ብሪክስ አቃፊ ለሆነ የመልማት መርህ

ከሰሞኑ በደበብ አፍሪካ በተካሄደው 15ኛ የብሪክስ አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ሀገራችን ለአባልነት ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት እንዳገኘ መገለጹ ይታወሳል። በዚህም ጉባኤ ላይ ሀገራችንን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶችን በአዲስ አባልነት ተመዝግበዋል።

በጉባኤው ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ‹ይህ ለሀገራችን ታሪካዊ ሁነት ነው። ኢትዮጵያ ሁሉንም አካታች ለሚሆን የበለጸገ የዓለም ስርዐት መስፈን ከሁሉም ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዚህ ጉባኤ ላይ ጥያቄአቸው ተቀባይነትን ያገኘ አዲስ አባላት ከፊታችን ባለው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ቡድኑን በይፋ እንደሚቀላቀሉ በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት በሲሪል ራማፎዛ በኩል ተገጿል።

አምስት ሀገራት ማለትም ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የተጣመሩበት ብሪክስ የተመሰረተው እንደፈረንጆቹ የዘመን ስሌት ከአስራ ሁለት ዓመት በፊት በ2009 ነው። መሰረቱን ሲያቆም ደቡብ አፍሪካ ባልተካተተችበት የአራት ሀገራት ምክር ሲሆን የኋላ ኋላ ከአንድ ዓመት ዝግመት በኋላ ማለትም በ2010 ደቡብ አፍሪካን አካቶ የቡድኑን ቁጥር አምስት አድርሷል።

ከጋርዮሽ የኢኮኖሚ ጥምረት ጎን ለጎን የጥቂት ሀገራትን የበላይነት ለመገዳደር አስቦና ተልሞ የተመሰረተው የአምስቱ ሀገራት ጥምረት የወደፊቷን ዓለም ገጽታ በበጎ ይቀይራሉ ተብለው ተስፋ ከተጣለባቸው ጥምረቶች አንዱ ነው። ባነገበው ዓላማና በሚከተለው ሁለንተናዊ መርህ በእስካሁኑ ጉዞው ከ40 የሚልቁ ሀገራት የአባልነት ጥያቄ አቅርበውበታል።

በራስ ወዳድነትና ሚዛናዊነትን በሳተ እሳቤ የሚንቀሳቀሰውን የዓለም ስርዐት ከማስተካከል አኳያ ትልቅ ድርሻ ያለው ብሪክስ እንደ አይ ኤም ኤፍ፣ የዓለም ባንክን እና ሌሎች የፋይንንስ ተቋማት አሰራራቸውን እንዲያሻሽሉ ጫና ከማድረግ ባለፈ፤ ለታዳጊ ሀገራት ምጣኔ ሀብት ድምጽና ውክልና ተቆርቋሪነትንም ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይታመናል።

ከምንም በላይ ስርዐት አልበኝነት ለሚታይባት ምድርና የሰው ልጅ ፍትህንና እኩልነትን ማምጣት፣ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረቅ ለፍትህ ተሟጋች ከመሆን አንስቶ እስከ አቅም ግንባታ የሚዘልቅ አቅም መፍጠር የቡድኑ ተቀዳሚ ዓላማ ሆኖ ከፊት ተቀምጧል። ዓለም ያለፈችባቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርዐቶች በማጤንና በመገምገም ሁሉን ያማከለ ሁነኛ ምላሽ መስጠት የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ ሆኖ እናገኘዋለን።

ከዶላር ውጪ ሌሎች ዓለም አቀፍ መገበያያዎች እንዲኖሩ፣ የዓለም ምጣኔ ሀብት እድገት ፍትሀዊ እንዲሆን እንደሚሰራ የሚጠበቅው ሕብረቱ፤ የተለያዩ ባህሎችን፣ አተያይና አረዳድ ታሪክ ያላቸውን ህዝቦች መያዙ እንደ አንድ ትልቅ አማራጭ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርገዋል። ጥምረቱ በሁሉም ረገድ የዓለምን ነባር ብልሹ አሰራር የሚሞግት፣ የሚያርቅና የሚያቀና አዲስና ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ መሆኑን መነሻውን በማየት መረዳት ይቻላል።

