አዲስ ዘመን ድሮ

የጳጉሜ ወር የአዲሱ ዓመት መሸጋገሪያ ድልድይ እንደመሆኑ በግለሰብም ሆነ በሀገር ደረጃ ለቀጣዩ ጉዞ ትንፋሽ ስበን የምንነሳበት ወሳኝ ጊዜ ነው። በመሆኑም ለአዲሱ ዓመት የሚደረጉ ዝግጅቶች የተለዩ ናቸው። ከ1962 እስከ 1984ዓ.ም ድረስ ባሉት የጳጉሜን ቀናት አዲሱን ዓመት አስመልክቶ የተከወኑ ጉዳዮችንና የተነሱ ሃሳቦችን የተወሰኑትን በአዲስ ዘመን ድሮ እናስታውሳቸዋለን። እውቅ ድምጻውያን ከተካተቱባቸው የሙዚቃ ድግሶች እስከ ዓመት በዓል ገበያ መነሻና መድረሻችንን በማድረግ እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል።

 ለበለጠ ድል መነሳት

-ከርዕሰ አንቀጽ..

በማንኛውም ጊዜና ሥፍራ ሕዝቦች አዲሱን ዓመት የሚቀበሉት የሰላምና የብልጽግና እንዲሆንላቸው በመመኘት ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብም እንዲሁ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ምኞትና ፍላጎቱ መጪው ዘመን ሰላም ሰፍኖበት ከረሀብና ከቸነፈር የሚላቀቅበትና ብሩህ የብልጽግና ዘመን ምዕራፍ የሚከፍትለት እንዲሆንለት ነበር።

ይሁን እንጂ ባለፉት ጊዜያት በተለይም የደርግ አፈናና ጭቆና ሰፍኖባቸው በቆዩት አሥራ ሰባት ዓመታት አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ያየውና የተገነዘበው ምኞቱና ፍላጎቱ እውን መሆኑን ሳይሆን እያደር የሰላም እጦት መባባሱን፣ የኑሮ ደረጃው እያሽቆለቆለ መምጣቱንና በአጠቃላይ ሕልውናው እየጨለመ መምጣቱን ብቻ ነው። በመሆኑም ሕዝቡ ኃይሉን ከዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በማደራጀት በመጨረሻ የሰቆቃው ምንጭ የነበረውን የደርግና የኢሠፓን ሥርዓት ወደ ታሪክ ትቢያነት ለውጦ ወደ አዲስ ዕድገትና ዴሞክራሲ ምዕራፍ የተሸጋገረው፤ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ይህን ድል የተጎናጸፈው በዚህ አዲስ ዓመት ዋዜማ እንደመሆኑ አዲሱን ዓመት የሚቀበለው በአዲስ የተሃድሶ መንፈስ ነው። አዲሱን ዓመት በአዲስ የሥራና የድል መንፈስ ይቀበሉታል የምንለውም ከዚህ ዕምነት በመነሳት ነው። (አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 1984ዓ.ም)

ልጃገረዶች በየመንደሩ እየዞሩ መጨፈር ባህላችን አይደለም

-ሊቀ ሥዩማን አክሊሉ ገብረኪሮስ

ልጃገረዶች ከበሮ ይዘው በየመንደሩ እየዘፈኑ ገንዘብ መቀበል ከጥንት የመጣ ባህል አይደለም። ይህን የገለጡልን ሊቀ ሥዩማን አክሊሉ ገብረኪሮስ ናቸው።

ሊቀ ሥዩማን አክሊሉ ገብረኪሮስ የድሮው ዕንቁጣጣሽ አከባበር እንዴት እንደነበረ እንዲገልጡልን ተጠይቀው “ልጃገረዶች በዛሬው ዕለት ልምላሜያቸው ያማረ ጣዕማቸው የጣፈጠ ዘሎባይኔ፣ ዓደይ አበባ ቀጥፈው እንግጫ በመንቀል አበባዎቹን በእንግጫ አሥረው ያቆማሉ። ይህንንም አሥረው ያቆሙትን አበባ ወደ አስራ ሁለት ሰዓት ገደማ በመያዝ ይጨፍራሉ። በበነጋው ቤተሰቦቻቸውን እንኩአን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁ በማለት ይገልጣሉ። ቤተሰቦቻቸውም ያለው ፍሪዳ አርዶ፤ጠጅ ጥሎ፣ ነጭ ጤፍ ጋግሮ ይጋብዛቸዋል። የሌለውም ጠላ ጠምቆ፣ ዶሮ አርዶ ቄጤማ ጎዝጉዞ ይሸኛቸዋል።

ልጃገረዶቹም የቀጠፉትን አበባ በየቡሐቃው፣ በየገንቦው ላይ በየቤቱ ዕቃ ላይ በማሰር እስከ ጥቅምት ወር ድረስ ያኖሩታል። ይህም ማለት ጊዜው የአበባ ወራት ነው ብሎ ለመግለጥ ነው። የጥንቶቹ ልጃገረዶች ዕንቁጣጣሽን የሚያከብሩት በዚህ ሁኔታ እንጂ እየዞሩ ገንዘብ በመለመን አይደለም ብለዋል። (አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 1956ዓ.ም)

ለዘንድሮው ዕንቁጣጣሽ በአንስታይ ድምጻውያን ተጫዋቾች ልዩ ልዩ ዜማዎች ተዘጋጅተዋል

የዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በማድረግ በሀገር ፍቅር፣በቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር፣በማዘጋጃ ቤት፣ እንደዚሁም በ3ቱ የጦር ሠራዊቶች፣ ማለት በክብር ዘበኛ፣በጦር ሠራዊትና በፖሊስ የሙዚቃ ጉአድ ከ29 በላይ ልዩ ልዩ ሙዚቃዎች እንደተዘጋጁ ከየድርጅቱ የተገኘው ዜና አስታወቀ።

ዘፋኞች ከሚያቀርቡት መካከል የክብር ዘበኛዋ ወይዘሮ ብዙነሽ በቀለ ዘንድሮስ ስንት ዜማ ይዛ እንደምትቀርብ ተጠይቃ ስትመልስ “ያጠናኋቸው 14 ዘፈኖች ናቸው። ከእነርሱም መካከል የጊዜው ሁኔታ ታይቶ ሶስት ወይም አራት ጨዋታዎችን ሳልጫወት አልቀርም። አቀራረቤም ተመልካቹን ሕዝብ ከልብ ለማስደሰት ሲሆን፤ እንደሚደሰቱም ተስፋ አለኝ በማለት ገልጣለች። ድምጻዊዋ ተጫዋች ብዙነሽ በቀለ በዘፋኝነት ሥራ አስራ ስድስት ዓመታትን ያሳለፈች ስትሆን፤በዚህም ጊዜ ወደ ሁለት መቶ የሚሆኑ ዘፈኖችን ተጫውታለች። የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ከብዙነሽ በቀለ ሌላ የ18 ዓመት ወጣት የሆነችው ሰላማዊት ሀብቴ በዛሬው ዕለት ሁለት ዘፈኖችን ይዛ እንደምትቀርብ ገልጦአል።

“ለአዲሱ ዓመት ሶስት ዜማዎችን ይዤ ቀርቤአለሁ። ከእነርሱም መካከል ኀዘኑን ተቀማ የሚለው አድናቆትን እንደሚያገኝ አምናለሁ።” ይህን ያለችው በዘፋኝነት 14 ዓመት ያገለገለችው የፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ድምጻዊት ተጫዋች ኂሩት በቀለ ናት። ኂሩት ቀደም ሲል ከዘፈነቻቻው ዘፈኖች መካከል ሕይወት እንደሸክላ የሚለውን የምታፈቅር ስትሆን ባለትዳር ወይዘሮ ናት። የፖሊስ ሠራዊት ከኂሩት ሌላ ዘሪቱ ጌታሁንና ወይንሸት ሙሉነህን እንደሚያቀርብ ታውቆአል። (አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 1962ዓ.ም)

ሴቶች በዓመት በዓል ገበያ

“ገብስማ ዶሮ አለህ? ልበ ወርቅስ?” ይህ ሰሞኑንና በዛሬው ዕለት ከሴቶቹ ዘንድ ለዶሮ ነጋዴዎች የሚቀርብ ጥያቄ ነው። መልሱ አለ፤ ቢሆንም ዋጋው ከፍተኛ ነው። ስለዚህም ዶሮ ነጋዴ የሆኑትን አቶ በቀለ ቶላን አነጋግረናቸው “የዶሮ ዋጋ በአሁን ጊዜ ከ75 ሳንቲም ወደ 1ብር ከፍ ብሎአል። ይህም የሥጋ ዶሮ ሳይሆን የመልክ ነው” ብለዋል። ለምን ከፍ እንዳደረጉ ተጠይቀው ሲመልሱ፤በአጭሩ ትርፍ የሚገኘው በአሁኑ ጊዜ ስለሆነ ነው ሲሉ ገልጠዋል።

በዶሮ ዋጋ ከፍተኛነት የተማረሩት አንዲት ገበያተኛ “በ 1ብር ዶሮ ገዝቼ ከምበላ አጋማሹን ጨምሬ ቆዳ መልስ በግ አልገዛም ወይ?” በማለት ተናግረዋል። ለዓመት በዓሉ ዋጋ የጨመሩት ዶሮ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ዕንቁላልም ከጳጉሜን አንድ ቀን ጀምሮ በ25 ሳንቲም አራት መሸጥ ጀምረናል ሲሉ የዕንቁላል ነጋዴው አቶ እሸቱ ገልጠዋል። (አዲስ ዘመን ጳጉሜን 4 ቀን 1962ዓ.ም)

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You