አዲሱን ዓመት በተስፋ እና በሥራ ለመቀበል

አዲስ ዓመት ሊገባ በጣት የሚቆጠር ቀናት ናቸው የቀሩት።የክረምት ወቅት አልቆ ለብርሃናማው በጋ ሊለቅ በዝግጅት ላይ ነው።ምድሪቱም በአደይ አበባ ፍክት ብላ ፣አምራ እና ደምቃ ስትታይ አዲስ ዓመትን በተስፋ እንድንቀበለው አንዳች መልዕክት ትሰጣለች። ‹‹እንኳን አደረሳችሁ።›› ለመባባል የቀሩን ቀናቶች ናቸው።

አዲስ ዓመት መጣሁ መጣሁ እያለ ባለበት በዚህ ወቅት በተሰነባቹ ዓመት ያየነው፤ ለአዲሱ ዓመት መሸጋገር ያለባቸውን ፣ መታረም እና መበረታታት አለባቸው ያልናቸውን ሀገራዊ ጉዳዮቻችንን በዚህ ፅሁፍ በወፍ በረር ለመቃኘት ሞከርን።

በቅድሚያ ባለፈው ዓመት ከዛም በፊት የሀገር ዋነኛ ፈተና የሆነው የሰላም ጉዳይ ነው ።በአንድም ይሁን በሌላ ይህ ችግር ዋጋ ያላስከፈለው ዜጋ አለ ብሎ ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም።

ሰላም በዜጎች የእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ካለው የጎላ ስፍራ አንጻር የሰላም እጦቱ እንደ ሀገር ከፍ ላለ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጎናል። ዜጎች በሠላም ወጥተው እንዳይገቡ ፤ያሻቸው ቦታ ሄደው ሠርተው፣ ነግደው ፣ ኑሯቸውን እንዳይመሩ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል።

በያዝነው ዓመት በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት በሕወሓት እና በመንግሥት መካከል የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨቱ የሚበረታታ ነው። ስምምነቱን ተከትሎም ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፤ ብዙ ጉዳዮችን ተስፋ እንድናደርግ አስችሎናል።

እንደ ሀገር ከጦርነቱ ምንም አላተረፍንም። ይልቁንም ወደኋላ ተጎተትንበት፣በገንዘብ ከሰርን፣ የበርካቶችን ወንድም እህቶቻችንን ሕይወት አጣን።አካል ጉዳት የደረሰባቸው ጥቂቶች አይደሉም።ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የከፋ ሕይወት ለማሳለፍ የተገደዱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው።

አሁን በሁለት ወገን የነበረው ጦርነት አብቅቷል። ዛሬ ላይ ሰዎች እንዴት መረዳት እንዳለባቸው፣ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎችም ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል ጥሪ እያደረጉ፤ ዳግም ተከፍተው አገልግሎት ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው። ይህ ሲሆን እንደመስማትም ሆነ እንደ ማየት ምን የሚያደስት ነገር አለ? ይህንን በአዲሱ ዓመት ተግባራዊ ሆኖ እንደምናየው ተስፋ አደርጋለሁ።

በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችግር በአንድም ይሁን በሌላ እልባት እንዲያገኝ እየተሠራ ነው። ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከጅምሩ አንስቶ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚበረታቱ ፣ እውቅና የሚሰጣቸው ናቸው።ይህንኑ አጠናክሮ በአዲሱ ዓመት መቀጠል ያስፈልጋል። ከግጭቱ ሊያተርፍ የሚችል አካል ካለመኖሩ አንጻር ከትናንት ተሞክሯችን መማር ተገቢ ነው።

በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሰላም ችግር ለመቅረፍ የተጀመሩ ጥረቶች ፍሬ አፍርተው በክልሉ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ፣ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ ጥረቶች ፍሬ እንዳያፈሩ አሉታዊ ተጽእኖ የነበራቸው አካላት እራሳቸውን በአግባቡ በማየት ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል።

ሌላው የሚመጣው ዓመት ትልቁ ሥራችንና ተስፋችን በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኩል የተጀመረው ሥራ ነው። በሀገሪቱ እዚህም እዛም የሚታየውን የሰላም መደፍረስ ለማጥራት ብሎም ችግሮቻችንን በንግግር እና በውይይት ለመፍታት ሁነኛ እድል ነው።

ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም ለመጪዎቹ ትውልዶች ባለ ትልቅ ውለታ መሆን ነው ።ይህንን እውነታ ታሳቢ አድርጎ በኃላፊነት መንፈስ መንቀሳቀስም የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው።

የኑሮ ውድነቱ ዕለት ዕለት እየፈተነን ይገኛል።በመንግሥት በኩል ፈተናውን ለማቅለል ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም ይህ ነው የሚባል ለውጥ እያየን አይደለም። በዚህም ምክንያት የብዙዎች ሕይወት ለፈተና ተዳርጓል። ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ከመንግሥት ይጠበቃል።

በትምህርት በኩል ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ለማዳረስ እየተደረጉ ያሉትን እንቅስቃሴዎች በበጎ ማንሳት ይቻላል። የተለያዩ ሪፎርሞች ተደርገዋል። ያሉ ድክመቶችን በማረም ጠንክሮ ከተሠራ ብቁ፣ተወዳዳሪ እና በራሱ የሚተማመን ዜጋን ለሀገር ማፍራት ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

ነገር ግን በትምህርት ቤቶች ላይ እየታየ ያለውን በማን አለብኝነት የሚደረገውን የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሪ፤የእለት ጉርሱን ለማግኘት ለሚጨነቀው ወላጅ መርዶ እንደማርዳት ያህል ከሆነ ውሎ አድሯል።

መንግሥትም በችግሩ ዙሪያ ጣልቃ በመግባት ችግሩን ለመቅረፍ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። የወላጆችን አቅምና አጠቃላይ የሆነውን ሀገራዊ እውነታ ያገናዘበ የመፍትሔ ሃሳቦችን ማስቀመጥ ይኖርበታል። በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለማስተማር የሚደረገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆንም የመጽሐፍት እጥረቱን ከወዲሁ ማጤን ተገቢ ነው።

በፀጥታ መደፍረስ፣ በተፈጥሮ እና በሌሎች ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎች ከመርዳት አንጻር በርከት ያሉ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፤ ሥራዎቹ ከችግሩ ስፋት አንጻር በቂ ሆነው አልተገኙም።

ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት መንግሥትም ሆነ መላው ሕዝብ በአዲሱ ዓመት በኃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል፤ የዜጎችን ችግር በጋራ እና በትብብር መንፈስ መፍታት የአዲሱ ዓመት ተቀዳሚው የቤት ሥራችን መሆን ይጠበቅበታል።

ሙሰኝነት ፣ ሌብነት የሕፃናት ሥርቆት እና ወዘተ በ2015 ዓ.ም ከሰማናቸው ዜናዎች መካከል ይጠቀሳሉ።ምንም እንኳን በፀጥታ ኃይል (ፖሊስ) በኩል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ቢታወቅም ያለ ጉቦ ሥራቸውን የማይሠሩ ባለሙያዎች እየበዙ ፣ በተለያዩ መንገዶች በግለሰብ ሆነ በቡድን ደረጃ የሚከናወኑ ወንጀሎች እየሰፉ እንጂ እየቀነሱ አይደለም።ችግሩን ለመቆጣጠር በአዲሱ ዓመት ሕዝቡና የፀጥታ አካላት ተናበው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።

ለአብነት ያህል የተወሰኑትን አነሳን እንጂ ፣በመጪው አዲሱ ዓመት ወገባችንን አጥብቀን ጥርሳችንን ነክሰን የምንሰራቸው ብዙ ሥራዎች እንደሚጠብቁን ይታመናል። ሥራዎቹ ስኬታማ እንዲሆኑ ታዋቂ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ እና ሌሎች ተሰሚነት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ለዚህም በቂ ዝግጁነት እንደሚኖራችሁ ተስፋ አደርጋለሁ።

እየመጣ ያለውን አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ጽሑፌን በምርቃት ልቋጨው፤ በአዲሱ ዓመት ሰላምን ዘርተን ሰላምን ለማጨድ ያብቃን፤ አዲስ ዓመት፤ አዲስ ተስፋ የምናይበት፤ መልካሙን ሁሉ የምንሰማበት ያድርግልን፤ በእኩልነት፣በመከባበር እና በመፈቃቀር የምንኖርበትን አዲስ የአስተሳሰብ መሠረት ያልብሰን።አሜን!

መልካም አዲስ ዓመት

 በምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን    ረቡዕ ጳጉሜን ቀን 1 2015 ዓ.ም

Recommended For You