን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ ምርታማነትን መጨመር ይገባል፡፡
ፖለቲካው የተረጋጋ ማድረግ ይገባል፡፡ ሰዎች ወደ ሥራ እንዲገቡና በንግድ፣ በኢንዱስትሪውና በግብርና ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መጀመሪያ ሰላም ማረጋገጥ ያስፈልጋል ፡፡
የኢኮኖሚው ብሩህ ተስፋ
ሁልጊዜ ተስፋ አለ፡፡ ተስፋውን ወደ እውነት ለመቀየር ነው ጥረት መደረግ ያለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውጭም ሆነ አገር ውስጥ ያለውን የተማረ ሰው ኃይልና የሰው ጉልበት በትክክል ሥራ ላይ ብታውለው፣ የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣት ብዙ ጊዜ አይፈጅባትም፡፡ መንግሥታዊ አስተዳደሩ ከተስተካከለ ጥሩ ለውጥ ይመጣል፡፡ በአገሩ ጉዳይ ያገባናል የሚል ሁሉ ስለተጠራ የዳያስፖራውን አቅምም መጠቀም እንዲቻል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2011
ጌትነት ምህረቴ