ብሪክስ እንዳነሳሱ መድረሻውም የዛን ያክል ተስፋ ሰጪ ነው። በአሁኑ ሰዓት በምዕራባውያን ልብ ውስጥ ብርቱ ስጋትን በመፍጠር ላይ የሚገኝ የብዙሀን ነጸብራቅ ነው። ስጋቱን ከፍ ያደረገው ደግሞ በኃይል የበላይነት ወደአንድ ጎን ያጋደለውን ኢኮኖሚ ሚዛን በማስተካከል ፍትህ ላጡ ሀገራትና ህዝቦች የሚሞግት መሆኑ ነው።

በእንዲህ አይነቱ የጋራ ድምጽን ባነገበ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በራስወዳድነት የተሞላውን አሁናዊ ዓለም አቀፍ ስርዓት መቋቋም አይቻልም። ህብረቱ አዳዲስ አባሎችን እየጨመረ በሀሳብና በተግባር፣ በአቅምና በገንዘብ እየጎለበተ በሄደ ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጨባጭ የፍትህ ለውጥ እንደሚያመጣ በብዙዎቹ ታምኖበታል።

ደቡብ አፍሪካ ላይ በተዘጋጀው ጉባኤ ላይ አዲሶቹን አባላት እንኳን ደስ አላችሁ ከማለት ጀምሮ ልዩ አቀባበልን በማድረግ ‹ኑ አብረን እንስራ፣ የሚለው የህብረቱ ድምጽም የዚሁ እውነታ አንዱ መገለጫ ነው።

አምስቱ የብሪክስ አባላት የህዝብ ቁጥር እንደዋነኛ የኢኮኖሚ መገንቢያ አቅም ተደርጎ በሚወሰድበት በዚህ ዘመን በህዝብ ቁጥራቸው ግንባር ቀደምት ናቸው፤ ቻይናና ህንድ በህዝብ ቁጥራቸው ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፉ ናቸው። ብራዚልን ብንወስድ በአራተኛ ደረጃ ላይ የምናገኛት ሀገር ናት።

በኢኮኖሚ ደረጃም እጅግ የበረታ አቅም ያላቸው፣ መጪውን የዓለም ፖለቲካና ኢኮኖሚ ይቆጣጠራሉ ተብለው ከተተነበየላቸው ውስጥ የተቀመጡ ናቸው። ከጠቅላላው የዓለም ህዝብ 3.24 ቢሊዮን የህዝብ ቁጥር ይዘዋል። በጋራ 26 ትሪሊዮን ዶላር ታቅፈዋል። ይሄ አሀዝ የዓለምን 26 ከመቶ ምጣኔ ሀብት የሚይዝ ነው።

ብሪክስ መነሻውን ያደረገው በሶስት አበይት ዓላማዎች ነው። የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ትብብርን በመፍጠር የንግድ ልውውጡን በማስፋት በኢኮኖሚው ዘርፍ የማይበገር ሚና መጫወት ነው። ሁለተኛው በሁሉም ዘርፍ ቀጣይነት ያለውን እድገት ማበረታታት ሲሆን በሶስተኛነት የምናገኘው ፖለቲካዊ አንድምታ የሚለውን ነው። እኚህን ሶስት ተቀዳሚ ዓላማዎች ወደ አንድ ስንጨምቃቸው ፍትህና እኩልነት የሚል የጋራ መጠሪያ ይሰጡናል።

