
አዲስ አበባ፡- ሆስፒታሉ በሚሰጠው የተቀላጠፈ አገልግሎት ህብረተሰቡን ደስተኛም አጋዥም ማድረግ መቻሉን የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አስታወቀ:: ሆስፒታሉ በ2013 ዓ.ም በአገልግሎት አሰጣጡ ከጤና ሚኒስቴርም ከክልል ጤና ቢሮም ተሸላሚ መሆኑ ተገልጿል::
የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ካሊድ ሸሪፋ ጳጉሜን 1 የአገልግሎት ቀንን አስመልክቶ ከኢፕድ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ፤ ሆስፒታሉ ህመም አጋጥሟቸው የሚመጡ ተገልጋዮች አስፈላጊውን ህክምና ሁሉ በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያገኙ ባለው አቅም ሁሉ እየሠራ ይገኛል::
ቀደም ሲል በአካባቢው በቅርብ የሚገኝ ሆስፒታል ባለመኖሩ በወሊድ ጊዜ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል እናቶች እና ሕጻናት ለሞት ይዳረጉ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው ያሉት ዶክተር ካሊድ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ህብረተሰቡ ከራሱ ኪስ አዋጥቶ ሆስፒታሉን ገንብቷል:: ለዚህ አበርክቶውም ህብረተሰቡ በሆስፒታሉ ሊያገኝ የሚገባውን ሁሉ አግኝቶ እንዲሄድ ከሠራተኞች እስከ ሥራ ኃላፊዎች ድረስ ህዝቡን ለማገልገል እየተጉ ይገኛሉ ብለዋል::
ሆስፒታሉ እንደ ሀገር አሉ የሚባሉ የስፔሻሊቲና የሰብ ሽፔሻሊቲ የህክምና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ እየሰጠ እንደሚገኘ አመልክተው፤ በዚህም በሆስፒታሉ አገልግሎት ፈልገው በሽታቸው ከአቅም በላይ ሆኖ ወደ ሌላ ሆስፒታል ሪፈር የሚደረጉ የታካሚዎች ቁጥር ከዜሮ ነጥብ አምስት በመቶ ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል::
በሆስፒታሉ አገልግሎት አሰጣጥ ህብረተሰቡ ደስተኛም አጋዥም መሆኑ በየጊዜው በምንሰራው ጥናት አረጋግጠናል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ከዚህ በጨማሪም በ2013 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በሆስፒታሎች በተደረገ ውድድር የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንደኛ ሆኖ ተመርጦ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል::
ዶክተር ካሊድ ለዚህ ውጤት ዋናው ምክንያትም የሆስፒታሉ ሠራተኞች አገልግሎት ፈልጎ የሚመጣ ሰው አገልግሎቱን ማግኘት አለበት የሚልና ሥራን ማሳደር ተገቢ አይደለም የሚሉ መርሆች የሚከተሉ በመሆናቸው ነው ብለዋል::
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ስፔሻላይዝድ ሀኪሞች፣ በብዙ ሆስፒታሎች የማይገኙ የህክምና መሳሪያዎች፣ የላብራቶሪ ግብዓቶች ፣ የመድሃኒት አቅርቦቶችና ትላልቅ የህክምና ማሽኖችን አሟልቷል:: በቀጣይም እነዚህን የህክምና መሳሪያዎችና ግብዓቶች በአግባቡ በመጠቀም ለታካሚው ህብረተሰብ ተገቢውና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል::
ዶክተር ካሊድ ሆስፒታሉ ጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸው ፕሮጀክቶችን የሚተገብርና በተለየ መልኩ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለይቶ ለህብረተሰቡ እየሰራ በመሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን አትርፏል ነው ያሉት::
ሥራ አስኪያጁ ህብረተሰቡ እንዳይኑ ብሌን በሚያየው ሆስፒታል የሚፈልገውን አገልግሎት አግኝቶ እንዲሄድ በቀጣይም በትጋት መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል::
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም