ሕዝብን ማገልገል ክብር ነው!

 ሕዝብ የስልጣን ምንጭና ባለቤት ነው። የሕዝብን የስልጣን ባለቤትነት አምነው የተንቀሳቀሱ ሀገራት በእድገት ተመንድገው፤በዴሞክራሲ አብበው ታይተዋል። ሕዝብን ለማገልገል እንጂ በሕዝብ ለመገልገል ፍላጎቱ የሌላቸው አገልጋዮች ያሏቸው ሀገራት ማኅበራዊ እርካታን ከማረጋገጣቸው ባሻገርም ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባቸው ናቸው።

በማንኛውም መንገድ ሕዝብ መደመጥን ይፈልጋል። ለጥያቄዎቹ ተግባራዊ ምላሽ ይሻል፤ ካልሆነም ጥያቄዎቹ ምላሽ ያላገኙበትን ተጨባጭ ምክንቶች ማዳመጥን ይፈልጋል። ይህ ካልሆነ ሰሚ እንዳጣና ተገቢው ክብር እንዳልተሰጠው ሊቆጥር ይችላል። ይህ ደግሞ የመጨረሻ ውጤቱ የመልካም አስተዳደር ችግር ይሆናል።

በተለይም በዚህ የቴክኖሎጂና የግሎባላይዜሽን ዘመን ከሕዝብ ፍላጎት በተጻራሪ ቆሞ የስልጣን ዘመንን ማራዘም ከማይቻልበት ሁኔታ ላይ ደርሰናል። የእያንዳንዱ ዜጋ ድምፅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ፣ የእያንዳንዱ ዜጋም ጥያቄ ዕውቅና መስጠት ሊታለፍ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።ከሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ተቀባይነት እያጡ፣ በሕዝብ ይሁንታ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች ተቀባይነት እያገኙ መሄድ ጀም ረዋል።

ኢትዮጵያም የዓለም አንድ አካል ናትና ይህን እውነታ መጋራቷ አይቀርም። በርግጥ ኢትዮጵያ ለዘመናት በንጉሳዊ፤ በወታደራዊና ከዚያም ቀጥሎ በመጣው ቡድን ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት ስር በመቆየቷ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ባህል ገና አልጎለበተም። በሕገ መንግሥት ደረጃ ዜጎች ከመንግሥት ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው ቢገለጽም በተግባር ብዙ ርቀት የሚቀረው ነው።

በእርግጥ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ሀገራት ይቅርና ባደጉትም ሀገራት ቢሆን ሁሉንም የሕዝብ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም። ሆኖም የታቀደው ነገር ያልተሳካበትን ሁኔታ መግለጽና ለሕዝብም ተገቢውን መረጃ መስጠት ግን የሕዝብ አገልጋይነትንና ቅንነትን መላበስን እንጂ በኢኮኖሚ ማደግን ፤ በቴክኖሎጂ መገስገስን አይጠይቅም። ዋናው ነገር የሕዝብ አገልጋይነት ስሜትና ቅንነት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ብዙ ቅን አገልጋዮች አሏት። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሕዝብን በቅንነት የሚያገለግሉ፤ በምልጃና በጉቦ የማይደለሉ፤ ለዘመድ አዝማድ አድልኦ የማይፈጽሙ አገልጋይ ዜጎች ያሏት ሀገር ናት። በትራንስፖርት ዘርፉ፣ በጤናው መስክ፣ በፀጥታና ደኅንነት ሙያ፤ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎትና በመሳሰሉት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሕዝብ ኖረው ለሕዝብ የሚሞቱ አገልጋዮችን መቁጠር ይቻላል።

ከዚሁ በተጸራሪ ግን አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎቶቻቸው ሲስተጓጎሉ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ብለው የሚቀመጡ፤ በማን አለብኝነትና በምንቸገረኝነት የሚያልፉና ምንም አይነት ሕዝባዊ ተቆርቋሪነት የማይታይባቸው ናቸው።

መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት። ዜጎች እንግልት ደረሰብን፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር ተሰቃየን ፣ ውጣ ውረዱ አንገላታን የሚሉ አቤታዎችን ማዳመጥና ይህንኑ ተግባር የፈጸሙ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ መወሰድ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከዛ በመለስ ቢያንስ ለተስተጓጎሉ አገልግሎቶች ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ግን ሊለመድ የሚገባው አሠራር መሆን አለበት።

ይህ ሲሆን በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን ይኖራል። የመንግሥት ዕቅዶች የመተግበር አቅማቸው ያድጋል፤ልማት ይፋጠናል፤ብልሹ አሰራር ይቀንሳል፤ የዜጎችም ሕይወት ይለወጣል።

የዛሬውንም የአገልጋይነት ቀንም በተለያዩ ሙያ ላይ ተሰማርተው ኢትዮጵያን እያገለገሉ ያሉ አገልጋዮች የሚመሰገኑበትና ከፍ የሚሉበት ነው። በርካታ ተቋማትም በራቸውን ከሌሊቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ለተገልጋዮች ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ። ስለዚህም በዛሬው ቀን ስለ አገልጋይነት አስበን ስንውል አገልጋይነት ያለውን ክብርና ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት መሆን ይኖርበታል። አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሕዝብን ማክበር ባህል ሊያደርጉት ይገባል!

አዲስ ዘመን    ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም

Recommended For You