ብሪክስ መነሻው ፍትህአዊ ዓለም አቀፍ ስርአት መፍጠር ነው። ወደ አንድ በኩል ያዘነበለ የዓለምን ሸፋፋ አቋም ማስተካከል ነው። ያለፍትህ የተያዙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነትን ማዳከምና ሀገራት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴአቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲከውኑ ማስቻል ነው። የጋራ እሴት፣ የጋራ የኢኮኖሚ ጥምረት በመመስረት የእርስ በርስ መደጋገፍን ማሳደግ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ዓለም በሁለት ጎራ እየተከፈለች ያለች ይመስላል። የመጀመሪያው አሜሪካ እና ምዕራባውያን ወዳጆቿን ያቀፈው ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሪክስ ቻይና፣ ሩሲያን ፣ ህንድ ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካን የያዘው /ብሩሪክስ / ነው ።

አሜሪካ በምትመራው አሁነኛ የዓለም ስርዓት ብዙ የዓለም ሀገራት ተጽዕኖ ውስጥ ወድቀዋል። ይሄን ተጽእኖ ለመፋቅ እንደብሪክስ ያሉ በጋራ ሀሳብ የጋራ ህልም ያለሙ ሀገራት ወዳጅነትን ፈጥረው በኢኮኖሚና በፖለቲካው ዘርፍ ልዩነትን ለመፍጠር መነሳታቸው የሚበረታታ ነው። አማራጭ የዓለም ስርዓት ለመፍጠርም የተሻለ እድል ይፈጥራል።

ብሪክስ የብዙ አስተሳሰቦች፣ የብዙ ፍላጎቶች፣ ለፍትህ የቆሙ የብዙ መሻቶች ጥርቅም ከመሆኑ አንጻር፣ ይሄ አስተሳሰብ እንደ አፍሪካ ላሉ በድህነትና በኋላ ቀርነት ከፍ ሲልም በጦርነትና ባለመረጋጋት በሚታመሱ ሀገራት ላይ የራሱ የሆነ በጎ ውጤት ይዞ እንደሚመጣ ይታመናል። ከኢኮኖሚና ከፖለቲካ መረጋጋት እኩል በሰላምና በሌሎች ማህበራ እሴት ግንባታዎች ላይ የራሱ አስተዋጽኦ ያለው ስብስብ ነው።

ማንም ገብቶ በሚወጣበት፣ ማንም የፈለገውን አድርጎ እንዲህ አድርግ እንዲያ አድርግ በሚልበት የአፍሪካ አህጉር ውስጥ ጣልቃ ገብነትን ከመከላከል እና የራስን እድል በራስ ከመወሰን አንጻር ድርሻው የላቀ ነው። በሀገራችን አሁናዊ ሁኔታ ውስጥም ከሰላም ፈጣሪነት እና ከኢኮኖሚ መነቃቃት ጋር አስተሳስረን ልናይም የሚገባ ክስተት ነው።

ጥምረቱ መነሻው ሀሳብ ነው። በአንድነት ለአንድነት አይነት መልዕክት ያለው ሁሉን አቃፊ የአዲስ ስርዓት ጅማሬ ነው። የፍትህና የአብሮ መልማት እሳቤ ጎልቶ የሚደመጥበት ነው። ይህ እሳቤ አማራጭ አጥቶ ለከረመው ለአፍሪካ ሀጉር ሁለንተናዊ ተሀድሶን የሚያመጣ የንቃት፣ የብርታት ድምጽ ነው።

በአፍሪካውያን ልብና መንፈስ አእምሮ ውስጥ ከፍ ያለ መነቃቃት መፍጠር የሚችል ነው። ይህ በሁሉም ረገድ ድጋፍና ትብብር ያልተለየው ተያይዘን ዓለምን እናያያዝ አይነት መነሻ ያለው የብሪክስ የአስተሳሰብ መሰረት ሀገራችንን በብዙመልኩ እንደሚጠቅማት ለመገመት የሚከብድ አይደለም።

ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ትልቅ አቅም መፍጠር የሚያስችል ነው። እንደ አንድ አባል ሀገር ለሰላምና ለጀመርናቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሀሳብ እና የንቃት አውድ ሆነው ሊያገለግሉን ይችላሉ።

ብሪክስ ባጠቃላይ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ‹የአዲስ ስርዓት ውልደት ነው ብሎ ለመቀበል ጊዜ ቢጠይቅም፤ ከተነሳበት የአስተሳሰብ መርህ አንጻር በስብስቡ ተስፋ ማድረግ ግን ብዙም እንደአላዋቂነት የሚያስቆጥር አይሆንም። በጥምር ጉባኤው በኩል የሚስተዋሉ የለውጥ ቁርኝቶች መጪውን ጊዜ ተስፋ እንድንጥልበት እድል የሚሰጡን ናቸው።

ከግለኝነትና ከአንባገነንነት በጸዳ መንገድ የዓለምን ችግር በዓለም አቀፍ ሀሳብና መፍትሄ ለመፍታት ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የመረጠ ስብስብ ነው። ሀገራችንም ከዚህ ጥምረት የራሷን አስተዋጽኦ በማድረግ ከራሷ አልፋ ሌሎችን እንደምትጠቅም በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ሰንቋል።

እንደ ሀገር ሀገራችን ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር ነች። በአፍሪካ እና በምስራቅ አፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ግስጋሴዋ ቀዳሚ ሆና ትጠቀሳለች። በታሪክ፣ በባህል፣ ለሰላም ባላት ጽኑ መሻትና ዓለም አቀፉን የቅኝ ወራሪ ስርዓት ታግላ በመጣል ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝብ የንቃት እና የነጻነት ፋና ወጊ ነች፣ በቆዳ ስፋት፣ በተፈጥሮ ሀብቶቿ በሌሎችም በርካታ ጸጋዎቿ የአባልነቷ ጥያቄ ተቀባይነትን አግኝቷል።

ከምንም በላይ የብሪክስ አባል መሆኗ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያሳየችው ተጨባጭ ስራ ለእንዲህ አይነቱ መልካም አባልነት አሳጭቷታል። ከዚህ አይነቱ እድልና ድልን ከያዘው መልካም አጋጣሚ በመማር ቀጣይም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሻለ ስራ በመስራት ሌሎች እድሎችንም መፍጠር እንደሚቻል ጥቁምታ የሰጠ ነው።

በሰላምና በተረጋጋ ማህበራዊ ንቃት ሀገሪቱ ውስጥ ተጨባጭ ዘላቂ ሰላም ከመጣ ከየትኛውም ሀገር በላይ ለእንዲህ አይነቱ ዓለም አቀፍ አባልነት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። የድሌም ተጠቃሚ በመሆን ለውጥ ለማምጣት የሚከብደን አይሆንም።

ሀገራችን የብሪክስ ጥምረት ውስጥ የራሷን ሀሳብ፣ የራሷን አቋም፣ የራሷን እውነት ይዛ ለዓለም ፍትህ ዘብ የምትቆምበት ጊዜ ላይ ነች። እድልና አጋጣሚዎችን ካገኘን ብዙ ስራዎችን ለዓለም እንደምናበረክት ያለፉ ታሪኮቻችንን ማየቱ በቂ ነው። በጀመርነው መንገድ ቀጥለን በኢኮኖሚውና በፖለቲካው አሁን ያለውን የህዝብ ጥያቄ በመመለስ የተሻለች ሀገር መፍጠር እንችላለን።

ለዓለም ሰላም፣ ለዓለም እኩልነት ከነጻነት ናፋቂዎች ጋር መሰለፋችን ታሪክ ትላንትናን ሲበረብር የሚያገኘው ዘመን ተሻጋሪ ድላችን ነው። ድል የሚጣፍጠው ከውጤት ጋር በመሆኑ እድሉን ወደ ፍሬ ለመለወጥ አሁን ላይ ሀገራዊ ፈተና የሆነብንን የሰላም እጦት በሰላም ለመፍታት ሁላችን ዘብ ልንቆም ይገባል።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ነሐሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You